Saturday, 04 March 2023 11:40

አንድ ላይ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

እኔ ጋደም ስል፣ አንቺ ትነቂያለሽ፤
ለኔ ፀሃይ ስትወጣ፣ በጨረቃ ብርሃን፤
… በክዋክብት ደምቀሽ፣ አንቺ ታልሚያለሽ፤
እስኪ ለጨረቃ፣ እስኪ ለፀሃይዋ፤…
…እስኪ ለክዋክብት
ባንቺ አማላጅነት፣ በእኔ አማላጅነት እንለምናቸው፤
ክረምትና በጋ፣ መዐልትና ሌሊት…
… ደቂቃና ሰዓት እንዳይለያዩአቸው፤
ተቃቅፈው ተዛዝለው፣ አንድ ላይ ይምጡልን፤
እኛም አንድ ላይ፣ አቃቅፈው አዛዝለው፤
በፍቅር ሰረገላ፣ ወደ ሀሴት ህዋ…
… ወደ ደስታ ጠፈር፣ አጅበው  ያብርሩን፤
እያስፈነደቁ በእልልታ ያምጥቁን።
አሜን!አሜን! አሜን!
የራስጌ ማስታወሻ፡- ጉድ ነው! ወደ ትግል ሜዳ ከመውጣቴ በፊት ከደርግ ተደብቄ ከነበርኩባቸው ቦታዎች ባንዱ፣ በአካባቢው ትኖር የነበረችውን ሊበን ወድጃት ነበርና፣ ትግል ሜዳ ከወጣሁ በኋላ ትዝ ብትለኝ፣ ፍቅሬ ተቀስቅሶ ይህንን ግጥም ጻፍኩኝ። በወቅቱ 20ኛ ዓመቴን ይዤ ነበር። ከድል በኋላ እንደሰማሁት፣ ባህር ማዶ እንደወጣች ነች። ትዳር ይዛ ወልዳ ከብዳለች። ይመቻት! እርሷም በራስዋ፣ እኔም በራሴ አለን።
(“ታሪክና ጥበብ የግጥም መድበል”፤ ህላዌ ዮሴፍ፤ 2007 ዓ.ም)




Read 1910 times