Monday, 09 January 2023 10:18

የሴት መሀንነት

Written by  ሀይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

በአለም አቀፍ ደረጃ በአንድ አመት ውስጥ ከ10 እስከ 15 በመቶ የሚሆኑ ጥንዶች የመሀንነት ችግር ያጋጥማቸዋል። መሀንነት በሁለቱም ፆታዎች ላይ የሚከሰት ሲሆን በችግሩ ላይ ግማሽ በግማሽ (እኩል) ድርሻ አላቸው። ወንዶች ላይ ስለሚከሰት ልጅ ያለመውለድ ችግር ከዚህ ቀደም በነበረው እትም ይዘን ቀርበናል። በዚህ ፅሁፍ ስለ ሴቶች መሀንነት ትኩረት አድርገናል።  
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የመሀንነት እና የስነ ሆርሞን ህክምና ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር አቤል ተሾመ እንደተናገሩት የወር አበባ ሳይዛባ ኡደቱን ጠብቆ የሚመጣ፣ እንቁላል በአግባቡ የሚመረት፣ የተመረተው እንቁላል የሚተላለፍበት መስመር ክፍት እና አገልግሎት የሚሰጥ እንዲሁም ማህፀን ፅንስ የሚቀበል(የሚሸከም) ከሆነ አንዲት ሴት መፀነስ ትችላለች። ነገር ግን ከእነዚህ ነገሮች አንዱ ከተጓደለ ልጅ ያለመውለድ ችግር ሊያጋጥም ይችላል።
በተፈጥሮ የሚከሰት መሀንነት
ተርነር ሲንድረም [Turner syndrome] እንቁላል ማምረቻ (ovary) ሙሉበሙሉ አለመኖር (አለመፈጠር)
 ማህፀን አለመኖር
አንዲት ሴት ይዛ የምትወለደው እንቁላል ወደ 2 ሚሊየን ነው። ይህ እንቁላል ከእናቷ ማህፀን ጀምሮ እንዲሁም በየወሩ በሚኖራት የወርአበባ ኡደት አማካኝነት እየቀነሰ ይሄዳል። ይህ እንቁላል የመቀንስ ኡደት ከ35 አመት (እድሜ) በኋላ ይበልጥ ይጨምራል። ከእዚህ እድሜ በኋላ ቁጥር ብቻ ሳይሆን የእንቁላሎች ጥራትም ይቀንሳል።
ፓሊሲስቲክ ኦቫሪ ሲንድረም [Polycystic ovary syndrome]; ብዙ የእንቁላል ከረጢት ይኖራል። ነገር ግን እንቁላል በየ[አንድ] ወር አይለቀቅም።
እድሜያቸው ከ40 አመት በታች በሆኑ ከ1 መቶ ሴቶች መካከል 10 ሴቶች ላይ እንቁላል ማለቅ ያጋጥማል። ይህም ያለ እድሜ ማረጥ ማለት ነው። በየትኛውም ልጅ መውለድ ይቻላል ተብሎ በሚገመትበት እድሜ ላይ ሊከሰት ይችላል።  
ከጊዜ በኋላ የሚከሰት መሀንነት፤
መድሀኒቶች; ለምሳሌም ለአይምሮ ህመም የሚወሰድ መድሀኒት የሴት እንቁላል እንዳይለቀቅ ሊያደርግ ይችላል።
ለካንሰር ህመም የሚሰጥ የጨረር ህክምና፤
የአባላዘር በሽታ እና ኢንፌክሽን [የቲቢ ኢንፌክሽን በልጅነት ከነበረ]
የማህፀን ግድግዳ ላይ እጢ መኖር፤
የሴት መሀንነት ምልክቶች፤
የወር አበባ ኡደት መዛባት; የወር አበባ ከ21 እስከ 35 ቀናት ውስጥ በየወር[1 ወር] ኡደት ማድረግ ሲኖርበት በጣም ቶሎ ቶሎ ወይም ዝግይቶ የሚመጣ ከሆነ የመሀንነት አንዱ ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል። በተጨማሪም ግዜውን ጠብቆ ኡደቱን የሚያካሂድ መሆን አለመሆኑን በሚኖረው ምልክት ማወቅ ይቻላል። ይህም አንዲት ሴት የወርአበባ ከማየቷ አስቀድሞ ጡት የመወጠር፣ የጀርባ ህመም እና ሌሎችም ከወርአበባ መምጣት ጋር ተያይዞ የሚሰማት ስሜት(ምልክት) ማለት ነው። ይህ ምልክት ያልተዛባ የወርአበባ ኡደት መኖሩን እና እንቁላል በአግባቡ እየተመረተ መለቀቁን ማሳያ መንገድ ነው።
አነስተኛ የሆነ የወርአበባ ማየት እና ሙሉ በሙሉ አለመኖር
በተፈጥሮ የሚከሰት (ተርነር ሲንድረም) ያጋጠማቸው ሴቶች በልጅነት እድሜ ላይ የልብ ህመም ማጋጠም፣ የአፍንጫ አጥንት ሰፊ መሆን፣ ትናጋ (ሀይአርቺ ፓሌት) ወደ ውስጥ ስርጉድ ማለት፣ የእንቅርት (ጎይተር) መኖር፣ አንገት በጣም አጭር እና ቆዳው የተሸበሸበ መሆን፣ ደረት ግልብጥ ማለት እና አምስተኛ የእጅ ጣት በጣም አጭር መሆን ሊስተዋል ይችላል።
በጉርምስና ወቅት የሚኖር የሰውነት ቅርፅ ለውጥ፣ ጡት ማደግ፣ ቁመት መጨመር እና ሰውነት ላይ ፀጉር መብቀል ላይኖር ይችላል።
በተፈጥሮ ሙሉለሙሉ እንቁላል ማምረቻ የሌላት ሴት የወርአበባ ኡደት አይኖራትም(አታይም)።
የህክምና አይነቶች
አይ ዩ አይ (IUI); አንዲት ሴት እንቁላል በአግባቡ ማምረት ካልቻለች (ኦቩላቶሪ ዲስኦርደር ካለባት) እንቁላል ማፋፊያ እንዲሰጣት ይደረጋል። ይህ ህክምና የሴቷ የእንቁላል ማምረት ችግር እንዳለ ሲታወቅ ብቻ ሳይሆን የማህንነት ችግር የማን እንደሆነ(ከጥንዶቹ) መለየት በማይቻልበት ወቅት ይሰጣል። ሴቷ[ሚስት] የወርአበባ በምታይበት ወቅት እንቁላል ማፋፊያ ይሰጣታል። ይህ የፋፋ እንቁላል ከከረጢት እንዲወጣ እና ወደ የማህፀን ቱቦ እንዲገባ(እንዲሄድ) ይደረጋል። የወንዱ[ባል] ዘር ፈሳሽ ተወስዶ በቤተሙከራ [ላብራቶሪ[ የተለያየ ሂደቶችን ካለፈ በኋላ የተሻለ እንቅስቃሴ ያለው የዘር ፍሬ ይመረጣል። የተመረጠው የዘር ፍሬ በመርፌ(ሲሪንጅ) ወደ ማህፀን ውስጥ በማስገባት ጽንስ እንዲፈጠር ይደረጋል።
አይ ቪ ኤፍ(IVF); የአይ ዩ አይ ህክምና ውጤታማ ካልሆነ ማለትም ለሶስት ጊዜ ተሞክሮ ካልተሳካ ወይም የማህፀን ቱቦ(መስመር) መዘጋት ሲያጋጥም አይ ቪ ኤፍ አማራጭ ይሆናል። ህክምናው የሚሰጠው የሴት እንቁላል እና የወንድ የዘር ፍሬ በላብራቶሪ እንዲገናኝ (እንዲዋሀድ) በማድረግ ፅንስ በመፍጥር ወደ ማህፀን በማስገባት ነው።
ከላይ ከተጠቀሱት መንገዶች በተጨማሪ የሴት እንቁላል እና የወንድ የዘር ፍሬ ተወስዶ በሌላ ሴት ማህጸን ኪራይ እንዲረገዝ እስከማድረግ የሚያስችል የህክምና ዘዴ አለ፡፡ ይህ ህክምና ግን በኢትዮጵያ እየተሰጠ አይደለም፡፡ ምክንያቱም በህግ ማእቀፍ ፍቃድ ያልተሰጠው በመሆኑ ነው ሲሉ የህክምናው ባለሙያ ተናግረዋል፡፡
የመሀንነት እና የስነ ሆርሞን ህክምና ሰብ ስፔሻሊስት ለሆኑት ዶ/ር አቤል ተሾመ “ለመሀንነት ችግር በኢትዮጽያ የሚሰጠው ህክምና ምን ያህል ውጤታማ ነው?” የሚል ጥያቄ አቀረብንላቸው። የህክምና ባለሙያው “ህክምናውን ካገኙ 10 ሴቶች መካከል አንድ ሴት ትፀንሳለች። እንዲሁም በተደጋጋሚ ሲሞከር የመፀነስ እድል ይጨምራል” በማለት ምላሽ ሰተዋል። ባለሙያው አክለውም አይ ዩ አይ (IUI) እስከ ሶስት ጊዜ መሞከር እንደሚቻል እና ካልተሳካ አይ ቪ ኤፍ(IVF) መሞከር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። “ተስፋ መቁረጥ አያስፈልግም” ብለዋል የህክምና ባለሙያው። ነገር ግን እንደ ባለሙያው ንግግር የሴት እድሜ ከ35 አመት በላይ ከሆነ የመሳካት እድል እንደሚቀንስ ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል። የሴት ልጅ እድሜ ከፍ እያለ ሲሄድ የእንቁላል ቁጥር ብቻ ሳይሆን ጥራቱም ይቀንሳል። ስለሆነም የህክምናው መሳካት ወይም አለመሳካት ላይ የሴት እድሜ(የእንቁላል በቁጥር እና በጥራት መኖር) ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል።
የመሀንነት መከላከያ መንገዶች
በወጣትነት (ከ35 አመት በፊት) መውለድ; የህክምና ባለሙያው እንደተናገሩት ከሴት ልጅ እድሜ ጋር ተያይዞ የእንቁላል ማለቅ ወይም ጥራት መቀነስ ለመፀነስ ብቻ ሳይሆን ከተፀነሰ በኋላ ፅንሱ እንዲቋረጥ (ውርጃ)፣ የተለያየ ተፈጥሯዊ ችግር ያለበት ልጅ እንዲፀነስ እና የአፈጣጠር (ተፈጥሯዊ) ችግር ያለበት ልጅ እንዲወለድ ሊያደርግ ይችላል። የወንድ የዘር ፍሬ እክል ካላጋጠመው በእድሜ መጨመር አያልቅም[አይቀንስም]። ስለሆነም በተለይ ሴቶች በወጣትነት እድሜ ማለትም ከ35 አመት በፊት እንዲወልዱ ይመከራል።
ልቅ የሆነ የግብረ ስጋ ግንኙነትን መከላከል; ለመሀንነት በሽታ አንዱን ምክንያት ኢንፌክሽንን የሚፈጥር እንደመሆኑ እራስን ከአባላዘር በሽታ መጠበቅ ያስፈልጋል።
ለካንሰር ህመም የሚሰጥ የጨረር ህክምና ካለ አስቀድሞ ወደ የመሀንነት እና የስነ ሆርሞን ህክምና ሰብ ስፔሻሊስት ወይም የማህፀን እና ፅንስ ህክምና ስፔሻሊስት ጋር መሄድ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ጨረሩ ልጅ ያለመውለድ ችግርን ሊያስከትል ይችላል። ስለሆነም ወደ ባለሙያዎች መሄድ የሴት እንቁላል ወይም የወንድ የዘር ፍሬ ላይ አደጋ ከመድረሱ አስቀድሞ በህክምና ባለሙያዎች ተወስዶ ፅንስ ለመፍጠር ያስችላል። ከታካሚዎች በተጨማሪ የካንሰር ህክምና የሚሰጡ የህክምና ባለሙያዎች እንዲተባበሩ ዶ/ር አቤል መልዕክት አስተላልፈዋል።
የመሀንነት እና የስነ ሆርሞን ህክምና ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር አቤል ተሾመ አክለው የመሀንነት ችግር የሁለቱም ፆታ መሆኑን በመገንዘብ አስቀድሞ ለመከላከል እንዲሁም ህክምና ለማግኘት ሁሉም ማህበረሰብ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል።

Read 1377 times