Saturday, 28 January 2023 21:29

የአመጻ እርሾ

Written by  ድረስ ጋሹ
Rate this item
(5 votes)

 [ፀጉሩ በእድፍ የተፈተለ፣ ትክሻው ለቅራቅንቦዎቹ የደነደነ፣ አንደበቱ ለነገር የተባ (የሰላ)፣ ጣቶቹን ቅርጭጪት ያራራቃቸው፣ ባለ ሦስት layer ገላ ያለው አዋቂ እብድ]
መዘጋጃቤቱን እየዞረ አመጻውን ሲያስተጋባ ይውላል። “እናንት ፖለቲከኞች፤ ሆድ እና ዝና ያጎለመሳችሁ፣ እናንት የእፍኝት ልጆች” ...ጮክ ብሎ...
“እየመራን ነው አላቸሁ ልበል?.. የሚመ˙ራስ እውር ነው።” [የመዘጋጃ ቤቱ ዘብ ኮፍያውን አስተካክሎ፣ ክላሹን አቀባብሎ ተጠጋው።]
ልፈፋውን ጎላ አድርጎ ቀጠለ።
“ሕዝብ እንደ ግመል? ... ሕዝብ እንደ ግመል አንዴ በጠጣው እስከ ስንት ቀን ይቆይ?..እኛ ሻኛ አለን? ... በሱፍ በከረባት የተጠረዘ ገላችሁ፣ የታረዝን ሰዎችን ካላሳሰባችሁ ሙት ናችሁ...ሙት ናችሁ...ሙታን! የቁም በድን!”
አካሉ የደነደነው ዘብ ከውልብታ የፈጠነ ምት መታው። እብዱ መጻዕጉ ወደቀ። የመዘጋጃ ቤቱ ዘብ ጥቁር ፊቱ ሲቀላ፣ሁለት መጫኛ ይወጣው የሚመስል ከንፈሩ ሲደንስ ይታያል። ልድገምህ ልተውህ ዓይነት...
 [ሰውነቴን ወረረኝ፣ እብዱን ከወደቀበት አንስቼ ከመዘጋጃ ቤት አራቅሁት። የመንገድ ላይ ግቡሳኖች በፌስታል ከቋጠሩት ቡሌ አጎረሱት። በከስክስ የተመታ ማጠፊያውን አሹለት። የተበጣጠሰ ካርቶን አጋርተው እንዲተኛ ፈቀዱለት። ዳግም እንደማገኘው ቃል ገብቼ ተነሳሁ። እያጠጣረ ...”በዚች ምድር ላይ አሳሳቢ ጉዳይና ትርጉም ሊሰጠው የሚችል ነገር ከሌለ ሰው ምንን ይመርጣል?..እራሱን ማጥፋት? ገዳይነትን መላበስ? ወይስ ውል አልባ ኑሮ መግፋት?...እንደኔ አመጻ ..አመጻ ይቀላል፤  [Imagine if there was no meaning or purpose. What then? Suicide?  Murder? Nihilism?  Camus advocates rebellion.  Why is that?  It’s because the universe and life itself is absurd]” አለኝ። ካልጠበቅኩት አንደበት በወጣው እንግሊዘኛ ወ ሐሳብ ደነገጥኩ።
እየተብሰከሰከ በተበረዘ ዓይኑ ያየኛል።
እንባው በጅምር ቀርታለች። «ጨርሼማ አላለቅሳትም» የሚል ይመስላል። በከስክስ ሲነ˙ረት ከመውደቅ ባለፈ አልጮኸም፤ ይልቅ ሳይመታ ሲጮህ ነበር። ሲመታህ ለምን አላለቀስክም ስለው፤ «ሥጋዬን ነው የለኮፋት፤ ለእርሷ ደግሞ አልጮህም፤ ነፍሴን ለነካኝ ጉዳይ ግን እንዴት ስጮህ እንደነበር አይተሃል! ... የውሸት ሥር እስካልተነቀለ፣ ፍትሕ የታሰበውን እስካላከለ ኹሌ አመጻ አለ። ለአንድነትና ለሥርዓት መሟገት ይቀጥላል፤ እንዳይሳካ የታወቀ ለሆነም ኹሉ (The rebel exists because falsehood, injustice, and violence exist.  Because of this, rebels will always exist. .  The rebel fights for unity and order, and also remain aware that this unity and order is impossible.)”
ጎዳና ያፈራውን ሰጡት፤ ቀማመሰ። ፍቅር ከቤት ሸሽታ ጎዳና ላይ መዋል ማደሯን አየሁ። አንደኛው የጀመረውን ሲጋራ ሌላኛው ሲጨርሰው አስተዋልኩ። ያበድኩ እኔ ወይስ እነሱ? ለጊዜው ግራ ገብቶኝ ወደ ኪራይ ቤቴ ተመለስኩ።
[ድቡልቡል እግር፣ ወፍራም ሥጋ፣ ሽግናም ጥርስ፣ ጥፍጥፍ ፊት አከራዬ ናት።]
ስገባ .... ጠራችኝ።
አጠገቧ ቁጭ ብዬ ውሎዬን ተናዘዝኩ። እንደ ልጇ ታየኛለች፤ እኔ እንደ አከራይ ነው እማያት። ተከራይ አሁንም እህል ይፈጅ በኋላም ጅብ ያስፈጅ እንድትል እመኛለሁ። የምትውልልኝ ውለታ ቢገዝፍም የምከፍላትን ኪራይ ነው የማስበው። የመኖር ቀጭን ክር፣ ልትበጠስም ከሌላ ድር ልታብርም ፈቃዱ አላት። ከኹሉም መለየትን (soltuide) የፈለገች ነፍስ ግን ዕጣ ፈንታዋ ዓለምን መካድ ነው። «ይቀርብኛል »የሚለውን ፍራቻ መጋፈጥ ነው የብቸኛ ነፍስ ምሷ።
በሬን ዘግቼ ወጥ እየሠራሁ ነው።
አላንኳኳችም ገባች። እንዴ? ከማለት በቀር ቃል አጠረኝ። «ኪራይህን አልከፈልክም» የሚለውን ቋሚ ንቅሳት ከግንባሯ ላይ አነበብኩ። በአንዴ ተቀየረችብኝ። እኔም ተሽመደመድኩ የለኝማ።
«እማ፤ ደመ-ወዝ ሰሞኑንኮ ስላልገባልኝ ነው።»
«ወዝህ ይርገፍ! ... ቤቴን ልቀቅ! ቶሎ በል» [ቀጭን ትዕዛዝ]
ለመያዝ የማታዳግት ዕቃዬን ጠቀላልዬ ወጣሁ። በሩን ስሻገር ውለታዋን ገደል ጣልኩት እንደ አቴቴ። ለማወደስ የፈጠኑለት ለመጥላትም ይሆናል። የሰራሁትን ሳልበላ መገፍተር እንደሌለብኝ ብቻ እያሰብኩ ወደ መንገድ ተገፈተርኩ! ...
[ትናንት ያየኋት የፍቅር ከተማ መንገድ! የቀናሁባትም ዛሬ ለእርሷ ታጨኹ። ጊዜ ይፍጅ እንጅ ሰው ኹሉ መጀመሪያ ወደ ወደደው ይነጉዳል።]
ደቃቃ ፍራሼን ከሃብታም አጥር ስር አጋደምኩ። ሁለቱ ሱሪዎቼን አቆላልፌ ትራስ አበጀሁ (ቤት ውስጥም እንዲሁ ነበር የኖርኩት)፣ ኩርቱ ፌስታሌን ከትራሴ አስቀመጥኩ፤ኑሮ ጀመረ...
ወጥ ሲሰራ ጨው ይጨመራል ማጣፈጫ፣ በርበሬ ሲዘጋጅ ቅመም ይጨመራል ማጣፈጫ፣ ሰው መኖር ሲጀምርም ያምጻል ማጣፈጫ።
አመጼን አዋለድኩ። እንቁላል-እጭ-ጉልምስ -አዋቂ ሆነች። ሰው ካላመጸ አይኖርማ። አመጹ ከሰብዓዊነት ይጸነሳል፤ መዳረሻው ውጥንቅጥ-ፖለቲካውንና ሌሎች ፍንጋጤዎችን አይሆንም ማለት ይሆናል። መንገድ ዳር ብርድ እየጠለዘኝ፣ ስትፈልግ ፀሐይዋም እየቆላችኝ፣ እሳት ላይ ያለ ብረት ምጣድም ሆኜ ተቃውሞዬ ናረ። እንደ እብዱ..ቀን እንደ አገናኘን..ቀን እንዳለያየን...እንደዛ ነፍሱ ተቃወም እንደምትለው ሰው ሆንኩ።
በአማረ ልብስ የተጠረዙ ቆሻሻ ገላዎችን፣ በቆሻሻ ገላ ውስጥ የሸመቁ ጉድፋም ነፍሶችን ጠላኋቸው። ምንም እንኳ ድህነት ቢጋልበኝ ሥጋዬን ነው። በነፍሴ ግን ሐብታም ነኝ። የሚበጅ የማይበጀውን አውቃለሁ። ተቃውሞ ለእኔ ወፍ ዘራሽ አይደለችም፤ ይልቅ ዘርቼ ያበቀልኳት ትጉህ ገበሬ እንጂ!
ከረፋዱ 4:30።
ሳምሶኔቱን ይዞ ወደ መዘጋጃ ቤቱ የሚገባ ባለሥልጣን፣ ሀበሻዋን ለማኝ አልፎ ሶሪያዊቷን ሲረዳ አየሁት። ውስጤ ተመሰቃቀለ። አጎብዳጅ ልለው ፈለግሁ ...ግን ኹለቱም ሰው ናቸው ብዬ ናቅኩት።
ተሲዓት።
ፍራሽ ያነጠፍኩባት ቦታ ለአረንጓዴ ልማት እንደምትፈለግ ተነገረኝ። ለሌሎች ሊቃወም የሚያኮበኩበው ህሊናዬ ለእራሱ ሲመጣ ደስ አለው ችግር ኖር። ዘቅዝቃችሁ ብትገድሉኝ፣ ነፍሴ ከሥጋዬ እስካልተለያየች ድረስ አለቅም አልኩ። ጥቋቁር ዱላዎች ጀርባዬን ተዋወቁት። የተለያየ ቅርጽ በልስልስ ገላዬ ላይ አተሙ። ቀጠቀጡኝ። «ዘመናዊ ሎሌዎች፣ የአባይ ባሮች አልኳቸው» ወጣልኝ።
ከቦታዬ  አለቀቅኩም። ውበት ከሕይወት በፊት አትመጣም። ዓጽናፈ-ዓለሙ (universe) ራሰ ከብዶ ቢሆንም በአመጽ ይገራል። ኤርኔስቶ ራፋይል ገቫራ ዴ ሴርና ላንቺ ታጋይነቱ ራሱን ነጻ ለማውጣት ነው፤ የእኔም አመጻ እንዲሁ ነው። ምናልባት ቼ ራሱን ነጻ ሲያወጣ ሌሎች የብርኀን ዘንግ ካዩ እንዲሁ በእኔ አመጻ የተፈቱ ሽባዎች ይኖራሉ። አምጻለሁ።
አመጻ መረዳትን ትወልዳለች። ለመረዳት ...ለመኖር አምጻለሁ። ዝምታ ውስጥ ያለ ብሶት ማለት በተዘጋ በር ውስጥ ያለ የድንጋይ ከሰል ጭስ ነው። መውጫ ካልተሰጠው አፍኖ ይገድላል። ያ እንዳይሆን ጎዳናዬን ተናንቄ አመጼን አፋፋለሁ።
[ጠይም ሴት፣ ጠይም ቡና ]
ትመጣለች ልታጠጣኝ። የምትብሰለሰለውን ስተነፍሰው ይቀላታል። አንዳችን ለአንዳችን «አፈ-» ሆነን ተፈጥረናል። በሌሎች አንደበት ራስን ማድመጥ፣ መመርመር። ቡናዋን እልፋለሁ። አዋጋታለሁ። ትኼዳለች ደስ ብሏት። እኖራለሁ የቅርብ እሩቅ ትዝታዋን።
የገበያ ቀን።
ሰው በሌሊት ወደ አንዲት ስፍራ ይግተለተላል። አንገቴን ሰገግ አድርጌ አየኋቸው። የሚከልለኝ ግድግዳ እና ባጥ የለም። የእኔ ባጥ ሰማይ ወለሌ ምድር ሆኗል። በሰፊው መንገድ የጉንዳን ሰልፈኞች መስለው ይራመዳሉ። «በነዱት የሚኼድ፣ በቀደዱለት የሚፈስ ሕዝብ» አልኩ። ደገምኩና፤ «ሰፊውን እንጅ ጠባቧን መንገድ የሚፈራ ሕዝብ» ሠለሥኩና፤ «መካተቻው ሞት የሆነ የኑሮ ሰልፈኛ» ብዬ ተኛሁ።
«እናንት ገበያተኞች፣ የዋጋ ሰዎች፣ አይቀንስም? አይጨምርም? ባዮች፣ሥጋ አድላቢዎች፣ ለነፍሳችሁ ምን ይዛችኋል? ሞት ቢመጣ ምን ተይዞ ጉዞ?» የሚል ልፈፋ አነቃኝ። ላምጽ ተነሳሁ፤ እንደ አጋጣሚ የመዘጋጃ ቤቱ እብድ ነበር። ተቃቀፍን፤ ተላቀስን። ዝምድናችንን አመጻ መዳላድል ሆነችው። ለግዑፋን ድምጽ፣ ለድሎታዊያንም እሬት ነን።
ተመልሼ የተኛሁበትን ጠቅልዬ አስቀመጥኩ።
ቀርቦ የማድርባትን አየ። ከፌስታሉም ኹለት የፋፋ ጉርሻ ቸረኝ። አፌን ስከፍት ዓይኔ ተደፈነ፤ ይህም አንዱ ሲጠቀም ሌላው መታቀቡን አረዳኝ።
“መጻዕጉ ሰማኸኝ? ሰዎች ለኹለት ነገር ይገዛሉ። ለሐሳብ አልያም ለቁስ፡፡ ለቁስ የሚኖሩት ቁስ ለማግኘት ይሰራሉ። ለሐሳብ የሚኖሩት ለስሜታቸው ይኖራሉ። ድንገት፣ ብቸኝነት ቢዋረሳቸው ሐሳባዊው ሐሳብ ካጣ የአእምሮ ባርያ፣ ቁስ አዳኙም ለነገሮች ገረድ ሆኖ ያልፋል። ከዚህ ኹሉ ቀድመው ለምን አያምጹም? ምክንያትና ተስፋ ኹለቱ ለሕይወት አምድ ናቸው። ምክንያት ካለ፣ ተስፋ ካለ ሰው ያምጻል!..አዎ ያምጻል!”
ከአንገቱ ቀና ብሎ...
“አዎ! ስለነጻነት ማወቅ ነጻ አያደርግም። ይልቅ አመጻ ነጻ ያደርጋል። ሲጀመርስ ምንነታችን ምንድን ነው? እኛ በተፈጥሯችን ራስ ወዳድ እና ክፉዎች ነን (Hobes)? እኛ በተፈጥሯችን ምክንያታዊ ነን (most Greek philosophers)? እኛ ተፈጥሯችን ጥሩ ሆኖ ማህበረሰቡ ነው የሚያበላሸን ((Rousseau)? እኛ በተፈጥሯችን ሰራተኞች ነን (Marx)? እኛ በተፈጥሯችን ዕውቀት ፈላጊዎች ነን (Hegel)? እኛ ማህበራዊ እንስሳ ነን (Confucius)? እኛ ግን ምንድን ነን ወንድሜ? የተመጠነ፣ የተሰፈረ ማንነት ነው ያለን? እሺ ነጻ ፍቃዱስ? essence እና existence ታዲያ ምን ለያቸው?  ፔንታጎኖች በጋራ የሚኖራቸውን ባሕርይ እኛ ሰዎችም አናጣም። ነገር ግን ፔንታጎን ከፔንታጎንነት እንደማይቀየር ኹሉ እኛም ከእኛነታችን አንቀየርም ማለት ነው? ነጻ ነን እንቀየራለን ..ለዚህም እናምጻለን!”
ከአፉ ተቀበልኩት ነገሩን።
አመጻ የታቀደ፣ የረቀቀ፣ የተነደፈ ሆኖ አያውቅም። ይልቅ እሱን አብዮት እንለዋለን እንጅ። እምነት ቤቱ አመጻ አለው፣ ቤተ መንግሥቱም። ሰላምህን ልንጠቅህ ሲልህ እምቢ ካልክ፣ ሰላም ያስፈልግሃል ማለት ነው። አመጻ ከልብ ይመነጫል _ለሚያስፈልግ ነገር። ለሥነ-ምግባሩ፣ ለፖለቲካውና ለተለያዩ ዓላማዎች አመጻ አለ። እኛም በአየናቸው ህፀፆች ኹሉ ልናምጽ ትስማማለህ መጻዕጉ? አዎ አለኝ። እጅ ለእጅ ተያይዘን የእውነት ወታደሮች ለመሆን ተማማልን።
በገበያው መሐል ገባን።
ሚዛኖች ተኮልኩለዋል። እህል ሊመዝኑ፣ ዋጋ ሊተመንባቸው። ባለቤቶቻቸው ግን አልተመዘኑም። ቢመዘኑም ቴቄል (ተመዘንክ ከሚዛንም ጎደልክ)።
ለሥጋ ይሆኑት ኹሉ አሉ። ዘላለማዊ ፋብሪካ የሆነው ሰው። ያስገባል-ይፈጫል-ያስወጣል። ይኼንን ዑደት መሻር ይቻል ይሆን?
«መጻዕጉ?»
«ወዬ»
«ገበያ መሐል ቆመን ምን ተሰማህ?»
«የሰው ኹሉ ፍላጎት ይለያያል። አንዱ ሽንብራ አንዱ ጤፍ ይሸምታል። በየቤቱ የጎደለው ነገር ተለያየብኝ»
«ሁሉም ግን ተመሳሳይ ነው። ኹሉም ለስጋ። ለአፈር ፍሪዳ።»
 በየመታጠፊያው እየገባን የሚጠሩ ስሞችን ሰማን። ለዕቃ ማሻሻጫ የሚሆኑ የመላዕክት-አስማትን። ሙስሊሙ በአላህ፣ ክርስቲያኑ በእግዚአብሔር እየማሉ ይሸጣሉ። አመጽን። መሐል ገበያ ቆመን ጮህን ...
«ይሁዳ ለብር የሸጠውን አምላክ ዛሬም ከሸቀጣችሁ ጋር እየሸጣችሁት ነው። ለዕቃ ማሻሻጫችሁ አደረጋችሁት። ፖለቲከኞች በየመድረኩ “ያሉት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ እያሉ ይምሉ ይገዘታሉ”፤ እናንተም መሃላችሁ ከዚህ አልሸሸ። እውነት መሐላ አይሻትም፤ ለማመንም መሐላ አያስፈልግም። በድርጊት ተግባቡ...»
ምንጩ ያልታወቀ ምት።
ኹለታችንንም አጋጩን። ደም ሲዘንብ በእጄ ገደብኩ። ፊት ለፊት ከመጻዕጉ ጋር ተያየን_የናረ አመጻ። አመጻችን በረታ፤ ምስማር ሲመቱት እንደሚጠብቀው፣ ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን፣ ብረትም በእሳት ቅርጽ እንደሚይዝ...እንደዛ እንደዛ ለመሆን!


Read 1077 times