Saturday, 14 January 2023 10:44

7ኛው ቻን ትናንት ተጀምሯል ዋልያዎቹ ከሞዛምቢክ ይጫወታሉ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን አዘጋጅነት በየሁለት አመቱ የሚካሄደው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ቻን ለሰባተኛ ጊዜ በአልጄርያ አዘጋጅነት ትናንት ተጀምሯል፡፡ በመክፈቻው ጨዋታ ላይ በምድብ 1 የሚገኙት አልጄርያና ሊቢያ የተጫወቱ ሲሆን በዚሁም ምድብ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከሞዛምቢክ ጋር ዛሬ 10 ላይ ይጫወታል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለ3ኛ ጊዜ በሚያደርገው የቻን ተሳትፎው የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግብ ከፌደሬሽኑ የላቀ ድጋፍ አግኝቷል፡፡ ሻምፒዮናው ከመጀመሩ በፊት ለስምንት ቀናት በሰሜን አፍሪካዋ ሞሮኮ ዝግጅት ሲሰራና የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን ሲያደርግ መቆየቱ የተሰጠውን ትኩረት ያመለክታል፡፡
የቻን ጨዋታዎችን በመላው አፍሪካ የማስተላለፍ ፍቃድ ያለው ሱፕርስፖርት ሲሆን የዋልያዎቹን ፍልሚያዎች በልዩ ቻናል 240 ላይ እንዲሁም በፉትቦል ኤችዲ ቻናል እንደሚያስተላልፍ የዘገበው ሶከር ኢትዮጰያ ነው።
7ኛው ቻን ከመጀመሩ ሁለት ቀናት ቀደም ብሎ  ያለፈው ሻምፒዮን ሞሮኮ ከተሳትፎ ራሷን ያገለለችበት ውሳኔ አስታውቃ ነበር። ዋናው ምክንያት በሁለቱ የሰሜን አፍሪካ አገራት መካከል ያለው የፖለቲካ ውጥረት፤ የሞሮኮ ብሄራዊ ቡድን በሚያርፍበት ከተማ እና በሚጠቀመው አየር መንገድ ዙርያ የተፈጠሩ ውዝግቦች ናቸው፡፡ የሞሮኮ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተቃራኒ ቡድኑን በሞሮኮ አየር መንገድ ቻርተር በረራ ወደ ኮንሰተንቲን ሊጓጓዝ ያቀረበው ጥያቄ የአልጀሪያ መንግስት አልተቀበለውም፡፡ የሞሮኮ ፌዴሬሽን በምላሹ ደስተኛ ባይሆንም ትናንት በውድድሩ ላይ እንደሚሳተፍ አስታውቋል። በነገራችን ላይ በቻን ተሳትፎ ላይ ቅሬታ በማሰማት ሞሮኮ ብቸኛዋ አይደለችም፡፡ ካሜሮን ከጸጥታ ጋር በተያያዘ  ላለመሳተፍ አቅማምታ ነበር። ኡጋንዳና ሊቢያም በህጋዊ እና በፋይናን ጉዳዮች ተሳትፏቸውን ለመሰረዝ አመንትተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ቻን ለአውሮፓ እግር ኳስ መልማዮች አዳዲስ አፍሪካዊ ተጨዋቾችን የሚያገኙበት መድረክ እየሆነላቸው መምጣቱን የቢቢሲ ሀተታ አመልክቷል፡፡ በ22ኛው የዓለም ዋንጫ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ግማሽ ፍፃሜ የደረሰው የሞሮኮ ቡድን ላይ የታዩት ተጨዋቾች የዚሁ ሻምፒዮና ውጤት ናቸው፡፡ በቻን ሻምፒዮናው ላይ በእንግሊዝ እና ፈረንሳይ ለሚገኙ ክለቦች የሚሰሩ መልማዮች በስፋት  ይሰማራሉ ብሏል- የቢቢሲ ዘገባ፡፡ ከአውሮፓ ክለቦች ባሻገር በአህጉራዊ ደረጃ ለሚገኙ የአፍሪካ ክለቦች አዳዲስ ተጨዋቾችን ከተለያዩ አገራት ለመውሰድ ቻን ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረላቸው ይገኛል፡፡
ለሶስት ሳምንታት የሚካሄደውን ቻን የአልጄርያዎቹ ከተሞች አልጀር፤ አነናባ፤ ኮንታቲንና ኦራን ያስተናግዱታል፡፡ ተሳታፊ 18 ብሄራዊ ቡድኖችን በዋና አሰልጣኝነት በመያዝ 15 አፍሪካውያን አሰልጣኞች የሚገኙ ሲሆን  ባለፉት 6 የቻን ውድድሮች አምቱ አፍሪካውያን እንደነበሩ ተወስቷል፡፡ ሳንቶስ ሙቱባይል ከዲሪ ኮንጎ ጋር በ2009፤ ሳሚ ትራቤሊዚ ከቱኒዚያ ጋር በ2011፤ ፍሎረንት ኢቤንጌ ከዲሪ ኮንጎ በ2016፤ ጀማል ሴሚና ሁሴን አማውንታ ከሞሮኮ ጋር በ2018 እና በ20120 ላይ ቻንን ያሸነፉ ትውልደ አፍሪካዊ አሰልጣኞች ናቸው፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን እንዳስታወቀው በ7ኛው ቻን ላይ 52 ዳኞች የተመደቡ ሲሆን 19 የመሐል ዳኞች፤ 12 ረዳት ዳኞችና 12 የቪድዮ ረዳት ዳኞች ናቸው፡፡ 3 የሴቶች ዳኞች ከዝርዝሩ ውስጥ ይገኙበታል፡፡

Read 827 times