Print this page
Saturday, 24 December 2022 15:25

(Education to Protect Tomorrow) ነገን ለመጠበቅ …ትምህርት…

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(2 votes)

እንደውጭው አቆጣጠር ኖቨምበር 14 በየአመቱ የስኩዋር ሕመምን በሚመለከት የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የተለያዩ ስራዎች የሚታዩበት፤ የወደፊቱም የሚታቀድበት እለት ነው፡፡ በመሆኑም እ.ኤአ. ኖቨምር 14፤2022 ነገን ለማዳን ዛሬ ማስተማር በሚል መሪ ቃል የተለያዩ እንቅስቃሴዎች በአለም አቀፍ ደረጃ ተካሂደዋል፡፡
ሄልዝ ላይን የተባለው ድረገጽ ኦውገስት12/2022 እንዳስነበበው ይህ በየጊዜው የታማሚዎች ቁጥር እየጨመረ እንዲሄድ የሚያደርገው ህመም በየአመቱ ኖቨምበር 14 እየታሰበና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እንዲሁም ለተሸለ ስራ የሚያበረታቱ ድርጊቶች እንዲፈጸሙ እና በህክምናው ዘርፍ የተጠናከረ ስራን ለመስራት የሚያበረታታ መሆኑን ገልጾአል፡፡ በዚህም አስቀድሞ መከላከል፤ የተሻሉ የምርመራ ስራዎች፤ ሕመሙን በሚመለከት አስፈላጊ የሆኑ አስተዳደራዊ ስራዎችን መስራት በሚያስችል መልኩ የሚመለከታቸውን ሁሉ ለመዘጋጀት ያበቃል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት 16 September 2022 ያወጣው እውነታ የሚከተለው ነው፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ እ.ኤ.አ በ1980 የነበረው የስኩዋር ህመም ታማሚ 108 አንድ መቶ ስምንት ሚሊዮን ሲሆን እ.ኤ.አ በ2014 ይህ ቁጥር ወደ 422 አራት መቶ ሀያ ሁለት ሚሊዮን አድጎአል። የህመሙ ስርጭት በተለይም በመካከለኛው እና ዝቅተኛ ደረጃ ላይ በሚኖሩ ሀገራት ከፍተኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት በከፍተኛ ሁኔታ እና በፍጥነት እያደገ በመሄድ ላይ ያለ ነው፡፡
የስኩዋር ሕመም የአይነስውርነትን፤ የኩላሊት መዳከምን፤ የልብ ሕመምን እንዲሁም ስትሮክ እና በእጅና እግር ላይ ችግር ይፈጥራል፡፡
እ.ኤ.አ በ2000 እና 2019 መካከል በስኩዋር ሕመም ምክንያት የሚደርስ ሞት በእድሜ ልዩነት በ3% ጨምሮአል፡፡
እ.ኤ.አ በ2019 የስኩዋር ሕመም እና የኩላሊት ሕመም በስኩዋር ህመም ምክንያት ወደ 2 ሚሊዮን ለሚሆኑ ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኖአል፡፡
ጤናማ የሆነ ምግብ መመገብ መደበኛ የሆነ የአካል እንቅስቃሴ ተመጣጣኝ የሆነ የሰውነት ውፍረት እንዲኖር ማድረግ፤ እንደ ሲጋራ ማጤስ የመሳሰሉ እጾችን መጠቀም ማቆም የመሳሰሉትን እርምጃ መውሰድ በተለይም ሁለተኛ ቁጥር የተሰጠውን የስኩዋር ሕመም ለማዘግየት ይረዳል፡፡
የስኩዋር ሕመም ሊቆጣጠሩት እና በህክምናም ሊረዳ የሚችል ሲሆን አኑዋኑዋርን ማስተካከል ወይንም የተመደበውን መድሀኒት በትክክል አለመውሰድ የመሳሰሉት ነገሮች ካሉ ግን ለችግሩ ያጋልጣል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት በስኩዋር ሕመም ዙሪያ ያደረገው ምልከታ እንደሚያስረዳው የስኩዋር ሕመም መዳን የማይችል ከፍተኛ ክትትል የሚፈልግ ሕመም ነው፡፡ ይህ ህመም የሚከሰተውም ፓንክሪያሲስ ወይንም በአማርኛው ጣፊያ የተባለው አካል በቂ የሆነ ኢንሱሊን በሰውነት ውስጥ ማምረት ሳይችል ሲቀር ወይንም የተመረተውን ኢንሱሊን ሰውነታችን በትክክል መጠቀም ሳይችል ሲቀር ነው፡፡
ኢንሱሊን በሰውነታችን በደም ውስጥ የሚኖረውን ግሉኮስ የሚቆጣጠር ሆርሞን ነው። ባልተለመደ ሁኔታ በደም ውስጥ የስኩዋር መጠን ከፍ ሲል ከቁጥጥር ውጭ ወደሆነ የስኩዋር ህመምተኝነት የሚዳርግ ሲሆን በተጨማሪም ከጊዜ በሁዋላ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎች እንዲጎዱ ከማድረግ ባሻገር በተለይም የነርቭ እና የደም ስሮች እንዲጎዱ ምክንያት ይሆናል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት ዘገባ እንደሚያስረዳው እ.ኤ.አ በ2014 8.5% የሚሆኑ ታዳጊዎች እና እድሜአቸው 18 አመት የሚደርስ እና ከዚያም በላይ ያሉ በስኩዋር ህመም የተያዙ ነበሩ፡፡
እ.ኤ.አ በ2019 የስኩዋር ሕመም ለ1.5 ሚሊዮን ሰዎች የሞት ምክንያት እና 48% ከሚሆኑ ሁሉም ሞቶች የስኩዋር ሕመም የተከሰተው ከ70 አመት በታች ባለው የእድሜ ክልል ነው፡፡
ከላይ ከተጠቀሰው በተጨማሪ 460,000 የሚሆነው የኩላሊት ሕመም እና በዚያም ምክንያት የሚከሰተው ሞት ምክንያቱ የስኩዋር ሕመም ምክንያት ሲሆን ከፍተኛ በሆነው በደም ውስጥ በሚገኘው ግሉኮስ ምክንያት ደግሞ ወደ 20% የሚሆነው ከልብ ሕመም ጋር ተያይዞ የሚከሰተው ሞት ምክንያት ነው፡፡
በስኩዋር ሕመም ምክንያት የሚከሰተው ሞት እ.ኤ.አ በ2000 እና 2019 መካከል ወደ 3% የሚሆን የሞት መጠን የጨመረ መሆኑ ግልጽ ሲሆን ይህም በእድሜ የሚለያይ ነው፡፡ በዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት የሞት መጠኑ ወደ 13% የጨመረ ሆኖ ተመዝግቦአል እንደ የአለም የጤና ድርጅት ዘገባ፡፡
በንጽጽር ሲታይ እ.ኤ.አ ከ2000 እስከ 2019 ባለው ጊዜ በአለም አቀፍ ደረጃ በንክኪ ከማይተላለፉት አራት ሕመሞች ማለትም ከልብ ሕመም፤ካንሰር፤ የመተንፈሻ አካላት ሕመም ወይም የስኩዋር ሕመም በእድሜአቸው ከ30-70 በሚሆኑ ሰዎች የሚከሰተው ሞት በአለም አቀፍ ደረጃ ወደ 22% የቀነሰ መሆኑ ተመዝግቦአል፡፡ የስኩዋር ሕመም አይነቶች በተለያዩ ስያሜዎች የተመዘገቡ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል፡-
ቁጥር አንድ የስኩዋር ሕመም
ቁጥር አንድ የስኩዋር ሕመም የሚከሰተው ኢንሱሊን ከማጣት ነው፡፡ በሰውነት ውስጥ የሚመረተው ኢንሱሊን የተሰኘው ሆርሞን ባለመመረቱ ምክንያት ለቁጥር አንድ የስኩዋር ታማሚነት የተዳረጉ ሰዎች በህክምናው ዘርፍ የኢንሱሊን እርዳታ እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2017 ወደ 9 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በቁጥር አንድ የስኩዋር ሕመም ተጠቂ የነበሩ ሲሆን አብላጫዎቹም ሰዎች ከፍተኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት የሚኖሩ ሰዎች ነበሩ፡፡ ይህ ህመም ምክንያቱም ሆነ መከላከያው የታወቀ ነው፡፡ ምልክቶቹም፡-
ቶሎ ቶሎ ሽንትን መሽናት፤
የክብደት መቀነስ፤
የእይታ መዳከም፤
የመሳሰሉት በድንገት ይከሰታሉ፡፡
ቁጥር ሁለት የስኩዋር ሕመም
ሁለተኛው አይነት የስኩዋር ሕመም ሰውነት የተመረተውን ኢንሱሊን የተባለ ሆርሞን የማይጠቀምበት መሆኑ ነው፡፡ በአለም ላይ ከ95% በላይ የሆኑ የስኩዋር ታማሚዎች በቁጥር ሁለት የስኩዋር አይነት የታመሙ ናቸው፡፡ ይህ የስኩዋር ህመም በአብዛኛው ከልክ በላይ በሆነ የክብደት መጠን እና አካላዊ እንቅስቃሴ በማይደረግበት ሁኔታ የሚከሰት ነው፡፡
ይህ አይነቱ የስኩዋር ሕመም ምልክቶቹ ከቁጥር አንድ የስኩዋር ሕመም ምልክቶች ብዙም የማይለዩ ሲሆን የሚሰሙትም በዝቅተኛ ደረጃ ሊሆን ይችላል፡፡ ታማሚዎች ሕመሙ የሚታወቅላቸው ቁጥር 2 የስኩዋር ሕመም ከተከሰተ ከአመታት በሁዋላ የጤና ችግር ከማስከተል ደረጃ ላይ ከደረሰ በሁዋላ ሊሆን ይችላል፡፡  እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ይህ የስኩዋር ሕመም በታዳጊዎች ላይ የሚታይ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን ህጻናትም ላይ መታየት ጀምሮአል፡፡
በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የስኩዋር ሕመም፡-
በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የስኩዋር ሕመም በደም ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ የሚከሰትን ግሉኮስ ምክንያት የሚያደርግ ነው፡፡ ሴቶች በእርግዝና ወቅት የሚከሰተው የስኩዋር ሕመም በእርግዝናው ወቅት እና በወሊድ ጊዜ ለተለያዩ ችግሮች ሊያጋልጣቸው የሚችል ሲሆን እነዚህ ሴቶች እና የሚወለዱት ልጆቻቸው በወደፊት ሕይወታቸው ለቁጥር 2 የስኩዋር ሕመም ሊጋለጡ እንደሚችሉ ህክምናው ይገልጻል፡፡ በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት የስኩዋር ሕመም በእርግዝናው ክትትል ወቅት በሚደረግ ምርመራ የሚገኝ እንጂ ታምሜአለሁ ብሎ ወደ ሐኪም በመቅረብ የማያስረዱት ለሐኪም የሚያስረዱት አይደለም፡፡
በዚህ አመት የአለም አቀፍ የስኩዋር ሕመም ቀን መሪ ሀሳብ ነገን ለመጠበቅ ዛሬ ማስተማር የሚል ሲሆን በዘርፉ ለተሰማሩ የጤናባለሙያዎች (ተገቢውን ምርመራ እና ሕክምና ማድረግ እንዲሁም ታካሚዎቻቸውን በተገቢው በማማከር እንዲንከባከቡ) በተጨማሪም ሕዝቡን ስለስኩዋር ህመም ምንነት እና ለህመሙም ከተጋለጡ በምን መንገድ እራሳቸውን መርዳት፤ ማስተዳደር፤ እንዳለባቸውና ውስብስብ ከሆነ ችግር እራሳቸውን እንዲያላቅቁ ማስቸል ነው፡፡  
ነገን ለመጠበቅ… ትምህርት…
Education to Protect Tomorrow

Read 10695 times