Saturday, 04 February 2023 18:39

በተበጣጠሰ ሃሳብ ተበታትኖ መፍረስ አለ። ሕይወትን በሚያዋህድ ጥበብ መትረፍስ ይቻላል?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

 አንዳንዴ ከብዙ ጥረት በኋላ፣ የሰላም ንጉሥ ወይም የፍትሕ መንግሥት ይመጣና፣ ለሰዎች እፎይታን ይሰጣል። ከከተማ ወንበዴና ከወሮበላ፣ ከበረሃ ሽፍታና ከጨካኝ ወንጀለኛ፣ ከጭፍን አመፅና ከትርምስ የሚያድን ሕግና ሥርዓትን ይፈጥራል። ወይም ነባር ጅምሮችን ያፀናል፤ ያሻሽላል።
አንዳንዴ ደግሞ፣ ሕግና ሥርዓትን የማስከበር ግዴታ የተሸከመ መንግሥት፣ በተቃራኒው አበሳውን እያግተለተለ ያመጣዋል። ኃላፊነቱን በአናቱ ገልብጦ፣ ቁም-ስቅል የሚያሳይ ይሆናል። ዜጎችን የሚፈጅና የሚያሰቃይ፣ የሚዘርፍና የሚያዋርድ፣ እብሪተኛ ንጉሥ ወይም አምባገነን መንግሥት፣ አገሬውን እያተራመሰ ያስጨንቃል።
በዚያ ክፉ ዘመን ቤተመንግሥት ማለት፣ ንፁሐን ዜጎችን ብርክ የሚያስይዝ አስፈሪ አምባ ይሆናል። ፓርላማው፣ ባለስልጣናትን የሚቆጣጠር የሕግ አለኝታ ከመሆን ይልቅ፣ አገሪቱን የሚቀራመቱበትና ዜጎችን ኪስ በርብረው አራግፈው የሚያራቁቱበት የሥልጣን ቅርጫ ይሆናል።
ስርዓት የተበላሸ ጊዜ፣…ፍርድ ቤቶች የባለስልጣናት መገልገያ፣ ማስመሰያና መደራደሪያ ቦታዎች ይሆናሉ። ፖሊሶች የሰላማዊ ሰዎች መተማመኛ እና አለኝታ ከመሆን ይልቅ አስፈሪ ተኩላ ይሆናሉ።
የሕግ ሰይፈ መጽሐፍና የፍርድ ሚዛን የያዘችው የፍትሕ አድባር፣… ለታይታ ብቻ እንደቆመች ትቀራለች። “ለታይታ ቆመች እንጂ፣ ለፍትሕ ዓይኗ ተደፍኗል” ብለውን ይማረሩባታል። ቅሬታቸውንም ለመግለፅ ዓይኗን በጨርቅ ይሸፍኗታል። በእርግጥ የዓይኗ ግርዶሽ፣ የኋላ ኋላ፣ “የሰው ፊት አይታ አታዳላም” የሚል በጎ ትርጉም ተሰጥቶታል። እንጂ፣… የታሪኩ መነሻ ግን የቅሬታና የምሬት ስሜት ነው። “ለፍትሕ ዓይኗን ጨፍናለች፤ ታውራለች” የሚሉ ዜጎች ናቸው፤ በአመፅ መንፈስ አይኗን በጨርቅ የጋረዱባት።
“ቪ” የተሰኘው አመፀኛ ግን፣… ቅሬታውን በቀላል መንገድ ለመግለጽ አልፈለገም (V For Vendetta በተሰኘው ፊልም)። አመፀኛው ተበዳይ፣… የሕይወት ዘመን ምሬቱ በዋዛ አይወጣለትም። የመንግሥት ሥርዓትን ከፖሊስ እስከ ፓርላማ፣ ከፕሮፓጋንዳ አውታር እስከ ቤተ መንግስት ድረስ ሁሉንም ለመናድ ቆርጧል።
የተሻለ ለውጥና ስርዓት እንደሚመጣ እርግጠኛ አይደለም። መንግስትን የማፍረስና የመገንደስ አላማ ላይ ነው ያተኮረው።
ለጊዜው ግን፣ አንዲቷን ሐውልት ለማፈንዳት ወስኗል። አዎ፣ በክፉ ስርዓት ሳቢያ አገሬው የምድር ሲዖል ሆኗል። መንግስትና ፖሊስ፣ አቃቤ ህግና ፍርድ ቤት ሁሉ፣… “ለፍትሕ” ታስበው፣ የተዋቀሩ ተቋማት በሙሉ፣ በተቃራኒው በበደልና በግፍ መዶሻ እለት በእለት አገርን ይወቅራሉ።
አመፀኛው ሰውዬ አሻፈረኝ ለማለት የተነሳው ግን እንዲህ በደፈናው ለአገርና ለፍትህ በማሰብ አይደለም። በግል ተበድሏል። ስጋና ነብሱን አቃጥለውበታል።
ለዚህም ነው ማመፁ። ሐውልት ማፈንዳቱ። ታዲያ እንደ መጨረሻ ግብ አይደለም። አመፁን በይፋ የሚያሳውቅበት፣ “ሀ” ብሎ የሚያውጅበት፣ የመጀመሪያው ደወል ነው፤ የእለቱ አመፅና ፍንዳታ። ከታሪከኛው ፍርድ ቤት አናት ላይ በክብር የተተከለው የፍትሕ ሐውልት ላይ፣ ፈንጂ ጠምዶ አዘጋጅቷል።
በሚቀጥለው ዓመት፣ በዛሬዋ እለት፣ የአገሪቱን ግዙፍ ፖርላማና ቤተመንግስቱን አፈነዳለሁ ብሎም ቃል ይገባል። ዜጎች በዚያው እለት በአመፅ ወደ አደባባይ እንዲወጡም ይጠይቃል። ፓርላማውን (ቤተመንግስቱን) ሲያፈነዳ በእልልታና በሆታ እንዲያጅቡት ነው? ፍንዳታው ርችት አይደለም። ግን የተስፋ ብርሃን ይሆንላቸዋል ብሎ አስቧል። ማን አሰበ? ማን አፈነዳ?
እንግዲህ ስለ አመፀኛው ሃሳብና ተግባር ትንሽ አውርተናል። ማን እንደሆነ ግን አላወቅንም። ስሙን እንኳ አልተናገርንም። የፊልሙ ርዕስ እንኳ፣ “ቪ” ከሚል ቁንፅል ፊደል በስተቀር ስሙን አይገልጽልንም።
እንዲያውም፤ ቪ የሚለው ፊደል የሰውዬውን ስም ሳይሆን፤ የሰውዬውን ሃሳብና ተግባር የሚወክል እንደሆነ ይነግረናል - V For Vendetta በማለት። በፊልሙ ውስጥ የትረካው ሌላኛዋ ዋና ገፀባሕሪ ግን ሰውዬውን ትፈልጋለች። ሃሳብና ድርጊቱን ብቻ ሳይሆን ሰውዬውን።
እንዲህ ትላለች።
Remember, remember
The 5th of November
The gunpowder treason and plot
I know of no reason
Why the gunpowder treason
Should ever be forgot
የሰውዬውን ሃሳብና ተግባር፣ ዓላማና አመፅ መረሳት የለብሽም ተብላ ተምራለች።
እሷ ግን ስለ ሰውዬው ትጠይቃለች። ሰውዬውን ማስታወስና አለመረሳትስ? በተቆርቋሪነት ትሞግታለች።
But what of the man?
I know his name was Guy Fawkes... and I know in 1605, he attempted to blow up the Houses of Parliament.
But who was he really? What was he like?
We are told to remember the idea and not the man.
Because a man can fail. He can be caught, he can be killed and forgotten.
But 400 years later... an idea can still change the world.
I have witnessed firsthand the power of ideas.
I’ve seen people kill in the name of them... and die defending them.
But you cannot kiss an idea... cannot touch it or hold it.
Ideas do not bleed. They do not feel pain.
They do not love.
And it is not an idea that I miss.
It is a man.
A man that made me remember the 5th of November.
A man that I will never forget.
ሰውዬውን ሳይሆን ሃሳቡን እንድናስታውስ ነው የተነገረን ትላለች ጀግናዋ ገፀባሕርይ - የፊልሙ መክፈቻ ላይ።
ሰውዬው እንደ ወንበዴና እንደ አሸባሪ በመንግስት ተይዞ ህዝብ በተሰበሰበበት አደባባይ ሲሰቀል ያሳያል ፊልሙ።
የታዋቂዋ ተዋናይት ደግሞ፣… እንዳንረሳ እንዳንዘነጋ፣ እንድናስታውስ እንድንዘክር ትወተውተናለች። Remember, Remember, The Fifth of November? የዕለቱን ድርጊት ወይስ ሰውዬውን?
ሰውዬውን ሳይሆን ሃሳቡን እንድናስታውስ ነው የተነገረን ትላለች በቅሬታ። በእርግጥ፣ “ሃሳቡን አስታውሱ” የተባለው አለምክንያት እንዳልሆነ ታውቃለች።
“ሃሳብ” እንደ ሰው አይደለም። ሃሳብ፣…ጊዜና ቦታ አይገድበውም።
ሰውዬው ሊታመም ሊሞት ይችላል። ወይም ጠላቶቹ ሊያስሩት ሊገድሉት ይችላሉ።
ስህተት ቢሰራ፣ ተግባሩ ቢሰናከል፣ ጥረቱ ሁሉ መና ይቀራል።
ሴራው ተነቅቶበት፣ አሳዳጆቹ ደርሰውበት፣ እቅዱን ያከሽፉበታል፤ ያጠመደውን ያመክኑበታል።
ሃሳብ ግን አይታመምም፤ አይሞትም። ከመቶ ከሁለት መቶ ዓመታት በኋላም፣ አያረጅም። እድሜህ አብቅቷል አይባልም። በካቴና በሰንሰለት እጅ እግሩ አይታሰርም። ሃሳቦች እንደጠመንጃ እንደ ፈንጂ በነጣቂ አይወሰዱም።
ሃሳብ ከእልፍ ዓመታት በኋላም፣ በሰዎች ዘንድ ይሰርጻል። የተለያዩ ሰዎች እንደየዝንባሌያቸውና እንደየአቅማቸው፣ እንደየአገራቸው ሁኔታና እንደየዘመኑ ቴክኖሎጂ፣ ሃሳቡን ተገንዝበውና አክብረው ያስፋፉታል፤ ወደ ተግባር ይተረጉሙታል።
ለዚህ ነው፣ ሰውዬውን ወይም ተግባሩን ሳይሆን ሃሳቡን አስታውሱ መባሉ።
ግን ሰውዬውስ? በማለት ትጠይቃለች- ጀግናዋ አፍቃሪው። ሃሳብ አይታይም፤ አይጨበጥም ትለናለች። ሃሳብን አይዳስሱትም። ሃሳብን አያናግሩትም በማለት፣… ትኩረቷ ከሰውዬው ጋር እንደሆነ በናፍቆት ትገልጻለች።
“ሃሳብን መውደድ” የሚሉት ነገር ቢኖር እንኳ፣ ከመውደድ አልፋ እጅግ ሃሳብን ብታፈቅረውም እንኳ፣ እንዴት ብላ ታቅፈዋለች? የት አግኝታውስ ሃሳብን ትስመዋለች?
ሃሳቡንና አላማውን ማስታወስ፣ ተግባርና ታሪኩን መዘከር ብቻ ሳይሆን፣ ሰውዬውን ማሰብ ያንን ጀግና በአካል ማግኘት ትፈልጋለች።
በአንድ በኩል፣ ሃሳብን ወይም ታሪክን ብቻ በቁንፅል በማውለብለብ፣ የሰዎችን ሕይወት የመዘንጋት ሰበብ ከመፍጠር እንድንታቀብ እየገሰፀችን ሊሆን ይችላል።
ደግሞምኮ፣ የተሳሳተ ሃሳብና የተዛባ ወሬ ይዘን ነው፣… በእነዚሁ ሰበብ የሰዎችን ሕይወት ለመማገድ የምንቻኮለው።
ሃሳብንና አላማን፣ ተግባርንና ንብረትን፣ የግል ማንነትና ህልውናን አንድ ላይ የሚያጣምር የሚያዋህድ አስተሳሰብ ያስፈልገናል።
በሌላ በኩልም፣ የልብወለድ ፈጠራ ውስጥ ዋና ዋናዎቹን ሶስት ገጽታዎች መጥቀሷ ነው።
አንደኛ ነገር፣ የፈጠራው ጠቅላላ መልዕክት ወይም የድርሰቱን ሁለመና የሚቀርጽ አቃፊ መንፈስ “ጭብጥ” ወይም theme ይሉታል። ይሄ እንደ ሃሳብ ነው።
ተግባርና ታሪኩስ? ሁለተኛው ነገር ይሄ ነው።
የድርሰቱ ትረካ፣… የድርጊት ውጣ-ውረድና እጥፋት፣ የመንስኤና የውጤት ሰንሰለት፣ የሰበብና የመዘዝ ጅረት፣ ሴራ (plot) ይሉታል። ከሰውዬው ድርጊትና ታሪክ ጋር ይዛመዳል።
ሦስተኛ ነገር፣ “የሰውዬው ማንነት” ማለቷ ነው። ይህም ገፀ-ባሕርይ (ካራክተር) የሚባለው የድርሰት ገጽታን ያመለክታል።
የልብ ወለድ መፅሐፍ፣ ፊልም ወይም ትያትር፣… ሦስቱንም የሕይወት ገጽታዎች አጣምረው በምልዓት ያዋሀዱበትና የገለጹበት ብቃት ነው፤ የጥበባቸው ልክ።
አንዱ ገፅታ፣… ለብቻው ያለ ሌላው በሕይወት አይቆይም።
ጥቅል የሃሳብና የመንፈስ ማዕቀፍ ባይኖረው ወይም ቢጎድለው ምን ማለት ነው? ደራሲው ምን ይፅፋል? ፊልም ሰሪው ምን ያሳየናል? ድርሰቱ ውስጥ መግባት ያለበትና የሌለበት፣ ፊልሙ ላይ መታየት የሚኖርበትና የማይኖርበት ነገር ለይቶ ማወቅና መወሰን አይችልም። ለተመልካችም ቅዠት እንደማየት ነው። ቅዠት ባይሆን እንኳ እንደ ሰርከስ፣ ቁርጥራጭ ትዕይንት ይሆንበታል። አንባቢም፣ ከምዕራፍ ምዕራፍ፣ ከአንቀጽ አንቀጽ፣ አራምባና ቆቦ የሚረግጥ፣ ጭራና ቀንዱ የማይታወቅ፣ የገለጻዎችና የትረካዎች ብጥስጣሽ ግርግር ይሆንበታል።
ኪነጥበብ “ጥቅል የሃሳብና የመንፈስ ማዕቀፍ ያስፈልገዋል”። እንዲህ ማለት ግን፣ ትንታኔ ማቅረብ ማለት አይደለም። የትረካ ክስተቶችና ድርጊቶችን እንደየክብደታቸው ለመምረጥና ቅጥ እንዲይዙ፣ በትክክልም ለማቀናበር ነው-የጭብጥ ፋይዳ።
በእርግጥ፣ ድርጊቶችና ክስተቶች፣ አየር ባየር የሚመጡ አይደሉም። የሰዎች ድርጊቶች ናቸው። በሰዎች ላይ የሚደርሱ ክስተቶች ናቸው። የገጸ-ባህርያትን ማንነት የሚያንጸባርቅ ታሪክ ነው፤ የድርጊትና የክስተት ትረካው።
ታዲያ፣ “የገፀባሕርያት ማንነት” በእውንና በአካል የሚገለጸው ወይም የሚታየው፣ በተግባራቸውና በታሪካቸው ነው። በሃሳባቸው፣ በአላማቸው፣ በንግግራቸው፣ በውሳኔቸው አማካኝነት ነው የገጸባህርያቱን ማንነት እንደራሳችን ለማወቅ የምንችለው።
እንዲያም ሆኖ፤ ድርጊቶቻቸው፣ ከገጸባህርያቱ ማንነት የሚመነጩ፣ ነባር ባሕርያቸውንና ብቃታቸውን የሚመጥኑ መሆን አለባቸው።
ምናለፋችሁ? ያለ ገጸባሕርይ ማንነትና ብቃት ያለገጸባሕርይ አላማና ዝንባሌ፣… ቅጥ ያለው ተግባር፣ መልክ የያዘ ትረካና ታሪክ አይኖርም። በግልባጩስ?
ያለ ተግባርና ያለ ትረካ፣ የገጸባሕርይን ማንነት መግለጽና መገንዘብ አይቻልም።
በአጭሩ፣ ዋና ዋናዎቹ የኪነ-ፅሁፍ ገፅታዎች፣ እርስበርስ የተቆራኙ ናቸው።
የድርሰቱን ጥቅል መልዕክት የምናገኘው፣ ከገፀባሕርያቱና ከታሪካቸው ነው።
ግን ደግሞ፣ ገጸባሕርያቱና ታሪካቸው በጥበብ ተመርጠው በደራሲው ብልሃት የተቀናበሩት፣… ለድርሰቱ ጥቅል መልዕክት በሚኖራቸው ፋይዳ ነው።
ከዚህ አንጻር ሲታይ፣ ዋናው ነገር ትረካው ነው፤…
ወይም ትልቁ ነገር የገጸባሕርያቱ ማንነት ነው፤…
ወይም ደግሞ መሰረታዊው ነገር፣ የድርሰቱ ጥቅል መልዕክት ነው ብሎ መናገር ያስቸግራል።
አንዱ ያለ ሌላው አይኖርምና።


Read 789 times