Sunday, 12 March 2023 10:30

የጤፍ ዋጋ ንረቱ ነዋሪውን አስመርሮታል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(6 votes)

- ሚኒስቴር መ/ቤቱ የጤፍ ዋጋ መናር አይመለከተኝም ብሏል
      - በበርካታ የጤፍ መሸጫ ስፍራዎች የሚሸጥ ጤፍ የለም
      - አንድ ኩንታል ጤፍ ከ9ሺ እስከ 10 ሺ ብር እየተሸጠ ነው
        
         በአዲስ አበባ ከተማ ከቀን ወደ ቀን በከፍተኛ መጠን እየጨመረ በመጣው የጤፍ ዋጋ ንረት፣ ነዋሪው ክፉኛ ተማርሯል። በከተማዋ በሚገኙ የጤፍ መሸጫ መጋዘኖችና ወፍጮ ቤቶች ውስጥ ለገበያ የሚቀርብ ጤፍ የለም። ጤፍ ነጋዴዎቹ እንደሚናገሩት ከአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ የሚገባው የጤፍ ምርት ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ እየገባ አይደለም።
በከተማዋ የተለያዩ አከባቢዎች ለጤፍ ሸመታ የወጡ የከተማዋ ነዋሪዎች  እንደሚሉት፤ የጤፍ ዋጋ ጭማሪው ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ ለመግዛት አልቻሉም። ከቀናት በፊት ከ6000-6500 ይሸጥ የነበረው የጤፍ ምርት፣ በአሁኑ ወቅት ከ9ሺ እስከ 10ሺ ብር ጭማሪ ማሳየቱንና ይህም ከመግዛት አቅማቸው ጋር በፍጹም ሊገናኝ እንደማይችል ተናግረዋል። አሁን ወቅቱ ምርት የተሰበሰበበትና  በተሻለ  ሁኔታ ለገበያ የሚቀርብበት ቢሆንም፣ የእህል ዋጋ  በተለይም የጤፍና የስንዴ ዋጋ እንደ ሰማይ እየራቀ መምጣቱ  በአንዳንድ አካባቢዎች የሚደረገውን ኢኮኖሚያዊ አሻጥር የሚያመለክት ነው ተብሏል።
በዕለት ተዕለት የፍጆታዎች እቃዎች ላይ በህገወጥ መንገድ ጭማሪ በሚያሳዩ ወገኖች ላይ አስፈላጊውን እርምጃ እወስዳለሁ ያለው መንግስት ሰሞኑን እየታየ ባለው የጤፍ ዋጋ ንረት ላይ ምንም አይነት እርምጃ ለመውሰድ አለመቻሉ ተገቢነት የሌለውና መንግስት ለዜጎቹ ያለውን ቸልተኝነት የሚያሳይ ነው ሲሉም ነዋሪዎቹ ያማርራሉ።  
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር  አጠቃላይ የኑሮ ውድነቱን በተመለከተ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደማይመለከተው ጉዳዩ ዘርፈ ብዙ ተዋንያን የሚሳተፉበት እንደሆነ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አብራርቷል።  ዋጋ ባልወጣበት ነገር ላይ ኃላፊነት መውሰድ አይቻልም መባሉም ተዘግቧል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አሁን ለተፈጠረው የጤፍ ዋጋ ኃላፊነት "ማንዴት"  እንደሌለውና የንግድ ሥርዓቱን በተመለከተ  በቀጣይ ጥናት አድርጎ  ምላሽ ምላሽ እንደሚሰጥ ነው ያስታወቀው።


Read 4844 times