Saturday, 24 December 2022 15:28

አብዛኛው ፖለቲካችን “ምነው ፕራንክ” በሆነ የሚያሰኝ ነው!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(4 votes)

 የሃይማኖቱን ሽኩቻ ሰከን ረጋ ብናደርገው ይሻላል!
                      
          ወደ ዛሬው የፖለቲካ በፈገግታ ዋነኛ አጀንዳዬ ከመግባቴ በፊት አንድ የዩቲዩብ ቻናል ላይ ያነጣጠረ ትዝብቴን ሳስቀድም። በእርግጥ ይህ ትዝብቴ ለዋነኛው አጀንዳዬ ማጠናከሪያ እንደሚሆነኝ አምናለሁ። (“ከእናንተ ባላውቅም” ነው የሚለው ሃበሻ የልቡን ተናግሮ!)
የዩቲዩብ ቻናሉ የአንዲት ወጣት አርቲስት ነው። (አታስዋሹኝ አላውቃትም!) ፌቨን ከተማ ትባላለች። እናላችሁ… ከሰራችው ቪዲዮ ስር የሰፈረው መግለጫ፤ “አርቲስት ትዕግስት ግርማን ፌቨን ከተማ ፕራንክ አደረገቻት- ቲጂን ያስለቀሳት ጉዳይ” ይላል።  (እንደተለመዱት ዩቲዩብ ርዕሶች!) በኋላ ላይ ቪዲዮውን ስመለከት ግን ፕራንክ አይደለም ያደረገቻት። ቀልቧን ነው የገፈፈቻት። እርር ብግን አድርጋ ቢሮውን ጥላ እንድትወጣ ነው ያስገደደቻት፡- ያውም ስሜቷ ክፉኛ ተነክታ እያለቀሰች። (ወጣቷ አርቲስት ይሄንን ነው ፕራንክ ብላ የምትኩራራው!)
ይታያችሁ፤ በቪዲዮው መግቢያ ላይ ለተመልካቾች አርቲስት ትዕግስት ግርማን ፕራንክ ልታደርጋት መሆኑን አስቀድማ ትናገራለች- የቻናሉ ባለቤት ፌቨን  ከተማ። ግን ደግሞ ከዚህ ቀደም ፕራንክ አድርጋም ሆነ ተደርጋ እንደማታውቅ አልሸሸገችም። የመጀመሪያዋ የፕራንክ ሙከራዋ መሆኑ ነው!
ልብ አድርጉልኝ፤ አርቲስት ትዕግስት ግርማ አንጋፋ የኪነጥበብ ባለሙያ ናት- ተወዳጅና ዝነኛ!ወደ ወጣቷ አርቲስት ፌቨን ቢሮ ያመጣት ጉዳይ ደግሞ “ለፕሮግራሜ ሃሳብ ስጭኝ” በሚል በቀረበላት ጥያቄ መሰረት ሙያዊ ምክር ለመለገስ ነው። ለሥራና ለቁም ነገር ነው ማለት ነው፤ ከቤቷ ተነስታ የመጣችው። ወጣቷ አርቲስት ግን ጉድ ሰራቻት፡፡ (ለነገሩ ራሷንም ነው ጉድ የሰራችው!) ፕራንክና ቁምነገርን አምታታችው። በዚህም ከፕራንኩም ከቁምነገሩም ሳትሆን ቀረች፡፡ (ቢያንስ ለዚያች ቅጽበት!) በዚያ ላይ አክብራት ምክር ልትለግሳት የመጣችውን አንጋፋ አርቲስት አስቀየመቻት፤ አሳዘነቻት፤ አስለቀሰቻት። (“ዲዛስተር” ነው ላል ፈረንጅ!)
በነገራችን ላይ ፕራንክ አድራጊዋና ተደራጊዋ ከዚያን ቀን በፊት የረባ ትውውቅ የላቸውም። (ወጣቷ አርቲስት አንጋፋዋን አርቲስት በአንድ አጋጣሚ እንዳገኘቻትና እንደተዋወቁ ብትገልጽም፤ አንጋፋዋ ግን አታስታውስም!) በአጭሩ ለፕራንክ የሚያበቃ ትውውቅ የላቸውም! አንጋፋዋ አርቲስት የምታውቀው ነገር ቢኖር፣ በአካል ለማታውቃት ታናሿ (በዕድሜም በሙያም!) አርቲስት ሙያዊ ምክር ልትለግስ ቢሮዋ ድረስ መጥታ ክፉኛ ማዘኗንና ስሜቷ መነካቷን ነው፡፡ የዕቅዱ አካል ባልሆነ በፕራንክ ሳቢያ!!
እንግዲህ አርቲስት ትዕግስት ግርማ ወደተጋበዘችበት ቢሮ ስትገባ ነው አስደንጋጩ ፕራንክ የሚጀምረው። አኩርፋ ትጠብቃታለች- ባለጉዳይዋ አርቲስት ፌቨን። ከዚያም በስልክ ንግግራቸው አንጋፋዋ አርቲስት የቢሮውን አድራሻ ስትጠይቃት በደንብ ስላልመለሰችላት፤ “የገጠር (የክፍለ ሀገር) ልጅ ነሽ፤ ቦታ አታውቂም” እንዳለቻት በማስታወስ ነው፤ መቀየሟን የምትነግራት፡፡ “ከቀጠሮው ሰዓት አርፍደሽ መጥተሸል” የሚልም አክላበታለች። (በእሳት ላይ ቤንዚን በሉት!)
ለነገሩ ትንሽ ጥርጣሬ አድሮባት ነበር - አንጋፋዋ አርቲስት፡፡ “ፕራንክ ልታደርጉኝ አይደለም አይደል?” ስትል  ጠይቃ ነበር። ነገር ግን “ዓይኔን ግንባር ያድርገው” ዓይነት ምላሽ ነው የሰጧት። ከዚያ ሆድ ብሷት “ሁላችሁንም ስላስቀየምኳችሁ  ይቅርታ” ብላ ጥታቸው ወጣች። ካሜራማኑ ሳይቀር እየተጯጯሁ ወጥተው ፕራንክ መሆኑን ነግረዋት ነው የተመለሰችው፡፡ ነገር ግን “The damage is already of  done” ይላል ፈረንጅ። (ጉዳቱ ደርሷል) ምክንያቱም አርቲስቷ  “እኔ ከቤቴ የወጣሁት የአቅሜን ልመክርና ሰውን ላስደስት እንጂ ላስቀይም አይደለም” በሚል ስሜት ክፉኛ አዝና እስከ ማልቀስ ደርሳለች።
ጉዳዩን ስንጠቀልለው፤ ወጣቷ አርቲስት ከህይወት ተሞክሮ ማነስና ከዕድሜዋም ለጋነት የተነሳ (አማካሪም ከማጣት ሊሆን ይችላል) “ለፕሮግራሜ ሃሳብ ስጭኝ” ብላ የጋበዘቻትን አንጋፋ አርቲስት ክፉኛ አስቀይማታለች- ሞክራው በማታውቀው ፕራንክ! ሁሌም ግን ዋናውን ጉዳያችንን ትተን ተቀጥላው ወይም ጥቃቅኑ ላይ ስንንጠለጠል፣ ለእንዲህ ያለ አደገኛ ክስረት እንዳረጋለን። (በዚህ አጋጣሚ የባለፈው ሳምንት የአዲስ አድማስ ዕትም፣ “ነፃ ሃሳብ” አምድ ላይ የወጣውን “አውራ የኑሮ ጉዳዮችን ከጥቃቅን አጃቢ ወጎች ጋር አናምታታ” የሚል ምርጥ ጽሁፍ ታነቡት ዘንድ እጋብዛችኋለሁ፤ በርግጠኝነት ታተርፉበታላችሁ። ቢያንስ ፕራንክና ቁምነገርን ከማምታታት ትድናላችሁ።
***
የፕራንክ ነገር ሲነሳ ሁሌም ወደ አዕምሮዬ ምን ከተፍ እንደሚል ታውቃላችሁ? “ምነው አብዛኛው ፖለቲካችን ፕራንክ በሆነ!” የሚል ሃሳብና ምኞት ለምን ብትሉ… ፖለቲካችን የለየለት ሆረር ነዋ! (Horrifying, terrifying, appaling, scary, shocking…) ወዘተ በሚሉ የፈረንጅ ቃላት የሚገለፅ!! ወደ ዋናው አጀንዳችን ስንመጣ ታዲያ አብዛኛው የአገራችን ችግርና ቀውስ ምንጩ የወጣት አርቲስት ዓይነተ ነው፡፡  ዋና የህይወት ጉዳዮችን ትተን ቅጥያ ቅርንጫፎች ላይ ማተኮራችን!! ፕራንክና ቁምነገርን መደባለቃችን ነው፡፡ አሁን ለምሳሌ ከሰሞኑ በአንዳንድ የመዲናዋ ት/ቤቶች ከሰንደቅ ዓላማ መስቀልና ከመዝሙር ጋር ተያይዞ የተቀሰቀሰውን ሁከትና ግጭት ተመልከቱልኝ። ዕውቀት ለማዳረስ ከተከፈቱ ት/ቤቶች ጋር ምን ያገናኘዋል? ልጆቻችን ወደ ት/ቤት የሚሄዱት እኮ ባንዲራ ለመስቀልና መዝሙር ለመዘመር አይደለም፡፡ ትምህርትና ዕውቀት ለመቅሰም እንጂ!! ማንም የት/ቤት ደጃፍን ያልረገጠ ኢትዮጵያዊ እኮ ባንዲራ መስቀልም ሆነ መዝሙር መዘመርም አያቅተውም። ለዚህ ት/ቤት መግባት አያስፈልግም እያልኳችሁ ነው!
እናም የት/ቤቶች አጀንዳ ሆኖ ውዝግብ ሊያስነሳና ግጭት ሊቀሰቅስ ባልተገባ ነበር። አስቡት… በዚህ ከትምህርት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በሌለው (ፖለቲካ በተጫነው በሉት) ጉዳይ ሳቢያ የተስተጓጎለውን የመማር-ማስተማር ሂደት! በተፈጠረው ግጭት የተጎዱትን ተማሪዎችና መምህራንን! የወደሙትን የት/ቤቶች ንብረት! የት/ቤቶች አጀንዳ ያልሆኑ ጉዳዮችን በግድ አጀንዳ አድርገን ምን አተረፍን? ብለን ስንጠይቅ ደግሞ… “ግጭት፡፡ ኪሳራ። ውድመት። ጥላቻ። ሁከት። አለመረጋጋት። ስጋት።” የሚል ነው መልሱ። ምናለፋችሁ… ጥፋት ብቻ ነው ያተረፍነው!! ያውም ከትምህርት ጋር ባልተገናኘ አጀንዳ፡፡ ያውም ጥበብ በጎደላቸው የብሔር ካድሬዎች ቀስቃሽነት!
የሚገርመው ደግሞ ምን መሰላችሁ? ት/ቤቶችንና መምህራንን እንዲሁም የትምህርት ቢሮዎችን (ወይም በቀጥታ ት/ሚኒስቴርን) በቀጥታ የሚመለከት አንድ አስደንጋጭ የጥናት ውጤት በቅርቡ ይፋ ተደርጎ ትኩረት ሳይሰጠው መቅረቱ ነው።
ከትምህርት ጋር በቀጥታ የሚገናኘው፤ ነገር ግን ማንም ትኩረት ያልሰጠው አስደንጋጭ የጥናት ውጤት ምን ይላል መሰላችሁ?
“በኢትዮጵያ 68% የሁለተኛ ክፍል ተማሪዎችና 51% የሦስተኛ ክፍል ተማሪዎች ማንበብና መፃፍ እንደማይችሉ የራይዝ ኢትዮጵያ ጥናት አመለከተ፡፡” የሚል ነው። ይሄ ነበር ቤተሰብን፤ መምህራንን የት/ቢሮን፣ የመንግስት ባስልጣናትን ሊያሳስብና ሊያስደነግጥ የሚገባው ጉዳይ! እስካሁን ግን የመገናኛ ብዙኃን የመወያያ አጀንዳ እንኳን አልሆነም፡፡ (ዋናውን ትልቅና ወሳኝ ጉዳይ መሳት ይሏል ይሄ ነው!)
ወዳጆቼ፤ የዘር ፖለቲካ (በቤት ስሙ ፅንፈኛ ብሄርተኝነት) ያመጣብን መዘዝ ሳያንስ፤ አሁን ደግሞ የሃይማኖት ትንኮሳ (ሽኩቻ) በአደባባይ እያስተዋልን ነው፡፡ (በእጅጉ ያስደነግጣል! ይታያችሁ… በትግራይ ጦርነት እስከ 500ሺ (ግማሽ ሚሊዮን) ህዝብ እንዳለቀ ነው የሚነገረው። በወለጋ አሁንም ድረስ ዘር-ተኮር ፍጅት ባለበት በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሃይማኖት ተቋማት በጋራ ለፈጣሪያቸው መፀለይ ሲገባቸው፤ የሃይማኖት ጦርነት ለማወጅ አገሪቱ ለ2 ዓመታት ከዘለቀ ደም አፋሳሽ ጦርነት ለመውጣት መከራዋን እየበላች ባለችበት በዚህ ፈታኝ ወቅት፤ ሌላ ስጋት በአገር ላይ መጋረጥ ምን የሚሉት ሙያ ነው?
ለመሆኑ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ዋነኛ ሥራቸውና ተግባራቸው ምንድን ነው? (ለሰላምና ለፍቅር ተግቶ መጸለይ መስሎኝ!!
ዛሬ በእልህና በማን አለብኝነት የሚወራወሩት የቃላት ጥይት፤ ነገ የለየለት ጦርነት ሊቀሰቅስ እንደሚችል ዘንግተውት ይሆን? (ወይስ እነሱም እንደ ፖለቲከኞቹ የመጣው ይምጣ ብለው ህዝቡን ለእልቂት ሊዳርጉት ነው?) አየችሁ እንዲህ ዓይነቱን መቅሰፍት የሚመስል አደጋ ስሰማ ነው “ምነው ፕራንክ በሆነልን” ብዬ የምመኘው፡፡
የሃይማኖት ተቋማቱም ወደ እዚህ ዓይነት አስደንጋጭ ሽኩቻ የሚገቡት ከዋና ዓላማቸውና ተግባራቸው በመራቃቸው ነው፡፡ ሰላም፣ ፍቅርና መከባበርን ከመስበክ ይልቅ ጥላቻ ንቀትና እልህ ላይ በማተኮራቸው!!
እርሱ የፍቅር ዓምላክ ሰላሙን ያውርድልን!!

Read 949 times