Friday, 06 January 2023 00:00

የእኛ ሰው በኳታር “ሰብለ እንጀራ በኳታር”

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(1 Vote)

 ከቤት ሰራተኝነት ለመውጣት
እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊት ኳታር የገባሁት ሰው ቤት ለመስራት ነው፡፡ 4 ዓመት ከመንፈቅ ሰው ቤት ሰርቻለሁ፡፡ ግን ሁልጊዜም ህልም ነበረኝ፡፡  በቤት ሰራተኛነት ተወስኜ መኖር የለብኝም ብዬ አስብ ነበር፡፡ የተሻለ  መስራት እንደምችል ውስጤም ይነግረኝ ነበር። ራሴን እንዴት ነው የማሳድገው ብዬ ሁሌም እጨነቃለሁ፡፡
ልጅ እያለሁም እንደዚያው ነው፡፡ ወደፊት ምን መሆን ትፈልጊያለሽ ብለው ሲጠይቁኝ፤  “ደሞዝተኛ መሆን አልፈልግም” ነበር የምለው። ሁሌም የማስበው ነጋዴ መሆን አለብኝ ብዬ ነበር፡፡
በኳታር  ሰው ቤት ተቀጥሬ  እንዴት ነው  የራሴን ሥራ  የምሰራው እያልኩ አስብ ነበር፡፡ የሰው ቤት ስራ ብዙ መስዋዕትነት ያስከፍላል፤ ይሰለቻል፤ ይደክማል፡፡ አሰሪዎቼ በወር እስከ 500 ሪያል ይከፍሉኝ ነበር፡፡ በእነሱ ስፖንሰርነት የተሻለ ስራ ማግኘት እንደምፈልግ ስጠይቃቸው፣ ከሆነልሽ ብለው ፈቀዱልኝ፡፡ ስራ አፈላልጌ ሆላንዶች ጋር ተቀጠርኩና በወር 1200 ሪያል ደሞዝ አገኝ ጀመር፡፡ በነበረኝ ትርፍ ጊዜ ተጨማሪ ሥራ  የምሰራበትን ሁኔታ  ከመሞከር አልቦዘንኩም፡፡ ‹‹ገልፍ ታይም›› በተባለ ጋዜጣ ላይ የስራ ፍለጋ ማስታወቂያ በክፍያ ማውጣት ጀመርኩ፡፡  “ኢትዮጵያዊ ሴት ነኝ ፤ በፅዳትና ሌሎች የቤት ውስጥ ስራዎች ልምድ አለኝ...” በማለት ሙሉ ስሜንና የምገኝበትን ስልክ ቁጥር በጋዜጣው አሳትሜ ማስታወቂያ አወጣ ነበር፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ በትርፍ ሰዓት የምሰራባቸውን ቀጣሪዎች ማፍራት ቻልኩ፡፡  ከዋናው ስራዬና ከሌሎቹ ተጨማሪ ስራዎች የማገኘው ገቢ ቤት ተከራይቼ እንድኖር አስቻለኝ፡፡
ወደ እንጀራው ጋገራ ስትገባ
በመጀመርያ ፈትያ ከምትባል ግማሽ ሀበሻና ግማሽ የመናዊ  ሴት ጋር ተዋወቅን፡፡ እንጀራ እየጋገረች ትሸጥ ነበር፡፡ የሩዝ እንጀራዋን እንዴት እንደምትሰራም አስተማረችኝ፡፡ በየሳምንቱ አርብ ቤቴ ውስጥ መጋገር ስጀምር ወዳጆቼ  ቤቴ መምጣት ጀመሩ፡፡ እንጀራ እየጋገርን ወጥ እየሰራን እናስተናግዳቸው ነበር፡፡ አንዳንዶቹ  እንጀራውን በቋሚነት ብትጋግሪ እንወስድልሻለን ማለት ጀመሩ፡፡ በመጥበሻ የምንጋግረውን የሩዝ እንጀራ አርብ አርብ የሚወስዱልን ደንበኞች አገኘን፡፡ ከዚያ በኋላም ከየመን ተለቅ የሚል መጥበሻ ፈትያ አመጣችልን፡፡ መክደኛ እንደ አክንባሎ ያለው ነበር፡፡ እንደዚህ እየተባለ  እንጀራ ጋግሮ የመሸጡ ቢዝነስ ተጀመረ። “እንጀራውን በብዛት ከጋገርሽ ገበያውን አመጣልሻለሁ” ብሎ ያበረታታኝ አሁን በአገር ቤት የሚገኘው ማሹ የሚባል ጓደኛዬ ነው። ፀሃይ የምትባለው እህቴም፤ አዎ እንጀምረው አለችኝ። እንጀራችንም ተፈላጊ እየሆነ መጣ፡፡ ስንጀምር በሳምንት አንዴ የነበረው ተቀይሮ በሳምንት ሁለቴና ሶስቴ መጋገር ጀመርን፡፡ ከዚያም በየቀኑ መጋገራችንን ቀጠልን ማለት ነው፡፡
“ሰብለ እንጀራ” እየታወቀ ሲመጣ
ያኔ እንጀራውን የምንጋግረውና የምንሸጠው በተከራየሁበት ቤት ውስጥ ነበር፡፡ ለሰባት ስምንት ዓመታት በዚያ መንገድ ሰራሁ፡፡ ከአገር ቤት ምጣድ አስመጥተን ነበር የምንጋግረው።  ከዋናው ስራዬ ጎን ለጎን ባለኝ ትርፍ ጊዜ በቀን 100 እንጀራ እጋግር ነበር፡፡ በኋላ ላይ እየደከመኝ ሲመጣ ስራውን የሚያግዘኝ ሌላ ሰው ቀጠርኩ፡፡ ከአገር ቤት ካመጣኋት ልጅ ጋር  ቡኮውን አብረን እያቦካን እንጀራውንም እየጋገርን ተጋግዘን መስራት ቀጠልን።  እንጀራውን እየጋገርን ስንሸጥ ከዚያው ጋር የሚሄደውን ባልትና የመስራት ሃሳብ መጣ። በርበሬውን፤ ሽሮውን እንዲሁም ሌላውን ቅመማ ቅመም በማስመጣት ለገበያ ማቅረብ ጀመርን፡፡ በአጠቃላይ በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ ለ10 ዓመታት ቆየን፡፡
እንጀራችን በጣም ተፈላጊ እየሆነ መጣ። የምንሸጠው ግን ደንበኞቻችን የተከራየንበት ቤት ድረስ እየመጡ ነበር፡፡ አከራያችን ቤቱን እፈልገዋለሁ ብሎ ሊያስወጣን ሲወስን፣ ተለቅ ያለ ቤት መከራየት እንዳለብኝ አሰብኩ። አሁን የምንኖርበትን ግዙፍ ቪላ ቤት ተከራየሁ፡፡ አዳዲስ ሰራተኞችም ጨመርኩ። እንጀራ የሚጋግሩ ሴቶች ተቀጠሩ፡፡ አንድ ባንግላዲሻዊ እቃ በማውረድ የሚያግዘን  ነበር።  ባንግላዲሻዊው አስተምሩኝና እኔም እንጀራ ልጋግር አለ፡፡ በቀን አምስት እንጀራ እየጋገረ እንዲለምድ ፈቀድኩለት፡፡ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ምርጥ እንጀራ መጋገር ቻለ፡፡ “ወንድሜን አስመጭውና አብረን እንስራ” አለና እሱም መጥቶ ተቀጠረ፡፡ ዛሬ ባንግላዲሻዊያኑ ወንዶች ናቸው የሚጋግሩት፡፡
መኖርያችን በነበረውና እንጀራውን በምንጋግርበት   ቤት ደንበኞችን ማግኘት አልቻልንም፡፡ በዙሪያችን የሚኖሩት የአገሬው ሰዎች ናቸው፡፡ ስለዚህም  ለኢትዮጵያውያኑ   እንጀራውን የምንሸጥበት ሱቅ መከራየት እንዳለብኝ ወሰንኩ፡፡ አሁን ከምንገኝበት መደብር አነስ ያለ ቤት ነበር የተከራየሁት፡፡ በወቅቱ እንጀራ ለመሸጥ እንዴት ቤት ትከራያለሽ ያሉኝ ነበሩ፡፡ እንጀራ ብቻ ሳይሆን አብሬ የምሰራቸውን የባልትና ውጤቶች በማሰብ ነበር ሱቁን የጀመርኩት፡፡ ከእንጀራው በኋላ የባልትና ውጤቶችን ከዚያም  ሌሎች  እቃዎችን እያስገባሁ የሱቁን አቅርቦት አስፋፋሁት፡፡ ከዚያም በኋላ  የተከራየሁት የመጀመርያ ሱቅ ለገበያው አልመች አለ፡፡ ዛሬ የምንገኝበትና ሚዘር በተባለው የዶሐ ከተማ አንዱ ክፍል ግዙፍ ሱቅ ተከራይቼ ገባሁ፡፡ “ሰብለ እንጀራ ትሬዲንግ” በሚል እየሰራንበት እንገኛለን።
እንጀራውን ተወዳጅ ለማድረግ
ስራውን ስንጀምረው እንጀራውን በትክክል  ማውጣት ከባድ ነበር፡፡ ብዙ እንጀራ ይጣላል። አየሩ ሞቃት  ስለሆነ ሊጡ  ይፈላል፤ ይበላሻል። የሊጡ ሽታም ጥሩ አልነበረም፡፡ እናም ችግሩ ሲበዛ መፍትሄ መፈለግ ግድ ሆነ። በመጀመርያ ዱቄቱን ፍሪጅ ውስጥ ከትቼ ማቀዝቀዝ ጀመርኩ። ከፍሪጅ ወጥቶ ሲቦካ ቶሎ ሊጥ አይሆንም፤ ቀስ እያለ ነው የሚቦካው፡፡ እንደገና ሊጡ ውስጥ ደግሞ በትልልቅ የላስቲክ ጠርሙሶች በረዶ አደርግና እጨምረዋለሁ። ሊጡ በረዶ ይሰራ ነበር፡፡ የእንጀራውን ጠረንም እያሻሻለው  መጣ። በሌላ በኩል አይን አላወጣም ብሎም እንቸገር ነበር፡፡ ቤኪንግ ፓውደር አድርገን ሞከርነው፡፡ በጣም የሚያምር አይን ይወጣው ጀመር፡፡
በመጀመርያ የሩዝ እንጀራ ነበር የምንጋግረው፡፡ በኋላ ላይ ቆንጆ ጤፍ ከኢትዮጵያ ማስመጣት ጀመርን፡፡ ከጤፉ ጋር  ሩዙን በመቀላቀል እንጀራው መጋገር ቀጠለ፡፡ የሩዝ እንጀራ የተለመደና ሁሉም የሚጋግረው ስለነበር፣ ከአገር ቤት ጤፍ በማስመጣት ልዩ እንጀራ ጋግሮ መሸጡ ለንግዳችን ወሳኝ እርምጃ ነበር፡፡ ጥሩ ጤፍ ለማግኘት ኢትዮጵያ ተመላልሼ ጠያየቅሁ፡፡ ከአምራቾች ጋር በአጋርነት መስራት አለብሽ ተብዬ ተመከርኩ። ተፃፅፍኩ እና በቀጥታ ጤፉን አገር ቤት አምራቾች ማስመጣት ጀመርኩ፡፡ ያን ጤፍ ምንድነው የምናደርገው… ዱቄቱን ለሚገዛ አንዱ እሽግ 5 ኪሎ ነው፤ እንሸጣለን፡፡ የጤፍ እንጀራውን በደንብ ስንቀጥለው ኢትዮጵያ ውስጥ ሊጥ ከምታቦካና ምርጥ እንጀራ ከምትጋግር ባለሙያ ጋር ተገናኘሁ፡፡ ወደ ኳታር አስመጣኋት፡፡ እኛ ዛሬ አብሲት ጥለን በማግስቱ ነበር የምንጋግረው፡፡ አዲሷ ሙያተኛ ዛሬውኑ አብሲቱን ጥለን ዛሬውኑ እንጋግረው አለች፡፡ ስንሞክረው የተሳካ ሆነ፡፡
ወደ ጥሩ የጤፍ እንጀራ እስክንመጣ ለ6 ወራት ያህል ተቸግረናል፡፡ በፊት እንጀራ በሳምንት ሁለቴ ከኢትዮጵያ እጭን ነበር፡፡ ሁሌም ግን ጉምሩክ ላይ ችግር ይገጥመናል። ሲጫን ይዘገያል፤  በቀዝቃዛ ክፍል ሳይደረግ ይመጣል፤ ይበላሻል፡፡ ከኢትዮጵያ በምናስመጣው እንጀራ ሸጠን ከምንጠቀመው ኪሳራው እየበዛ መጣ፡፡ ለማስጫኛ የሚከፈለውም በጣም ውድ ነው፡፡ ለሰው ደስ እንዲለው ብቻ አመት በዓል ሲሆን እንጀራውን ቆጮውን አይቡን አስመጣለሁ እንጂ እንጀራ ሙሉ ለሙሉ እዚህ ነው የምንጋግረው፡፡ እንጀራውም ባልትናውም አገር ቤት ካለው የራሴ ማምረቻ የሚቀርብ ነው፡፡ ቄራ አካባቢ “ሰብለ እንጀራ” በሚል የምንሰራበት ድርጅት አለ፡፡ የባልትና ውጤቶችን በርበሬውን ሽሮውን ቅቤውን በዚሁ ቤት አዲስ አበባ ላይ አዘጋጅተን ነው ወደ ኳታር የምናስገባው፡፡
ሰብለ እንጀራ ታሽጎ ሲቀርብ
መጀመርያ ላይ እንጀራውን  ዝም ብለን ነበር የምንሸጠው፡፡ ከዚያም ለእንጀራው የማሸጊያ ፓኬጅ መዘጋጀት እንዳለበት አሰብኩ፡፡ ቻይና የሚመላለሰው ወንድሜ ዲያቆን ጎርፉ ቻይና ውስጥ ስላለው ፓኬጂንግ ይነግረኝ ነበር፡፡ በአሊባባ አማካኝነት   የምግብ ማሸጊያ የሚሰራ ሰው ቻይና ውስጥ አገኘሁ፡፡ ለእንጀራ የሚሆን ማሸጊያ እንዲሰራልን ጠየቅነው፡፡ ቻይናዊውም ወዲያውኑ ዲዛይኑን ሰርቶ ላከልን፡፡ እንዲህ ማሰራት ከተቻለ ብለን እንጀራውንና የባልትና ውጤቶቹንም ስማችን ያለበት ማሸጊያ  ውስጥ አድርገን ለደንበኞቻችን ማቅረብ ጀመርን፡፡
የምንሸጣቸው እንጀራዎች ኤክስፓየርድ ዴት (የአገልግሎት ማብቂያ ቀን) አላቸው። አገሩ ሙቀት ስለሆነ እንጀራው ከሶስት ቀን በላይ አይቆይም፡፡ ሚዘር በተባለው ስፍራ ወደሚገኘው የእኛ መደብር መድረስ ለማይችሉ ደንበኞች በተለያዩ የከተማው ክፍሎች በሚገኙ ከ20 በላይ ሱቆች በየቀኑ እየሄድን እንጀራችንን እናቀርባለን፡፡ እንጀራውን ለማቅረብ በየሱቆቹ ስንሄድ ያላቸውን ክምችት እናያለን፤ የተበላሸ እንጀራ ካላቸው ያለምንም ክፍያ እንቀይራላቸዋለን፡፡ በየሱቁ ለእንጀራው ማስቀመጫ የሚሆን ነገር በማከፋፈል  ደንበኞቻችን በአቅርቦታችን እንዲደሰቱ እናደርጋለን፡፡
ስንጀምረው በቀን ከ30 እስከ 50 እንጀራ እንጋግር ነበር፡፡ አሁን በቀን 700 እንጀራ እየጋገርን ነው፡፡ አርብና ቅዳሜ እስከ  1000 እንጀራ የምንጋግር ሲሆን በአመት በዓል የምንጋግረውና ለገበያ የምናቀርበው እስከ 2000 እንጀራ ይሆናል፡፡ በመጀመርያ በሩዝ ስንጋግረው የአንድ እንጀራ  ዋጋ  3 ሪያል ነበር፡፡ አሁን ጤፍ ሲሆን 4 ሪያል ነው፡፡ እንጀራውን ከእኛ ወስደው ለሚያከፋፍሉት በ3 ሪያል ነው የምንሸጥላቸው፡፡ በቀን እስከ 100  እንጀራ የሚወስዱ የሬስቶራንት ባለቤቶችም ደንበኞቻችን ናቸው፡፡
(ይቀጥላል)


Read 1480 times