Saturday, 04 February 2023 18:27

መንግስት በሃይማኖት ጉዳዮች ጣልቃ እንዳይገባ ተጠየቀ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(5 votes)

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) መንግስት በሃይማኖት ጉዳዮች ላይ የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት በአስቸኳይ እንዲያቆም ጠይቀዋል። ሰሞኑን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የውስጥ ጉዳይ በተለያዩ አቅጣጫዎች እየታዩ ያሉት የመንግስት ጣልቃ ገብነት መዘዛቸው ከባድ መሆኑን ተረድቶ፣ በአስቸኳይ ህግና ሥርዓትን አክብሮ እንዲያስከብር ፓርቲዎቹ ጠይቀዋል፡፡
ኢዜማ ትናንት ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው፤ በጉዳዩ ውስጥ በሚስተዋለው የመንግስት ጣልቃ ገብነት ሣቢያ ደም አፋሣሽ ግጭቶችን ሊያስከትሉ የሚችሉ አዝማሚያዎች እየተስተዋሉ መሆኑን ጠቁሞ፤ መንግስት ራሱን ገምግሞ አፋጣኝ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
የሃይማኖት ተቋማት ላይ በማናቸውም ሁኔታ የሚደረጉ ጣልቃ ገብነቶች መዘዛቸው ብዙ ነው ያለው ኢዜማ፤ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሁሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል ብሏል፡፡  
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በበኩሉ ትናንት ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው፤ መንግስት በእምነት ተቋማት ጉዳዮች ውስጥ በተደጋጋሚ በአሸማጋይነት፣ በአደራዳሪነትና በዳኝነት ስም ጣልቃ እየገባ፣ “መንግስት- በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም” የሚለውንና የመንግስት አስተዳደር መርህን እየጣሰ ይገኛል ብሏል። ይህም የመንግስት ጣልቃ ገብነት በአገሪቱ ዘላቂ ቀውስና  ችግርን የሚያስከትል በመሆኑ አብን ድርጊቱን በጽኑ እንደሚቃወመው አመልክቷል።
በየጊዜው በእምነት ተቋማት ውስጥ በሚፈጠሩ የውስጥ ችግሮች ውስጥ ዘሎ የመግባት የመንግስት ዝንባሌና ልማድ፣ አሁን በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ የተፈጠረው ውስጣዊ ችግር ፖለቲካዊ ቅርፅ  እንዲይዝና ከቁጥጥር ውጪ የሚሆንበት ዕድል እንዲፈጠር እያደረገ ነው ብሏል- አብን በመግለጫው።
መንግስት አሁን እየሄደበት ያለውን ከመርህና ከህግ የሚጣረስ አካሄድ ሙጥኝ የሚል ከሆነ- በአገርና በህዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑን ሊያውቀው ይገባል ያለው የአብን መግለጫ ፤ ለሚደርሰው አገራዊ ውድቀትና ኪሳራ ከተጠያቂነት የማያመልጥ መሆኑን ሊገነዘብ ይገባል ሲል አሳስቧል።

Read 2748 times Last modified on Saturday, 04 February 2023 18:45