Sunday, 12 March 2023 10:34

ፍቅር እስከ መቃብር፣… ከተሰራ አይቀር፣ በተሟላ ጥበብ!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

 እንሞክረው ብለው የሚነካኩት አይደለም
ፍቅር እስከ መቃብር፣… የተሰኘውን ረዥም ልብወለድ ድርሰት፣ በተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ የመስራት ሃሳብና እቅድ መጥቷል። ቀላል ሀሳብ ቀላል ስራ አይደለም። አይሆንምም። ከባድነቱ፣… በአንድ በሁለት ምክንያት ብቻ አይደለም።
በጣት ከሚቆጠሩ የአገራችን የጥበብ ድርሰቶች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው - “ፍቅር እስከ መቃብር”።
“ራሱን የቻለ ትልቅ ዓለም ነው” ብለው ቢገልጹት፣ ቅንጣት አይበዛበትም። ምናባዊ ፈጠራ ነው - ልብወለድ ድርሰት። ግን በአካል የሚገቡበትና የሚዳስሱት ዓለም፣ በእውን የሚያዩት፣ የሚኖሩትና የሚያጣጥሙት ዓይነት ሕይወት ነው- ፍቅር እስከ መቃብር።
ያንን ዓለምና ሕይወት፣… በሚጨበጥ በሚታይ ምስል፣ ከነዝርዝሩና ከነለዛው በምልዓት ቀርጾ ማሳየት እጅግ ከባድ ስራ ነው። ድርሰቱን ወደ ተከታታይ የቲቪ ድራማ መተርጎም፣… ጥበበኞችን ይፈታተናል።
ሌላው ይቅርና ድባቡን ብቻ በአሳማኝና በአመቺ ሁኔታ መፍጠር እንኳ፣ ትልቅ ፈተና ሊሆንባቸው ይችላል። የሁለት መንገደኞች አምስት መስመር ንግግር በመጽሐፍ ላይ ቀላል ሊመስል ይችላል። በፊልም ሲቀረፅስ?
ብቸኛው በዛብህ አገሩን ጥሎ እጅግ ርቆ ለመሄድ ወስኗል። ጉዞው በዲማ በኩል ነው- በስመ ገናናዋ ከተማ በኩል። ያው፣ ጉዞው በእግር ነው። ትንሽ መንደር አጠገብ ሲደርስ አንዱን መንገደኛ ጠየቀ። ታዲያ ዘልሎ ወደ ጥያቄ መግባት የለም። ሰላምታ የግድ ነው። ከሰላምታ በኋላ፣… በዛብህ ጠየቀ።
“የኔ ጌታ፣ ዲማ ከዚህ ብዙ ያስኬዳል?
 “ደርሰዋል”
“ከዚህ ከመንደሩ ወዴት ነው?”
“ከየትኛው መንደር?”
“እዚህ እፊቴ ከማየው?”
“ሙሉ ጦቢያ የሚያከብረውን ደብር እርስዎ መንደር ቢሉት ክብሩ አይቀንስም” አለ ሰውዬው።
የተከበረው ቦታ ጋ ደርሷል ለካ። ዲማ፣… በአካል እንደ መንደር ናት። በመንፈስ የአገር አድባር ናት። ይህን እውነታና መንፈስ፣ በፊልም ማሳየት ካልተቻለ ምኑ ተሰራ?
የአለቃ ክንፉ መንደር ነው-ቦታው። በድፍን አገር አቻ የሌላቸው የቅኔ ሊቅ ናቸው። በመቶ የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከየአገሩ እየመጡ የሚማሩት እሳቸው ጋ ነው። በእርግጥ በዛብህ የቅኔ ሊቃውንት ዘንድ ሄዶ ተምሯል። የአለቃ ክንፉን ቅኔ የመስማትና የማየት እድል ሲያገኝ ግን ገና ጀማሪ የሆነ ያህል ተሰማው። እሱምኮ የዋዛ ሰው አይደለም- የቅኔ ጥበበኛ፣ ዜማ አዋቂ፣ የጣዕመ ዜማ ፏፏቴ ነው። ማን ይስተካከለዋል?
እንግዲህ፣ ስድስት መስመር የሁለት ሰዎች ንግግር ይህን ሁሉ መንፈስ ያዘለ እንደሆነ አስቡት። ይህን መንፈስ በአካል የሚያሳይ፣ ድባቡን ዘርግቶ ተመልካችን ጎትቶ የሚያስገባ መሆን አለበት- በፊልም ሲዘጋጅ። ቀላሏ ነገር እንዲህ ከባድ ከሆነች፣ ሌላውማ እንዴት ይሆን!
መቼም፣ የይድረስ ይድረስ፣ “ወጪ የማብቃቃት”፣ የግብር ይውጣ ስራ አይሆንም በሚል እምነት ካሰብነው ማለቴ ነው። እንዲሁ እንሞካክረው ብለው የሚነካኩት ዓይነት ድርሰት አይደለም - “ፍቅር እስከ መቃብር”።
ከተሰራ አይቀር፣ በሙሉ መንፈስና በሙሉ አቅም መሆን አለበት።
አለበለዚያ፣ ቢቀር ነዋ የሚሻለው። ጊዜው እስኪደርስ ባይነካኩት ነዋ የሚመረጠው።
ጥንቅቅ ባለ ጥበብና በሙሉ አላማ እንስራ ከተባለ ደግሞ፣ ያው፣… ፈተናው ብዙ ነው። ቴዎድሮስ ተክለአረጋይ ከባድነቱን ለመግለፅ፣ “ፍቅር እስከ መቃብር ነው መጽሐፉ” ብሏል - በርካታ ነጥቦችንም በመጥቀስ። የስራው ከባድነት እጅግ በዝቶና ገዝፎ ቢታየው አይገርምም። ድርሰትና የቴሌቪዥን ድራማ፣ ሙያውና ስራው ናቸው።
ከድርሰቱ ባሕርይ የሚመነጩ ፈተናዎችም አሉ። ሃሳብ፣ ኑሮ፣ ልማድ፣ ስሜት፣ ተግባር፣ ባሕርይ፣ ባሕል ሁሉ… አብረው የተዋሃዱበት ሃይለኛ ድርሰት ነው።
ድርጊት ወይም ተግባር ብቻ በሌጣው የገነነበት አይደለም።
ለብቻው የተነጠለ የሀሳብ ትንታኔና ንግግር የበዛበት አይደለም።
የሰው ባሕርይ ለብቻው ተገንጥሎ የሚተነተንበትና የሚገለጽበትም አይደለም።
ሃሳብ፣ ድርጊት፣ ባህርይ እርስ በርስ የተሳሰሩ ናቸው- በምርጥ ድርሰት ውስጥ። እየተጣመሩ ወይም እየተካረሩ፣ ከጅምር እስከ ፍፀሜ የሚገሰግሱ ወይም የሚጦዙ ናቸው። የሃሳብና የተግባር፣ የባሕርይና የማንነት… በአጠቃላይ የሕይወት ምልዓት ነው። የሃሳብና የጭብጥ፣ የአላማና የተግባር ትልም፣ የማንነትና የገጸ ባህርያት ፅኑ ውህደትን የተቀዳጀ ድርሰት ነው።
ይህን እጅግ የበለጸገ የጥበብ ሥራ፣ ይህን ጥበበኛ የልብወለድ ድርሰት ወደ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ተርጉሞ መስራት… እንደ ቴዎድሮስ “እግዚሄር ይርዳችሁ!” ያስብላል። ይህም ብቻ አይደለም።
ከድርሰቱ የጥበብ ልሕቀት ተነሳ፣ ብዙ ሰዎች የሚስቷቸው ድንቅ ገጽታዎች መኖራቸውም፤ ስራውን ያከብዱታል። ነገሩ አስገራሚ ነው።
በአንድ በኩል የድርሰቱ ድንቅ ገጽታዎች፣… ምስጢር አይደሉም። በገሃድ የሚታዩ ናቸው። የአንባቢን መንፈስ የሚማርኩና የሚመስጡ ናቸው- የድርሰቱ ድንቅ ገጽታዎች።
ነገር ግን፣… ብዙዎች በሃሳብ ሊተነትኗቸው ሲሞክሩ ይስቷቸዋል።
አንድ የማያሻማ የድርሰቱ አስገራሚ ባህርይ እንመልከት። የፊታውራሪ መሸሻ ማንነትን አስተውሉ።
“ግጭት”፣ የድርሰት ሞተር ነው። እዚህ ላይ መሳሳት፣ ጥበብን ያሳጣል።
የተካረረ ግጭትና ውጣ ውረድ የድንቅ ድርሰት ገጽታ ነው ይባላል። ብዙ ጊዜም፣ ግጭቱ፣ በሁለት ባለታሪኮች መካከል ይሆናል። ይህ ትክክል ነው።
ግጭቱ፣ በመልካም ሰው እና በክፉ ሰው ማኸል ነው የሚለው አስተሳሰብ ግን በጣም ያሳስታል።
 በገጸ-ባሕርያት መካከል የሚፈጠር ቅራኔወደ ግጭት እየተመነዘረ ይፋጫል። እየተካረረ ሄዶም ወደ ሃይለኛ ፍልሚያ ይጦዛል ይባላል። ምርጥ ድርሰት ይህን የታሪክ ትልም ያሟላል። ግን እንደሚታሰበው አይደለም።
የምርጥ ምርጥ ድርሰቶች ውስጥ እንደምንታዘበው፣ ልቀው የወጡ የዓለማችን የጥበብ ፈጠራዎች ላይ እንደምናየው፤ ቅራኔው፣ ግጭቱና ፍልሚያው፣… በጥሩ እና በእኩይ ገጸባህርት መካከል አይደለም።
የመልካም ገጸ ባሕርያት ግጭት ነው- ሃይለኛው ግጭት። ብርቱዎቹ ተቀናቃኞች፣ ከሞላ ጎደል የየራሳቸው ብቃትና በጎ ማንነት ያላቸው ጠንካራ ባለታሪኮች ናቸው።
በነባር ምሳሌ እንግለጸው ከተባለ፣ የአኪሊስ እና የሄክቶር ተቀናቃኝነት፣ የዣን ቫልዣና የዣቬር ቅራኔ ልንለው እንችላለን።
በዘመነኛ የሆሊውድ አገላለጽ ደግሞ፣ የባትማን እና የሱፐር ማን ትንቅንቅ ነው።
 የመልካም ገፀ ባሕርያት ነው- ዋናው ግጭት። በእርግጥ ምርጥ የልብ ወለድ ድርሰቶች ውስጥ፣ እኩይ ገፀባሕርያት ይኖራሉ። ግን ዋና ባለታሪኮች፣ ዋና ተፋላሚዎች አይደሉም።
ፍቅር እስከ መቃብርም እንደዚያው ነው። ዋናዎቹን ገጸባሕርት አስታውሱ። የየራሳቸው እንከን ቢኖራቸውም፣ ክፉ ተብሎ ሙሉ ለሙሉ የሚፈረጅ ገጸባሕርይ ግን የለም ማለት ይቻላል።
በሆነ ባሕርያቸው አንጀት የሚያሳርሩ እጅግ የሚያናድዱ ሊሆኑ ይችላሉ። ግን፣ ከምቀኝነት ከክፋት አይደለም። ከምራቸው ከልባቸው በጎ ነው ብለው ላመኑበት ሃሳብ፣ መልካም ነው ብለው ላመኑበት ባሕል በሙሉ ወኔ ይሰለፉለታል፡፡ የሞላጫነት፣ የሸፍጥ፣ የመሰሪነት ባሕርይ ብዙም አይነካካቸውም ቢባል ለማጋነን አይደለም።
ባልና ሚስት ፊታውራሪ መሸሻና ወ/ሮ ጥሩአይነት፣ ክፉ ገፀባሕርያት አይደሉም።
በእርግጥ፣ አንዳንድ ሃሳባቸውና አነጋገራቸው፣ ዛሬ ዘመን ላይ ሆነን ስንሰማቸው አናዳጅ ቅዠት አስቂኝ ኋላቀርነት ሊመስለን ይችላል። ግን፣ አይደለም። ቀልድና ቧልት አይደለም። “ኮሚክ” ገጸባሕርያት አይደሉም።
ፊታውራሪ መሸሻ፣ በራሳቸው የሚተማመኑ፣ ጀግና ሰው ናቸው። ግን ከአቅማቸው በላይ የሆነ አገርን የሚቀይር የለውጥ ማዕበል ገጠማቸው።
ለውጥ ደግሞ፣ ለክፉም ለበጎም ነው። ለበጎ ተብሎ የታሰበ ለውጥ እንኳ፣ ብዙ መዘዞችና ጣጣዎች እንዳሉት፣ ባለፉት 5 ዓመታት አይታችኋል። ከዚያ በፊትም ባለፉት 30 ዓመታት፣ ከዚያ በፊትም ባለፉት 50 ዓመታት በታሪክ አይታችኋል፤ ወይ አንብባችኋል።
የለውጥ ተስፋዎችን ብቻ ሳይሆን የለውጥ አደጋዎችንም ማየት፣ እንዲሁ ባዶ ድርቅና ወይም ቀሽም ኋላቀርነት አይደለም።
ማንም ተነስቶ፣ ቆዳ ፍቆ፣ አህያ ጭኖ ገንዘብ ያገኘ እንደሆነ፣… ቀኝ አዝማች፣ ግራ አዝማች፣ ፊታውራሪ የሚሉ ማዕረጎችን የሚገዛ ከሆነ፣… ይህ ምን የሚሉት ለውጥ ነው? ሰርቶ አርሶ ብር ይሰብስብ። ይቅናው። ነገር ግን፣ ከአባት ከአያት የጦር ወይም የአስተዳደር ጥበብን ያተለማመደ ሰው፣ በገንዘብ የጦርና የአስተዳደር ማዕረግ መግዛት ስለቻለ ስልጣኔ ይባላል? የጦር ሜዳ አይቶና ረግጦ የማያውቅ ሰው፣ የቀኝና የግራ ክንፍ አዝማች፣ ቀድሞ የሚሰለፍ ፊታውራሪ የሚል ሹመት ከገበያ መግዛት ከቻለ፣ አገርና ታሪክ ተበላሸ ማለት አይደለም?
 ይህ ሁሉ ሲሆን፣ የፊታውራሪ መሸሻ መንፈስና የውስጥ ኩራት እንዴት እንደሚቆጣ ይታያችሁ።
ችግሩ፣ ጉዳዩ የልምድና የሙያ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ የትውልድ ሀረግና የዘር ጉዳይ እንደሆነ ማመናቸው ነው። ወደ ጥፋት የሚያደርስ ክፉ ስህተት እየፈጸሙ እንደሆነ አለማወቃቸው ስንት ጉዳት አደረሰ!
ነገር ግን፣…ቀሽም አድሃሪ ወይም አስቂኝ ብለን የፊታውራሪ መሸሻን ሃሳብና ባሕርይ ማንቋሸሽና ማናናቅ፣ ነገሩን መሳት ይሆናል። ፊታውራሪ መሸሻ ፣ ስህተታቸው ቢበዛም፣ ጠንካራ ናቸው- ቀሽም፣ ደካማ፣ ወይ ክፉ ሰው ተደርገው የተቀረፁ ቢሆኑ ኖሮ፣ የድርሰቱ መልዕክትና የታሪክ ትልሙ ሌላ ይሆን ነበር።
በአጭሩ ምን ለማለት ፈልጌ ነው?
የፊታውራሪ መሸሻ የግል ማንነትና ሰብዕና፣ ሃሳብና ተግባር በግልጽ የሚነበብ የሚታይ ቢሆንም፣ ብዙዎች ይስቱታል። የልብወለድ ድርሰት ፍልሚያ፣ የጥሩና የእኩይ ገፀባሕርያት ግጭት ነው የሚል የደመነፍስ ስሜት ነው የሚያሳስታቸው።
የጠንካራ ገፀባሕርያት ፍልሚያ ነው የልብወለድ ድርሰት ሞተር፣ የታሪክ ትልሙን የሚሾፍር ግጭት። ከእንከን ያልራቁ ቢሆኑም ጠንካራና መልካም ጎን ባላቸው ገፀባሕርያት መካከል የሚሽከረከርና የሚጦዝ ነው- የታሪኩ ሴራ።
ሌላ ብዙ ሰዎች የሚስቱት ገጽታም መጥቀስ ይቻላል።
ወይ አልተቀበሉት ወይ አላሳደዱት። ጉዱ ካሳ አሉት።
“ጉዱ ካሳ” የሚል ስያሜ ስንሰማ፣ “እብዱ ካሳ” የሚል ይዘት ያለው ሊመስለን ይችላል። ግን፣ በአካል፣ በአለባበስ፣ በውጫዊ አኗኗር፣ በተግባር፣ በአነጋገር፣ በልማድ፣… በግላጭ “እብድ” የሚያስብል ነገር አይታይበትም።
 ትዳር ላይ በጣም ያፈነገጠ ነገር ሰርቷል ይባል ይሆናል። ሌላውን ሁሉ የሚያስንቅ ጉድ! የባላባቶች፣ የመኳንንት፣ የመሳፍንት ዘር መሆኑ ብቻ አይደለም። የተማረ የተመራመረ ሊቅ ነው። ግን የሚስቱ፣ “ባርያ”… ያው “የባርያ ልጅ” ናት።
ጉድ! ጉድ! ዘር አሰዳቢ!
እንዲያም ሆኖ፣ ትዳሩን አይተው፣ እንዲሁ እንደ ቀልድ የሚያንቋሽሹትና የሚሰድቡት ዓይነት አይደለም- የትዳር አኗኗሩ። ስነ-ሥረዓት የያዘ ጨዋ የትዳር ኑሮ ነው ያለው።
ጉድ የሚያስብሉ ነገሮችን ሊሰራ፣ ሊናግር ይችላል። ግን፣ በቀላሉ የሚያናንቁት፣ የሚያብጠለጥሉት፣ የሚያጥላሉት ዓይነት ደግሞ አይደለም።
ሃሳብና ንግግሩ ለብዙ ሰዎች አይጥማቸው አይዋጥላቸው ይሆናል። ነገር ግን፣ የጠላትነት አይደለም፤ የመቀባጠርም ጉዳይ አይደለም፤ ደስ አይበላቸው የሚል የአፈንጋጭት ሱስ አይደለም፤ የተቃወሰ የዘፈቀደ ተግባር፣ ወይም የባጥ የቆጡን የሚዘባርቅ ንግግርም አይደለም።
የዘመኑ ሰዎችን ግራ ያጋባቸዋል- የጉዱ ካሳ ነገረ ስራ።
ወይ አልተቀበሉት፤ ወይ አላሳደዱት፤ ወይ አልናቁት፣ ወይ አላካበሩት። ወይ አልናቁት፣ ወይ አላደነቁት። ወይ አልጠሉት። ወይ አልወደዱት። ቅይጥ ነው መንፈሳቸው- ጉዱ ካሳ ሲሉት። በእርግጥ፣ ከፊታውራሪ መሸሻ ጋር ብዙ ጊዜ ይጋጫል። ይናደድባቸዋል። አንዳንዴ እሳቸውም ይይበሳጩበታል።
ግን፣ በየፊናቸው ሁለቱንም ወጥሮ የያዘ ሌላ ኃይል ደግሞ አለ። “ለውጥ” የሚባል ነገር።
ለፊታውራሪ መሸሻ፣ ዘመኑ ሁሉ እጅና እግሩ የተምታታበት፣ ጭራ ቀንዱ የማይታወቅ፣ መላ ቅጥ የሌለው የለውጥ ዘመን ሆኖባቸዋል። ሰው የጠፋበት የታመመ ዘመን ነው ብለው ያስባሉ። የዘመኑ በሽታ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰበት፣ መያዣ ማቆሚያ በሌለው የለውጥ ወረርሽኝ፣ አገርና ባሕል ቅጣምባሩ እየጠፋ ነው ይላሉ- ፊታውራሪው።
ለጉዱ ካሳ ደግሞ፣ ነገሩ ተገላቢጦሽ ነው። የእውቀት፣ የስልጣኔ፣ የነፃነት ለውጥ እንደምኞቱ፣… በጥቂት ንግግሮች፣ በአመት በሁለት ዓመት ጥረት የሚሳካ አለመሆኑ ነው የሚቆጨው።
ሰዎች፣ እንዴት ጥቅምና ጉዳትን እየለዩ እያመዛዘኑ የሚበጃቸውን አይመርጡም እያለ ይንገበገባል። የለውጥ ጅረት፣… እንደ ጠብታ በጥቂቱ፣ እንደ ኤሊ በዝግታ የሚጓዝ እየሆነበት፣ ጉዱ ካሳ ቢያዝንም፣ ችግሩን ሁሉ በፊታውራሪ ላይ አያላክክም። ጉዳዩ ከሳቸውም በላይ እንደሆነ እየገባው ይመጣልና።
ጉዱ ካሳ፣… ከዘመኑ የቀደሙ የስልጣኔ ሃሳቦችንና ተግባሮችን የያዘ ጠንካራ ገጸባሕር ነው። ግን፣ ዝም ብሎ የዲስኩርና የፕሮፓጋንዳ ጉዳይ አይደለም። የሕዝብ ፍላጎት፣ የሕዝብ ውሳኔ… ምናምን እያለ፤ አያነበንብም። የሕዝብ ተቆርቋሪ ነን የሚሉ አላዋቂዎች ይሳሳታሉ። ሁሉም ሰው ጥበበኛና ሊቅ፣ ገበሬና አናፂ ሁሉ አገርን የሚያስተዳድር ፈላስፋ የሚሆን ይመስላቸዋል። ጉዱ ካሳ ግን ግልብ አብዮተኛ አይደለም።
የባሕል ነገር ቀላል እንዳልሆነ ይገባዋል። በራሱ ሕይወት፣ በእለት ተእለት ኑሮው ውስጥ፣ የባሕል መልክና ልክ ክፉና ደጉን ሁሉ፣ በእውን እየኖረበት ነውና።
ምርጥ የልብ ወለድ ጥበብ የሰዎች ድንቅ ታሪክ እንጂ ትንታኔ አይደለም።
ባሕል እና የባሕል ለውጥ፣ ለሁለቱ ተቀናቃኞች፣ ለፊታውራሪ መሸሻና ለጉዱ ካሳ፣ የኑሮ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሕይወት ትርጉምን ሁሉ የሚዘውር ዋና ጉዳይ እንደሆነ፣… ከድርሰቱ መገንዘብ እንችላለን።
ታዲያ፣ ድርሰቱ ውስጥ፣ የባሕልና የለውጥ፣ የአገርና የዘመን ትንታኔዎችን በሌጣው እናገኛለን ማለት አይደለም። ያማ የቀሽም ድርሰት ገጽታ ነው።
ምርጥ ድርሰት፣ ፈታኝና ድንቅ የሰዎች ሕይወት ነው… የውጣ ውረድ ኑሮ፣ የውድቀት ወይም የስኬት፣ የሞት ሽረት ታሪክ ነው። የታሪኩ ትልም ከብዙ መከራ በኋላ በስኬት ወደ ተራራው ከፍታ የሚያከንፍ ወይም እስከ መጨረሻዋ ጠብታ እየፈተነ ቁልቁል ወደ ገደል የሚያንደረድር ሊሆን ቢችልም፣ ታሪኩ ግን ድንቅ ጥበበኛ የጽናትና የብርታት ታሪክ ነው። የመልካም ፍልሚያና የጀግንነት ታሪክ ነው።
እናም ድርሰቱ የነፊታውራ መሸሻና የነጉዱ ካሳ፣ የሰብለወንጌልና የበዛብህ፣ የእንቆጳና የአበጀህ በለው ታሪክ ነው። የሃሳብ ትንታኔ አይደለም።
ነገር ግን ሃሳብ የለሽ ወይም ብትን ሃሳብ አይደለም።
 የገፀባሕርያቱ ታሪክ የዘፈቀደ የገጠመኞች መዝገብ፣ ውጥን ቅጡ የወጣ የክስተቶችና የድርጊቶች የትውስታ ወግ አይደለም።
ጥቅል የሃሳብና የመልዕክት ማዕቀፎችን ያጎዳኘ ልብወለድ ታሪክ ግን፣ ውጥንቅጥ የያዘ ነው። ቅጥ አምባር አለው። የገፀ ባሕርያቱን ታሪክ ተመስጠን ተቆርቁረን ስናነብ፣ ጠቅላላ መንፈሱንና ጥቅል መልአክቱን፣ የሃሳብ መሰረቶቹንም እንጨብጣለን- በውስጠ ታዋቂነት።
አንባቢዎች፣ “የዚህ ድርሰት ጭብጥ ወይም መልዕክት ምንድነው?” ብለው ላይመረምሩ ይችላሉ። በገፀ ባሕርያቱ ታሪክ እየተማረኩ፣ ልባቸው እየተንተለጠለ ሲከታተሉ፣ የድርሰቱን ጠቅላላ ሐሳቦችና መልዕክቶችን በስሜት ደረጃ ይገነዘባሉ። ወይም ይገባቸዋል። ከዚያም አልፈው ከሞላ ጎደል በግልጽ ነገሩንና አካሄዱን ይጨብጣሉ። የድርሰቱን ጭብጥ ይረዳሉ፣…እንዲሉ።
ለደራሲው፣… አቅጣጫ ጠቋሚ መነሻ የሃሳብ ውጥኖችን ጨምሮ፣… በድርሰቱ ሂደት እየጎሉና እየጎለበቱ የሚሄዱ የድርሰቱ መልዕክች፣ የድርሰቱ ካርታ እንጂ የድርሰቱ ጉዞ አይደሉም። በቀጥታ የሚጽፏቸው አይደሉም። ይልቅስ፣ የገጸባሕርያትና የታሪክ ማዕቀፍ ናቸው- የድርሰቱ ጭብጦች።
አዎ፣ ፍቅር እስከ መቃብር፣… የስልጣኔና የኋላቀርነት፣ የነባርና የአዲስ ልማድ፣ የፅናትና የለውጥ ሃሳቦችን ወይም ጭብጦችን ያዘለ ነው።
ነገር ግን በስልጣኔ ወይም በልማድ ላይ ያተኮሩ የሃሳብ ትንታኔዎችን ያቀርባል ማለት አይደለም። የጥናት ጽሁፍ ሳይሆን ልብወለድ ታሪክ ነው።
በባሕል ዙሪያ እጅግ አስገራሚ፣ በገሃድ የሚታዩ ግን ልብ የማንላቸው፣ ላይ ላዩን ብቻ ሳይሆን የውስጡን የጥልቁን፣ በቅንጥብጣቡ ወይም በደፈናው ሳይሆን፣ በተጨባጭና በሰፊው፣ የተመረጡ ዝርዝሮችን የሚያዋህዱና ምልዓትን የሚያላብሱ በርካታ ሃሳቦችን ያስጨብጣል።
ነገር ግን፣ ድርሰቱ ባህላዊ አይደለም። ባሕልን የሚያስጠና ወይም የሚያስተዋውቅ፣ ባሕልን የሚያዳንቅ ወይም የሚያንቋሽሽ አላማ የያዘ አይደለም።
ድርሰቱ የሰብለወንጌልና የበዛብህ ታሪክ ነው።
ነባር ባሕል ያነሳቸዋል፤ ይጥላቸዋል- በዛብህና ሰብለወንጌል።
እሷ የነገስታት የትውልድ ሃረግ የሚተረክላት የፊታውራሪ ልጅ ናት።
እሱ አባትና እናቱ የሞቱበት፣ ዘመድ አልባ የስለት ልጅ ነው።
እሷ በብዙ የታሪክ ሃረጋት የተከበበች፣ እሱ ታሪክ አልባ፣
እሷ ከአጎቷ አዲስ የስልጣን ሃሳቦችን እየሰማች እየተማረች ያደገች፣ ናት።
 እሱ የሺ ዓመታት ሃይማኖታዊ የስነ-ምግባር ስርዓትና የቅኔ ጥበብ ውስጥ የተጓዘ ወጣት ነው። በታሪከኛና በጥበበኛ አድባራት ውስጥ፣ ከጥንት በረዥም ዘመን ተቃኘውን የዜማ ጥበብ የተማረ፣ እጅግ ባማረና በላቀ አስደናቂ ብቃት እንደጉድ የተወራለት ወጣት ነው።
ነባሩ የጥንት ጥበብ… እንደ አዲስ ወደ ከፍታ የሚያደርስ የልህቀት መንደርደሪያ ሆኖለታል።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ በነባር ባሕል ሳቢያ፣ ወላጅ አልባ ስደተኛ ብቻ ሳይሆን፣ “የሚታይ እንጂ የማይበላ ፍሬ” ብለው የሚያወሩበት ባይተዋር ሆኗል።
ሰብለወንጌልም፣ በነባር የጥንት ባሕል የታሰረች የታፈነች ወጣት ናት። ብዙ ነገሯንም ያሳጣታል።
በሌላ በኩል ግን፣ በነባር ባሕል አማካኝነት፣ ማንበብና መጻፍ የምትማርበት እድል ተፈጥሮላታል። ይህም ነው፤ በዛብህና ሰብለወንጌል የሚቀራረቡበት፣… የፍቅር ሕይወትን በጭላንጭል የሚያዩበት የራሳቸውን ዓለም የሚፈጥሩበት እድል!
በእርግጥ፣ ይሄው ነባር ባሕል፣ የኋላ ኋላ ዓለም-ለምኔ የሚያስብል የገሃነም ገጽታውን ያመጣባቸዋል። ያው፤ ፍቅር እስከ መቃብር የተባለው ለምን ሆነና!
ምን ለማለት ፈልጌ ነው?
ትልልቅና እጅግ ጥልቅ ሃሳቦችን፣ አገራዊና ዘመን ተሻጋሪ መልዕክቶችን አሰናስሎ አቀናብሮ የያዘ ድርሰት ነው።
ነገር ግን፣ የሃሳብ ወይም የትንታኔ ድርሰት አይደለም።
 የበዛብህና የሰብለወንጌል ሕይወት ነው- ድርሰቱ።
እንዲህ ሲባል ግን፣ከውስጠ ታዋቂዎቹ የሃሳብ ማዕቀፎች ውጭ፣ የልብወለዱ ታሪክ ብቻውን ይቃናል ማለት አይደለም።
ለዘመናት ከዳበረው ከነባር የቅኔና የዜማ ጥበብ ውጭ፣ ከጥንታዊ ባህልና ከሃይማኖታዊ አውድ ውጭ፣ ከአድባራትና ከልማዳዊ የአከባበር ስርዓት ተነጥሎ፣ የበዛብህ የቅኔ እና የዜማ ልሕቀት ለብቻው በባዶ አየር ሊቆም አይችልም። አለበለዚያ፣ ኦና ይቀራል። የጥበብ አውዱንና የበዛብህን የጥበብ ልህቀት አጉልቶ ማሳየት ካልቻለ፣ የገጸ ባሕሪውን ማንነትና የታሪኩን ትልም ያኮመሽሽብናል።
ነገር ግን፣ ድርሰቱ ሃማኖታዊ አይደለም። የዜማና የቅኔ መማሪያ፣ የታሪክና የባህል ማስጠኛም አይደለም።
የበዛብህና የሰብለ ወንጌል ሕይወት ከነአውዱ፣ አላማና ተግባራቸው፣ አቅማቸውና ብቃታቸው፣ ፍርሃትና ወኔያቸው፣ የውጣውረድ የሞትሽረት ታሪካቸው ነው- ድርሰቱ።


Read 1013 times