Saturday, 11 March 2023 00:00

ጥበብን ሲያከብሩ፣… ጥበበኛውንም።

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ፍቅር እስከ መቃብር፣… የአገራችን የጥበብ ጉልላት ነው። “የአገራችን” ማለቴ፣ የደራሲውን ተዓምረኛ የጥበብ ብቃት ለመንጠቅና “የጋርዮሽ” ብቃት ለማስመሰል አይደለም። “አለንበት” በሚል ስሜት፣ የክብር ክፍፍልና የኩራት ሽሚያ ለመፍጠርም አይደለም።
የጥበብ አዝመራው፣ ከጥበበኛው ደራሲ የፈለቀ፣ የድንቅ ብቃትና የትጋት ውጤት፣ የተትረፈረፈ በረከት ነው። ክብርም ኩራትም፣ የጥበበኛው ነው።
የሌሎቻችን ፋንታ፣ አስደናቂውን የጥበብ በረከት ማጣጣምና ማመስገን ነው። ደግሞም፣ መታደል ነው። “ፍቅር እስከ መቃብር”ን የመሰለ የጥበብ ስራ፣ በየቀኑና በየዓመቱ ይቅርና፣ በአስር ዓመትም የሚገኝ ቀላል በረከት አይደለም።… ጥበብን የማጣጣም እድል የሚያበረክቱልን ጥበበኞች ይብዙልን እያልን ማመስገን፣ የሁላችንም ሃላፊነትና ችሎታ ነው። ማመስገን ከፈለገ ግን፣ አያቅተንም፣ እንችላለን ማለቴ ነው።
ጥበበኞቹ አድናቆትና አክብሮትም ይገባቸዋል። በጥበብ ስራዎቻቸው ከብረዋልና፣… የዚያኑ ያህል ማክበር ያስፈልጋል። በዚህ ቀና መንገድ ነው፣… የጥበባቸው የመንፈስ ልጅነትን፣ የመንፈስ ወራሽነትንና ተካፋይነትን መላበስ የምንችለው። “የአገራችን” ብለን የመናገር ብቃትንም የምናገኘው።
የጥበብ ማማ ጉልላቱን አይተንና አጣጥመን፣ መንፈሳችንንም አድሰንና አበልጽገን፣ በምስጋናና በአድናቆት ካላከበርን፣ ጉድለቱ ለየራሳችን ነው። የጥበበኞቹን ክብር አይደለም የምናጎድለው። እነሱማ በራሳቸው ድንቅ ስራ ከብረዋል።
የጥበብ ነገሥታትን ካላከበርን፣ በመንፈስ ድህነትና ንፍገት መማሰን ይሆንብናል። አነስ-መለስ ያሉ የጥበብ ባለቤቶችንና የጥበብ ፍሬዎችን የማጣጣምና የማመስገን፣ የማድነቅና የማክበር አቅማችንን እያመከንን ማንነታችንን እናራቁታለን። “ማመስገን፣ ማድነቅና ማክበር ለራስ ነው” የሚባለው ለቀልድ ወይም ለወግ ያህል ብቻ አይደለም።
ደራሲ ሀዲስ ዓለማየሁ፣ ባለቅኔው የትያትር ፀሐፊና ገጣሚ ፀጋዬ ገብረመድህን፣ ዛሬ በዘመናችን ደግሞ ሰዓሊ መዝገቡ ተሰማ፣… በየራሳቸው መስክ መጥቀው የወጡ የጥበብ ብርሃናት ናቸው።
ካበረከቱልን የጥበብ ስራዎቻቸው በተጨማሪ፣ የጥበብ ልሕቀትን የማየት እድል የፈጠሩልን የብቃት አርአያዎች ናቸው። እነዚህን ቁምነገሮች ልብ እንድንል የሚያግዝ አጋጣሚ መፈጠሩ መልካም ነው። ይህን እንደ ምርቃት ልትቆጥሩት ትችላላችሁ። ዋናውና ትልቅ ፀጋ ግን፣ የጥበብ ስራቸው ነው - የሀዲስ ዓለማየሁ ድርሰት።
ድርሰቱን ወደ ቲቪ ድራማ ለመቀየር መታሰቡ መልካም ነው። ታዲያ ድርሰቱን ስናከብር ደራሲውንም እናክብር።


Read 869 times Last modified on Sunday, 12 March 2023 11:52