Sunday, 22 January 2023 00:00

የኢሰመኮ ምክትል ኮሚሽነር ምን ይላሉ?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 -”የሽግግር ፍትህ እውነቱን ለማውጣት፣ ተጎጂዎችን ለመካስ፣ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው”

      የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ፣ ከእንግሊዝኛው  “አዲስ ስታንዳርድ” ጋር ከሰሞኑ ባደረጉት ቃለምልልስ፣ በአገሪቱ በሚፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ዙሪያ በስፋት አውግተዋል።
የሽግግር ፍትህ  አስፈላጊነትን በተመለከተ  እንዲሁም በኮሚሽኑ የገለልተኛነት ጥያቄ ላይም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የአገሪቱ የሰብአዊ መብት አያያዞች እንዴት ይሻሻሉ ለሚለውም መፍትሄ ጠቁመዋል፡፡ ምክትል ዋና  ኮሚሽነሯ የመጀመሪያና ሁለተኛ ድግሪያቸውን በህግና በሰብአዊ መብት ያገኙ ሲሆን ለ25 ዓመታት በተለያዩ  ድርጅቶች  ውስጥ በዲሞክራሲ እንዲሁም በሴቶችና ህጻናት መብቶች ላይ ሰርተዋል። ከቃለ-ምልልሱ መርጠን እንዲህ ተርጉመን አቅርበነዋል፡፡

            በጦርነቱ የተፈፀሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በተመለከተ ኢሰመኮ ከተባበሩት መንግስታት ጋር በመሆን ያደረገው ምርመራና ያወጣው ሪፖርት በሁለቱም ወገኖች ተቀባይነት አግኝቷል?
በሁለቱም ወገኖች እንኳን ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ነገር ግን በሰነዱ ውስጥ የቀረቡት አብዛኞቹ ምክረሃሳቦች መከናወን ያለባቸው በገዢው መንግስት ነው። ብዙዎቹ ሥራዎች በአቃቢያነ- ህግ ነው መከናወን ያለባቸው፣ ለምሳሌ እንደ ወንጀል ምርመራና ክስ መመስረት ያሉት፡፡ ሪፖርቱን ተከትሎ የመንግስትን አፈፃፀም ተከታትለናል፣ እናም አንዳንዶቹ ምክረሃሳቦች ትኩረት አግኝተዋል፡፡ ሆኖም በግጭቱ ሚና የነበራቸው ህውሓት እና የኤርትራ መንግስት ምክረ ሃሳቦቹን አልተቀበሏቸውም፡፡ ምክረሃሳቡ ተቀባይነት እንዲያገኝ ግፊት እያደረግን ነው፡፡ አሁን የሰላም ስምምነቱ ተፈርሟል፤ በስምምነቱ ላይም የሽግግር ፍትህ ተካቶበታል፡፡ እኛም ምክረሃሳቦቹን እንዲቀበሏቸው ግፊት ማድረጉን እንቀጥልበታለን፡፡
ምክረሃሳባችሁ በሁሉም ወገኖች ተቀባይነት ያላገኘበትን ምክንያት ለማወቅ ያደረጋችሁት ሙከራ አለ?
እንዳልኩት በሥልጣን ላይ ባለው መንግስት ተቀባይነት ማግኘቱ ለእኛ እንደ ትልቅ አዎንታዊ ሂደት የሚቆጠር ነው፡፡ ምክንያቱም አብዛኞቹን ምክረ ሃሳቦች መተግበር ያለበት መንግስት ነው። ነገር ግን ከምክንያታቸው አንዱ የገለልተኝነት ጥያቄ ነው፡፡ ሪፖርቱ በገለልተኝነት እንዳልተሰራ ነው የሚያስቡት፤ እናም ምርመራው በሌላ አካል መከናወን አለበት ብለው ይሞግታሉ፡፡ አሁን ግን የሰላም ስምምነቱ ትግበራ እየተከናወነ ሲሆን ይህም በዚያ ሪፖርት ውስጥ ካሉት ምክረ ሃሳቦች አንዱ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር፣ ምክረ ሃሳቡ እየተተገበረ ነው፤ የሽግግር ፍትህም በስምምነቱ ውስጥ ተካትቷል፡፡
እስካሁን ባደረጋችሁት ምርመራ በአገሪቱ የሚፈፀሙ ዋነኞቹ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ምንድን ናቸው?
በአገሪቱ እየተፈፀሙ ያሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በርካታ፣ ውስብስብና ባለብዙ መልክ ናቸው፡፡ አንዱን ከሌላው ለመለየት ወይም አንዱ ከሌላኛው ይበልጣል ለማለት ቀላል አይደለም፡፡ ነገር ግን ከግጭት ጋር ተያይዞ የሚፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እጅግ አስከፊ ናቸው፡፡ አያሌዎች ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመት፣ የመሰረተ ልማት መፈራረስ፣ የመማር መብት መስተጓጎል፣ የጤናና አገልግሎት መቋረጥ፣ የእንቅስቃሴ ገደብ፣ የኮሙኒኬሽን መሰረተ ልማት ውድመት እንዲሁም በርካታ ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ይፈጸማሉ፡፡ በተለይ በመላው ዓለም በአንደኝነት ያሰለፈን፣  የሰዎች የአገር ውስጥ መፈናቀል ነው፡፡
ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በተጠለሉበት ሥፍራ ለበርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እየተዳረጉ ናቸው፡፡ መፈናቀላቸው ሳያንስ፣ ዘላቂ መፍትሄ ሳያገኙ ለተራዘሙ ችግሮች ተዳርገዋል፡፡ በተጨማሪም በእነዚህ ሥፍራዎች በሴቶችና በህፃናት ላይ የሚፈፀሙ በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች አሉ፡፡ ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ በስፋት የተነሳው ፆታዊ ጥቃት፣ በስፋት ተፈፅሟል፡፡፡ የጥቃት ተጎጂዎች የሚፈልጉትን አገልግሎት ማግኘት ባለመቻላቸው የበለጠ እየተጎዱ ነው። በጦርነቱ ሳቢያ የአካል ጉዳተኞች ቁጥርም ጨምሯል። ሃቁን ለመናገር በአገሪቱ ያሉትን የአካል ጉዳተኞች ቁጥር በትክክል አናውቅም። አሁን ግን ተጨማሪ የአካል ጉዳተኞች ያሉን ሲሆን ከጉዳታቸው የሚያገግሙበት አገልግሎት እያገኙ አይደሉም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ፤ የዕድሜ ባለፀጋ አዛውንቶችም ለበርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተዳርገዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ መሻሻል ይኖርባቸዋል፡፡
በኮሚሽኑ ላይ የገለልተኝነት ጥያቄዎች ይነሱበታል፡፡ አንዳንዶች ኮሚሽኑ በመንግስት ላይ ጥገኛ በመሆኑ በገለልተኛነትና በሃላፊነት አይንቀሳቀስም ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ የእርስዎ ምላሽ ምንድን ነው?
ለገለልተኛነት አንዱ እርምጃ የየትኛውም ፓርቲ አባላት ያልሆኑ መሪዎች እንዲኖሩ ማድረግ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ሁሉም ኮሚሽነሮች ከፖለቲካ ትስስር ነፃ ናቸው፡፡ ይኼ በምርጫ ወቅት አንዱ መስፈርትም ነበር፡፡ ሁለተኛ፣ ኮሚሽነሮቹ የተመረጡት በልምድና ትምህርታቸው ላይ መሰረት ተደርጎ ነው፡፡ በሰብአዊ መብት መስክ በአመራርነት ልምድ አላቸው፡፡ በአመራር ደረጃ ላይ ያለነው በሙሉ በምርጫ ውሰጥ አልፈናል፣ እናም መነሻችንም ሆነ መድረሻችን የሰብአዊ መብቶችን ማስጠበቅ ነው፡፡ በምርመራችንና በሪፖርታችን አንዱ ወገን ላይደሰት፣ ሌላው ደግሞ ሊደሰት ይችላል፡፡ እኛ ግን ወገንተኛ አይደለንም፡፡ ወገንተኛ ከሆንንም፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሰለባዎችን ድምጽ እንዲሰማ  ለማድረግ ነው- ጉዳታቸውንና ስቃያቸውን  የሚያሳዩ ሰነዶች በማቅረብ። በተረፈ ግን ለማንም ወገንተኛ አይደለንም፡፡ ዋነኛ ሥራችን መሬት ላይ ያለው እውነታ ነው፡፡ ሥራችንን የምናከናውነው መሬት ላይ ባለው መረጃና በዓለማቀፍ ግምገማ መሠረት ነው፡፡ ለዚህም ነው ጉዳዩን እንደሰማን ሪፖርት የማናወጣው። ሥራችን የሚወሰነው መሬት ላይ ባለው እውነታ ነው፡፡
ነገር ግን በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ በፍጥነት ሪፖርት ታወጣላችሁ፣ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ደግሞ ትዘገያላችሁ የሚሉ ቅሬታዎች ይሰነዘራሉ፡፡ ለምንድነው እንደዚያ የሚሆነው?
በመሬት ላይ ያለው ሁኔታ ነው አንድ ሪፖርትን በፍጥነት እንድናወጣና እንድናዘገይ የሚያደርገን። አብዛኛውን ጊዜ በግጭት አካባቢዎች ከሆነ መዘግየት ይኖራል፣ ምክንያቱም ቦታው ላይ መድረስና ምርመራ ማድረግ፣ ከዚያም ሪፖርት ማውጣት አለብን። ጉዳዩ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ስለተሰራጨ ብቻ በመሬት ላይ ያለውን ሁኔታ በቅጡ ሳንመረምር ሪፖርት አናወጣም፡፡ ለመዘግየቱ ትልቁ ምክንያት ቦታው ላይ በፍጥነት ለመድረስ አስቸጋሪ በመሆኑ ነው፡፡ ሌላው ምክንያት የተቋማዊ አቅማችን ጉዳይ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የድጋፍ ሰጪ ክፍሉን ጨምሮ ጠቅላላ ሰራተኞቻችን 360 ገደማ ናቸው፡፡  በዚህ አቅም በሁሉም አካባቢዎች የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር፣ ለማረጋገጥና ሪፖርት ለማውጣት ይቸግረናል፤ በዚህም የተነሳ ሪፖርቶቹን እናዘገያቸዋለን፡፡
የሰላም  ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እየፈጸሙ እንደሚገኙ በርካታ ሪፖርቶች ያሳያሉ። ከዚህ ጋር በተያያዘ ኢሰመኮ ያደረገው ነገር አለ?
እዚያ መሄድ ስላልቻልን ይሄንን ጉዳይ ማረጋገጥ አልቻልንም። ስለዚህ ለጊዜው ምንም ማለት አልችልም።
ብዙዎች በፌደራል መንግስትና በህወሓት መካከል ለተፈረመው የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ሂደት፣ ውጤታማ የሽግግር ፍትህ መኖር አለበት ብለው ይሞግታሉ። ከዚህ አንጻር ምን መደረግ አለበት ብለው ያስባሉ?
በምርመራችን ላይ የሽግግር ፍትህ ስርዓት እንደ ምክረ ሃሳብ በግልጽ ተጠቅሷል። ኢትዮጵያ ውስጥ ትክክለኛ የሽግግር ፍትህ ሂደት መተግበር አለበት ብለን እናምናለን። ህጋዊ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ በአገር አቀፍ ደረጃ መተግበር እንዳለበት ሃሳብ ተጠቁሞ ነበር፤ ይህም ሀሳብ በሰላም ስምምነቱ ላይ የተካተተ ሲሆን መንግስት እየሰራበት ነው።
የሽግግር ፍትህ ሥርዓት አራት ዋነኛ ዓላማዎች አሉት። የመጀመሪያው ተጎጂዎችን መልሶ ማቋቋም ነው፤ ሁለተኛው የሰብአዊ መብት ጥሰት ወንጀሎች የሚመረመሩበትና ወንጀል ፈጻሚዎች በህጉ መሰረት የሚቀጡበትን ሁኔታ መፍጠር ነው፤ ሦስተኛው እውነትን ማፈላለግ ማውጣት- የችግሩን መንስኤ ማወቅ ከተጎጂዎችና ግጭቱን ከጀመረው ወገን ጋር ውይይት በማድረግ ስምምነት ላይ መድረስ ነው። አራተኛው ደግሞ ተመሳሳይ ችግር ዳግም እንዳይከሰት አስፈላጊውን የፖሊሲ ማዕቀፍ የመቅረጽ ሂደት ነው። ከዚህ አንጻር ብዙ መሰራት ያለባቸው ስራዎች አሉ።
ኢሰመኮ ስራውን በገለልተኛነትና በውጤታማነት ለማከናወን የሚገጥሙት ትላልቅ ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?
የኮሚሽኑ ራዕይ ለሰብአዊ መብቶች ክብር መስጠት ባህል ሆኖ ማየት ነው። ያንን ለማድረግ ህብረተሰባችን የሰብአዊ መብት እሴቶችን ማወቅ፣ መገንዘብና መጠቀም ይኖርበታል። ይኼ ትልቅ ሥራ ነው። ሰብአዊ መብቶችን ማረጋገጥ፤ ማስተማርና የአቅም ግንባታን መስጠት፤ በዚህም ህዝቡና ባለስልጣናት ሃላፊነቶቻቸውን የሚያውቁ፣ በዚያም መሰረት ማስፈጸም ይችላሉ።
የኮሚሽኑ ሃላፊነት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በፖሊስ ጣቢያ፣ በወህኒ ቤቶችና ት/ቤቶችን ጨምሮ በሌሎች የሰብአዊ መብቶች በሚጣሱባቸው አካባቢዎች ጥሰቶቹን ለመከላከል እርምጃዎች መወሰዳቸውን ማረጋገጥ መሆኑን፣ ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ማስተማር አስፈላጊ ነው።
እኛን ከሚገጥሙን ተግዳሮቶች መካከል በአንዳንድ ቦታዎች ጉብኝት እንዳናደርግና የተወሰኑ ሰዎችን እንዳናነጋግር መከልከላችን ነው። አንዳንዴ ሁኔታውን እንዲያመቻቹልን የበላይ አለቆችን እናነጋግራለን። እንዲያም ሆኖ ፈታኝ ነው። ሌላው ያወጣናቸውን ምክረ ሃሳቦችን የመተግበር ጉዳይ ነው። በአጠቃላይ ስራ አስፈጻሚው አካልና ህብረተሰቡ የኮሚሽኑን ሃላፊነትና ስልጣን እንዲረዱና ምክረሃሳቦችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ እንዲሁም ምርመራ ለማድረግ ስንፈልግ ሁኔታዎችን እንዲያመቻቹልን ጥሪ እናቀርባለን። ኢትዮጵያ ውስጥ ለሰብአዊ መብቶች ክብር መስጠት ባህል ሆኖ ለማየት እንችል ዘንድ ህብረተሰቡና ስራ አስፈጻሚው የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቀርባለሁ።

Read 750 times