Saturday, 28 January 2023 20:45

2.5 ቢ ብር የወጣበት “ሀይሌ ግራንድ አዲስ አበባ” ባለ 5 ኮከብ ሆቴል በሙሉ አቅም ስራ ጀመረ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

ሀይሌ ሆቴሎችና ሪዞርቶችን በአምስት አመት ውስጥ 20 ለማድረስ እየተሰራ ነው   ባለፈው ጥቅምት 1 የሙከራ አገልግሎት ጀምሮ የነበረው “ሀይሌ ግራንድ አዲስ አበባ ሆቴል” ከትናንት በስቲያ ሃሙስ አንስቶ በሙሉ አቅሙ ስራ መጀመሩን ተገለፀ፡፡ በ15 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ሆቴሉ ለ450 ሰዎች የስራ እድል እንደፈጠረ ባለቤቱ አትሌት ሻለቃ ሀይሌ ገ/ሥላሴ ከትላንት በስቲያ ከስራ ባልደረቦቹ ጋር በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡ ለሀይሌ ሆቴሎችና ሪዞርቶች ስምንተኛ የሆነው ይህ  ሆቴል የመጀመሪያው ባለ 5 ኮከብ አፐር እስኬል አፕ ሆቴል ነውም ተብሏል፡፡ 130 ክላሲክ የመኝታ ክፍሎች፣ 14 ስዊት የመኝታ ክፍሎች፣ 12 ፕሪሚየም የመኝታ ክፍሎች፣ 1 ፕሬዝደንሽያል የመኝታ ክፍል ያለው ይሄው ግራንድ ሆቴል ደረጃቸውን የጠበቁ የሴቶችና የወንዶች የውበት ሳሎኖች፣ 4 አለማቀፍና አገር አቀፍ ትልልቅ ሬስቶራንቶች፣ ኬክ ቤትና ሱቆች፣ ሀይሌ ሩጫ የጀመረበትን ጭላሎ ተራራን ለማስታወስ የተሰየመውን ጭላሎ እና እንጦጦን ጨምሮ ስምንት የተለያየ ደረጃ ያላቸው የስብሰባ አዳራሾች የውበትና የጤና መጠበቂያ ማዕከል (ጅም ሀውስ)፣ 200 ተሽከርካሪዎችን የመያዝ አቅም ያለው የመኪና ማቆሚያ፣ ንፁህ አየር የሚያገኙበት ሩፍ ቶፕ አውት ዶር መንቀሳቀሻ ሰገነት፣ ከተማዋን በአምስት አቅጣጫ ማየት የሚያስችል የዕይታ አማራጭና ከ300 ሜጋ ባይት በላይ አቅም ያለው እንዲሁም ለእያንዳንዱ የመኝታ ክፍል አንድ አንድ ራውተር የተገጠመለት የዋይፋይ አገልግሎት ያለውና ከተማ ውስጥ ሆኖ ሪዞርት ውስጥ እንዳሉ ስሜት የሚሰጥ ብቸኛ ሆቴል ነው ተብሏል፡፡
ሀይሌ ሆቴሎችና ሪዞርቶችን በአምስት አመት ውስጥ 20 ለማድረስ የታቀደ ሲሆን የወላይታ ሶዶው ሀይሌ ሪዞርት ነሀሴ አጋማሽ ላይ እንደሚመረቅ በጋዜጣዊ መግለጫው ተብራርቷል፡፡  ሀይሌ  ሆቴሎችና ሪዞርቶች በጎንደር፣ በአዳማ፣ በሻሸመኔ፣ በዝዋይ፣ በሃዋሳ፣ በአርባምንጭና በሱሉልታ ከፍተኛ አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን በቀጣይም በደብረ ብርሃን ፣ በጅማ፣ በወልቂጤ እና በኮንሶ እየተገነቡ መሆናቸው ተብራርቷል፡፡
በቀጣይም ሀይሌ ሆቴሎችና ሪዞርቶች በምስራቅ አፍሪካ፣ በአፍሪካ፣ በአውሮፓና በሌሎች አለማት በተለያዩ መንገዶች መከፋታቸውን ይቀጥላሉ ተብሏል፡፡ ሀይሌ ግራንድ አዲስ አበባ ሆቴል ጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ ስራ ሲጀምር ለምረቃ ሊወጣ የነበረው 2 ሚሊዮን ብር ለበርካታ ትምህርት ቤቶች ለመማሪያ ቁሳቁስ መግዣ መዋሉም ተገልጿል፡፡  
በየቀኑ ሩብ ሚሊዮን ኮፒ የሚያሳትመው የኬንያው ተወዳጁ ጋዜጣ “ኔሽን” በቅርቡ የአትሌት ሻለቃ ሀይሌ ገ/ሥላሴን የቢዝነስ ተቋማት የሚያስቃኝ ዘገባ አውጥቷል፡፡ ከአትሌቲክስ መውጣቱን ተከትሎ ፊቱን ሙሉ ለሙሉ ወደ ኢንቨስትመንት ያዞረው ሀይሌ፤ ባለፉት 12 ዓመታት በሆቴልና ሪዞርት ዘርፉ ተሰማርቶ ስምንት ሆቴልና ሪዞርቶችን ገንብቷል፡፡ ከሰሞኑን መደበኛ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ሀይሌ ግራንድ አዲስ አበባ ሆቴል በመዲናዋ ግዙፍና ምርጥ ከሆኑ ሆቴሎች አንዱ መሆኑን “ለኔሽን” ጋዜጣ የገለፀው ሃይሌ ከሌሎች ትልልቅ ሆቴሎች ጋር እየተፎካከርን ነው ብሏል፡፡ “ጥራቱን የጠበቀ ለደንበኞች ምቹና ተስማሚ የሆነ  አገልግሎትና ድባብ መፍጠር ይገባናል፤ ያለበለዚያ ግን ደንበኞችህ ከጅህ ያመልጡሀል” ብሏል- ሀይሌ ከ “ኔሽን” ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ፡፡

Read 1569 times