Saturday, 18 March 2023 19:45

የብሊንከን ጉብኝት ኢትዮጵያን ወደ አጉዋ የመመለስ ዕድል ይኖረው ይሆን?

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

 የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን፣ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ያደረጉት ይፋዊ የስራ ጉብኝት፣ አገሪቱ ከቀረጥና ኮታ ነፃ የንግድ ችሮታ (አጐዋ) ዕድል ተጠቃሚነቷ እንድትመለስ የሚያደርግ ዕድል ሊኖረው ይችላል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከጉብኝቱ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ትግበራ በስምምነቱ መሰረት የሚፈፀም ከሆነ፣ ኢትዮጵያ ወደ አጉዋ የመመለስ ዕድል ሊኖራት እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ የውጪ ጉዳይ ሚኒስሩ በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ ከህወሃት አመራሮችና ከአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ጋር ተወያይተዋል፡፡
ለሁለት ዓመታትዎችን በዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት ሳቢያ ሻክሮ የቆየውን የኢትዮጵያንና የአሜሪካን ወደጅነት ለማሻሻል ያስችላል የሚል ተስፋ የተጣለበት ያጋለጠ የፌደራል መንግስትና የህወሃት ሃይሎች የፕሪቶሪያውያን ስምምነት ተግባራዊ እያደረጉበት ስላለው ሁኔታ በመገምገም፣ በጦርነቱ የተጎዱ ወገኖችን መልሶ ለመገንባት ሁነኛ መሰረት የሚጣልበት እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ብሊንከን በዚሁ ጉብኝታቸው ማጠቃለያ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተናገሩት ጦርነቱ የመቶ ሺዋች ህይወት የቀጠፈ በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶችና ህፃናትን ለወሲባዊ ጥቃት ያጋለጠ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ቀዬአቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ያደረገ በመሆኑ ግጭቱን በዘላቂነት በማቆም የንፁሃንን ህይወት ለመታደግ ሁለቱም ወገኖች ከፍተኛ ስራ ይጠብቃቸዋል ብለዋል፡፡ ጦርነቱን ከማቆም ጋር በተያያዘም ትልቅ መሻሻሎች መታየታቸውን የተናገሩት ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከወራት በፊት በፕሪቶሪያ የተፈረመውን ሰላም ስምምነት ተግባራዊ በማድረግ ረገድ የሚቀሩ በርካታ ጉዳዮች አሉ ብለዋል፡፡ በትግራይ የሰብአዊ መብት ጥሰቱ  በእጅጉ ቀንሷል ያሉት ብሊንከን፤ነገር ግን ይህ ሁኔታ እንደማንኛውም የአገሪቱ አካባቢ ዜሮ ደረጃ ላይ ሊደርስ ይገባልም ብለዋል፡፡
የአሜሪካ መንግስት ከሰሀራ በታች ላሉ የአፍሪካ አገራት የተዘረጋው ከቀረጥ ነፃ የንግድ እድል ተጠቃሚ የነበረችው ኢትዮጵያ፣ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ መታገዷን ተከትሎ፣ አገሪቱ ውሳኔው ከ200ሺ በላይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ከግጭቱ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌላቸው ህፃናትና ሴቶች የሚጎዳ ውሳኔ በመሆኑ አሜሪካ ውሳኔውን እንደገና እንድታጤንና ወደ ተጠቃሚነቱ እንድትመለስ ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ስታነሳ ቆይታለች፡፡ ይህ የአሁኑ የብሊንከን ጉብኝትም ከወራት በፊት በፕሪቶሪያ የፈረመችውን የሰላም ስምምነት ምን ያህል ተግባራዊ እያደረገች እንደሆነ በማየትና ለስምምነቱም ያላትን ቁርጠኝነት በመገምገም፣ አገሪቱን ወደ አጉዋ እድል ተጠቃሚነት ለመመለስ የሚያስችል እድል ይኖረዋል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በዚሁ የጉብኝት ማጠቃለያ ጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ፣ ስለዚሁ ጉዳይ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፤ ኢትዮጵያን ወደ አጎዋ ተጠቃሚነት ለመመለስ ማሟላት ያለባቸው ግልፅ የሆኑ መስፈርቶች እንዳሉ ጠቁመው ግጭት ከማስቆም ስምምነቱ ጋር በተያያዘ የአተገባበሩ ዘላቂነት መቀጠሉ ለዚህ ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለዋለ፡፡ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ትግበራ በስምምነቱ መሰረት  የሚፈፀም ከሆነ ኢትዮጵያ ወደ አጎዋ ዕድል ልትመለስ እንደምትችልም የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በሳምንታዊ መግለጫቸው ላይ እንደተናገሩት፤ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የጣለችውን የአጎዋ እድል እገዳ እንድታነሳ ጥያቄ መቅረብ ከጀመረ የቆየ መሆኑን ጠቅሰው፤ አገሪቱ ግን አሁንም እግዱን እንዳላነሳችና ተጨማሪ ምክክርና ውይይት እያደረገ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
አሜሪካ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት ምርቶቻቸውን ካቀረቡና ከኮታ ነፃ በሆነ ሁኔታ እንዲያስገቡ የሚፈቅደውን እድል እ.ኤ.አ በ2000 ላይ መስጠቷ የሚታወስ ሲሆን፤ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ የዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈፅሟል በሚል ምክንያት ኢትዮጵያ ከቀረጥ ነፃ እድል እንድትሰርዝ ማድረጓ ይታወቃል፡፡   


Read 1725 times