Saturday, 10 December 2022 13:26

ከማህፀን ውጪ የሚፈጠር እርግዝና

Written by  ሀይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(3 votes)

  ከማህጸን ውጪ የሚፈጠር እርግዝና በአለም አቀፍ ደረጃ ከ1 እስከ 2 በመቶ ይከሰታል። ይህም ማለት ከአንድ መቶ እናቶች ውስጥ 1 ወይም 2 እናቶች ይህ እርግዝና ያጋጥማቸዋል። በአፍሪካ ወደ 4 እንዲሁም በኢትዮጽያ ወደ 3 በመቶ የሙከሰት እድሉ ከፍ ይላል። በጥቁር አንበሳ የጽንስ እና ማህጸን ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሰኢድ አራጌ እንደተናገሩት ከማህፀን ውጪ እርግዝና ተፈጠረ የሚባለው እርግዝና መፈጠር ከሚገባው የማህፀን ክፍል ውጪ በየትኛውም የሰውነት ክፍል ላይ ሲከሰት ነው። እርግዝና በተፈጠረ ከ3 እስከ 5 ቀናት ውስጥ በማህጸን ግድግዳ ላይ መቀመጥ ሲገባው መንገድ ላይ በሚያጋጥመው ችግር[እክል] ምክንያት ከማህጸን ውጪ እርግዝና ይከሰታል። ከማህፀን ውጪ የሚፈጠር እርግዝና 95በመቶ የሚቀመጠው የማህፀን ትቦ (Fallopian tube) ላይ ነው። የተቀረው 5 በመቶ በእንቁላል ማምረቻ፣ በማህፀን ጫፍ (በር)፣ ልጅ በቀዶ ጥገና በተወለደበት ቦታ (ጠባሳ ባለበት) ላይ እና በሆድ እቃ ውስጥ ሊቀመጥ ይችላል። በሆድ እቃ ውስጥ የሚፈጠረው እርግዝና በአብዛኛው ጊዜ የሚከሰተው ፓሊስ ማን [police man] ተብሎ በሚጠራው የሆድ እቃን ከባእድ ነገር ለመከላከል በተሰራው ሽፋን (Omentum) ላይ ነው።
ከማህፀን ውጪ የሚፈጠር እርግዝና በብዛት የማህፀን ትቦ ላይ የሚፈጠርበት ምክንያት ትቦው የወንድ ዘር እና የሴት እንቁላል ማስተላለፊያ በመሆኑ ነው። እንዲሁም ይህ የሰውነት ክፍል ስስ ስለሆነ በቀላሉ በተለያዩ በሽታዎች ለቁስለት ይዳረጋል። የማህፀንን ትቦ በማጥቃት ለቁስለት የሚዳርጉት በሽታዎች የማህፀን ኢንፌክሽኖች ናቸው።
ዶ/ር ሰኢድ እንደተናገሩት ሁሉም አይነት የማህፀን ኢንፌክሽኖች የማህፀን ትቦዎችን በመጉዳት ከማህፀን ውጪ ለሚፈጠር እርግዝና አይዳርጉም። የማህፀን ትቦ ይጎዳሉ ተብለው ከተቀመጡ የማህፀን ኢንፌክሽኖች መካከል; የአባላዘር በሽታ በተለይም ክላማይዲያ [Chlamydia] እና ጎኖሪያ [Gonorrhea] በመባል የሚጠሩት በዋነኝነት ይጠቀሳሉ። በሽታዎቹ ከ50 በመቶ በላይ ምልክት ሳይኖራቸው የማህጸን ትቦን ሲጎዱ ይስተዋላል። ነገር ግን ምልክት በሚያስዩበት ጊዜ ጠረን ያለው ከማህፀን የሚወጣ ፈሳሽ እና ሆድ[ማህጸን] አከባቢ የህመም ስሜት ይኖራቸዋል። ነገር ግን ትቦውን የሚጎዱ እና የማይጎዱ ኢንፌክሽኖችን ለመለየት የህክምና ባለሙያዎችን ማማከር ይመከራል።
ከላይ የተጠቀሱት ምክንያቶች ወይም መንስኤዎች እንዳሉ ሆነው በአጠቃላይ 50 በመቶ ከማህፀን ውጪ የሚፈጠር እርግዝና ምክንያቱ አይታወቅም። እንዲሁም በሁሉም እናቶች ላይ ሊያጋጥም ይችላል። ነገር ግን ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ተብለው የሚጠቀሱ ይገኛሉ። እነዚህም;
ሲጋራ የሚያጨሱ እናቶች
የወሊድ መቆጣጠሪያ በአግባቡ አለመጠቀም
ደህንነቱ ባልተጠበቀ መልኩ ጽንስ ማቋረጥ
ከተለያየ ሰው ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነት መፈፀም [ከጥንዶች ውስጥ አንዱ ወይም ሁለቱ]
ክላማይዲያ [Chlamydia] እና ጎኖሪያ [Gonorrhea] ማለትም በአባላዘር በሽታ መጠቃት
በፐብሊክ ኢንፍላማቶሪ በሽታ [pelvic inflammatory disease] መጠቃት
ከዚህ ቀደም ከማህፀን ውጪ እርግዝና አጋጥሟቸው የነበሩ ሰዎች
እንዲሁም ለረዥም ጊዜ የማህፀን በሽታ ታማሚ ሆነው በህክምና ምርመራ ግን የበሽታው ምንነት ያልታወቀላቸው ሰዎች ሊጋለጡ ይችላሉ። “በአጠቃላይ ለዚህ እርግዝና የሚያጋልጡ በሽታዎች ምልክት የሌላቸው ኢንፌክሽኖች ናቸው ማለት ይቻላል። ምልክት የሌለው ኢንፌክሽን ደግሞ በጣም አደገኛ ነው” ብለዋል ዶ/ር ሰኢድ አራጌ። ስለሆነም በሽታው ታውቆ ህክምና ለማግኘት ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ባለሙያው ተናግረዋል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከማህፀን ውጪ እርግዝና ሲፈጠር 30በመቶ በሚሆኑ እናቶች በመጀመሪያ የእርግዝና ወቅት ላይ ምልክት አይታይም። ይህም እናቶች የከፋ ደረጃ ከደረሱ በኋላ ወደ ህክምና ተቋም እንዲሄዱ ያደርጋል።
ከማህፀን ውጪ የሚፈጠር እርግዝና ምልክቶች;
ማህጸን አከባቢ የህመም ስሜት መኖር; ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ከማህጸን ውጪ እርግዝና ባጋጠማቸው እናቶች ላይ የህመም ስሜት ይኖራል።
ደም መፍሰስ; የሚፈሰው ደም ብዛት ላይኖረው ይችላል። ከማህጸን ውጪ የተፈጠረ እርግዝና ሆድ ውስጥ ከፈነዳ ደሙም ሆድ ውስጥ ይፈሳል እንጂ ወደ ውጪ አይወጣም። ነገር ግን ከማህጸን የሚፈሰው ደም የህመም ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል። ነገር ግን ሁሉም ደም የፈሰሳቸው እናቶች ከማህጸን ውጪ እርግዝና አጋጥሟቸዋል ማለት አይደለም።    
የወር አበባ መዘግየት; የወር አበባ መዘግየት ከማህጸን ውጪ ለተፈጠረ እርግዝና ብቻ ሳይሆን ለአንዲት እናት እርግዝና መፈጠር ምልክት በመሆኑ ወደ ህክምና ተቋም መሄድ ያስፈልጋል። እንዲሁም ከተጠቀሱት ምልክቶች መካከል አንዱ ምልክት ብቻ ካለ ወደ ህክምና ተቋም መሄድ ያስፈልጋል።
ከዚህ በተጨማሪ አጠቃላይ የሆድ ህመም፣ እራስን መሳት፣ የደም ግፊት መቀነስ እና የጀርባ ህመም ሊያጋጥም ይችላል።
አንዲት እናት የወር አበባዋ በቀረ በ1 ሳምንት ጊዜ ውስጥ ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ ምርመራ ማድረግ እንደሚገባት ባለሙያው ተናግረዋል። ይህም ከማህጸን ውጪ እርግዝና ከተፈጠረ በእናት ላይ ጉዳት ሳያደርስ ህክምና ለመስጠት ያስችላል። በህክምና ተቋም ውስጥ ከማህጸን ውጪ የተፈጠረ እርግዝና በ3 አይነት የምርመራ ዘዴ ይለያል። የምርመራ መንገዶቹም ሽንት፣ ደም እና አልትራሳውንድ ናቸው።
እናቶች ወደ ህክምና ተቋም ለመሄድ በዘገዩ ቁጥር ለተላያዩ ችግሮች እና ጉዳቶች የመጋለጥ እድላቸው ይጨምራል። ከጉዳቶቹ መካከል;
በቀዶ ጥገና የማህጸን ትቦ እንዲወጣ ሊያደርግ(ሊያሳጣ) ይችላል።
ጽንስ ሆድ ውስጥ እንዲፈነዳ ወይም ሆድ ውስጥ ደም እንዲፈስ ያደርጋል።
ሆድ ውስጥ ደም ሲፈስ በሰውነት ውስጥ የሚገኝ ደም ሊያልቅ ይችላል
የእናትን ህይወት ያሳጣል
“በመጀመሪያ የእርግዝና 3 ወራት ውስጥ የእናትን ህይወት በማሳጣት ከማህጸን ውጪ የሚፈጠር እርግዝና ይጠቀሳል” ብለዋል ዶ/ር ሰኢድ አራጌ። ከማህጸን ውጪ የሚፈጠር እርግዝና እና ደህንነቱ ያልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ ከ3 ወር በታች የሚገኙ ነፍሰጡሮችን ህይወት በማሳጣት በቀዳሚነት እንደሚጠቀሱ ባለሙያው ተናግርዋል።
እናቶች ወደ ህክምና ተቋም ሳይሄዱ በዘገዩ ቁጥር በእናቶች ላይ የሚደርሰው ጉዳት እየጨመረ ይሄዳል። እርግዝናው ከማህጸን ውጪ መፈጠሩ በህክምና ባለሙያዎች እንደታወቀ ጽንሱ እንዲቋረጥ ይደረጋል። ምክንያቱም ጽንሱ ሊያድግ የሚችልበት አመቺ ወይም ተፈጥሯዊ የልጅ ማደጊያ ስፍራ ባለመሆኑ ነው። ስለሆነም ተፈጥሯዊ እና አመቺ ባልሆነ መልኩ የተፈጠረውን እንዲሁም ለእናት ሞት ምክንያት የሆነውን ጽንስ ለማቋረጥ እናቶች የወር አበባቸው መምጣት እንዳቆመ ወደ ህክምና ተቋም መሄድ ይገባቸዋል። በተመሳሳይ ከማህጸን ውጪ እርግዝና እንዲፈጠር የሚያደርጉ ምክንያቶችን በማስወገድ ወይም በመከላከል ተጠቂነትን መቀነስ ይቻላል። ነገር ግን በሁሉም ሴቶች ላይ ሊከሰት የሚችል መሆኑን እና ሙሉበሙሉ መከላከል እንደማይቻል መዘንጋት አይገባም። ስለሆነም የእናቶች ሞት እናዳይከሰት የህክምና ባለሙያዎችን ምክር ተግባራዊ በማድረግ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት።   



Read 12174 times