Saturday, 14 January 2023 11:35

ሰባት ቁጥር እና ሰባትነት

Written by  ኤፍሬም አሊ - የኛ መንደር
Rate this item
(1 Vote)

 በዚህ ቅኝት “ሰባት ቁጥር” መጽሐፍ፣ ከሒሳብ እና/ወይም ከሃይማኖታዊ አስተምህሮ አንጻር በይዘቱ ውስጥ የተካተቱትን ነገረ ቁጥር፣ የቁጥር ጽንሰ ሐሳቦች፣ አመዳደቦችና ተዛምዶዎች ይዳሰሳሉ። ይህም ዳሳሹ ከደራሲው የበለጠ መለኪያ አለው ለማለት ሳይሆን የይዘቶቹ  አቀራረብ በአመክንዮና በሌላ ተደራሲ አተያይ ይፈተሻሉ ለማለት ነው።
የዳሰሳው ዓላማ፡- ሒሳብና ቁጥር እንደ ሌሎች መንገዶች፣ ስልቶችና ቁሶች ሁሉ የሰውን ልጅ የዕለት ተዕለት ህይወት እንዲያግዙ በራሱ በሰው ልጅ የተፈጠሩ መገልገያው ናቸው። ከዚህ ያለፈ ተገላጭና ቀጥተኛ መለኮታዊም ሆነ መንፈሳዊ ትስስር የላቸውም፤ ማለትም ቅዱስም እርኩስም የሚባል ቁጥር የለም። በሳይንሳዊውም ሆነ በመንፈሳዊው አውድ፣ አፍቅሮተ/አምልኮተ ቁጥር የተወገዘና ከቁጥር አገልግሎት የማይመደብ፣ በዕውቀትነት ለማስተማርም ያልበቃ ነው። ስለሆነም የዚህ ዳሰሳ ዓላማ መጽሐፉን ማንቆለጳጰስ ወይም ማብጠልጠል
ሳይሆን ቁጥርና የቁጥር ጽንሰ ሃሳብን፣ ደራሲው የተነተነበትንና ያዛመደበትን መንገድ ለደራሲው እንዲሁም ለዚህ ጽሑፍ አንባብያን  ነጥሎ ማሳየት ነው።
የመጽሐፉ ርዕስ፣ የሽፋን ንድፍ፣ የውስጥ ገጾች ይዘትና ቅርጽ፡- መጽሐፉ “ሰባት ቁጥር” በተሰኘ  ርዕስ ተወክሏል። በውስጥ ክፍሉ “ሰው የመሆን ምስጢር መፍቻ” የሚል የርዕሱን ተቀጽላ መጠቀሙ፣ የመጽሐፉ ይዘት ሰባት ቁጥርንና ሰው መሆንን እንደሚያስተሳስር ቀድሞ ለመጠቆም መሆኑን ያመለክታል። የፊት ሽፋኑ የመጽሐፉን ስያሜ፣ የደራሲውን ስምና የታተመበትን ዓመተ ምህረት ይዟል። በተጨማሪም የሽፋኑ ስዕል የኢትዮጵያን ካርታ በእጅ መዳፍ ላይ አስቀምጦ ከላይ ከፍ ባለ መጠን በግዕዝ ቁጥር አሐዝ ሰባት ቁጥር (፯) ተቀምጧል። በጀርባ ሽፋኑ ደግሞ የደራሲውን ምስል፣ ደራሲው
መጽሐፉን ለማሳየት የተጠቀማቸውን መግለጫዎችና የመሸጫ ዋጋውን አካትቷል።
በውስጥ ክፍሉ መታሰቢያነቱን፣ ምስጋናን፣ መግቢያን፣ ማውጫን፣ በአስራ ሁለት ዋና ዋና ምዕራፎችና በስራቸው ባሉ ንዑስ ርዕሶች የተዋቀሩ ይዘቶቹን ከዋቢ መጻህፍት ዝርዝር ጋር (በአጠቃላይ 160 ገፆች) አስፍሯል። የወረቀቱ ስፋት A5 እንደመሆኑ በንጽጽር ከፍ ያለ የፊደል መጠንን ተጠቅሟል። የውስጥ ገጽ ንድፉ (ማውጫውን ጨምሮ) ለማንበብ ምቹና ያለ ዝንፈት በወጥነት የቀጠለ ነው። መጽሐፉ ሰባት ቁጥርን እንደ መነሻ ይዞ “ሰባት ቁጥር” ይገልጻቸዋል የሚላቸውን ነገሮች በብዛት ለመዘርዘር ስለሚጓዝ የተለያዩ ዘርፎች ውስጥ እየገባ ይወጣል። ሒሳብ፣ ፊዚክስ፣ ባዮሎጂ፣ ስነ ምድር፣ ፖለቲካ፣ ሃይማኖት፣ ሙዚቃ፣ ስነ ፈለክ . . . እያለ ብዙ የዕውቀት መስኮችን ነካክቷል። የሃሳብ አተናነተኑ ከጥልቀትና ከፋይዳ አንጻር ተወቃሽ ቢያደርገውም፤ ደራሲው እነዚህን ሁሉ ብትንትኖች በአስራሁለት ምዕራፎች ለመጠቅለል የሄደበት መንገድ የሚደነቅ ነው።
የአጻጻፍ ስልትና አገላለጽ፡- የመጽሐፉ የመጀመሪያ አንቀጽ “ሰባት ቁጥር በዓለማችን እጅግ ተወዳጅ ቁጥር ነው።” ሲል ይጀምራል። ደራሲው በዚህ መንደርደሪያ (በርዕሱ ማብራሪያ ላይ ወዳስቀመጠው) ሰባት ቁጥር ብዙ የተመሰከረለት፣ ታሪካዊና መንፈሳዊ ምስጢሮችን ያዘለና ከሰው ጋር
የተቆራኘ ቁጥር ነው ወደሚለው መዳረሻው ይጓዛል። ብዙ ነገሮችንም ሰባት እንደሆኑ ለማመልከት ከሰማኒያ በላይ ሰባቶችን (በሰባት የተዘረዘሩ ነገሮችን) አሳይቷል።
በዚህ መጽሐፍ የደራሲው ዋና ዓላማ ሆኖ የምናገኘው ሰባት ቁጥር ያለውን የተለየ ባህሪና ጠቀሜታ አጉልቶ መግለጽ ነው። ሰባት ቁጥር ከሳይንስም ሆነ ከሃይማኖት ጋር የተለየና ተፈጥሯዊ ጥብቅ ቁርኝት እንዳለውም ያትታል። እንዲህ በማለት (በመግቢያው ላይ)
ደራሲው ስለ ሰባት ቁጥር ያለውን እምነት ለመግለጽ ተጠቀመበት እንጂ በውስጥ ይዘቱ ቁርጥ ያለ ድምዳሜ ከመስጠት ተቆጥቧል። “የሰው ልጅና ሰባት ቁጥር”፣ “ኢትዮጵያና ሰባት ቁጥር” በሚሉት አርዕስት ሰባት የሆኑ ነገሮችን ቢዘረዝርም፣ “በሰባት ቁጥር ይህን ማድረግ አለብን/ እንችላለን” የሚል መደምደሚያ ላይ መድረስን አልደፈረም። ስለሆነም አንባቢን (ምናልባት) “ይገርማል!” ከማሰኘት ባለፈ ሰባት ቁጥርን በመጠቀም (ስለመጠቀም) የሚያስተላልፈው ቀመራዊም ሆነ ስልታዊ ዕውቀትን አልያዘም።
የአጻጻፍ ስልቱና የቃላት አጠቃቀሙ ገላጭና ምቹ ነው። ንባብን የማያደናቅፈው የዓረፍተ ነገር አወቃቀሩ የታለመለትን ሐሳብ በበቂ እንዲያስተላልፍ አድርጎታል። ከአንድ በላይ ጭብጥ ይዘው የረዘሙት አንቀጾች ግን ለማራኪ ገጽታው እንደ ነቅ የሚቆጠሩ ሳንካዎች
ናቸው። አልፎ አልፎ ያሉት የፊደልና የሐሳብ ግድፈቶች ከዝርዝሮቹ ብዛት አንጻር ጥቂት ሊባሉ የሚችሉ ናቸው። ይሁን እንጂ እውነታዎችን ሲያስቀምጥ አንዳንዶቹ የጽሑፉ ግድፈቶች ጉልህና አንባቢንም የሚያስቱ ናቸው። ለምሳሌ (ገጽ 7) የአንታርክቲካን
የቆዳ ስፋት መጠን በቀጥታ ወደ ህዝብ ብዛት ዝርዝሩ ስለገለበጠው፤ ሀገርም ሆነ ተወላጅ ነዋሪዎች የሌለውን በረዷማው አህጉር አንታርክቲካን “14 ሚሊየን ህዝብ አለው” የሚል የተሳሳተ መረጃ  ጽፏል። (ገጽ 85) ደግሞ በፊደል የተገለፀው “ሰባት ሺህ ሰባ ሰባት” 7077 ሆኖ ሳለ 7707 ተብሎ ተጽፏል። እነዚህን መሰል ዕውነታዎች ሲዘረዝር የትኛው ሃሳብ ከየትኛው ምንጭ እንደተወሰደ ስለማያሳይ፤ ግድፈቱ የደራሲው አልያም የምንጩ መሆኑን ለመለየት አያስችልም።
ስለ ሳይንስ፣ ሒሳብና ቁጥር፡- ሳይንስ የምክንያትና የውጤትን ግንኙነትና ትስስርን የሚቃኝ ስልታዊ ጥናት እንደሆነ ይተረጎማል። በዚህ መጽሐፍ ግን ሳይንስን በተሰጠው ትርጓሜ (ወይም ሌላ ደራሲው በገለፀው ትርጓሜ) በወጥነት ከመውሰድ ይልቅ፤ ለሐተታው ጥቅም ብቻ (በአሉታዊ
እና/ወይም በአዎንታዊ) እንደተፈለገው ተገልጿል። “ሰባት ቁጥርን ሳይንስም መንፈሳዊውም የተለየ ስፍራ ሰጥተው ያዩታል” ማለት ሲፈልግ፣ “በአብዛኛው በዚች ዓለም የፈጣሪን ቦታ ተክቶ በሰው ልብ ውስጥ የነገሰውን ሣይንስና ሰባት ቁጥር . . .” (ገጽ 60) በሚል ሳይንስን እንደ ሃይማኖት፣ ሳይንሳዊያንን ደግሞ እንደ አማኝ ይቆጥራቸዋል። በሌላ መልኩ ደግሞ የተመረጡ ምሳሌዎችን ከሳይንስ ሲወስድ፣ ከሃይማኖት ጋር ያለውን ግጭት ችላ ብሎ ያልፈዋል። ለምሳሌ፡- “ሳይንስም የሰው ዘር መገኛ ኢትዮጵያ ናት ማለቱ . . .” (ገጽ 17)  ከሃይማኖት ጋር የማይዛመደውን የዝግመተ ለውጥን ጽንሰ ሐሳብ ይመዝዛል።
ደራሲው ስለ ሒሳብ በጉልህ ያነሳው ነገር ባይኖርም፣ ለቁጥርና ለሳይንስ ከሰጠው ትርጓሜ አንጻር ሒሳብን እንደ የሰው ልጅ ግኝት አይመለከትም። “ቁጥር ምንድነው?” የሚለውን ጥያቄ ስናነሳ፤ ሐሳብ፣ መጠን ወይስ ውክልና በሚሉት ዙሪያ እናጠነጥናለን። የዚህን
መልስ ልክ እንደ ቃላት አገባቡና አገልግሎቱ ይወስኑታል። ደራሲው (ገጽ 40) ላይ “ሰባ ጊዜ ሰባት” ሲል 490 ማለቱ እንዳልሆነና “ብዙ” የሚል ሃሳብን የሚወክል መሆኑን “ገደብ የሌለው” ሲል ተርጎሞታል። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ ዝርዝሮቹ ላይ በሚያነሳቸው ሰባቶች ላይ
ደግሞ ለመጠን ገላጭነት እና ለተምሳሌታዊ ውክልና ስፍራ ሳይሰጥ ሁሉንም በምስጢራዊነት ይወክላቸዋል። “ሰባት ቁጥርን ሳይንስ ሲመረምረው የተፈጥሮ ምስጢራትን ለመፍታት ወሳኝ ቁጥር ነው።” (ገጽ 9) በሚለው ላይ ማንኛውም ነገር በሰባት ቁጥር ይሰራል በማለትም የሰባት ቁጥርን በ“አድራጊ ፈጣሪነት” ይተረጉማል። ለዚህ ሐሳብ መደገፊያነት ያቀረበው “ከጥንት ጀምሮ ሰባት  ቁጥር በታሪክ ተደጋግሞ የሚመጣና በጠቃሚነቱም ዙሪያ በርካታ አፈ-ታሪኮች (mythology) ይነገራሉ” የሚለውን አስረጂ ነው።
የሰባት ቁጥር ሐተታው አካሄድ፡- ደራሲው ስለ ሰባት ቁጥር ሲያትት መሰረት አድርጎ የሚያስቀምጠው የቁጥሩ መገለጫ የለውም። ቁጥሩን የምናገኝበት አገባብ ብዛትን (Quantity)፣ ስፍርን (Count)፣ ድግግሞሽን (Frequency)፣ ልኬትን (Measure)፣ ደረጃን (Level) ወይም ቅደም ተከተልን (Order) ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ሰባት ብሎ የሚያነሳቸው ጥሩ (የተቀደሱ) ነገሮችን ይሆናል ወደሚል ድምዳሜም እንዳንመጣ፤ “ሰባቱ የስኬት ምስጢራት” እና “ሰባቱ የውድቀት መንገዶች” አሉት፣ “ሰባቱ አባቶች” እና “ሰባቱ ኃጢአቶች”ም በዝርዝሩ ውስጥ ይገኛሉ። ይህ በቁጥሩ ማንነት ላይ ተመስርቶ ለአንባቢ ጠቃሚና ተተግባሪ ጭብጥ እንዳያስተላልፍ ያደርገዋል።
ሰባት ቁጥር በመጽሐፍ ቅዱስ ስንት ጊዜ ተጠቅሷል? ደራሲው በመግቢያው “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰባት ቁጥር 735 ጊዜ የተጠቀሰ ሲሆን . . . ” የሚል ሐረግ ተጠቅሟል። በዚህ ደራሲው መናገር የፈለገው “ያለ ምክንያት በርካታ ጊዜ አልተጠቀሰም” ማለትን ነው። ሰባት ቁጥርና ኢትዮጵያን ምን እንደሚያገናኛቸውና የሰው ልጅ ህይወቱን ሲመራ ሰባት የብርሃን መንገዶች ሊከተል እንደሚገባም በመጽሐፉ መግቢያ ላይ መሪ ፍንጭ ሰጥቷል። በእርግጥም ይህ ጽንሰ ሐሳብ (በመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ጊዜ የተጠቀሰ ከሆነ) በሒሳብም በአንድ ስብስብ ውስጥ ያሉ አባላትን ባህሪ ለመግለጽ ከምንጠቀመው ከማእከላዊ አዝማሚያን (central tendency) መግለጫዎች አንዱ ድግግሞሽ (Frequency) ስለሆነ ከሒሳብም ጋር ስምም ይሆናል።
“ሰባት ቁጥር በመጽሐፍ ቅዱስ  ስንት ጊዜ ተጠቀሰ?” ለሚለው ምላሽ ለመስጠት በቀጥታ መቁጠር እጅግ አድካሚ ነው። ሰባት ቁጥር በመጽሐፍ ቅዱስ (በ81 መጻሕፍትም ቢሆን) የተጠቀሰበትን ብዛት (በኮምፒዩተር በታገዘ ስልት - Iota Software/PDF) ስናይ ከ350 ያልበለጠ ሆኖ እናገኘዋለን። ደራሲውም በዚህ ስልት “ሰባት”ን በ“ሰባ” ተክቶ የተጠቀመ ወይም በRev.Will Nelken “SEVEN IS THE NUMBER OF COMPLETENESS” በሚለው መጣጥፍ ላይ “The number seven is used in the Bible 735 times” የሚለውን መረጃ የወሰደ ይመስላል። (ምክንያቱም “ሰባ” የሚለውን መፈለጊያ ቃል ተጠቅመን ስናይ ብዛቱ 746 ሆኖ ደራሲው ከጠቀሰው 735 ጋር ተቀራራቢ ሆኖ እናገኛለንና (ልዩነቱ በSoftware ማሻሻያ (Update) ምክንያት የሚመጣ ለውጥ ይሆናል)። ነገርግን በዚህ የፍለጋ ስልት “ሰባ” የሚለውን መፈለጊያ በመጠቀማችን ፈጽሞ ቁጥርም ያልሆኑ ቃላትን አብረው እንዲቆጠሩ ያደርጋል። ለምሳሌ ብንመለከት (የ‘ሰባ’ም፣ ደረ‘ሰባ’ት፣ እሰበ‘ሰባ’ለሁ፣ መለ‘ሰባ’ቸው፣ ‘ሰባ’ብራቸው፣ ትታ‘ሰባ’ላችሁ፣ ከፈሰ‘ሰባ’ትም፣ ቤተ‘ሰባ’ችሁ፣ አ‘ሰባ’ት ... የመሳሰሉ) በርካታ ቁጥር ያልሆኑ ቃላትን እናገኛለን። በእንግሊዝኛውም ቢሆን “seven” የሚለውን ቃል የያዙ ግን ሌሎች ቁጥሮችን ስንነጥል፤ ሰባት ቁጥር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሌሎች ባልተለየ (ከ“አንድ” እና ከ“ሁለት” ደግሞ በጣም ባነሰ) ድግግሞሽ የሚገኝ ቁጥር ሆኖ እናገኘዋለን።
የመጽሐፉ “ሰባት” ዝርዝሮችና ሰባት ያልሆኑ “ሰባቶቹ”፡- የመጽሐፉ ይዘትና አቀራረብ በሰባት ቁጥር ላይ ማጠንጠኑ ሁለት ችግሮችን ፈጥሮበታል። አንደኛው የጀመራቸውን ዕውቀት አስጨባጭ ይዘቶች ሳያሳውቅና በቂ ግንዛቤም ሳይፈጥር ዘልሎ ወደ ቀጣዩ ዝርዝር እንዲሄድ ያጣድፈዋል። ለምሳሌ ስለ ባህሪና ጠባይ ምንነትና ልዩነት፣ ስለ ሃይማኖት እምነትና መንፈሳዊ ምግባራት፣ ስለ ርዕዮተ ዓለማት ሃይማኖታዊ ምዘና እና ስለ ሚዛናዊነት እንዲሁም አንዳንድ ታሪካዊ፣ መረጃ ሰጪና የግሳጼ መልዕክቶች ያዘሉ ይዘቶቹ ተነክተው ብቻ ታልፈዋል። እነዚህ ቁምነገሮች የመጽሐፉን ሰፊ ክፍል መያዝ (ወይም ሙሉ በሙሉ መተካት) ይችሉ የነበሩ የተሻሉ ይዘቶች ናቸው።
ሁለተኛው ችግር ደግሞ መጽሐፉ ካካተታቸው “ሰባት” የሆኑ ዝርዝሮች ውስጥ ብዙዎቹ ደራሲው ባልበለፀገበት የዕውቀት ዘርፍ ውስጥ የሚገኙ በመሆኑ ለስህተት ዳርገውታል። በተለይ ከላይ እንዳነሳነው የሰባት ቁጥርን ምንነትና ጥቅም ባለማወቅ (በመተው) ወደ
ዝርዝሩ ማድላቱ በሰባት የማይገለጹ (ያልሆኑ)፣ የተሻሻሉ፣ የተለወጡ እና የማይቆጠሩ “ሰባቶችን” እንዲዘረዝር አድርጎታል። ለዚህ ገላጭ ምሳሌ የሚሆኑትን በሚያመች ምድብ ከፋፍለን እንደሚከተለው እንመለከታቸዋለን።
ያልተዛመዱ ሰባቶች፡- በዚህ መደብ ፈጽሞ በአንድነት የማይቆጠሩና የማይዛመዱ ሰባቶችን ቁልቁል ይዘረዝራል። ለምሳሌ በሰባቱ ሕይወት ዝርዝሩ ውስጥ (ገጽ 3) “የፈጣሪ ሕይወት፣ የሰው ሕይወት . . . የነፋሳት ሕይወት” አሉ፤ ሰባቱ አባቶች ላይ ደግሞ (ገጽ 80) ፈጣሪ፣ ወላጅ አባት፣ . .
. የጡት አባት . . . በማለት ሰብስቦ ፈጣሪን፣ ወላጅን፣ መካሪን፣ አስተማሪንና አሳዳጊን እንደ አንድ ዓይነቶች (አባቶች) አብሮ ይቆጥራል።
ተደግመው የሚቆጠሩ ሰባቶች፡- በሒሳብ ትርጓሜ መሰረት ስብስብ ማለት በውል የተወከሉ ነገሮች ጥርቅም ነው። ስለሆነም አንድን ነገር የየትኛው ስብስብ አባል መሆኑን ወይም አለመሆኑን በውል መለየት ይቻላል። በዚህ መጽሐፍ ግን ሰባቱ ምግበ ስጋ (ገጽ 19)፣ ሰባቱ ህሊናዎች (ገጽ 21)፣ ሰባቱ የገነት ዛፎች (ገጽ 95) . . . በሚል የቀረቡት ክፍፍሎች ተደራራቢነትን ያስተናግዳሉ። የበለፀገ ህሊና ንቁ ህሊናም ነው፣ የዓይን ማረፊያ ዛፍ የምግብም፣ የመድኃኒትም፣ የተፈጥሮ ሚዛን መጠበቂያም ሊሆን ይችላል፣ ማርን ደግሞ ከ“ሰባቱ ምግበ ስጋ” ዝርዝር ውስጥ ለመመደብ እንቸገራለን።
ከሰባት የተቆረጡ ሰፋፊ ይዘቶች፡- ለምሳሌ፡- ርዕዮተ ዓለማት (Worldviews) (ገጽ 53 - 59) በሚል ስር የተቀመጡት ሰባት ዝርዝሮች ውስጥ ያሉት ይዘቶች በስድስት ገጾች ይወሰኑ እንጂ የሰፊ ሃሳብ ቅንጭብ ናቸው። በዚህ አከፋፈል ዋናዎቹ መዘርዘራቸውና ንዑሶቹ እንደ ዋና መወሰዳቸው፣ በፍልስፍናና በሃይማኖት አስተምህሮ ሊለዩ የሚችሉት መቀላቀላቸውና ያልተካተቱት ደግሞ መዘለላቸውን ስናይ፤ ሰባትን ለማሟላት የተሄደበት መንገድ ካልሆነ በቀር ሃሳቡን በምክንያታዊ አዘራዘር መሰረት (ያለ “ሰባት”) ማስረዳት ቢቻል ተመራጭ ነበር።
ትርጉም የለቀቁ ሰባቶች፡- ሰባቱ የፈጣሪ እይታዎች (ገጽ 2) ላይ “አምላክ ፍጥረቱን ካለመኖር ወደ መኖር ሲያመጣ የተመለከተው ሰባት ጊዜ ነው።” በሚል መነሻ ኦሪት ዘፍጥረት ላይ የተጻፉትን “እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ” ዎች ቆጥሮ ብዛታቸውን ሰባት ያደርጋቸዋል። እዚህ ላይ “አየ” የሚለው ቃል የተጻፈበትን ድግግሞሽ ቆጥሮ “ሰባት ጊዜ ብቻ ተመለከተ” ማለት ከሃይማኖት ወደተለየና ወደተሳሳተ (“ከሰባት ጊዜ በላይ አላየም”) ትርጉም ይወስደዋል። በተመሳሳይ (ገጽ 105) ክርስቶስ በመጽሐፍ ቅዱስ “እኔ” እያለ አስተዋውቋል በሚል “ሰባቱ የክርስቶስ ማንነቶች” በሚል ሰባት ሆነው ተቀምጠዋል። ይህ ደግሞ የማይቆጠረውን መቁጠር ይሆናል።
ወደ ሰባት ያደጉ ሰባቶች:- ስያሜ የጋራ ስምምነት እንደሆነ ይታወቃል። ቀደም ሲል የተለያዩ የውቅያኖሶች ስያሜና ቁጥር የነበረ ቢሆንም የቅርብ መረጃዎች፣ ደቡባዊ ውቅያኖስን ጨምሮ ያሉት ውቅያኖሶች አምስት መሆናቸውን አስቀምጠዋል። ከጥንት ጀምሮ “ሰባቱ ባህሮች” የሚል አፈ-ታሪክ ነበር። ይህ አፈ-ታሪክ ከአሁኑ አጠራር ጋር ሲዛመድ፣ ሰሜንና ደቡብ አትላንቲክና ፓስፊክ ውቅያኖስን ለሁለት በመክፈል ሰባቱን ስፍራዎች ሊሆኑ ይችላሉ ተብሎ ይገመታል። በዚህ መነሻ (ይመስላል) (ገጽ 8) ደራሲው አምስቱን ውቅያኖሶች ሰባት በማለት ዘርዝሯል። በ“ሰባቱ ባህሮች” አፈ-ታሪክ መነሻ የአሁኖቹን ባህሮች ከቆጠርን ደግሞ ቁጥራቸው ሰባት ሳይሆን ወደ ሃምሳ ይጠጋል።
የተሳቱ ሰባቶች፡- እዚህ ላይ ነገሮቹ ሰባት የመሆናቸውን ትክክለኛ መረጃ ይዞ በመነሳት ያልሆኑ ሌሎች ሰባት ዝርዝሮች የገቡበት ነው። (ገጽ 10) “የሳይንስ ጠበብት፣ የስነመለኮት ሊቃውንት እና የስነ ፈለክ ተመራማሪዎች በጥናታቸው እንደገለጹት” በሚል ሰባት መለኪያዎችን  ይዘረዝራል። በሳይንስ መሰረታዊ ሆነው የሚታወቁት መለኪያዎች፤ ጊዜ (s)፣ ርዝመት (m)፣ ግዝፈት (kg)፣ የኤሌክትሪክ ፍሰት (A)፣ መጠነ ግለት (K)፣ የንጥረ ነገር መጠን (mol) እና የብርሃን ጥንካሬ (cd) ናቸው። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ “ቦታ” የሚለው “ርዝመት” ለማለት ነው ብለን ብንወስድ እንኳ ግዝፈትን፣ የኤሌክትሪክ ሞገድን እና ሙቀትን ተክቶ መሠረታዊ ያልሆኑትና በመሰረታዊያኑ ጥምረት የሚለኩት “አቅም” (power) (Watt (W) = kg.m2/s3)፣ “የድምጽ አቅም” (Decibel = W/m2) እና በብርሃን  አንፀባራቂነቱ የሚለካውን “ቀለም” አስገብቷል።
ያልተቆጠሩ ሰባቶች፡- በዚህ ስር ለመረዳት የማያዳግቱ ነገር ግን እንደየ ትርጓሜው (definition) መጠኑ ሊለያዩ የሚችሉ አከፋፈሎችን በሰባት ወስኖት እንመለከታለን። ለምሳሌ ሰባቱ ቀዳዳዎች (ገጽ 17) የላብ ማስወገጃ እንደ አንድ ተቆጥሮ የሴቶች ጡት ተዘሏል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ
ሰባቱ ፈሳሾች (ገጽ 18) በሚል የተዘረዘሩት ላይ (ለምሳሌ) የእናት ወተትን፣ የማህጸን ፈሳሽንና ሐሞትን አናገኛቸውም። በተቃራኒው ደግሞ (ገጽ 20) “አንጎል የቦካ ስፖንጅ መሳይ ሲሆን 70% የተሞላው በፈሳሽ ነው።” እንደማለቱ ይሄን ፈሳሽ በቀደመው ዝርዝር
ውስጥ አካትቶት አናገኘውም። ሰባቱ አዲሶች (ገጽ 104) ላይ “አዲስ ከተማ” እና “አዲስ አደባባይ” በዝርዝሩ ውስጥ ካሉ “አዲስ ዘመን” እና “አዲስ ተስፋ” የመሳሰሉት የማይገቡበት ምክንያት የለም።
ሰባተኛ ያልሆኑ ሰባቶች፡- በሒሳብ 3D ለምንለው ምስላዊ አገላለጽ እንዲያመች የምንጠቀማቸው ዘዌዎች (x-axis, y-axis, z-axis) ይኑሩ እንጂ አቅጣጫዎች እልቆቢስ (infinite) ናቸው። (ገጽ 49) “አቅጣጫዎች ሰባት መንገድ አሏቸው።” በሚል “ፊትና ኋላ”፣ “ግራና ቀኝ”፣
“ላይና ታች” ተብለው ስድስት አቅጣጫዎች ተደርገው “መሐል” ሰባተኛው አቅጣጫ ሆኗል። አቅጣጫ ማለት መነሻ ያለው ቀጥተኛ የመንገድ ትልም ስለሆነ “መሐል” (ነጥብ) መነሻ ስፍራ እንጂ ፈጽሞ አቅጣጫ አይደለም።
ምንጭ አልባ ሰባቶች፡- (ገጽ 67) “በዘመናዊ ሳይንስ ቀመር መሰረት፤ በዓመት ሰባት ጊዜ ፀሐይ ልትጋረድ ትችላለች።” ይላል፤ ነገር ግን የNASA ድረገጽ ላይ የምናገኛቸው ወቅታዊ መረጃዎችም ሆነ ሌሎችም ምንጮች በዓመት የሚኖረው የፀሐይ ግርዶሽ ከ2-3 ጊዜ እንደሆነ ነው ያስቀመጡት።
ማጠቃለያ፡- ደራሲው ይህን መጽሐፍ ያዘጋጀበት ምክንያት ሰባት ቁጥር ላይ ያለውን መደነቅ ለአንባብያን ለማጋባት እንደሆነ መረዳት ይቻላል። ደራሲው (በግልጽ ባያስቀምጠውም) ቁጥሮች የሰው ልጅ ችግሩን ለመፍታት እንዲያገለግሉት ያዘጋጃቸው ረቂቅ ቁሶች መሆናቸውን እንደሚያምን ሳይሆን፤ እንደ ሌሎች ፍጡራን ሁሉ ፈጣሪ ቀድሞ የፈጠራቸው እንከን አልባ ስሪቶቹ መሆናቸውን ያመነ ሆኖ እንመለከታለን። ለዚህ እንደ አንድ ማሳያ (ገጽ 103-104) “ሰባተኛው ዓመት የምድር እረፍት ነው” በሚለው ጽሑፍ ውስጥ የሰባት ቁጥር አስቻይነት ላይ እምነት እንዳለው፣ “የዚህ አዲስ ዓለም መሰረቱ ደግሞ ሰባት ነው።” በማለት ጽፏል።
የሒሳብና ሥነ-ትምህርት ሊቃውንት፣ በሒሳብ ረቂቅ ሐሳቦች ላይ “ግኝት ወይስ ፈጠራ” በሚል በሁለት ጎራ ይከራከራሉ። በሁለቱም ዘውግ ቢሆን ሒሳብና የሒሳብ ረቂቅ ሐሳቦች የሰው ልጅ ጥረት ውጤት መሆናቸውን፤ እንዲሁም ሊለወጡ ወይም ሊስተካከሉ
የሚችሉ መሆናቸው ላይ ግን አንድነት አላቸው። የቁጥሮችንም ጥንታዊ ታሪክ ስንቃኝ አብዛኛው ማኅበረሰብ ከ“አንድ” እና ከ“ሁለት” (ጥንድ) የዘለለ የቁጥር ስያሜና ምልክት ያለው ሆኖ አናገኘውም። ሲቆጥር የኖረውም “አንድ” እና “ጥንድ”ን በጣምራ በመጠቀም
ነበር። ሶስትን “አንድ ከጥንድ”፣ አራትን “ጥንድ ጥንድ” . . . እያሉ ነበር የሚቆጠሩት። ለዚህም ይመስላል ከ“አንድ” እና ከ“ሁለት” በስተቀር የሌሎቹ ቁጥሮች ስያሜ ተቀራራቢ የሆነው። ለምሳሌ በአማርኛ “አንድ ሁለት ሶስት አራት”፣ በእንግሊዝኛ “one two three four”፣ በፈረንሳይኛ “un deux trois quatre”፣ በሂብሪው “//////”፣ በኦሮምኛ “tokko lama sadii afur”፣ በሂንዱ “एक दो तीन चार” (ek do teen chaar) . . . መሆኑን ስንመለከት ስያሜያቸው በ“አንድ” እና በ“ሁለት” የተለያዩ ሆነው ለ“ሶስት” እና ለ“አራት” ግን ተቀራራቢ ድምፀት አላቸው። ይህም ቁጥሮችን በዓለም ዙሪያ ያለው የሰው ልጅ ተጠብቦ የደረሰባቸው የሐሳብ ምጥቀት ውጤት (በፈጣሪ ፀጋ የተገለፁለትም ብንል) እንጂ ጥንቱን የነበሩ ፍጡራን አልነበሩም ለሚለው አንድ አስረጂ ይሆነናል።
በመጨረሻም . . . የቁጥሮችን “ፍጽምና” ከፈጣሪ ስሪት ጋር ማዛመድና ከአገልግሎታቸው የራቀ ትርጉም መስጠቱ ከአፍቅሮተ ቁጥር ወደ አምልኮተ ቁጥር ያሻግራል። ለቁጥሮችም የሚሰጠው የተለየ ልዩ አቅም ትርጓሜያቸውን ወደሳተ እምነትና ቁጥርን አምኖ
ወደ መዘፈቅ ያስገባል። ይህ በቁጥር ላይ የሚጣል እምነት ለ(በ) ሥርዓት የተዘጋጁትን (ለምሳሌ መድኃኔዓለምን ከ27፣ ማርያምን ከ21፣ ሚካኤልን 12) እንደ ተፈጥሯዊ ተቆራኞች በመቁጠር በፍላጎት ለሚሰራ ቀመርና በምኞት ለሚሰጥ ተዛምዶ ይጥላል። ደራሲውም ማስተላለፍ የፈለገውን ሐሳብ በአግባቡ እንዲያደርስና ባልበለፀገባቸው ዘርፎች ገብቶ ከመስመጥ እንዲያድነው ይዘቶቹን በቁጥር ስፍር ሳይከረክምና የግድ ሳያጋባ ቢያቀርብ መልካም ነው እላለሁ።


Read 2047 times