Monday, 09 January 2023 10:03

ውዱ ኢትዮጵያዊ የህክምና ሰው በቀጠር (ኳታር)

Written by  ጌጡ ተመስገን (የጉዞ ማስታወሻ)
Rate this item
(0 votes)

 በቀጠር (ኳታር) አንቱ የተባሉ ኢትዮጵያዊ ፍለጋ ላይ ነኝ። አብዱጀሊል ሱልጣን   ደግ ልቡን ይዞ ከእርሳቸው ጋር ቀጠሮ ይዟል። ይሁንና እውቁ ሠዓሊ ተሰማ ተምትም በስልክ ደውሎ የአጭር አጭር ቀጠሮ ያዘልኝ።
በመኪና ወደ DOC Medical Center - Marina Lusail, Tower 50, Lusail, Qatar ከነፍን - ዶ/ር አማኑኤል ቶሎሳን ለማግኘት፤ ለማውጋት ተጣድፌያለሁ። በመላው ዓለም የሚፈለጉ ሰው - ስመ-ጥር የአጥንትና የአከርካሪ ቀዶ ህክምና ከፍተኛ ባለሙያ በሺዎች የሚቆጠሩ ህክምና ፈላጊዎች ፈውስና ደህንነት ለማግኘት፣ ቀጠሮ ለመያዝ በሚጣደፉበት ሰዓት (በተወደደ ጊዜ) አክብረውኝ የአጭር አጭር ቀጠሮ መስጠታቸው አስደንቆኛል፤ አስፈንድቆኛል።
DOC Medical Center ~ አስጎበኙኝ። ፍሬ ያፈራ ዛፍ ያጎነብሳል። ሙያ ከትህትና ጋር ሲሆን እንዲህ በእጅጉ ያስቀናል።
ዶ/ር አማኑኤል ቶሎሳ እ.ኤ.አ በ1964 ወለጋ ግምቢ ተወለዱ።
ከሊባኖስ ባለቤታቸው ጋር በትዳር ተሳስረው፣ ሁለት ልጆችን ወልደው ለመሳም በቅተዋል። አሁን በቀጠር (ኳታር) DOC Medical Center ባለቤትና የበላይ ኃላፊ ሆነው እየሰሩ ናቸው። የእርሳቸውንም፤ የኢትዮጵያንም ስም በድንቅ ሕክምናቸው ከፍ አድርገዋል።
በአጠቃላይ ህክምና የዶክትሬት ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ፊንላንድ በሚገኘው የኩኦፕዮ ዩኒቨርስቲ (University of Kuopio) በአጥንትና ትራውማቶሎጂ ትምህርት መስክ (Orthopedic and Traumatology) ተጨማሪ ትምህርት ተከታትለዋል፡፡
ዶ/ር አማኑኤል ቶሎሳ እንግሊዝ ሀገር ከሚገኘው ሊድስ ዩኒቨርስቲ በሰው ልጆች አሰቃቂ ገጠመኝ ምክንያት ለሚከሰት የአዕምሮ በሽታና በጀርባ ወይም በአከርካሪ አጥንት ህክምና ስፔሻላይዝድ ያደረጉ ሲሆን በመገጣጠሚያ መተካት (Joint Replacement) እንዲሁም በአሰቃቂ ገጠመኝ ምክንያት ለሚከሰት የአዕምሮ በሽታ (Trauma) ተጨማሪ ትምህርት ካናዳ ከሚገኘው ሰኒ ብሩክ የጤና ሳይንስ ማዕከል፣ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቶሮንቶ  ተከታትለዋል፡፡
ዶ/ር አማኑኤል እንግሊዝ ሀገር በሚገኘው ሮያል ኮሌጅ ኦፍ ሰርጂንስ  አባል ሲሆኑ በዚሁ ሀገር በብሔራዊ ጤና አገልግሎት እና በግል ባገለገሉበት የጤና ዘርፍ የ10 ዓመታት ቆይታቸው የዳሌና የዳሌ መጋጠሚያ አጥንት ጉዳቶች (Pelvic and Acetabulum Injuries) ህክምና የልዕቀት ማዕከል አቋቁመዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ዶ/ር አማኑኤል የመጀመሪያውን ሚኒማል ኢንቬሲቭ ቀዶ ጥገና ህክምና (Minimal Invasive Surgery (MIS)) የተሰኘ የዳሌ መተካት ህክምና በዌስት ዮክሻየር አስተዋውቀዋል፡፡
ዶ/ር ቶሎሳ እ.ኤ.አ በ2018 ዓ.ም ኳታር ዶሀ በሚገኘው አል አህሊ ሆስፒታል የአጥንት ህክምና ክፍል  ኃላፊ ሆነው ካገለገሉ በኋላ፣ ዲኦሲ ህክምና ማዕከልን (DOC Medical Center) መስርተዋል፡፡ ለበርካታ ዓመታት አጠቃላይ የጡንቻና የአጽመ-አካል (musculoskeletal) ህክምና አገልግሎት የሚሰጥ ክሊኒክ ለመክፈት የነበራቸው ርዕይ ተሳክቶ የዶሀ የአጥንት ህክምና ክሊኒክ DOC (Doha Orthopedic Clinic) መክፈት ችለዋል፡፡
ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ዶ/ር አማኑኤል በፊንላንድ፣ ካናዳ፣ እንግሊዝና ኳታር በሚገኙ ዓለም አቀፍ የማስተማሪያ ሆስፒታሎች የአጥንትና የጀርባ አከርካሪ ቀዶ ጥገና ሀኪም (Orthopedic and Spine Surgeon) በመሆን ሰርተዋል፡፡ በሚሰጡት ጥራት ያለው የአጥንት ህክምናና ቀዶ ጥገና አገልግሎት ከፍተኛ እውቅናና አንቱታን ማግኘት ችለዋል፡፡ ለበሽተኞቻቸው የሚሰጡት የህክምና አገልግሎት ዝግጁነት በሽተኞች ከሚጠብቁት በላይ ነው፡፡ የህክምና ክህሎታቸውና ውጤት-ተኮር ምግባራቸው በመላው ዓለም የሚገኙ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ህክምና ፈላጊዎች ፈውስና ደህንነት እንዲያገኙ አግዟል፡፡
ዶ/ር አማኑኤል ቶሎሳ ስፔሻላይዝ ያደረጉባቸው የትምህርት መስኮች፡-
የአከርካሪ አጥንት ቀዶ ህክምና /Spine Surgery/
የመገጣጠሚያ አጥንት መተካት ቀዶ ህክምና፤ ዳሌና ጉልበት /Joint replacement surgery (hip and knee)
የጉልበት አርትሮስኮፒ ቀዶ ጥገና /Knee arthroscopy surgery/
የእግርና ቁርጭምጭሚት ቀዶ ጥገና ህክምና /Foot and ankle surgery/
የክርን፣ የእጅ አንጓና እጅ ቀዶ ጥገና ህክምና /Elbow, wrist and hand surgery/
አዕምሮን በሚያዛባ ገጠመኝ የሚከሰት የአዕምሮ ቀዶ ጥገና ህክምና፣ የስብራት ህክምና /Trauma surgery – treatment of fractures/  ናቸው።
ቀኑ በኳታር ለሚገኝ አንድ የውጭ ዜጋ የፈውስ ቀን ነው፡፡ በአስቴር ሆስፒታል ዶ/ር አማኑኤል የዳሌ አጥንት መተካት ቀዶ ጥገና ህክምና ካደረጉለት በኋላ ቀጥ ብሎ በትክክል የሚራመድ ሰው፡፡ የቀዶ ጥገና ህክምናው ያስፈለገው ለጥቂት ወራት የሰውየው የዳሌ መጋጠምያ እየተበላሸና እንቅስቃሴውን እየገታው በመምጣቱ ነው፡፡ በሽተኛው ኦስቲኦአርትራይቲስ (osteoarthritis) በተሰኘ የሰውነት መገጣጠሚያ ያለመታዘዝ እክል ይሰቃይ የነበረ ሲሆን፤  ይህም በአጥንት መጋጠሚያዎች መካከል የሚገኘውን ማያያዣ ጡንቻ ስራውን በአግባቡ እንዳይሰራ በማድረግ እንቅስቃሴን በመግታት ህመም የሚያስከትል በሽታ ነው፡፡ ይህ እንደ ስፖርኛ ጥሩ የሰውነት አቋም ያለው ወጣት በሽተኛ ከቤተሰቦች ጋር የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን በማካሄድ ይህንን ችግር መጋፈጥ የግድ ሆነበት፡፡
“እጅግ በጣም የሚረብሽ ነበር፤ ሁሉም ነገር ቀጥ አለ፤ ለመራመድ ወይም መኪና ለመንዳት ሳስብ ድንገት መንቀሳቀስ አቃተኝ፤ በዶ/ር አማኑኤል ቶሎሳ የዳሌ አጥንት ቀዶ ህክምና ለማድረግ እስክወስን ድረስ ሁኔታው እጅግ አስደንጋጭ ነበር፡፡” ይላል ታካሚው፡፡  
ዶ/ር አማኑኤል በአንድ ወቅት ለዚህ ታካሚ ያከናወኑትን የዳሌ አጥንት መተካት ቀዶ ህክምና (Hip replacement surgery) በተመለከተ እንዲህ ብለዋል፡-
“ህመምተኛው ወደ እኔ የመጣው ቀጥ ያለ፣ አስቸጋሪና ጠንካራ የአጥንት መገጣጠሚያ እንቅስቃሴ መስተጓጎል፣ ብሽሽት ላይ የሚገኝ የህመም ስሜት እንዲሁም በጉልበት አካባቢ የሚሰማ የህመም ስሜት ዓይነተኛ ምልክቶችን ይዞ ነው፡፡ የዳሌ ወይም የወገብ መጋጠሚያ ጤና ሁኔታ በአጠገቡ ወይም ቀጥሎ ያለውን መጋጠሚያ፤ በዋናነት የጉልበት መጋጠሚያ (knee joint) ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል። በመሆኑም የቀዶ ጥገና ህክምና መደረግ ነበረበት። በደንብ የተገነባ ተክለ-ሰውነት ያለው ወጣትና ስፖርተኛ በመሆኑ የቀዶ ጥገናው ፈታኝ ሁኔታ ያደረገው እንደ ሲኒ ወይም ዋንጫ ጎድጓዳ ቅርጽ ያላቸውን የአጥንት ማስገቢያዎች (cups) እና መጋጠሚያውን በቦታው መመለስ ነበር፡፡”
 “ታካሚው ቀዶ ጥገና ህክምናውን ማግኘት እንደሚገባው አምኗል፡፡ ቤተሰቦቹም የኛ ክሊኒክ ምርጥ መሆኑን ስለሚያውቁ ወደ እዚህ ይዘውት መጡ፡፡ ቀዶ ጥገናውም አስቴር ሆስፒታል በሚገኘው የህክምና ቡድን በአግባቡ ተከናውኖ በሁለት ቀናት ውስጥ ታካሚው በደንብ ተሽሎት ወደ ቤቱ ተመልሷል፡፡” ያሉት ደግሞ ዶ/ር ሳሚር ሙፓን የአስቴር ሆስፒታል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡
ቀጥለውም እንዲህ አሉ፤ “እኛ የሰውነት መገጣጠሚያ ህመምና የእንቅስቃሴ ማጣት ምን ያህል አድካሚና ከጨዋታ ውጪ እንደሚያደርግ እንረዳለን፡፡ በሆስፒታላችን የሚገኘው የእኛ የህክምና ቡድን በሽተኞች የአጥንትና መገጣጠሚያ ቀዶ ጥገና ህክምናውን አግኝተው ወደ ቀድሞው መደበኛ ህይወታቸው እንዲመለሱ የሚያስችሉ ብቁ ባለሙያዎች ስብስብ ነው፡፡ ይህን ስራ ከጀመርንበት እ.ኤ.አ ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ በከፍተኛ የቀዶ ጥገና ስርዓት ትግበራ አስገራሚና ድንቅ ስኬቶችን በማስመዝገብ ላይ እንገኛለን፡፡”
“ባለፉት ሁለት ዓመታት በሀገሪቱ (ኳታር) ያሉት የመገጣጠሚያ ቀዶ ጥገና ህክምና ባለሙያዎች ዓለማቀፍ ደረጃ ያላቸው ሲሆኑ የሰዎች የህይወትና ኑሮ ደረጃ የሚያሻሽል ጥሩ የጡንቻና የአጽመ-አካል ችግሮችን ቀደም ብሎ ለመፍታት ያስችላል፡፡ በዚህም ኳታር በቅርቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚሰጥ የአጥንት መገጣጠሚያ መተካት ቀዶ ጥገና ህክምና መስጫ ማዕከል ትሆናለች፡፡” ሲሉ ዶ/ር አማኑኤል ቶሎሳ ተናግረዋል፡፡
ስለ ዶ/ር አማኑኤል ቶሎሳ ትሪብዩን ኒውስ ኔትወርክ  የተሰኘ የዜና አውታር እንደዘገበው፤ እኚህ ስመ-ጥር የአጥንትና የአከርካሪ ቀዶ ህክምና ባለሙያ ከፍተኛ የቀዶ ጥገና ዘዴዎችን በመጠቀም፤ በሰለጠኑ የሰመመን መድሀኒት ሰጪዎች፣ ነርሶችና ሌሎች የህክምና ሰራተኞች በመታገዝ፤ ዶሀ በሚገኘው የአስቴር ሆስፒታል ለአንድ የ54 ዓመት ዕድሜ በሽተኛ ያደረጉት ስኬታማ አጠቃላይ የጉልበት አጥንት መተካት ቀዶ ጥገና (total knee replacement) ህክምና የሰውየውን የአካል እንቅስቃሴ የመለሰ ነበር፡፡
ዶክተር ስትሬች /DR. STRETCH/ የሚል የህክምና ዘዴ ያስተዋወቁት እኚህ ውድ ኢትጵያዊ የህክምና ሊቅ፤ እ.ኤ አ. ጁን 27 ቀን 2013 ዓ.ም በተደረገ የህክምና ጉባኤ “ዶክተር ስትሬች ወደ ከተማችን እየመጡ ነው፤ ማንኛውም የሚያሰቃይዎትን ውጋትና ህመም ደህና ሰንብት ይበሉ!“ የሚል መሪ ቃል እንዲወጣ ምክንያት ነበሩ፡፡
በአል አህሊ ሆስፒታል የአጥንት ህክምና ክፍል ሀላፊና የአጥንት ቀዶ ጥገና አማካሪ የሆኑት ዶ/ር አማኑኤል ቶሎሳ፤” መንቀሳቀስህን/ሽን ቀጥይ /Keep Moving/” የተባለ ቀላል የእንቅስቃሴ መመሪያ አዘጋጅተዋል፡፡ በግምት 80% የሚሆን ህዝብ ቢያንስ ቢያንስ በህይወት ዘመናቸው የሆነ ጊዜ የጀርባ ህመም ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡ በማንኛውም ማህበረሰብ ውስጥ ከ10%-15% የሚሆነው ደግሞ የጀርባ ህመም እንዳለባቸው ይገልጻሉ፡፡ የጀርባ ህመም ህክምና በዓለም በጣም ውድ ከሚባሉት የጤና አገልግሎት አንዱ ነው፡፡ምናልባትም ከከፍተኛ ዋጋው በላይ እጅግ የሚረብሽ፤ የአገልግሎት ጥራቱ ሳይሻሻል ከዓመት ዓመት ዋጋው እየጨመረ የመጣ ጉዳይ ነው፡፡
ዶ/ር አማኑኤል እንዲህ ይላሉ፤ “ ሰዎች ከሚሰሩት ስራ ዓይነት፣ ከህይወት ዘይቤያቸው ወይም ከሰውነታቸው ክብደት ጋር የተያያዘ ቢሆንም የጀርባ ህመምን ለመከላከል ቁልፉ መፍትሄ  የሰውነት አካል እንቅስቃሴን በሚገባ ሁኔታ መጠበቅ ነው፡፡ በእኔ አስተያየት መከላከል በብዙ እጅ ከህክምና የተሻለ ነው፡፡ መሰረታዊ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ የጀርባ ህመምን ለመከላከል ቁልፍ መፍትሄ ነው፡፡ በርካታ የከፋና መካከለኛ የጀርባ ህመም የነበረባቸውን ታማሚዎች  የህክምና እገዛ አድርጌላቸዋለሁ፤ ከዚህ የተረዳሁት ታማሚዎች ችግሩ እንደተከሰተ ጊዜ ሳይወስዱ ወዲያውኑ ወደ ህክምና መሄድ እንዳለባቸው ነው፡፡”
  አክለውም፤ እኛ እዚህ አል አህሊ ሆስፒታል የምንገኝ የህክምና ባለሙያዎች መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንደ የጀርባ አከርካሪና የሆድ አካባቢ ጡንቻዎች የመሳሰሉትን ወሳኝ ጡንቻዎችን ለማጠንከርና ለማረጋጋት እንደሚያግዝ እናምናለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር አማኑኤል በአሁኑ ጊዜ በቅርቡ የተቋቋመውን በዋናነት በአጥንትና ተያያዥ ችግሮች ላይ የሚያተኩረውን ዲ ኦ ሲ የህክምና ማዕከል /DOC Medical Center/ እየመሩ የሚገኙ ሲሆን የበርካታ ሰዎችን የመንቀሳቀስ ሁኔታ የገደቡ የተለያዩ የአጥንትና ተያያዥ ችግሮች በማስወገድ ፈውስ የሰጡ  በዓለማችን ትልቅ የህክምና ሰው ናቸው፡፡
 “በአንድ ወቅት በሁለቱም ሽንጥ/ዳሌ በኩል ከፍተኛ የኦስቲኦአርትራይትስ (osteoarthritis) በሽታ ስትሰቃይ የነበረች ኢትዮጵያዊ ህመምተኛ ነበረችኝ። ከ20 ዓመታት በላይ ስትሠቃይ ቆይታ ነው ወደ ዶሀ ኳታር ለቀዶ ጥገና የመጣችው። የዚህች ሴት ታሪክ እጅግ አስገራሚ ነው። መራመድ ባለመቻሏ በምርኩዝ ዱላ ነበር የምትንቀሳቀሰው፤ ለአምስት አመታት በስህተት የሳንባ ነቀርሳ (tuberculosis) በሽታ አለብሽ ተብላ አግባብ ያልሆነ ህክምና ወስዳ ነበር። ነገርግን ታማሚዋ ትሰቃይ የነበረው አርትራይተስ በተባለ በሽታ ነበር። በእኔ ህክምና እገዛ ጤናዋ ሙሉበሙሉ ተመልሶ ወደ ሀገሯ ተመልሳ እየሠራች ቤተሠቦቿን እየረዳች ትገኛለች ።
“እንደዚህች ያለች ህይወቷ ወደ ቀድሞ ጤና ተመልሶ እጅግ በጣም ሀሴት ያደረገች ሴት በፍፁም አይቼ አላውቅም። በአሁኑ ጊዜ ሴትየዋ ጋንዲ ሆስፒታል አካባቢ በሚገኘው አድቬንቲስት ቤተክርስቲያን እየሠራች ትገኛለች” ሲሉ ዶ/ር አማኑኤል ገልፀዋል።
የሦስት ልጆች እናት የሆኑት እናት መብራቴ አጋ ስልክ ደውዬ ምስክርነታቸው ጠየኳቸው::  እንዲህ አሉ፤ “እግዚኣብሔር ይመስገን አሁን በሙሉ ጤንነቴ ላይ እገኛለሁ። ዶ/ር አማኑኤል ቶሎሳ እጅግ በጣም ጥሩ ሕክምና ሠርቶልኛል። በጣም፣ በጣም ላመሰግነው እወዳለሁ። ከእርሱ በፊት ብዙ የህክምና  ተቋማትና የተለያዩ ሐኪሞች  ጋር ቀርቤ ነበር። አንዳቸውም ከሕመሜ ሊፈውሱኝ አልቻሉም :: ዶ/ር አማኑኤል ብቻ ነው ፣ ችግሬን ሕመሜን ያወቀልኝ ልጄ!” ብለዋል።
በመላው ዓለም የኢትዮጵያ ልጆች በከፍታ ማማ ላይ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ ብዙ የቤት ሥራዎቻችንን ሊያግዙን የሚችሉ ልጆቿን በክብር ልትጣራ ይገባል። በአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ፣ የኢትዮጵያ ሜዲካል ቱሪዝም  እንዲመሰረት ልጆቿ ይናፍቃሉ።
ኢትዮጵያ ሆይ ! ...
ልጆችሽ አገር እና ሕዝብን ለማገልገል ብርቱ ሆነዋል።
ደስ ይበልሽ!


Read 1337 times