Saturday, 18 March 2023 20:07

ልዩ ዝክር ለአበበ ቢቂላ

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(0 votes)

 ኤርምያስ አየለ ታላቁን የማራቶን ጀግና አበበ ቢቂላን በልዩ ሁኔታ ለመዘከር በሮም፣ በአቴንስ፣ በቶኪዮና በፓሪስ ማራቶኖች ላይ  በባዶ እግሩ ሊሮጥ ነው። የ45 ዓመቱ ኤርምያስ ታላቁ ሩጫ በኢትጵያውያን በስራ አስኪያጅነት እንዲሁም የኢዮጵያ ሞተር ስፖርት ፌዴሬሽን በፕሬዝዳንትነት ማገልገሉ ይታወቃል።  በነገው ዕለት በጣሊያን በሚካሄደው የሮም ማራቶን ላይ በመሳተፍ ወደ ፓሪስ ኦሎምፒክ ጉዞውን እንደሚቀጥል ያስታወቀው ኤርምያስ፤  ከ15ሺ በላይ ተሳታፊዎች በሚሮጡበት ውድድር ላይ በባዶ እግሩ በመሮጥ የአበበን ታሪክ ማደስ ይፈልጋል። ኤርምያስ በባዶ እግሩ የሚሮጠው የአበበ ቢቂላን ድርጊትነት 42 ኪ.ሜ የማራቶን ርቀት ከ3፡30 እስ 4 ሰዓት  ውስጥ  ለመጨረስ መዘጋጀቱን አስታውቋል።
ከ63 ዓመታት በፊት በሮም በተካሄደው 17ኛው ኦሎምፒያድ ላይ ጀግናው አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ በመሮጥ፤ የዓለምን የማራቶን ሪከርድ  በ2፡15፡16 በሆነ ጊዜ በማስመዝገብ እንዲሁም መጀመሪያውን የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ በማስገኘት ታሪክ መስራቱ ይታወቃል። የአበበ ቢቂላ ድል ለስፖርቱ ብቻ አይደለም፤ ለጥቁር  ህዝቦች መነቃቃትን የፈጠረ አኩሪ ታሪክ  ነው ያለው ኤርምያስ የኢትዮጵያ ጽናት የሚያንጸባርቅና አገርን ለማስተዋወቅ የሚያግዝ ነው ተብሏል። ኤርምያስ ለሮም ማራቶን ልዩ ዝግጅት ያደረገ ሲሆን ባለፉት ሁለት ዓመታት የተካሄዱትን የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪ.ሜ የጎዳና ላይ ሩጫዎች እንዲሁም የሐዋሳ ግማሽ ማራቶንን በባዶ እግሩ በመሮጥ ልማድ አካብቷል።
ሰሞኑን በሮም ከተማ ተገኝቶ የመሮጫ ጎዳናውን የቃኘው ኤርምያስ አየለ  ለስፖርት አድማስ በቀጥታ ከስፍራው በሰጠው አስተያየት “የሮም አትሌቲክስን ዘንድሮና በቀጣይ ዓመታት የምሳተፈው የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ለማስተዋወቅና ትኩረት እንዲሰጠው ለማድረግ ነው። በሮም ማራቶን ላይ በመሮጫ ጫማዎች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚካሄድ ቢሆንም ምቾት ሳይፈለግ በጥንካሬና በፅናት ማሸነፍ እንደሚቻል ለማስረፅ ነው። ታሪካችን እንዲዘከርና ወጣቱ ትውልድ እንዲነቃቃም ምክንያት ይሆናል።” ሲል ተናግሯል።
“በሌላ በኩል የሮም ማራቶንን በባዶ እግር ከመሮጤ ጋር በተያያዘ ድንቅ  ኢትዮጵያ ብራንድ ኮንሰልታንት በማለት በመሰረትኩት የማርኬቲንግ ኩባንያ የአገር ገፅታን ለመገንባት ፤ የተፈጥሮ ሐብቷን ለመላው ዓለም ለማስተዋወቅ ነው።በአትሌቲክስ የአገራችንን መልካም ገፅታ ለማንፀባረቅና አበበ ቢቂላና ሌሎችም ታላላቅ አትሌቶች በመዘከር ለመሥራት በያዝነው አቅጣጫ ነው።” ብሏል።
የጣሊያንና የአውሮፓ ሚዲያዎች ባዶ እግሩን የሚሮጠው ኢትዮጵያ ብለው ብዙ ሽፋን እየሰጡኝ ነው ያለው ኤርምያስ እስከ 2024 የፓሪስ ኦሎምፒክ በተመሣሣይ መንገድ በመሥራት የኢትዮጵያን አትሌቲክስ በማርኬቲንግና ሌሎች የእድገት ስራዎች ለማጠናከር በሮም ማራቶን ተሳትፎ መሠረት እንጥላለን ሲል በውድድሩ ዋዜማ ከሮም አስተያየቱን አድርሶናል።
ኤርምያስ ሰሞኑን ይፋ እንዳደረገው ከሮም ማራቶን ተሳትፎ ከ8 ወራ በኋላ አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ በሮጠበት ግሪክ ማራቶን፤ የአበበ ቢቂላ 60ኛ ዓመት የኦሎምፒክ ድልን በሚያስታውሰው የቶኪዮ ማራቶንና  እንዲሁም በፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ በሚዘጋጀው 33ኛው ኦሎምፒያድ ላይ በባዶ እግሩ ለመሮጥ አቅዷል።

Read 677 times