Saturday, 25 March 2023 17:26

ዳሽን ባንክ ከ5 ቢ.ብር በላይ ከወለድ ነፃ ፋይናንስ ማቅረቡን አስታወቀ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

- ሸሪክ የተሰኘ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የጀመረበትን 5ኛ ዓመት አክብሯል
       - ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ አገልግሎት የሚሰጡ ቅርንጫፎቹን 62 አድርሷል
            
         ዳሽን ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ብቻ ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ የፋይናንስ አቅርቦት ማድረጉን አስታወቀ፡፡ ባንኩ ይህን ያስታወቀው ባለፈው ማክሰኞ መጋቢት 12 ቀን 2015 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ በባንኩ ዋና መስሪያ ቤት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የጀመረበትን አምስተኛ ዓመት ባከበረበት ወቅት ነው፡፡
ባንኩ ከ5 ዓመት በፊት ከወለድ ነፃ አገልግሎት ሲጀምር በዘርፉ በቂ ልምድና ክህሎት እንደሌለና ከፍተኛ ዝግጅት የጠየቀ ስለመሆኑ በበዓሉ አከባበር የመክፈቻ ንግግራቸው ላይ የገለፁት የባንኩ ዋና ስራ እስፈፃሚ አቶ አስፋው አለሙ በወቅቱ የራሱ የሆነ የፖሊሲ አሰራርና ማዕቀፎች ማዘጋጀትና መዘርጋት የዘርፉን የሰው ሀይል ማብቃት የአገልግሎቱን ልዩ ምልክት ማዘጋጀትና ሌሎችንም የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ባንኩ ሰፋ ያለ ጊዜ ወስዶ ማከናወኑን ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ባንኩ ከምንም በላይ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በአጭር ጊዜ ስኬታማና ከፍተኛ ተቀባይነት እንዲኖረው ያደረገው ራሱን የቻለ የሸሪአ አማካሪ ምክር ቤት አቋቁሞ በመጀመሩ እንደሆነ ያብራሩት ዋና ስራ አስፈፃሚው ከአምስት ዓመት በፊት በአንድ መስኮት መስጠት የተጀመረው ይህ አገልግሎት ዛሬ ላይ ከፍተኛ እድገት በማሳየት ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አግልግሎት የሚሰጡ 62 ቅርንጫፎች ባለቤት መሆኑ የስኬቱ ማሳያ ነው ካሉ በኋላ በተጨማሪም 700 በሚሆኑ ቅርንጫፎች በአንድ መስኮት አግልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝ ዋና ስራ አስፈፃሚው ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ዳሽን ባንክ በአሁኑ ወቅት ሸሪክ በተሰኘው በዚሁ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተጠቃሚዎችን ቁጥር ከ600 ሺህ በላይ ማድረሱንና ከ7 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰብ መቻሉም ታውቋል፡፡ ባንኩ ባለፉት አምስት ዓመታት በዚህ ዘርፋ ብቻ በተለያዩ ስራዎች ለተሰማሩ ደንበኞቹ ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ማቅረቡን የተናገሩ ሲሆን ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ ባንኩ በዚህ ዘርፍ የሰጠው የብድር መጠን ከ4.3 ቢሊዮን ብር በላይ እንደነበርና ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ92.3 በመቶ እድገት ማሳየቱም በስኬትነት ተነስቷል፡፡
ባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል አካታችነቱን ከማሳየቱም በላይ ዘርፉ የሚጠይቀውን ስነ ምግባር ተግባራዊ በማድረግ በኩልም ጉልህ ሚና ስለመጫወቱ ተገልፆ ባንኩ የማህበሰቡን የዘርፉ ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማሳደግ ጠንክሮ ይሰራል ተብሏል፡፡
ሸሪክ የተሰኘውን ይህንኑ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት 5ኛ ዓመት ባከበረበት ወቅት በዚህ ዘርፍ ጉልህ አበርክቶት ሲሰጡ የቆዩትን አንድ አባት ባለሞያ በአክብሮትና በሽልማት ያሰናበተ ሲሆን ሌሎችም አስተዋፅኦ ላበረከቱ ግለሰቦች የገንዘብና የእውቅና ሽልማት አበርክቷል፡፡ ባንኩ በሸሪክ በኩል ለበጎ አድራጎት ስራ የሰበሰበውን ከ575 ሺህ ብር በላይ ገንዘብ ለአራት በሴቶች አቅም ግንባታ፣ በበጎ አድራጎት፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በትምህርት ላይ ለሚሰሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አበርካቷል፡፡ በዕለቱ የብሄራዊ ባንክ ከፍተኛ ባለስልጣን የባንኩ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሸሪክ አገልግሎት ጠቃሚ ደንበኞችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡


Read 1832 times