Saturday, 18 March 2023 19:43

ምርጫ ቦርድ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ የሚፈጸመው እንግልትና ወከባ እንዲቆም ጠየቀ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

 - በመንግስት አካላት ላይ ክስ እመሰርታለሁ ብሏል
    - ቦርዱ ለጠ/ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ደብዳቤ ልኳል
                 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤያቸውን ለማከናወን እንዳችሉ ከተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት እየተደረገባቸው ያለው ወከባና ጫና እንዲቆም፤ እንዲሁም በመንግስት መ/ቤት ስር የሚተዳደሩ የስብሰባ አዳራሾች ለፖለቲካ ጠቅላላ ጉባኤዎች ክፍት እንዲደረጉና ይህም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤትና በክልል ፕሬዚዳንቶች ጽ/ቤት አማካኝነት እንዲፈጸም ውሳኔ መስጠቱን አስታውቋል።
ይህንኑ መመሪያ ማስተላፉን የሚገልጽና የመንግስት ተቋማቱ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት በኩል መመሪያ እንዲተላለፍ የሚጠይቅ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ልኳል።
በዚሁ የቦርዱ ደብዳቤ እንደተገለጸው፤ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ የማድረግ ግዴታ በህጉ የተጣለባቸው ሲሆን ይህንን የህግ ግዴታ ለመወጣት የአዳራሽ አቅርቦት ካላቸው ድርጅቶችና ሆቴሎች ጋር የሚያደርጓቸው ውሎች ተገቢውን ከበሬታ ሳያገኙ እንደሚቀሩ ታይቷል። ከዚህ አንጻር ገዥው ፓርቲ የመንግስት አካላት በሚያስተዳድሯቸው የስብሰባ አዳራሾች ላይ መጠቀም የሚችለውን ያህል፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ያለአድልዎ በእኩልነትና በፍትሃዊነት የመጠቀም መብት እንዳላቸውና የሚመለከታቸው የመንግስት አካላትም ይህንኑ አውቀው ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ቦርዱ በደብዳቤው ጠይቋል።
የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤቱ በስሩ ለሚገኙ የሚኒስቴር መ/ቤቶች ኤጀንሲዎችና መሰል ተቋማት ተገቢውን የስራ መመሪያ እዲያስተላልፍም ቦርዱ ጥሪ አቅርቧል።
ተቃዋሚ ፓርዎች ጠቅላላ ጉባኤያቸውን እንዲያካሂዱ የተለያዩ ወከባዎችና እንግልቶች በሚፈጽሙ የመንግስት አካላት ላይ ክስ እንደሚመሰርትም ቦርዱ አስታውቋል።

Read 2098 times