Thursday, 29 December 2022 07:59

የካንሰር ታካሚዎች ለህክምና እስከ ሁለት ዓመት ወረፋ ይጠብቃሉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ለውጭ ሀገር ህክምና በየአመቱ 100 ሚሊየን ዶላር ይወጣል

– አራት የጨረር ሕክምና መሳሪያዎች በመጋዘን ተቀምጠዋል

አዲስ አበባ፡- ከጊዜ ወደጊዜ እየተስፋፉ ከመጡ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መካከል አንዱ የካንሰር በሽታ ነው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው መረጃ መሰረት በኢትዮጵያ በየአመቱ 70 ሺህ ሰዎች በካንሰር የሚያዙ ሲሆን ቢያንስ 50 ሺህ የሚሆኑ ዜጎችም ለህልፈት ይዳረጋሉ፡፡

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ያሉት የካንሰር ህክምና መስጫ ማዕከላት ቁጥር እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ የገንዘብ አቅም ያላቸው ጥቂት ዜጎች ለሕክምና ባህር ማዶ ሲሻገሩ፣ ብዙዎች ግን ወረፋ እየተጠባበቁ ለህልፈት የሚዳረጉበት አጋጣሚ ብዙ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በሌላ በኩል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቀውንና ጨረር በማመንጨት ካንሰርን የሚገድለውን ‹‹ሌይነር አክስለሬተር›› የተሰኘ ዘመናዊ የካንሰር ህክምና መስጫ ማሽን እአአ በ2017 ወደሃገር ውስጥ አስገብቷል፡፡

ለጎንደር፣ ለሃይደር፣ ለጅማ፣ ለጥቁር አንበሳ፣ ለጳውሎስ፣ ለሐዋሳና ለሃሮማያ ዩኒቨርሲቲዎች ለእያንዳንዳቸውም አንድ ደርሷቸዋል፡፡ በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተር ወይዘሮ ሕይወት ሰለሞን እንደገለጹት፤ ሰባቱ ማሽኖች የተገዙት

 በ24 ሚሊየን ዶላር ወጪ ነው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶክተር አንዷለም ደነቀ፤ ባግባቡ ከተሰራ ባንከሩን ሰርቶ ማሽኑን ለማስገባት ከአንድ አመት በላይ አይፈጅም ይላሉ። ህንጻው ተገንብቶ፣ ሁለት ማሽን ተክሎ፣ ባንከሩ ተዘጋጅቶ፣ አስፈላጊ ግብአቶችን አስገብቶ ስራ ለማስጀመር እስከ አንድ ቢሊየን ብር ሊፈጅ ይችላል።

ከገቡት ማሽኖችም የጅማ፣ የጥቁር አንበሳና የሃሮማያ ስራ ሲጀምሩ፤ ቀሪዎቹ አራት ማሽኖች በየተቋማቱ እስካሁን በመጋዘን ተቀምጠዋል።

በውሉ መሰረት የማሽን ገጠማ ስራ (ኢንስታሌሽን) እና ተጨማሪ ስራዎች ማሽኑን ያቀረበው ኩባንያ ኃላፊነት ሲሆን፤ የካንሰር ማዕከል (ባንከር)፣ የህንጻ ግንባታና ባለሙያ ማብቃት ደግሞ የዩኒቨርሲቲዎቹ ኃላፊነት መሆኑንም ዳይሬክተሯ ይጠቁማሉ።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የካንሰር ህክምና ኢንስቲትዩት የካንሰር ማዕከል ኃላፊ ዶክተር አማረ አሰፋ እንደሚሉት፤ የካንሰር ህክምና መስጫ ማሽኑ ስራ ከጀመረ 15 ወራት ሆኖታል። በማዕከሉ በቀን እስከ 107 ሰው፤ በአመት እስከ ሁለት ሺ 500 ሰው ይታከማል፣ ስራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶም በጨረር ብቻ ከአንድ ሺህ በላይ ዜጎች መታከማቸውን ይገልጻሉ።

የጥቁር አንበሳ ማሽን በብልሽት ለሶስት ወራት አገልግሎቱን በማቋረጡ ጅማ ዩኒቨርሲቲ በርካታ ተገልጋዩችን በመቀበል ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደነበረበት፣ እንደአገር የማሽን ህክምና ከሚፈልገው ታካሚ ቁጥር ጋር ተመጣጣኝ አለመሆኑንም ይጠቁማሉ።

በሃገራችን በየአመቱ 150 ሺህ ሰው የጨረር ህክምና ይፈልጋል። ይህንን ህዝብ ለማከም ደግሞ ቢያንስ እስከ 200 ማሽኖች እንደሚያስፈልጉ፣ ለህክምናውም ዜጎች በየአመቱ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ እንደሚያደርጉ ይገመታል ሲሉ ዶክተር አማረ ይናገራሉ።

እንደርሳቸው ገለጻ፤ አቅም ያላቸው ህክምናውን ለማግኘት ወደ ታይላንድ ባንኮክ፣ ቱርክ፣ ሕንድ ይጓዛሉ። ለምሳሌ አንድ ሰው ህንድ አገር ለመታከም ሁለት ወራት ያህል ይፈጅበታል፣ የአልጋና የትራንስፖርት ወጪን ጨምሮ ከ16 እስከ 20 ሺህ ዶላር ይፈጅበታል። ለጨረር ህክምናው ብቻ ደግሞ 32 ሺ ዶላር ይከፍላል።

በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የካንሰር ህክምና ክፍል ኃላፊ ዶክተር ኤዶም ሰይፉ እንደሚናገሩትም፤ አዲሱ ማሽን ስራ ከጀመረ ሁለት ዓመት አስቆጥሯል። በቅርቡ ለሶስት ወራት በመበላሸቱ በርካቶች ተጉላልተዋል።

ችግሩ ተደራራቢ ህክምናውም ውስብስብ ሆኗል። በቀን ከ30 እስከ 40 በወር ደግሞ ከ400 እስከ 500 የሚጠጉ አዳዲስ ታካሚዎች ይመጣሉ። አብዛኞቹ ታካሚዎች የጨረር ህክምና ስለሚያስፈልጋቸው ለጨረር የሚመዘገበው ታካሚ እየጨመረ ይገኛል። አንድ ታካሚ ለህክምናው ስድስት ወራት ይቀጠር የነበረው ዓመት፣ አሁን ዓመት ከስድስት ወራትና ሁለት ዓመታትም ደርሰናል ነው የሚሉት።

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ጤና ህክምና ኮሌጅና በሕይወት ፋና ሁሉን አቀፍ ሆስፒታል የአስተዳደርና ልማት ዳይሬክተር አቶ ፊላ አህመድ በበኩላቸው፤ የጨረር ህክምና ማዕከል ስራ ጀምሯል፣ ጎን ለጎን ከፍቃድ ጋር ተያይዞ አስፈላጊ ዝግጅቶች እየተከናወኑ ይገኛሉ ይላሉ።

እስካሁን በጨረር ህክምናው 45 ሰዎች የሕክምና አገልግሎት አግኝተዋል። 20 ሰዎችም ተመዝግበው ህክምና ለማግኘት በመጠባበቅ ላይ ናቸው።

በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ህክምና እና የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶክተር አንተነህ ጋዲሳም፤ የማሽን ገጠማ ስራ እያለቀ መሆኑንና ከጨረር ህክምና ውጭ ያሉ ህክምናዎች እየተሰጠ እንደሚገኝ ይጠቁማሉ።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ እና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አሸናፊ ታዘበውም፤ ህክምናው የሚሰጥበት ክፍል /ባንከሩ/ ሙሉ ለሙሉ ማለቁን፣ ለመጀመር ቴክኒሽያኖችና የሰው ሃይል የማሟላት ስራ እየሰሩ መሆኑን ይገልጻሉ።

ጨረታውን ያሸነፈው የማሽን የገጠማ ስራ (ኢንስታሌሽን) የሚሰራው ‹‹ኤልስሜድ ኸልዝ ኬር ሶሉሽን›› የኢትዮጵያ ወኪል፣ ማኔጂንግ ዳይሬክተርና ባለቤት አቶ ዳዊት ሃይሉ ጨረታው በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በኩል እ.አ.አ በ2015 እንደወጣ ያስታውሳሉ።

በ2016/17 አካባቢ የሐዋሳና የሐረር ሳይቶች ዝግጁ መሆናቸው እንደተነገራቸው ኤልሲ ተከፍቶ ለሰባቱም አስፈላጊ እቃዎች እንዲገቡ መደረጉንም ነው የሚናገሩት።

የሐረማያ፣ የሐዋሳና የጎንደር ዩኒቨርሲቲዎች ፈጥኖ ወደ ትግበራ ለመግባት የጸጥታ ችግር፣ ከኮቪድ መከሰት ጋር ተያይዞ የእንቅስቃሴ ገደብ መጣሉ ተደማምረው ጫና ማሳደራቸውንም በምክንያትነት ያነሳሉ።

አቶ ፊላ በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ አስፈላጊ ግብአቶችን ከውጭ ለማስገባት የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ ስራው ለውጭ አካል በመሰጠቱ በራስ ጉዳይ የመጠመድና አስፈላጊ ግብአቶችን ለማስገባትም ችግር ማጋጠሙ ለመዘግየቱ ምክንያት መሆኑን ያነሳሉ።

ዶክተር አንተነህ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ፤ ማሽኑን እአአ በ2017/18 መረከባቸውን፣ በ2019 የገጠማ ስራው መጀመሩን፣ ገጠማውን የሚሰራው አንድ ቡድን በመሆኑ የጥቁር አንበሳንና የጅማን ጨርሶ ወደሐረር እስኪጓዝ መዘግየቱን ይገልጻሉ። ከሶስት ወራት በኋላም ወደ ትግበራ እንደሚገባ ይናገራሉ።

ዘገየ የሚለውን እንደማይስማሙበት የሚናገሩት ደግሞ ዶክተር አሸናፊ ናቸው፤ በእቅዱ መሰረት በጣም ዘገየ የሚባልበት ሁኔታ ላይ አለመሆኑን፣ የተጀመረው፤ የጅማ፣ የሐዋሳና የሀሮማያ ሳይቶች ከተጀመሩ ከዓመት በኋላ የጎንደር መጀመሩንና የዲዛይን ማሻሻያዎችም መደረጋቸውን ይገልጻሉ።

ከሌሎቹ ሳይቶች በተለየም የኒኩሊየር ሕክምና መስጫ አብሮ በመገንባቱ መዘግየት መፍጠሩን፣ የኒኩሊየር ማስወገጃውና የማሽኖቹ ተከላ ተጠናቅቆ እኤአ 2023 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ስራ እንደሚጀምርም ይገልጻሉ።

እስካሁን ጎንደር ሐዋሳ፣ መቀሌና (ሀይደር) ስራ አለመጀመራቸውን የሚያስታውሱት ኤልስሜድ ኸልዝ ኬር ተወካይ አቶ ዳዊት በበኩላቸው እንደሚገልጹት፤ ጎንደርና ሐዋሳ በወቅቱ የባንከሩ ሳይት ከተሰራ በኋላ ከፊት ለፊታቸው ትልቅ ህንጻ ስለገነቡ ማሽኑን ለመግጠም አልቻልንም።

አሁን ህንጻው ተጠናቅቆ ወደ ማሽን ገጠማ ስራ ገብተናል። የሐዋሳው በዚህ ወር፣ የጎንደሩ በሚቀጥለው ወር ይጠናቀቃል። የጳውሎስ ግን እስካሁን ገጠማ አልተካሄም። ሆስፒታሉ የካንሰር ማዕከልን ጨምሮ ሰፊ የግንባታ ስራ ላይ ይገኛል።

ስራ ያልጀመሩ ቀሪዎቹን ማሽኖች ወደትግበራ ለማስገባት ተግዳሮት የሆኑብን የሳይቶቹ ዝግጁ አለመደረግ ነው። አሁን ላሉ ለማሽኖች አስፈላጊ መለዋወጫ አስገብተናል። የግንባታ ብቻ ሳይሆን፤ የኤሌክትሪክና ማሽኑ የሚፈልጋቸው ግብአቶች መኖር ወሳኝ ነው ብለዋል አቶ ዳዊት።

መቀሌ የሚገኘው የሃይደር ሪፈራል ሆስፒታል ማሽኑን ከወሰዱ ሰባቱ ተቋማት አንዱ መሆኑንና ከሰሜኑ ግጭት ጋር ተያይዞ ባለፉት ሁለት ዓመታት ያለበትን ሁኔታ እንደማያውቁም፣ አሁን የሰላም ስምምነት በመፈጠሩ ቡድን ተዋቅሮ ያለበትን ሁኔታ እስከምንመለከት መረጃ የለንም የሚለው ምላሽ ወይዘሮ ሕይወትም አቶ ዳዊትም የሚጋሩት ምላሽ ነው።

የታካሚዎቻችንን ቁጥር በእጥፍ ማሳደግ እንፈልጋለን። አንድ ባንከር ዝግጁ አድርገናል፣ የሰለጠነ የሰው ሃይልም አለን፤ ቢያንስ አንዱ ሲቆም ሁለተኛው ማሽን አገልግሎት እንዲሰጥ ተጨማሪ ማሽን ያስፈልገናል የሚሉት ደግሞ አገልግሎቱን እየሰጡ የሚገኙት የጥቁር አንበሳና የጅማ ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው።

አስጊነቱ እየጨመረ ባለው በዚህ በሽታ ‹‹በዓመት ከ60 እስከ 70 ሺህ ሰዎች በተለያዩ አዲስ የካንሰር አይነቶች ይያዛሉ። በከፍተኛ ቁጥር ተጠቂ እየሆኑ የሚገኙት ደግሞ ሴቶች ናቸው›› ይላሉ በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተር ሕይወት ሰለሞን።

የራዲየሽን ቴክኒሽያንና የባዮ ሜዲካል ኢንጂነሮች ቁጥራቸው መጨምር አለበት፣ በቂ መለዋወጫ በመጋዘን መኖር ይገባዋል፣ ማሽኑ ሲበላሽ የሚያድሱና የሚያስተካክሉ ባለሙያዎችን ቁጥር ማሳደግ ይገባል የሚለውንም ምክረ ሃሳብ ሁሉም ባለሙያዎች ይጋሩታል።

በኢትዮጵያ መዳን እየቻሉ በህክምና እጦት የሚሞቱ በርካታ የካንሰር ታማሚዎች ቢኖሩም ከዚህ በተቃረነ መልኩ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ ሃገር ተገዝተው የገቡ የህክምና መስጫ መሳሪያዎች ሙሉ ለሙሉ ወደስራ ሳይገቡ ለአመታት ቆይተዋል። ይህ ደግሞ የሃገር ሃብት ያለአግባብ እንዲባክን ፣ ዜጎች በህክምና እጦት እንዲሞቱ፣ እንዲሁም ጥቂት አቅሙ ያላቸው ዜጎችም በሀገር ውስጥ መታከም እየቻሉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ አውጥተው ወደውጭ እንዲሄዱ በማድረግ የሀገር ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል። በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ተገዝተው የገቡት ማሽኖችም በወቅቱ ወደስራ ካልገቡ ሊበላሹና ለተጨማሪ ኪሳራ ሊዳርጉ ይችላሉ።

Read 1395 times