Saturday, 28 January 2023 21:02

“ብር ይሰጣል” አሉ።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

በቅርቡ መስከረም ወር ላይ፣ ብዙ ተበዳሪዎች እዳቸውን እንዳልመለሱለት ገልፆ ነበር። 9.3 ቢሊዮን ብር ብድር ቀልጦ እንደቀረበት ተናግሯል በ2014 ሪፖርት።
አሁንም ግን ብርድ እሰጣለሁ ብሏል - ለዚያውም ያለ ወለድ ያለ ማስያዣ።


   “ብር ይሰጣል አሉ” እየተባለ ሲነገርለት ከርሟል። የረዣዥሞቹ ሰልፎች ምስጢር ይሄው ነው።
ተመስጌን ያስብላል። እንኳንም፣ ገንዘብ ለማስከፈል አልሆነ! እንኳንም፣ የዳቦ፣ የዘይት ወይም የታክሲ ወረፋ አልሆነ! የኤሌክትሪክ ሂሳብ ለማስከፈል (“ካርድ ለማስሞላት) ስንትና ስንት ወረፋ አይተናል።
እነዚህ ሁሉ ወረፋዎች፣ “ብር ለማስከፈል” ደንበኛን የሚያጉላሉ እንደሆኑ አትርሱ።
ብር ለመስጠት ከሆነማ፣ ወረፋው እስከ ከተማው ዳርቻ ድረስ ቢጎተት፣ የሰው ሰልፍ እየተጠማዘዘ ቢረዝም ምን ይገርማል? በየእለቱ እየጨመረ፣ ቅዳሜና እሁድም አልቀረውም።
ደግነቱ ደግሞ፣ የምዝገባ ቀን ተራዝሟል። ለምን? “ብር ለመስጠት ነው አሉ”።
በእርግጥ፣… “ብር ለማበደር ነው” ብለን ወሬውን ብናስተካክለው አይከፋም። አበዳሪው ደግሞ “የልማት ባንክ” ነው።
ቢሆንም ግን፣ “ብር ከመስጠት አይተናነስም” ብለው የሚከራከሩ እንደሚኖሩ አትጠራጠሩ።
የአስረኛ ክፍል ትምህርት ያጠናቀቀና የራሱን ስራ ለመጀመር ያሰበ ማንኛውም ሰው፣ ለብድር መመዝገብ ይችላል ተብሏል።
ብድሩ ደግሞ ያለ ወለድ ነው።
ተዋሽና ተያዥ፣ ንብረትና ማስያዥ አያስፈልግም ተብሏል።
በዚያ ላይ፣ በደረቁ አይደለም። ተበዳሪዎች ያሰቡት እንዲቃናላቸው፣ ገበያ እንዲደራላቸው፣ ደንበኛ እንዲበዛላቸውና ስራው እንዲሳለጥላቸው፣ በነጻ የሙያ ሥልጠና እንዳዘጋጀላቸው ተናግሯል። ከሥልጠና በኋላ ብር ይሰጣቸዋል ወይም ያበድራቸዋል ማለት ነው።
ታዲያ፣ ይሄን ሁሉ ስትሰሙ፣ ምንም እንኳ ብር ለማበደር ቢሆንም፣ “ብር ከመስጠት አይተናነስም” ቢባልለት ይበዛበታል?
ወረፋ እየረዘመ፣ በድርብ እየወፈረ፣ ግራ ቀኝ ቢጠማዘዝ ይገርማል?
እንዲያውም ሲያንሰው ነው። ከሌሊቱ 9 ሰዓት ከሁሉም ቀድመው ከደጁ ስር ወረፋ ለመያዝ እንደመጡ አንዳንድ ትጉህ ተመዝጋቢዎች ተናግረዋል። በእርግጥ፣ እንዳሰቡት አንደኛ ተሰላፊ ለመሆን አልቻሉም። በውድቅት ሌሊት የመጡ ሌሎች በርካታ ተመዝጋቢዎች፣ ከነሱ ቀድመው እንደተሰለፉ በአድናቆት ገልፀዋል።
በሌላ በኩል ግን፣ ቅር ያሰኛል። ምነው? ምነው? ያስብላል። ደንበኞችን እንዲህ ማጉላላት ደግ አይደለም። ነው? አይደለም።
ደግነቱ፣ ብር ለማስከፈል ሳይሆን፣ ብር ለመስጠት ነው - ወረፋው።
ቢሆንም ግን፣ የቢዝነስና የሙያ ስልጠና በነጻ እሰጣለሁ የሚል የቢሊዮን ብሮች ተቋም፣… በወረፋ ብዛት ስሙ መነሳት የለበትም። አሰራሩ የተሳለጠ፣ የደንበኞች መስተንግዶውም የተፋጠነ መሆን ነበረበት። መሆን አልነበረበትም? ከወረፋ የጸዳ ፈጣን አገልግሎት መስጠት ነበረበት።
ወይስ ሆን ብሎ ነው? ተመዝጋቢዎችን ለመፈተን አስቦ የፈጠረው ዘዴ ይሆን እንዴ ወረፋው? ለነገሩ፣ ወረፋ የተወዳጅነት ምልክት የሚሆበት ጊዜ አለ።
በስልጣኔ ደህና በገሰገሱ አገራት ውስጥም፣ ወረፋ የሚፈጠርበት አጋጣሚ አይጠፋም። የሌሊት ወረፋም ጭምር እንጂ።
አዲስ የአይፎን ሞዴል ለገበያ በሚቀርብበት በመጀመሪያው እለት፣ ረዣዥም ወረፋዎች ታይተዋል- በጊዜው።
ትዝ ይላችሁ እንደሆነ፣ የጄኬ ሮውሊን ድርሰቶች (የሃሪ ፖተርን መከራና ጀብድ የሚተርኩ የልብወለድ መጻሕፍት) ታትመው ለአንባቢዎች በሚቀርቡበት እለት፣ ምድረ አሜሪካና ምድረ እንግሊዝ ቀውጢ ይሆኑ ነበር።
የሃሪ ፓተር ትኩሳትና ሞቅታ ልንለው እንችላለን። አዲስ ድርሰት ተሻምተው ለመግዛት በውድቅት ሌሊት ወረፋ የሚሰለፉ አንባቢዎች እልፍ ነበሩ። መጽሐፍ ለመግዛት! አስቡት።
“ብር ይሰጣል አሉ” ከተባለማ፣ እንዴት ወረፋ አይኖርም?
ደግሞም፣ አሰራሩን ማሳለጥና መስተንግዶውን ማፋጠን አቅቶት ሳይሆን፣ የተመዝጋቢዎችን ማንነትና የውስጥ ጥንካሬያቸውን ለማጣራት አስቦ ቢሆንስ?
“ወርቅ በእሳት ይፈተናል” ተብሎ የለ! ተበዳሪዎች ደግሞ፣ በወረፋ፣ በቀን ፀሐይና በማታ ብርድ ይፈተናሉ።
ብር ከመስጠቱ በፊት፣ የተመዝጋቢዎችን ብቃት ማረጋገጥ አለበት። የለበትም? ዋስ ጥሩልኝ አይልም። ማስያዣ ንብረት አምጡልኝ አይልም።
ስለዚህ፣ የተመዝጋቢዎችን ጥንካሬ ለመፈተን፣ ቁርጠኛ የሃሳብ አቋማቸውንና የመንፈስ ፅናታቸውን ለማጣራት ሌላ ምን ዘዴ አለ?
“ትዕግስትን የሚፈታተን ወረፋ”፣… አንድ የማጣሪያና የማረጋገጫ ዘዴ አይሆንም?
በወረፋ ቅር የተሰኘ፣ በረዥም ሰልፍ የተሰላቸ ተበዳሪ፣ በእኩለ ሌሊት ተነስቶ አንደኛ ለመሆን የሰነፈ ተመዝጋቢ፣… አርፎ መቀመጥ፣ እንቅልፉን መለጠጥ ይችላል።
በወረፋ ብር ለመቀበል ከታከተ፣ “ሰርቶ ብር ለማትረፍ” እንዴት ይተጋል?
እንግዲህ፣ ምዝገባው መንቀራፈፉና መንዛዛቱ፣ ሰነፎችንና ትጉሃንን ለመለየት ጠቀመ ማለት አይቻልም? ወረፋው መርዘሙ፣ በአጋጣሚ ሳይሆን በምክንያት ሊሆን ይችላል ብንልስ? ረዥሙ ወረፋ፣ በአሰራር ድክመትና በዝርክርክነት ሳቢያ የተከሰተ ሳይሆን፣ ተመዝጋቢዎችን ለመፈታተን ታስቦ የተፈጠረ ሊሆን ቢችልስ? ቢሆን ይሻላል።
አለበለዚያማ፣ የራሱን ስራ ማሳለጥ ያልቻለ ተቋም፣ እንዴት ለሌሎች ሰዎች የአሰራር ስልጠና እሰጣለሁ ይላል? ስልጠና መስጠትማ ይችላል። ምን ችግር አለው?
የኳስ አሰልጣኝ የግድ ምርጥ የኳስ ተጫዋች መሆን የለበትም። ስለ ቢዝነስ አመራር ለመፈላሰፍና አዳዲስ መፍትሄዎችን ለማፍለቅ የግድ የኩባንያ መሪ መሆን አያስፈልግም። የራስን ስራ ሳታሳልጥ ለሌሎች ሰዎች ስልጠና መስጠት አትችልም ከተባለ ነው ችግሩ። ግን መፍትሄ አይጠፋም። አሰልጣኞችን ማስመጣት ይችላል።
ጥሩ አሰልጣኞችን ማስመጣት ከቻለ ደግሞ፣ ለሰልጠናው የራሱንም ሰራተኞች ቢያስመዘግብ፣ ትልቅ ብልህነት ነው። አሰራሩን ለማሻሻልና ለማቀላጠፍ ሊረዳው ይችላል።
እውነት ለመናገር፣ የዓለም ባንክ ሰነድ እንደሚገልጽልን ከሆነ፣ የልማት ባንክ የራሱን አሰራር ማሻሻል ይችላል። ብር ከማበደር በተጨማሪ የማምረቻ ማሽኖችን ያከራያል። በዚህ በኩል አሰራሩን እንዳሻሻለ ተነግሮለታል።
በእርግጥ፤ ስለ ስራው ቅልጥፍና የዚህን ያህል መጨናነቅ የለብንም። “ብር ለመስጠት ቅልጥፍና አያስፈልገኝም” ቢለን፣ ምን ዓይነት መልስ ይኖረናል? ወረፋ ካልተመቻችሁ፣ መንገዱ ክፍት ነው። ማስያዣ ንብረት አስመዝግባችሁ ወለድ የሚያስከፍል ብድር ከሌሎች ባንኮች ጠይቁ።
ያለወለድ ያለማስያዣ የሚያበድር (ብር የሚሰጥ) ከፈለጋችሁ ወረፋ ያዙ ቢለንስ? መቼስ ምን ይደረግ!
ብዙ ሰው ለወረፋ በሌሊት ተነስቶ ይሄዳል። ቅሬታና ሃሜታ፣ ወቀሳና ነቀፋ የት ያደርሳል? ደግሞም፣ “ለብድር ወረፋ ያዙ” ብሎ በግዴታ አልጎተተን! ብር ልስጣችሁ ስላለ ትርፉ ቅሬታና ወቀሳ መሆን አለበት?
በእርግጥ፣ሌላ ዓይነት ትርፍ ለልማት ባንክ በጣም ሩቅና ብርቅ ነው።  ሁልጊዜ የዓመት ዓመት ወሬው፣ የትርፍ ዜና ሳይሆን የኪሳራ መግለጫ በር የምንሰማው። ስንት ዓመት? ከሃሜት፣ ከወቀሳና ከውንጀላ አምልጦ አያውቅም።
በገፍ ያበደረው ገንዘብ ቀልጦ ቀረ። ያለ ማስያዣ እያበደረ ካዝናው ተራቆተ። ትርፋማ ላልሆኑ ስራዎች “ልማታዊ ብድር” እየሰጠ ብዙ ቢሊዮን ብር አባከነ።… ከነዚህ ወቀሳዎች ጋር የሙስናና የሌብነት ውንጀላዎችም ይወርዱበታል።
አዎ፣ ብዙ ቢሊዮን ብር እንደወጣ መቅረቱ፣ ማባከኑ፣ ብን ብሎ መጥፋቱ፣ እውነት ነው። ነገር ግን፣ ያስወቅሳል ወይ? ያስወነጅላል ወይ?
ከነአፈጣጠሩ፣ ለትርፍ ሳይሆን ለኪሳራ ታስቦ የተቋቋመ ባንክ እንደሆነ ጠፍቶን ነው? ያለወለድና ያለ ማስያዣ ብድር ሲሰጥ “ልማታዊ ነው” ብለን ስናበቃ፤ ኪሳራ ደረሰበት ብለን ብንወቅስ ተገቢ ነው? ፍርደ ገምድል አይሆንም?


Read 1459 times