Saturday, 28 January 2023 20:46

በአዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አደረጃጀት ላይ በርካታ ክፍተቶች አሉ ተባለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“ህዝበ ውሳኔው መንግስት እንደሚለው ህዝቡን ያሳተፈ አይደለም”

   በአዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ የክልል አደረጃጀት ላይ በርካታ የህግ ክፍተቶች መኖራቸውን የገለፀው የወላይታ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፤ መንግስት የህግ ጥሰቶችን በአስቸኳይ እንዲያስተካክል ጠየቀ፡፡
በ2015 ዓ.ም በህጋዊነት ተደራጅቶ ተግባሩን እየፈፀመ መሆኑን የገለፀው የጋራ ምክር ቤቱ፣ ጥር 6 ቀን 2015 ዓ.ም በጠራው አስቸኳይ ስብሰባ፣ በበርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ መወያየቱን ገልፆ፤ በተለይ ግን ከቀድሞው ደቡብ ክልል ስድስት ዞኖችንና አምስት ልዩ ወረዳዎችን አንድ ላይ በማድረግ፣ “ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” የሚል መጠሪያ ያለው አዲስ ክልል ለማደራጀት ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም በሚደረገው ህዝበ ውሳኔ ላይ ትኩረቱን አድርጎ ማየቱንና በውይይቱም ላይ በርካታ ክፍተቶች መታየታቸውን ነው የተገለፀው፡፡ የወላይታ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የገለፀው ከህግ ክፍተቶችም አንዱ ህዝብ ውሳኔው ህዝቡ መምረጥ የሚፈልገውን አማራጭ ያላቀረበ በመሆኑ የዜጎችን የመምረጥ መብት የነፈገ ነው ሲል አጣጥሎታል፡፡
ይህን ክፍተት ለመሸፈን ሲባል በበርካታ ምርጫ ጣቢያዎችና ምርጫ ክልሎች ለመራጮች ምዝገባ ሂደት ጀምሮ የህግ ጥሰቶች መፈፀማቸውን የገለፀው የጋራ ምክር ቤቱ፣ መራጮች ወደ ምርጫ ጣቢያ ሳይመጡ በቀበሌ አመራሮችና በአካባቢው የህግ አስከባሪዎች በኩል የምርጫ ካርዶች ወጪ ከመደረጋቸውም በተጨማሪ መንግስት በሚያስቀምጠው አቅጣጫ ምርጫውን ለመዘወር የቀበሌ ህግ አስከባሪዎችና አመራሮች፣ የዜጎችን የምርጫ ካርድ በእጃቸው በመያዝ ህዝበ ውሳኔውን ቀን እየተጠባበቁ  እንደሆነ ደርሼበታለሁ ብሏል፡፡
በመሆኑም መንግስት በተለይም ምርጫ ቦርድ ይህን ህገ ወጥ አሰራር እንዲያስቆም ጥሪ አቅርቧል፡፡
“እስከ ዛሬ በአካባቢያችን ከተካሄዱትና ካሳለፍናቸው ምርጫዎች አንፃር ይህ የአዲሱ ክልል አደረጃጀት ህዝበ ውሳኔ ለበርካታ አመታት የሚፀና በመሆኑ በጉዳዩ ላይ የፖለቲካ ሀይሎች ፣ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችና መንግስት በጋራ በመወያየት ሀሳባቸውን ማንፀባረቅ ሲገባቸው፣ ይህ ባለመደረጉ ህዝበ ውሳኔው በርካታ ችግሮች ያሉበት ነው ብሏል፡፡
የጋራ ምክር ቤቱ ይህንን መነሻ በማድረግ ጥር 6 ቀን በአስቸኳይ የተጠራው የጋራ ምክር ቤት፤ በዚሁ አጀንዳ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ ባለ አምስት ነጥብ የአቋም መግለጫ ማውጣቱን ለአዲስ አድማስ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡
እየተካሄደ ያለው የህዝብ ውሳኔ ሂደት የዜጎችን የመምረጥ መብት ያላከበረና የመብት ጥሰትን ስለሚያመለክት በአስቸኳይ እንዲቆም ፣የህግ በላይነት እንዲከበር ብሎም በህዝበ ውሳኔው የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት እንዲሳተፉ፣ የዚህ አዲስ ክልል አደረጃጀት ፅንሰ ሀሳብ ባለቤት መንግስትና ገዢው ፓርቲ ሆኖ ሳለ ህዝበ ውሳኔ ላይ የሚቀርቡት ምልክቶች ለማህበረሰቡ በተመሳሳይ ሁኔታ ማስተዋወቅ ሲገባ አንዱን (የእርግቡን) ምልክት ብቻ የማስተዋወቅ ተግባር የምርጫን ሂደትና ሥነ ስርዓት የሚፃረር በመሆኑ መንግስት አካሄዱን በአስቸኳይ በማረም ተጨማሪ አማራጮችን ለመራጮች በማቅረብ እንዲያስተዋውቅ፣ ለህዝበ ውሳኔው የሚቀርበው አዲሱ “ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” ብዙ የክላስተር ማዕከላት ያሉት መሆኑ በመንግስት እየተገለፀ መሆኑ ይህ ጉዳይ በዜጎች ላይ ተጨማሪ አስተዳደራዊ፣ ኢኮኖሚዩዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን ሊያስከትል እንደሚችል የጋራ ምክር ቤቱን ስጋቱን ገልፆ፤ መንግስት አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደረግና የመፍትሄ አቅጣጫ እንዲያስቀምጥ እንዲሁም እንደ ወላይታ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም የሚደረገውን የአዲሱን ክልል አደረጃጀት ህዝበ ውሳኔ በተመለከተ የአካባቢው ማህበረሰብ ያለው ፍላጎትና ህዝበ ውሳኔውን ለማስፈፀም በመንግስት የተደረሰበት ሂደት አለመጣጣሙን መገንዘቡን የጋራ ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡ እነዚህ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ያሉበትን ህዝብ ውሳኔ ማድረግ ውጤቱ እንደማያምር በማሳሰብም፤ ህዝብና መንግስት ጋራ መግባባት ላይ እንዲደርሱ በቅድሚያ ሀገራዊ ምክክር ተደርጎ ቀጥሎ ህዝበ ውሳኔው እንዲደረግ ጠይቋል፡፡ የወላይታ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ኢዜማን፣ የወላይታ ህዝብ ዴሞክራቲክ ግንባር (ወህዴግ)፣ ህብረ ኢትዮጵያ ፖርቲን ፣ ነፃነትና እኩልነት፣ መላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ብልፅግና እና (ኢህአፓን) በአባልነት ያቀፈ የጋራ ምክር ቤት ነው፡፡

Read 1100 times