Thursday, 26 January 2023 00:00

ሱዳን በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ተቃውሞ እንደሌላት ገለጸች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 እየተጠናቀቀ በሚገኘው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ተቃውሞ እንደሌላት፤ የግድቡንም ሆነ የድንበር ጉዳዮችን በተመለከተ በጋራ መግባባትና ንግግር መፍትሔ ለመስጠት ዝግጁ መሆኗን ሱዳን አስታወቀች። አገሪቱ ይህንን ያስታወቀችው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በሱዳን ያደረጉትን የአንድ ቀን የስራ ጉብኝነት ተከትሎ በጋራ ባወጡት መግለጫ ላይ ነው።
የሱዳን ሽግግር ሉአላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ጀነራል አብደልፋታህ አል ቡርሃ ከሁለቱ አገራት መሪዎች ውይይት በኋላ በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሰፋ ያለ ውይይት መደረጉንና ሱዳንና ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብን በሚመለከት ሁሉም ጉዳዮች ላይ እንደሚስማሙና እንደሚደጋገፉ አስታውቀዋል።
በዚሁ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ማጠቃለያ ላይ በጋራ በወጣው መግለጫ፤ ሁለቱ አገራት የታላቁን ህዳሴ ግድብንም ሆነ የድንበር ጉዳይን በተመለከተ የህዝቦቻቸውን ጥቅም በሚያስከብር ሁኔታ በንግግርና በመግባባት መፍትሔ ለመስጠት መስማማታቸውን አመልክተዋል።
ይህ አሁን በሁለቱ አገራት መሪዎች መካከል የተደረገው ውይይትና የተደረሰበት ስምምነት ቀደም ሲል ሁለቱ አገራት ድንበራቸውን በአግባቡ ለመለያየት፣ ለአወዛጋቢ አካባቢዎች መፍት ለመፈለግ በጋራ አቁመውት የነበረውና ከሁለት ዓመት በፊት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ጦርነት ሲቀሰቀስ የሱዳን ሃይሎች በሃይል በመያዛቸው ሳቢያ የተቋረጠው የድንበር ኮሚሽን ስራውን እንዲጀምርና ለድንበር ይገባኛል ጥያቄ መፍትሄ ሊያበጅ ይችላል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል።
የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ሱዳን ተቃውሞ እንደሌላትና ግድቡን በሚመለከት ሁሉም ጉዳዮች ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመደጋገፍና በመግባባት ለመስራት እንደምትፈልግ ማሳወቋ ተቋርጦ የቆየው ንግግር እንዲጀመር ሊያደርግ የሚችልበት እድል እንደሚኖረው ተጠቁሟል።


Read 4011 times