Saturday, 07 January 2023 00:00

የአብርሃም በረከት ለኛ! የልጅ ልጆቹ ስለሆንን? ወይስ በመርሆቹ ስለተራመድን?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

 ለመጣላትም ለመታረቅም፣ ለመነሳትም ለመውደቅም፣… ሁሌም መንገድ አለ። መንገድ ባይታየን እንኳ “ሰበብ” ይኖራል።
የአረብ አገራት ከእስራአኤል ጋር ለመታረቅ፣ በወጉ ሰላምን ለማወጅ፣ በቀጥተኛ ንግድ ለመገበያየት ተስማምተው ተፈራርመው የለ!
ከመነሻውስ ለምን ፀብ ውስጥ ገቡ? “ወንድማማች ህዝቦች” እየተባለ ይነገርላቸዋል። ግን ለጦርነት ሰበብ አይጠፋም። ለነገሩ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች፣ የአንድ አገር ሰዎችስ መች ለጦርነት ሰበብ አጡ? ግን ሰላም ለማውረድና ለመታረቅም ሰበብ ይፈጥራሉ።
ድከሙ ሲላቸው፣ የ4ሺ የ6ሺ ዓመታት ታሪክ የኋሊት ተጉዘው፣ የእርቅ ሰበብ ጎትተው ያመጣሉ። ዘረኝነት ቢያስጨንቃቸው፣ ዘር ይቆጥራሉ። “የአዳምና የሔዋን ልጆች ነን። ሁላችንም የኖህ ዘር ነን” ይላሉ።
እስራኤልና የአረብ አገራት የፈረሙት ስምምነት ደግሞ፣ ከነስሙ… “የአብርሃም ውል” ይባላል። ሁላችንም የአብርሃም ወራሾች ነን ማለታቸው ነው።
መቼስ ምን ይደረግ? ለመታረቅ መሆኑ ግን በጎ ነው። ከልብ ከተመኙት፣ ከምር ከፈለጉት፣ የሚያቀራርብና የሚያስማማ ነገር፣ ጠፍቶ እንደማይጠፋ ይመሰክሩልናል።
ምንም በዘመንና በቦታ ቢርቅ፣ የተኳረፉ ሰዎችን የሚያወዳጅ፣ የተጣሉ ፀበኞችን አረጋግቶ የሚያስታርቅ አንዳች ዘላለማዊ እውነትና ትክክለኛ መርህ፣… በሁሉም ቦታ ሁሌም ይኖራል። በፈለግነው ጊዜ እናገኘዋለን።
ሌላው ቢቀር፣ የሰላምና የወዳጅነት “ሰበብ” አይጠፋም። እንደዚህ ለማለት ይመስላል - የአብርሃምን ሥም ማንሳታቸው።
በእርግጥ፣ በትክክለኛ አስተሳሰብ እስከሆነ ድረስ፣ የትናንትን ውርስ ማስታወስና መዘከር፣ ተገቢ ነው። ለዛሬ ተግባራችንና ለወደፊት ምኞታችን፣ አስማማኝ መነሻ ወይም መንደርደሪያ ሰበብ መፈለጋችን፣ የጥንት ትረካዎችንና ምሳሌዎችን መጥቀሳችን፣ አዲስ ነገር አይደለም። የሰው ተፈጥሯዊ አቅም ነው።
የኢየሱስ የትውልድ ትረካ ሀ ብሎ ሲጀምር፣ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓረፍተነገሮች ውስጥ የአብርሃምን ስም ሁለቴ ይጠቅሳል።
የጥንቱን መነሻ ማሰብና መዘከር ተገቢ የሚሆንበት መንገድ አለና። ግዴታም ነው። ሁሉም ነገራችን የትናንት ውጤትና መዘዝ ነው - ከትናንት ብርታትና ድክመት የሚመጣ።
በዚያ ላይ፣ እውነትና እውቀት፣ የስነ-ምግባር መርህና መልካም ሰብዕና፣… ዘላለማዊ ናቸው። ጊዜ አያልፍባቸውም። የትናንት ትክክለኛ መርሆች ለዛሬ ይሰራሉ።
ለነገሩ፣ የጥንት ትረካ፣ ከመርህ የተራራቁ የዛሬ ዘመን ሰዎችን ለማቀራረብ፣… በከንቱ የተጣሉ ፀበኞችን ለማስታረቅ ቢጠቅምና “በጎ ሰበብ” ቢሆን፣… መጥፎ ነው? አይደለም። ቢጨንቃቸው ነው፤ “ሁላችንም የኖህ ልጆች፣ የአብርሃም ወራሾች ነን” የሚሉት።
ግን ደግሞ፣ እያንዳንዱን ሰው በስነ-ምግባር መርህ አማካኝነት ከመዳኘት ይልቅ፣ ተወላጅነትን እንደ ማስታረቂያ ሰበብ ማጯጯህ፣ ለጥፋት ያመቻቸናል። የግል ማንነትንና የግል ሃላፊነትን እየጨፈለቁ፣ ሰዎችን በብሄር ብሔረሰብ ተወላጅነት ለማቧደን፣ የዘረኝነት ጎራዎችን ለመፍጠር በማሰብ፣… የጥንት ትረካዎችን እንደ ሰበብ እየመዘዙ የሚያመጡ ከንቱዎችና ክፉዎች ጥቂት አይደሉም።
የኢየሱስ የልደት ትረካ እነዚህን ሁለት ነጥቦች አጉልቶ ያሳየናል። የኢየሱስ ትረካ፣ አብርሃምን ይጠቅሳል። ግን ደግሞ… እያንዳንዱ ሰው በመልካም ፍሬው እና በገለባው እየተለየ፣ በግል ተግባሩ የፍትሕ ዳንነት እንደሚያገኝ ይልጽልናል።
በአንድ በኩል የአብርሃምን ስም መጥቀስከ መልካም በረከትን መዘከር ነው።
ነገር ግን፣ “የአብርሃም ልጆች ነን” በማለት የሚገኝ ሽልማትና ክብር እንደሌለ ያስተምረናል። እግዚሄር ከፈለገ ለአብርሃም ከድንጋዮች መሃል ልጆችን ይፈጥርለታል ይለናል። መልካምነት የግል ሃላፊነት እንደሆነ ይነግረናል - የኢየሱስ ትረካ።
ከመነሻውም፣ የአብርሃም ትረካ፣ ጥንትንና ዛሬን የሚያስተሳስር፣ “ለትውልድ የሚተርፍ በረከትን” እና “የግል ሃላፊነትን የሚያፀና የፍትህ ዳኝነትን” ያጣምራል።
አብርሃም ማለት፣. . .
ከ4000 ዓመት በፊት፣ ዛሬ እስራኤልና ፍልስጥኤም ወደምንላቸው አካባቢዎች በስደት የመጣ መሥራች አባት እንደሆነ ይነግሩናል፤ ሃይማኖታዊ የአብርሃም ትረካዎች።
አመጣጡ፣ “ኡር” ከተሰኘ ከተማ ነው። ተራ የከተማ ስም አይደለም። በጊዜው የዓለም ገናና መዲና ነበር። በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው አስደናቂ የሥልጣኔ ታሪክ የተመዘገበበት አካባቢ ነው፤ ቦታው።
የመጀመሪያው ትልቅ የሃይማኖት አድባር (ኢሩዱ)፣
የመጀመሪያው ትልቅ ከተማ (ኡሩቅ)፣…
በፅሁፍ የሰፈሩ የመጀመሪያዎቹ የሕግ አንቀጾች በይፋ የታወጁበት የሰፊ ግዛት መዲና (ኡር)…
እነዚህ የአለማችን ቀዳሚ ከተሞች፣ ቅርብ ለቅርብ ናቸው። በሃያ በአርባ ኪሎሜትር ቢራራቁ ነው። በዛሬዋ ኢራቅ በስተደቡብ፣ በቁፋሮ የተገኙት ጥንታዊ ከተሞች የመጀመሪያዎቹ የሰው ልጅ የሥልጣኔ ተጓዦች ናቸው።
የእውቀትና የፅሁፍ፣ የመስኖ እርሻና የሕንፃ ግንባታ፣ አገር አቋራጭ ጥርጊያ መንገድና የንግድ ልውውጥ፣ የስነ-ምግባር መርሆችና የመንፈሳዊ ሰብዕና አክብሮት፣ የግል ማንነትና የግል ንብረት፣ የግል ሃላፊነትና የፍትህ ዳኝነት፣ ሕግና ስርዓት…
ዋና ዋናዎቹ የሥልጣኔ ገጽታዎች፣ በተመሳሳይ ቦታና ዘመን መብቀላቸው፣ ቡቃያቸውም እየበረከተ መልካም ፍሬ ማሳየት መጀመራቸው ይገርማል? አዎ፣ የሰው ስራ ይደንቃል። ግን ደግሞ ለምን ይገርማል?
መንገዳቸውን በትጋትና በብልሃት የሚያቃኑ ፈርቀዳጅ የጥበብ ሰዎች፣ እንደ አብሪ ኮከብ ናቸው።
እልፍ አእላፍ ሰዎችን ያነቃሉ። የእውነት ችቦ እየኮሱ የአእምሮ ብርሃን ይሆናሉ።
ፈር እየቀደዱና የተቃና መንገድ እየጠረጉ፣ የእልፍ አእላፍ ሰዎችን እርምጃ ያሳልጣሉ። የእግር ግስጋሴ ይሆናሉ።
በመልካም ሰብዕናና በሙያ ብቃት፣ ለብዙ ሰዎች በአርአያነት ውስጣዊ መንፈስን ያድሳሉ፤ ያበረታሉ።
ጥበበኞች ያሳውቁናል። ግን ደግሞ ለላቀ እውቀት ያነሳሱናል። ከነሱ ተምረን ከነሱም በላይ እንድናውቅ የአእምሮ ብርሃን ስለሚፈነጥቁልን ነው አብሪ ኮኮብ የምንላቸው!
ኑሮን የሚያሻሽል አዲስ ዘዴ ይፈጥሩልናል። ግን ደግሞ ወደ ላቀ ከፍታ እንድንቀጥል ይገፋፋናል። ከነሱ አይተንና ልምድ ቀምሰን፣ ከነሱም አልፈን እንድንገሰግስ የተቃና መንገድ ያሳዩናል። “ባንተ ምክንያት ዓለም ይባረካል” ይባልላቸዋል - እንደ አብርሃም።
መልካም ስነ-ምግባርንና የተቀደሰ የሕይወት ትርጉምን ከነጣዕሙ በእውን እንድንቀምሰው፣… የመንፈስ ምግብ ይሆኑልናል። በሃሳብና በትንታኔ፣ በምክርና በማብራሪያ፣ በመርህና በእለት ተግባር ብቻ ሳይሆን፣… በእነዚህ ሁሉ የታነፀ መልካም ማንነትን፣ ያማረ ሰብዕናን ተጎናጽፈው… በእውን ያሳዩናል።
መልካምነትን ከመላበስ አልፈው እንደ ሁለተኛ ተፈጥሮ ከሁለመናቸው ጋር እያዋሃዱ ሕይወታቸው ያደርጉታል፤ ይኖሩበታል። በዚህም መንፈሳዊ ክብርን ያሳዩናል። በአርአያነት የውስጣዊ ብርታት ምንጭ፣ የመንፈሳዊ ኃይል ጮራ ይሆኑልናል።
አንዳንዴ ግን፣ ጥበበኞች የለኮሱት ችቦ ደብዝዞና ተዳፍኖ፣ የጠረጉት የተቃና መንገድና የገነቡት ሕንፃ ተሸርሽሮና ተንዶ፣ ታሪካቸው ተረስቶና አርአያነታቸው በአሸዋ ተቀብሮ፣ ከሰዎች አእምሮ ተሰርዞ፣ ከምድረ ገፅ ተጠራርጎ ሊጠፋ ይችላል።
አንዳንዴ ደግሞ፣ ደብዛዛውን የትናንት ችቦ ተቀብሎ እንደገና የሚያደምቅ፣ የተዳፈነውን ገላልጦ እንደገና ነፍስ የሚዘራ፣… ቢያንስ ቢያንስ ደግሞ የስልጣኔ ቡቃያዎች ለጊዜው ቢጠወልጉም ታሪካቸውና አርአያነታቸው እንዳይጠፋ የሚቆረቆር፣ ምንጭነታቸውን የሚዘክርና የሚመዘግብ ሰው ይኖራል።
የባቢሎንና የነነዌ ታሪክ ይህን ይመሰክራል። የኡር ተከታዮች ናቸውና። የሃይማኖት ትረካዎችም ይህን ያረጋግጣሉ። የአብርሃም መነሻ ከኡር ነውና።
የመጀመሪያዎቹን የሥልጣኔ ቡቃያዎች (ቀዳሚዎቹን ከተሞች) በአርአያነት የሚያከብሩና የሚዘክሩ ነበሩ - የባቢሎን እና የነነዌ ገናና የሥልጣኔ ፍሬዎች። ባቢሎንና ነነዌ በዛሬዋ የኢራቅ መዲና በባግዳድ አጠገብና በአገሪቱ በስተሰሜን በኩል የነበሩ ገናና ከተሞች ናቸው። የአብርሃም ትረካም እነዚህ ቀዳሚ የሥልጣኔ ምንጮችን የሚዘክር ነው።
የአብርሃም ትረካ ከበኩር የሥልጣን አካባቢ ተነስቶ፣ ወደዛሬዎቹ የእስራኤልና የፍልስጥኤም አካባቢ ይጓዛል። ግን እዚሁ አያበቃም። ወደሌላው የሥልጣኔ ማዕከል ለጊዜያዊ ስደት ይወርዳል - ወደ ግብፅ።
ትረካው በስተሰሜን ከነባቢሎን ባሻገር የፋርስ ከተሞችን ያካትታል። በስተደቡብ ከግብፅ ባሻገር የሱዳን የኢትዮጵያ ጥንታዊ ትረካዎችንም ያጣቅሳል፤ ሃይማኖታዊው የአብርሃምና የልጆቹ ትረካ።
የአይሁድ፣ የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖታዊ ትርካዎች፣… ይህን የአብርሃም ትረካ ይጋራሉ።
ሙሴ ለመጀመሪያ ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር የተገናኘበት የኦሪት ትረካ ይህን ይመሰክራል። “የአብርሃም አምላክ…” በማለት ነው እግዚሄር ከሙሴ ጋር የሚተዋወቀው።
በእስልምና ውስጥም፣ አብርሃም እንደ ቀዳሚ የሃይማኖት አባት ይቆጠራል።
የኢየሱስን ትውልድ የሚተርክልን የመጀመሪያው የክርስትና መፅሐፍም፣ አብርሃምን ለመጥቀስ ጊዜ አይፈጅበትም።
“የኢየሱስ ክርስቶስ የትውልድ መፅሐፍ፣… የዳዊት ልጅ የአብርሃም ልጅ” በማለት ይጀምራል፤ የማቴዎስ ወንጌል ትረካ። እንደ ርዕስ ይመስላል ነገሩ።
ቀጥሎ ያለው ዓረፍተ ነገር፤ ይህን ርዕስ የሚዘረዝር ነው፡፡
አብርሃም ይሳቅን ወለደ፤ ይሳቅም ያዕቆብን ወለደ፡፡ ያዕቆብም ይሁዳንና ወንድሞቹን ወለደ እያለ ትውልድ ይቆጥራል፡፡…(ወደ ግብፅ የተሰደዱ የያዕቆብ ቤተሰቦች፣ እነ ዮሴፍና ወንድሞቹን ማለት ነው)፡፡
ያው፤ እንደ አይሁድ እና እንደ እስልምና ትረካዎች፤ የክርስትና ሃይማኖታዊ ትረካም፤… አብርሃምን በመጥቀስ ነው የሚነሳው፡፡ አብርሃም የባቢሎንንና የግብፅን ጥንታዊ ትረካዎች ከኢየሩሳሌም ጋር የሚያዛምድ የትረካ መቋጠሪያ አይደል!
የኢየሱስ የትውልድ ትረካም፣ የአብርሃምን ስም ከመጥቀስ ባሻገር፣ እስራኤላዊያን ወደ ባቢሎን የተሰደዱበት የምርኮ ትረካን እንደ አንድ አንጓ አጉልቶ ያሳየናል። የእስራኤል ልጆች ወደ ግብፅ በረሃብ የተሰደዱበትን ትረካ የሚዘክር ክስተትም በኢየሱስ ልደት ውስጥ ተካትቷል። ገና በጨቅላነቱ ወደ ግብጽ በስደት ሄዷል - ከማርያምና ከዮሴፍ ጋር።
ምን ለማለት ፈልጌ ነው?
ከጥንቱ ጅምር ጋር በማስተሳሰር ነው፤ የዛሬን ክስተትና የወደፊቱን አቅጣጫ የሚተርኩልን። እናም፣ በሃይማኖታዊ የትረካዎች ሰንሰለት ላይ፣ አብርሃም እንደ ዋና የመሸጋገሪያ ድልድይና እንደ መነሻ አንጓ ነው።
ፍፁም እምነት ወይስ ጠንካራ መርህ?
አብርሃም፣… በአንድ በኩል፣ ጽኑ የፍቅርና የፍትህ መርሆችን የጨበጠ፣ ጨዋና ጠንካራ ሰው እንደሆነ ትረካው ይነግረናል።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ የ“ፍፁም እምነት” ቀዳሚ ምሳሌ ተደረጎ ይቆጠራል፡፡
“የምትወደው ልጅህን ለእግዚሄር ሰዋ” የሚል፣… ለወላጅ ብቻ ሳይሆን ለሰሚ አእምሮ ሁሉ የሚከብድና የሚዘገንን ትዕዛዝ የመጣበት ሰው ነው፡፡
የመጀመሪያ ወንድ ልጆች፣ እንደ በኩር ልጅ፤ እንደ ወራሽ ልዩ ክብር ሊያገኙ ይችላሉ። ነገር ግን፣ ፈተናውና አደጋውም በዚያው ልክ በነሱ ላይ ይበዛል፡፡ ቤተሰብንና አካባቢን፣ ከተማንና አገርን ከአደጋ ለመታደግ ወደ ጦርነት የሚዘምቱት፣ ከእያንዳንዱ ቤተሰብ በእድሜ የደረሱ ትልልቅ ወንዶች፣ በኩር ልጆች ናቸው፡፡
ወላጆች ልጃቸውን ለዘመቻ አሳልፈው ሲሰጡ፣ ወደ ሞት መንጋጋ እንደሚሄድ አይጠፋቸውም፡፡ “በኩር ልጆቹን ገብሮ” የሚለው አባባል የተፈጠረው አለምክንያት አይደለም፡፡
መራራ ነው። ግን ደግሞ ምን ሌላ አማራጭ አለ?
ብዛቱና አይነቱ ይለያያል እንጂ፣ ወደ ጦርነት የሚያስገባ ጥቃትና ወረራ፣ አልያም ከንቱ የጦርነት ሰበብና ማመከኛ ጠፍቶ አያውቅም፡፡
ያኔ፣ ወላጅ ወደ ጦርነት ይዘምታል - ሸክሙን በልጆች ላይ ጭኖ፣ ለአደጋ አጋልጦ፡፡
አልያም፣ በእድሜ የደረሱ ልጆቹን ወደ ጦርነት ይሸኛል - ልጅን ወደ ሞት መንደር መሸነት፣ አሳዛኝና ዘግናኝ ቢሆንም።
የአብርሃም ትረካ፣ ይህን አስከፊ የሕይወት ገፅታ ልብ እንድንለው፣ ከምር እንድንገነዘበው የሚያገለግል “ምሳሌያዊ ፈተና” ሊሆን ይችላል፡፡ ፈተናው፣ አስከፊና መራራ እንደሆነ ጥያቄ የለውም። የጦርነትን ክፋት ማን ይጠፋዋል? ግን ደግሞ፣ በአገራችን እንደተመለከት ነው። ብዙ ሰው የጦርነትን ክፋት፣… መራራነቱን ዘግናኝነቱን ይረሳዋል። ጦርነት አፍጥጦ ከመጣ በኋላ፣ እልቂቱና ሃዘኑ፣ ውድመቱና ጉስቁልናው አገር ምድሩን ሲያተራምስ ነው የሚቆጠቁጠን።
ባለፉት ጥቂት አመታት በስፋት እንደታዘብነው፣ ጦርነትን አቅልሎ የማየት አላዋቂነት፣ በብሽሽቅ  መንፈስ ጥላቻን የማዛመት ክፋትና ጦርነትን እስከ መናፈቅ የሚደርስ ጭፍን የስካር ስሜት፣ ሞልቶ ይትረፈረፋል። መዘዙ ደግሞ ብዙ ነው፡፡ ሕይወትን በገፍ ይቀጥፋል። ቤተሰብን ይለያያል፡፡
ወላጅ ልጆቹን ወደ ሞት ይሸኛል።
ከዚህ የከፋ የሕይወት ገፅታ ይኖራል?
ይህን እንዳንዘነጋ፣… ሁሌም አስተዋይና ጠንቃቃ እንድንሆን የሚያገለግል በጣም ከባድ ምሳሌያዊ የተግሳጽ መልዕክት ከአብርሃም ትረካ ብናገኝ ጥሩ ነው፡፡
በእርግጥ፣ የትረካው መልዕክት ሌላ ነው የሚያስብል መንፈስም ይዟል - የአብርሃም ትረካ። ፍፁም እምነትን፣ ፍፁም ታዛዥነትን የሚያሳይ ትረካ እንደሆነ የሚገልፁ አሉ፡፡ ሊሆን ይችላል፡፡ ይመስላልም።
ግን ደግሞ፣ አብርሃም የመርህ ሰው ነው። “የዳኝነት ፍርድ፣ በእያንዳንዱ ሰው ተግባርና ባሕርይ ልክ መሆን አለበት” የሚል ፅኑ የፍትህ መርህ የያዘ የቅንነት ሰው እንደሆነ ትረካው አስቀድሞ በሰፊው ይገልፅልናል፡፡
ትረካው እንዲህ ነው።
የሃጥያትና የወንጀል ጎሬ ሆናለች የተባለችውን ከተማ በእሳት ለማጥፋት ሁለት መላዕክት በእግዚአብሄር ሲሰማሩ አብርሃም ያያል።
በዝምታ አላለፈውም። ይሁን ብሎ አልተቀበለውም። ከታላቅ ትህትና ጋር ለፍትህ በፅናት ቆሞ ሞግቷል - በፍቅርና በተቆርቋሪነት መንፈስ። ትረካውን እንመልከት።
እግዚሄርም አለ፣
“እኔ የማደርገውን ከአብርሃም እሰውራለሁን? አብርሃም በእውነት ታላቅና ብርቱ ሕዝብ ይሆናል። የምድር አሕዛብም ሁሉ በእርሱ ይባረካሉ። ጽድቅንና ፍርድን በማድረግ የእግዚሄርን መንገድ እንዲጠብቁ፣ ልጆቹንና ከእርሱ በኋላ ቤቱን እንደሚያዝዝ አውቃለሁና”…
አብርሃም የተሞገሰው፣ ለጽድቅ እና ለፍትህ ባለው ጠንካራ ፍቅር እንደሆነ ልብ በሉ። እግዚሄር አብርሃምን ከማድነቅ አልፎ፣ ሃሳቡን ያዋራዋል። ከአብርሃም የምሰውረው ምስጢር የለም ይላል። ስለመዓተኛዋ ከተማ ይነግረዋል። ኃጥያታቸው እጅግ ከብዳለች በማለትም፣ ስለከተማይቱ ሰዎች ያወራለታል። በከተማይቱም ላይ የቅጣት መዓት እንደሚያወርድባት ይጠቁመዋል።
አብረሃምም ቀረበ… በማለት ትረካው ይቀጥላል። አስገራሚውን ውይይት ያስነብበናል። አብርሃም ለእግዚሄር ይናገራል።
“በውኑ፣ ጻድቁን ከኃጢአተኛ ጋር ታጠፋለህን? 50 ጻድቃን በከተማይቱ ውስጥ ቢገኙ፣ በውን ሁሉን ታጠፋለህን? ከተማይቱን በእርሷ ስለሚገኙ 50 ጻድቃን አትምርምን?” አለ።
አብርሃም በዚህ አላበቃም። ተጨማሪ
መከራከሪያውንም አቅርቧል። ከማሳመኛና ከማግባቢያ አገላለፅ ጋር። አብርሃም ለእግዚሄር ይናገራል።
ጻድቁን ከኃጢያተኛ ጋር ትገድል ዘንድ፣ ጻድቁም እንደኃጢያተኛ ይሆን ዘንድ፣… እንደዚህ ያለው አድራጎት ከአንተ ይራቅ። የምድር ሁሉ ፈራጅ፣ በቅን ፍርድ አይፈርድምን?” አለ አብርሃም።
እግዚሄርም፣ …”በከተማይቱ ውስጥ አምሳ ጻድቃን ባገኝ፣ ስፍራውን ሁሉ ስለ እነርሱ እምራለሁ” አለ።
አብራሃም ግን በዚህ አልረካም።
“እኔ አፈር አመድ ስሆን፣ ከጌታዬ ጋር እናገር ዘንድ አንዴ ጀመርሁ። ከሃምሳ ጻድቃን አምስቱ ቢጎድሉ ከተማይቱን ሁሉ በአምስቱ ምክንያት ታጠፋለህን?” ብሎ ጠየቀ።
አብርሃም ጉዳዩን ለማክበድ፣ እንዴት አገላለፁን እንደገለበጠው ልብ በሉ። በአምስት ሰዎች ጉድለት ብቻ ከተማዋ እንድትጠፋ እንደመፍረድ ነው ብሎ ጉዳዩን ተረጎመው። እግዚሄር፣ ይህን የአብርሃም አገላለፅ በሚያስተካክል መንገድ መልስ ይሰጠዋል።
አርባ አምስት ጻድቃን በከተማይቱ ቢያገኝ፣ ከተማዋን እንደማያጠፋት ነገረው።
አብርሃም አሁንም ተከራከረ።
ምናልባት አርባ ቢገኙስ?
ለአርባው ስል አላደርገውም።
ጌታዬ አይቆጣ። እኔ እናገራለሁ። ምናልባት እዚያ ሠላሳ ቢገኙሳ?
እዚያ ሠላሳ ባገኝ አላጠፋትም።
ደግሞም፣ ከጌታዬ ጋር እናገር ዘንድ አንድ ጊዜ ጀመርሁ። ምናልባት እዚያ ሀያ ቢገኙሳ?
እዚያ ሀያ ቢገኙ፣ ስለ ሀያው ስል አላደርገውም።
እኔ ደግሞ፣ አንድ ጊዜ ብቻ ብናገር ጌታዬ አይቆጣ። ምናልባት አሥር ቢገኙሳ?
ስለ አሥሩ አላጠፋትም አለ።
እግዚሄርም ከአብርሃም ጋር ንግግሩን በጨረሰ ጊዜ ሄደ። አብርሃምም ወደ ስፍራው ተመለሰ።
የከተማዋ ንፁሀን ሰዎች ቁጥራቸው ከአሥር ያነሰ ከሆነ፣ ከወንጀለኞች ጋር አብረው ይጥፉ ማለት አይደለም። ከከተማዋ እንዲወጡ ማድረግ ይቻላልና። ደግሞም፣ እንዲወጡ ተደርገዋል። ይህም በትረካው ተገልጿል።
ገና ከመነሻው፣ አብርሃም ለጽድቅና ለፍትህ ጠንካራ መርህና ፍቅር እንዳለው የተነገረን እውነትም ትክክል ነው። እግዚሄር ያሞገሰውስ በዚህ ምክንያት አይደል!
“አድናቆትም ሆነ ተግሳፅ፣ ቅጣትም ሆነ ሽልማት፣… ማንኛውም ዳኝነትና ፍርድ በጅምላ መሆን የለበትም” የሚል ነው የአብርሃም የፍትህና የፍርቅ መርህ።
እንያንዳንዱ ሰው እንደ የስራው እንደ የባሕርይው መታየትና ዳኝነት ማግኘት አለበት። ንጹሐንን ከወንጀለኞች ጋር አዳብሎ እንደጥፋተኛ ማየት “ቅን ዳኝነት” አይደለም። ንጹሐን ሰዎች ከወንጀለኞች ጋር ቅጣት ሊፈረድባቸው አይገባም።
“እንዲህ አይነቱ አድራጎት ከአንተ ይራቅ። የምድር ሁሉ ፈራጅ፣ በቅን ፍርድ አይፈርድምን?” ይላል አብርሃም- ለእግዚሄር።
የአብርሃም ተቆርቋሪነትና መከራከሪያ፣ ወዲህ ወዲያ አይወላውልም። … በጠንካራ የፍርትህና የፍቅር መርህ ላይ ፀንቶ የቆመ ነው የአብርሃም እምነት።
አነጋገሩ በአጽንኦት ነው። ነገር ግን እንዲሁ መሟገቻ አገኘሁ በሚል ስሜት ወይም በአመፀኛ መንፈስ አይደለም። እንዲያውም፣ በትልቅ አክብሮትና ትህትና ነው የሚናገረው። ግን ደግሞ፣ በፅኑ የፍትህና የፍቅር መርህ!
ከእግዚሄር ጋር ሲሰነባበቱ፣… የአብርሃም የቀድሞ እምነት ይበልጥ ቢጠነክር አይገርምም። “እግዚሄር እውነትም በፍትሕና በፍቅር መርህ፣ በቅንነት የሚፈርድ ዳኛ ነው” ብሎ አብርሃም ከልብ ቢያምን አይደንቅም። ከእግዚአብሔር ጋር በግልጽ ተነጋግሯል።
ስለ አሥር ሰዎች፣ ከተማይቱን እምራለሁ ብሎታል። ምንም እንኳ ከተማዋ የእልፍ ወንጀለኞች መነሃሪያ ብትሆንም፣… ለ10 ንጹሐን ሲል የማያጠፋት ከሆነ፣… የፍቅር ተቆርቋሪነትን ይመሰክራል። የፍትህ ዳኝነትንም ያሳያል። አስር ባይሞሉም እንኳ፣ ከወንጀለኞች ጋር አልተቀጡም።
ይህን ትረካ ስናገናዝብ፣ አብርሃም ማለት፣ ያለ ጥያቄ፣ ያለ ሃሳብ፣ ያለ መርህ፣… እንዲሁ በጭፍን አምኖ በዘፈቀደ የሚታዘዝ ሰው ነው ማለት እንችላለን? እንዴት ተደርጎ!
አዎ፣ በአንድ በኩል፣ ጠንካራ እምነት እንዳለው ትረካው ይነግረናል።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ጠንካራ የፍትህና የፍቅር መርሆችን በፅናት የያዘ ሰው እንደሆነ ትረካው ይገልፅልናል።
ስለ ፍትህ ዳኝነት ከእግዚሄር ጋር ተነጋግሮ፣ መከራከሪያና ጥያቄ በተደጋጋሚ አቅርቦ፣ በግልፅ አረጋግጧል። ይህም፣ እምነቱን አጠንክሮለት ሊሆን ይችላል። ለዚህም ይሆን “ልጅህን ሰዋ” የሚለውን ትዕዛዝ በእምነት የተቀበለው? ወይስ ምሳሌያዊ ትረካ ይሆን?
የመጀመሪያ ልጆች ላይ የሚደርሰውን ጫናና ሃላፊነት፣ እንዲሁም የዘመቻ ሽኝትና የጦርነት እልቂት በጥንቱ ዘመን በሰፊው ይታወቃል።
ደግሞም፣… በምሳሌያዊ አነጋገር ብቻ ሳይሆን፣… ቃል በቃል ልጆችን መስዋዕት የማድረግ አሳዛኝና ዘግናኝ የእምነት ቅኝቶች በጥንት ዘመን እንደነበሩ አብርሃም ማወቁ አይቀርም።
የሆነ ሆኖ፣… የአብርሃም ትረካ፣ ጠንካራ እምነትን ብቻ ሳይሆን፣ ጠንካራ የፍትህና የፍቅር መርህን የሚያሳይ ገፅታ እንዳለው መርሳት የለብንም ለማለት ነው።

Read 1098 times