Saturday, 04 February 2023 20:34

በፍም እሳት ማቃመስ... (Initiating by fire)

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(1 Vote)

 (ስለአልኬሚ፣ አራቱ የአካል ረቂቅ ባህሪያት - [እሳት፣ መሬት፣ አየር እና ውኃ] ስለ ሥነቁጥር፣ አልፋ እና ኦሜጋ እንዲሁም ደራጎን አንዳንድ ረቂቅ መንፈሳዊ (mystical) ሀሳቦች)
ተፈጥሮ ህብሯ፣ መገለጫ መልኳ (manifestation) እልፍ ነው፡፡ ውሉን ካገኘኸው፣ ከውሻ ጩኸት፣ ከውኃ እናት እንቅስቃሴ ትማራለህ፡፡ ከቴሌስኮፕና ማይክሮስኮፕ በላይ ደመነፍስህን ታምነዋለህ። የተፈጥሮን ውል ካገኘኸው ስለሁሉም ነገር ለመማር ዓይኖችህን መጨፈን ብቻ እንደሚበቃህ ይገባሃል፡፡ ዝም ረቂቅ ጸሎት፣ ዝም በመንፈስ መገናኘት እንደሆነ ይገለጥልሃል። ረቂቁ ነገር ያለው ያልተጻፈው፣ ያልተነገረው ፈጽሞ ሊጻፍ የማይችለው ውስጥ (in the inexplicable) መሆኑን ትቀበላለህ፡፡ ከቀኖና ይልቅ ኅሊና በላጭ መሆኑ ፍንትው ይልልሃል፡፡
ዝሙን መለማመድ፣ የተፈጥሮን ረቂቅ ውል ማሰስ ረቂቅ መንፈሳዊ ፍለጋ (mysticism) ነው። ሚስቲሲዝምን ከምሥራቁ ዓለም የሐይማኖት እና አስተሳሰብ ጽንፍ ጋር ብቻ አያይዘው የሚያስቡ ሰዎች ያስቁኛል፡፡ አፍሪካዊ የቮዶ (vodooo) አማኞችን ጠይቋቸው... ‹‹ነጮች ወደ ቤተክርስትያን ሄደው ተሰባስበው ስለመለኮት ይጮሃሉ፡፡ እኛ ግን እንዲሁ በመደነስ ብቻ መለኮታዊያን እንሆናለን›› ይሏችኋል። (The white people go to church and speak about God. but we simply dance and become God.)
ሚስቲሲዝም የትም አለ፡፡ ‹ስህተተኛው ታናሽ ወንድማችን› የሚሉትን ዘመናዊውን የሰው ልጅ ሽሽት በኮሎምቢያ አይደፈሬ የተራራ ሰንሰለቶች የሚኖሩት የኮጊ(Kogi) ጥንታዊ ቅዱስ ሕዝቦችም አኗኗርም ሆነ በእናትህ ‹ዓይኔ ተርገበገበ ማንን ሊያሳየኝ ይሆን?› ብሂል ውስጥ ሚስቲሲዝም አለ፡፡ አያቶችህ ‹‹ወፍ መለሰችኝ፤ ‹ስቅ አለኝ ማን አነሳኝ፤ እጄን አሳከከኝ ምን ላገኝ ይሆን?› ሲሉ ምን ማድረጋቸው መሰለህ? በምክንያት፣ በስግብግቡ የሰው ልጅ አእምሮ ከማይደረስበት ከረቂቁ ተፈጥሮ ጋር ሲመሳጠሩ እኮ ነው!
ቢሆንም ዝሙን ጭጩን በምልዓት ለመዋረስ የተዘጋጀን ስላለመሆናችን (since we are incapable of being silent) ከማይነገረው ከዝምታው ጥልቅ ጥቂት ሀቲቶችን ለማፍካት መውተፍተፋችን ጤንነት እንደሆነ ተቀብለን እንቀጥላለን...


                              
ምስል- አንድ መሰረታዊ የአልኬሚ ትዕምርቶች (symbols)
መጽሐፈ ሥነ ፍጥረት ‹‹እሁድ በመጀመሪያው ሰዓተ ሌሊት ፬ቱን ባህሪያት ውኃ፣ መሬት፣ አየር፣ እሳት) ካለመኖር (እምኀበ አልቦ ሀበቦ) ሰራቸው ይለናል፡፡ እነዚህ የሰው ልጅ አካል የተቀመረባቸው አራት የስጋ ወይም የአካል ባህሪያት እሳት፣ ውኃ፣ መሬት እና አየር የረቂቁ የአልኬሚ ጽንሰ ሀሳብም መሰረታዊ ትዕምርቶች(symbols) መሆናቸውን ልብ ማለት ያሻል፡፡  ውኃ፣ እሳት፣ አየር፣ መሬት በየትኛውም የዓለም ክፍል፣ በየትኛውም ቋንቋ፣ ዘመን፣ መንገድ መንፈሳዊ ሐሰሳ የሚያደርጉ መሰጠቱ ያላቸው ሁሉ የሚጨባበጡባቸው ስጋችን የታነጻባቸው ባህሪያት ስለመሆናቸው በብዙ ታትቷል፡፡
ረቂቃዊያን (mystics) ግን መቃተት፣ መቃበዛቸው የቱንም ያህል ሰርቦላ ቢሆን ዞሮ ዞሮ ያው ስሪታቸው የወል(communal) ነው፡፡ የውኃ፣ አየር፣ የመሬት እና የእሳት... ሕልማቸውም ልዩነት የለውም፡፡ በየትኛውም መንገድ ያምልኩ ያመስግኑ ዞሮ ዞሮ ራስን ማብቃት፣ የሰውን መለኮታዊ ማንነት ማንቃት፣ ከስሜት፣ ከስግብግብነት... አዙሪት መንጻት ዓይነት... ሆኖም የተሰራንባቸው አራቱ አካለ ባህሪያት መግነጢሳዊ ኃይለ መልኮች (form of energies) እንጂ እንዲያው በሌጣው የሚፈከሩ ቁሳዊ ‹ኢንቲቲስ› አይደሉም፡፡ እነዚህን አራት ስነባህሪያት በቅጡ በማጥናትና በማሰልጠን በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ ያንቀላፋውን የደራጎን ጉልበት ማንቃት እና ወደ ቀደመ መለኮታዊ ማንነቱ መመለስ ይቻላል፡፡ እንዴት የሚለውን ዘግየት ብለን እንቀጥልበታልን፡፡ በቅድሚያ አራቱን ኃይለ ባህሪያት አንድ በአንድ እንያቸው...  
 

                         
ምስል - ሁለት አራቱ የአካል ባህሪያት እና መገለጫቸው
እሳት

    እሳት ሥሪቱ ፍጹም የእንከንየለሽነት፣ የምኅረትየለሽነት መሆኑ እሙን ነው። የእሳትንም ያህል ፍጹም ቅን፣ ገር እና በስነተፈጥሮው ቀጥተኛ ነገር መኖሩን አላውቅም፡፡ እሳት ከብሉያት፣ ነብያት፣ ወንጌላዊያን፣ ከአፈታሪኮች እና ባለቅንያት ዘመን ጀምሮ ብዙ የተባለለት መለኮት አከል ረቂቅ ክንውን ሆነ፡፡ የሰው ልጅ ከተሰራባቸው አራቱ የስጋ ባህሪያት ውስጥ ምናልባት ከአየርም በላይ እጅግ ረቂቁ ይኸው እሳት ሳይሆን አይቀርም፡፡ እሳት ሲፈጅ፣ ሲበላ እንጂ ሲያርፍ ማደሪያው የት፣ ሲግለበለብ መከሰቻው ከወዴት እንደሆንስ ስንኳ የሚያውቅም የለም፡፡ እሳት የነካውን ሁሉ የሚያነጻ (purifying) ወይም የሚያገረጣ (terrifying) አቅም አለው፡፡ ቁም ነገሩ ለየትኛው አሰልጥነነዋል የሚለው ብቻ ነው፡፡
እሳት ንጹህ ነው፡፡ ቅን ነው፡፡ ገር ነው። ግን ደግሞ አውዳሚ፣ ጨራሽ፣ ፈጅ፣ ቀሳፊ ቁጡም ነው፡፡ የዚህ ረቂቅ የነበልባል ፍጥረት ጥሪ እና ምሪት ሰብዓዊነትን ማበልጸግ መሆኑ ጥንት ከአፈታሪክ፣ ከነፕሮሚተስ ዘመን ጀምሮ ይታወቃል፡፡ ሁላችንም ውስጥ ስንረሳው እንደ ‹ዶርማንት ቮልካኖ› ወይ በተኛበት ሳር እንደሚበቅልበት ዘንዶ ሊያንቀላፋ በጎሬያችን ተወሽቀን እንድናጎላጅ ሊያሰንፈን፣ ስናነቃው ግን ከራሳችን አልፎ ለዓለሙ በሙሉ ሊትረፈረፍ የሚያስችል እሳታዊ ኃይል በውስጣችን አሸልቧል፡፡ የረቂቁ መንፈሳዊ ሽግግር ጠበብት አልኬሚስቶች የሰው ልጅን እሳታዊ ባህሪይ ራስን ከመግዛትና ለራስ ከሚሰጥ ዋጋ ጋር ያያይዙታል። የእሳት ገዥ ሥነ ባህሪ(Dominant form of energy) ያላቸው ግለሰቦች ለሚከውኑት ማንኛውም ተግባር ጥልቅ ፍቅር (passion) ይኖራቸዋል፡፡ የኃይል ባለቤቶችና እና አንደበተ ርቱዓን ናቸው፡፡ ሆኖም የሚንቀለቀል ነበልባላዊ ፍላጎታቸውንና ጉልበታቸውን በጊዜ መግራት ካልቻሉ ደፋርነታቸው፣ እንግዳነታቸው እንደ ብልግና(arrogancy) ሊቆጠርባቸው ይችላል፡፡
ውኃ


‹‹In one drop of water are found all the secrets of all the oceans; in one aspect of you are found all the aspects of existence.››  Kahlil Gibran
‹‹The sound of water is worth more than all the poets’ words.›› – Octavio Paz
ውኃ ሕይወት ነው፡፡ ንቅናቄ (movement) ደግሞ ይሄን የሕይወትነት ጸጋውን ያድስለታል። የወንዝ ውኃ ከኩሬ መብለጡ ንቅናቄ ሕይወት ቢሆን አይደለምን? ውኃ ያድሳል፤ ያነጻል፤ ይፈውሳል፤ ያሻግራል፡፡  ግን ደግሞ ይሸረሽራል፤ ይበረብራል፤ አለት ይሰባብራል። ቅርጸ ተለዋጭነቱም (በጠጣር፣ በፈሳሽና በትነት መልክ መከሰት መቻሉ) ተሻግሮ አሻጋሪነቱ ይገለጣል፡፡ አካላችን የሚያድሰው ዋነኛው ኃይል እሱ ነው፡፡
የውኃ ገዥ(Dominant) ሥነ ባህሪይ ያላቸው ሰዎች የተረጋጉ፣ ጸጥተኞች፣ በሰከነ ከባቢ ሳይቀር ገለል ማለትን የሚመርጡ ቁጥቦች ናቸው፡፡ በተጨማሪም ብልሆች፣ ጥልቆች፣ ረቂቆች፣ በራስ መተማመን ያላቸው፣ ፈተናን መቋቋም የሚችሉ ይሆናሉ፡፡
አየር


አየር ከደመነፍስ፣ ከመንፈስ (spirit) ጋር የተያያዘ ስነ ባህሪ ነው፡፡ ረቂቅ ነው፡፡ አይያዝ፣ አይታይ፣ አይጨበጥም፡፡ ሆኖም በዙሪያ ገባው ላይ በሚፈጥረው ተሻጋሪ ተጽዕኖ በቀላሉ እንረዳዋለን፡፡ ረቂቅ ቢሆንም ቅሉ እንደ አንዳች፣ ወይ እንደ ጠባቂ መልአክ ዘወትር አጠገባችን መሆኑን በውል እንገነዘባለን፡፡ እንደ እሳት እና ውኃ ሁሉ የለውጥ አቀጣጣይ (catalyst)፣ እንደ ውኃ ሰጋር (ተንቀሳቃሽ) ባህሪይነት አለው፡፡
የአየር ገዥ (Dominant) ሥነ ባህሪ ያላቸው ሰዎች ቅን፣ ቻይ፣ ሰዎችን መመዘን የማይወዱ ነጻ ሰዎች ናቸው፡፡ በተጨማሪም  አየር የዕውቀት የመብቃት ሥነ ባህሪ ነው፡፡
መሬት


መሬት ከአራቱ የአካል ባህሪያት በላይ የመስከን፣ የመርጋት፣ ስር የመያዝ ምልክትነት አለው፡፡ የመሬት መሪ ሥነ ባህሪ ያላቸው ሰዎች መጋቢ (በመንፈስ፣ በደመነፍስ)፣ አበልጻጊ፣  ተንከባካቢዎች፣ ታማኞች፣ ቅኖች፣ ጽኑዎች ናቸው፡፡
ለምሳሌ ባለሙያዎች የሀዲስ ኪዳንን አራት ወንጌላዊያን ዘገባዎች ባህሪያት በማጥናት ብቻ ወንጌላዊያኑ የነበራቸውን ገዥ (Dominant) የአካል ባህሪያት ማመላከት ችለዋል፡፡
ማቴዎስ (አየር)  - የኢየሱስ ክርስቶስ አስተምህሮቶች በመስበኩ....
ማርቆስ (እሳት) - በወንጌሉ ላይ የኢየሱስ ክርስቶስ ተግባራት ላይ በማተኮሩ...
ሉቃስ (መሬት)  - በወንጌሉ ላይ የኢየሱስ ክርስቶስ ምድራዊ ሕይወት ቀለም ላይ በማተኮሩ...
ዮሐንስ (ውኃ) - በወንጌሉ እና ራዕዩ ላይ የኢየሱስ ክርስቶስን ረቂቅ ምስጢራዊ ፍኖት ለማቅለም በመምረጡ...
ጥቂት ነጥቦች ስለአልኬሚ
የረቂቁ አልኬሚ ፍልስፍና መስራች ስሙ ሐርሜስ ትሪስሜጊስተስ (Hermes Trismegistus) ይባላል፡፡ እግዚአብሔራዊ አረዳዳችን ላይ ከቀኖና የተሻገረ ረቂቅ አምልኮአዊ ፍልስፍና ካረቀቁ ሰዎች ቀዳሚው እሱ ሳይሆን አይቀርም፡፡ (God is a circle, whose centre is everywhere, and His circumference nowhere.) ግብጻዊ ቢሆንም ግሪካዊያን የሚጠቀሙባቸውን 42 የሚደርሱ መጻሕፍት የጻፋቸው እርሱ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ሰውዬው ፍጹም የላቀ ሰው ነበር፡፡ የሳይንስ፣ የሐይማኖታዊ ዕሳቤዎች፣ ሒሳብ፣ ጂኦሜትሪ፣ አልኬሚ፣ ሕክምና፣ ፍልስፍና እና አስማት የመሣሠሉ ጥበባት ሁሉ መስራች ነው ይባልለታል። ሙሴ በእስራኤል ታሪክ ታላቁ ነብይ ሆኖ እስራኤላዊያንን ከአራት መቶ ዘመናት አገዛዝ ቀንበር ነጻ ከማውጣቱ በፊት ከኢትዮጵያዊው ዮቶር ሌላ በዚሁ ጥቁር ግብጻዊ ሐርሜስ ትሪስሜጊስተስ ክትትል እና አስተምህሮ ስር እንዳደገ የሚነገር ታሪክ አለ፡፡
በሌላ በኩል በመጽሐፍ ቅዱሳዊ አቆጣጠር፣ ከአዳም ስደት በኋላ ከጥፋት ውኃ በፊት በግብጽ እንደኖረ የሚተረክም ሌላ የታሪክ ፈርጅ አለ፡፡ አንዳንዶች ትሪስሜጊስተስ ከጥፋት ውኃ በፊት የኖረው የመጽሐፍ ቅዱሱ ሔኖክ (የቅዱስ ቁርዓኑ እድሪስ) ነው ይላሉ፡፡ ሌሎች በአንጻሩ ሔርሜስ ትሪስሜጊስተስ ፈጠራ፣ ስያሜው ራሱ ከግሪኩ የጣዖት አምላክ ሔርሜስ እና ከግብጹ ቶት ተዳቅሎ የተገኘ ፍጹም ምናብ ወለድ ሰው ስለመሆኑ ይከራከራሉ፡፡
ሆኖም ብዙ ክፍለዘመናት በኋላ ብቅ ብሎ መዳን ረቂቅ የአልኬሚ ሽግግር መሆኑን በተግባር ያሳየው ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ። ኢየሱስ አልኬሚስት ነበር፡፡ ከእናቱ ጋር በቃና ዘገሊላ በታደመበት ሰርግ ለሰርገኛው የሚቀርብ ወይን በተሟጠጠ ጊዜ ውኃውን ወደ ወይን ቀየረ፡፡ በሌላ ጊዜ ጥቂት ቁራሽ ዳቦዎችንና ጥቂት ዓሶችን በበረከት አባዝቶ ሺዎችን መግቧል፡፡ እንደ ክርስትና አስተምህሮ ፍጽምናውን መቀዳጀት የሚቻልበትን መንገድ የቀየሰ ብቸኛው መሲህ እርሱ ነው፡፡
የመጀመሪያዎቹ አልኬሚስቶች ጠቢባን ሁሉም ጽድቁም፣ ኩነኔውም፣ ጋኔሉም ያለው ውስጣችን መሆኑን ያወቁት አይመስልም። ከኢየሱስ መወለድ በፊት ለሺህ ዘመናት የተፈራረቁት አልኬሚስቶች የሞትን መድኃኒት፣ ወይ ብረትን ሁሉ ወደ ወርቅ የምትቀይረውን ተዓምረኛ ድንጋይ ይፈልጉ ዘንድ በከንቱ ቃተቱ። ከኢየሱስ መወለድ በኋላ በመካከለኛው ዘመን በተለይ በአውሮፓ የነበሩ የአልኬሚ ጠበብት በአንጻሩ ቀቢጸ ተስፋውን እርግፍ አድርገው ትተው የክርስቶስን አብነት ተከተሉ፡፡ ኢየሱስ ከውልደት እስከ እርገት የተጓዘባቸውን ረቂቅ ትእምርታዊ ሽግግሮች ከሰባቱ የአልኬሚ የልውጠት ደረጃዎች (The 7 stages of alchemy) ጋር እያነጻጸሩ በምሥሎች ጭምር አስደግፈው ጻፉ፡፡ እንደ አጠቃላይ በምልዓተ ዓለሙ የሚከናወነው፣ የመፍካት፣ የማበብ፣ የማፍራት፣ የመገርጣት፣ የማርገፍ የማቆጥቆጥ፣ የመፍረስ፣ የመበስበስ... ሂደት ሁሉ የዚህ አልኬሚያዊ ሂደት መገለጫ ነው፡፡
ለመሆኑ ኢየሱስ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዳይካተቱ ከተገፈተሩት መጻሕፍት አንዱ በሆነው የቶማስ ወንጌል ላይ ‹‹በውስጣችሁ ያለውን እሱን ካወጣችሁት ያድናችኋል። በውስጣችሁ ያለውን ያንን ማውጣት ካልቻላችሁ ግን መጥፊያችሁ ይሆናል፡፡›› ሲለን ምን ማለቱ ነበር? (When you bring forth that within you, then that will save you. If you do not, then that will kill you.)
በውስጣችን ያለው ያ ስናሰለጥነው ሊያድነን፣ ልናወጣው ባንችል ግን ሊገድለን የሚችል እርሱ ምንድን ነው? ኢየሱስ በራሳችን እና በዙሪያችን የከበበን የነተበ ፈሪሳዊ ዓለም ላይ እንድናምጽ እያተጋን አልነበረምን? የራሳችንን መስቀል ተሸክመን ወደ ራሳችን ቀራኒዮ እንድንዘምት... ልክ እንደተጋዳሊ (Hero ) ከራስ ለሚልቅ ዓላማ እንድንሰለፍ እያነቃን? ዋሻ ውስጥ ተጋድሞ የጸሐይቷን መውጣት ሲጠብቅ እንቅልፍ ጥሎት ዘመናት እንደሚፈራረቁበት፣ ሳር እንደሚበቅልበት ዘንዶ በውስጣችን ያንቀላፋውን ያንን ስናነቃው፣ ስናሰለጥነው ሊያጀግነን  የሚችል ደራጎን ማስደንበር እንችል ዘንድ እያተጋን?  
 
ምስል ሦስት - ስፔናዊው እውቅ ሰዓሊ ፒካሶ በበርካታ የቀለም ቅብ ምስሎቹ ላይ ራሱን በበሬ (Bull - Dragon) በመመሰል ይታወቃል፡፡
ደራገን (Dragon - Serpent) ከአልኬሚ (Alchemy) ጽንሰ ሐሳብ ጋር ተያይዞ የሚነሳ እሳት እንደሚተፋ፣ በክንፍ እንደሚበር የሚታሰብ የእባብ ዝርያ እንሰሳ ነው፡፡ ነገርግን ደራጎኖች የሰው ልጅ ስነልቦናን እንደጥናት ዘርፍ ከመመስረቱ ሺህ ዘመናት በፊት ለጭቁኑ አእምሮው(shadow) መገለጫ ይሆኑት ዘንድ የፈጠራቸው ምናባዊ መመሰያዎች እንጂ በሕልውና የነበሩ ፍጥረታት አይደሉም፡፡
ደራጎኖች ውስጣችን የታመቀው ስናነቃው፣ ስናሰለጥነው ሊያመጥቀን ሊያስፈነጥረን የሚችል ንጹህ ንቁ ኃይል አመልካቾች ናቸው፡፡ ደራጎኖች ከመገራታቸው ከመታረቃቸው በፊት ስግብግቡን አኔነት(ego) ይሸከማሉ፡፡ ደራጎኖች መጀመሪያ ከሸለብታቸው ሲቀሰቀሱ አፍራሽ፣ አደፍራሽ ናቸው፡፡ ከተገሩ በኋላ ግን የነቃውን እነ (divinity) ይመስሉታል፡፡ ሽግግሩ ዘመናትን ሊወስድ በአብዛኛው ላይቋጭም ቢችልም ቅሉ...
የደራጎኑ ጌታ ገበሬም ይሁን ሐያሲ የደራጎኑን ቁጣ ማስከን መግራቱን እስኪሰለጥንበት ሁሉንም ማተረማመሱ፣ ማፈራረሱ አይቀርም። ይህ በድራጎን የተመሰለ እምቅ ኃይል በሁላችንም ውስጥ ይገኛል፡፡ የሰው ልጅ አካል ከአፈር፣ ከአየር፣ መሬት እና እሳት ኃይለ ባህሪያት(form of energies) ተሰራ ብለናል። ደራጎኖች በአካል ላይ የሚሰለጥኑ ገዥ ኃይላት እንደመሆናቸው አካል የተሰራንባቸውን አራት ባህሪያት (ውኃ፣ እሳት፣ መሬት፣ አየር) ይወርሳሉ። በዚህም አግባብ በሰው ልጆች እዝነ ልቦና ውስጥ አራት ዓይነት የድራገን ኃይለ ስሪቶች ይኖራሉ፡፡ ሆኖም ምንጊዜም አንደኛው ኃይለ ስሪት ገዥ(dominant) ሆኖ መውጣቱ ግዴታ ይሆናል፡፡ ገዥውን ስነ ባህሪይ ለይቶ ማወቅ ብሎም ማሰልጠን ደግሞ የተስተካከለ ሰብዕና የላቀ ኃይል ያላብሳል፡፡
(ይቀጥላል)

Read 1060 times