Print this page
Saturday, 03 December 2022 12:39

ጋዜጠኛ ግሩም ሰይፉ ከቢቢሲ ጋር

Written by 
Rate this item
(2 votes)

      25 ሺ ገደማ ኢትዮጵያውን በኳታር ይኖራሉ

       ግሩም ሰይፉ ጋዜጠኛ ነው። አዲስ አድማስ ለተሰኘው ጋዜጣ ስፖርታዊና ማኅበራዊ ጉዳዮችን በመፃፍ ይታወቃል። ግሩም የኳታር የዓለም ዋንጫ ዝግጅትን ለመታደም ወደ ዶሃ ያቀናው ከመክፈቻው ጥቂት ቀናት ቀድሞ ነው።
ዶሃ ከአዲስ አበባ 2200 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ ትገኛለች። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኳታር ኤርዌይስ በየቀኑ መንገደኞችን ያመላልሳሉ።
ግሩም፤ ነፋሻማዋን አዲስ አበባ ለቆ ወደ ዶሃ ሲያመራ የጠበቀው የግንቦት ሃሩር ነው። ነገር ግን ይህ ወቅት ለኳታሮች ቀዝቃዛው ወር ነው።
“ዶሃ የቀትር ፀሐይ የሚባል የለም” ይላል። ምክንያቱም ቀኑን ሙሉ የዶሃን አሸዋማ መሬት የሚቀጠቅጠው ፀሐይ ሃሩር ነው።
ኳታር፤ በሜትሮሎጂ ዘገባ አገላለፅ፤ “በአብዛኛው ፀሐያማ” ናት። በአብዛኛው ከማለት ከንጋት እስከ ምሽት ማለት ሳይቀል አይቀርም። አሁን ባለው የአገሪቱ የአየር ሁኔታ ዝቅተኛው የሚባለው 23 ድግሪ ሴንትግሪድ የሚጀምረው ሌሊት 10 ሰዓት ገደማ ነው።
ዎርልድ ፖፑሌሽን ሪቪው የተሰኘው ድረ-ገፅ፣ የኳታር ሕዝብ ብዛት በዚህ ዓመት 2.7 ሚሊዮን ይገመታል ይላል።
ከእነዚህ መካከል ካታሪ የሚባሉት አረቦች 15 በመቶውን ይይዛሉ። ሕንዳዊያን፣ ፊሊፒናውያን እንዲሁም ሌሎች የእስያ አገራት ዜጎች ኑሯቸውን በኳታር ይመራሉ።
ከዚህ ባሻገር በርካታ ኢትዮጵያዊያን፣ ኤርትራዊያንና ኬንያዊያን በዋና ከተማዋ ዶሃ እንዲሁም በአር ራያን ይገኛሉ።
በነዳጅ ሃብት የበለፀገችው ኳታር፤ እነሆ በአረቡ የዓለም ሲዘጋጅ የመጀመሪያው የሆነውን የዓለም ዋንጫ በማስተናገድ ላይ ትገኛለች።
ቶለመ
“ኢትዮጵያዊያን የሥራ ሰዎች ናቸው ይባላሉ”
ግሩም፤ ካሜሩን ከሰርቢያ የሚያደርጉትን የቀን 7 ሰዓት የምድብ ጨዋታ ታድሞ ለመዘገብ እየተጓዘ ሳለ ነው በስልክ ያገኘነው። በየገባህበት ሥፍራ ሁሉ የአየር ማጤዣ ተገጥሟል የሚለው ግሩም፣ ይህ ቴክኖሎጂ ባይኖር ኖሮ ኳታር ለኑሮ ከባድ ትሆን እንደነበር ይናገራል።
“አሁን ለምሳሌ በአገሩ ሰዓት አቆጣጠር 5 ሰዓት ከምናምን ነው። እኛ አገር ግንቦት ወር ላይ ያለው የሚያማርረው ሙቀት ነው አሁን እዚህ ያለው።”
ግሩም የኳታር ነዋሪዎችን ስለ አየር ሁኔታው ሲጠይቃቸው፤ “በብርድ ወቅት መጣህ” በሚል ዓይን እያዩት፤ “ኧረ እንዲያውም ይሄ እኮ ቀዝቃዛው ጊዜ ነው” ይሉታል።
ኳታር፤ ለዚህ ነው ይህንን ወቅት ለዓለም ዋንጫ የመረጠችው እንጂ ለወትሮው የዓለም ዋንጫ በሰኔ ነበር  የሚዘጋጀው።
ከፋርስ ባሕረ ሰላጤ የሚነሳው ነፋስ፣ የኳታር ምሽትን ቀዝቀዝ አድርጎታል።
ኳታር፤ ይህን የዓለም ዋንጫ ስታዘጋጅ ከምዕራቡ ዓለም ከፍተኛ ተቃውሞ ደርሶባት ነበር። አገሪቱ የሰብዓዊ መብት አይከበርባትም፣ ስታድየሞቹ ሲታነፁ በርካታ የጉልበት ሠራተኞች ሞተዋል፣ የአየር ሁኔታው ምቹ አይደለም. . . ብቻ ብዙ ነቀፋ አስተናግዳለች።
ነገር ግን ጋዜጠኛ ግሩም፤ ይህ ነቀፋ ተጋኗል የሚል እምነት አለው። “የኳታር ዜጎች በጣም ሰላምተኞች ናቸው። እንግዳ ተቀባይነታቸውን ማየት ችያለሁ። በአረቡ ዓለም መዘጋጀቱ የአረቡ የዓለም ለእግር ኳስ ያለውን ፍቅር ለማሳየት ልዩ አጋጣሚ ነው” ይላል።
ኻሊፋ ኢንተርናሽናል ስታዲየም
እንደሱ አመለካከት፤ ዶሃ ወደፊት ልክ እንደ ዱባይ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚመጡ ጎብኚዎች የምታስናግድ መናኸሪያ እንደምትሆን አምነት አለው።
ግሩም፤ በዶሃ በተዘዋወረባቸው ቦታዎች በርካታ ኢትዮጵያውያን ኑሮን ለማሸነፍ በተለያየ ሥራ ተሠማርተው ሲተጉ አይቷል።
“ስታዲየሞች ውስጥ በጎ ፈቃደኛ ኢትዮጵያውያንን አግኝቻለሁ። አንድ የሥነ-ጥበብ ባለሙያ ኢትዮጵያዊም ተዋውቄያለሁ። በዓለም ዋንጫው ከትላልቅ የብሮድካስት ኩባንያዎች ጋር የሚሠራ ኢትዮጵያዊም ማግኘት ችያለሁ።”
ጋዜጠኛው ግሩም እንደሚለው፤ ከ20 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ኳታር ውስጥ ይኖራሉ።
ስለአገሪቱ የተለያዩ መረጃዎችን የሚያወጣው ‘ኦንላይን ካታር’ የተሰኘው ገፅ፤ ቢያንስ 25 ሺህ ኢትዮጵያዊያን እንደሚገኙ አስፍሯል።
“በቤት ሠራተኝነት የሚሠሩ አሉ። የሚማሩ አሉ። የሕንፃ ግንባታ ባለሙያዎች፤ የታክሲ ሾፌሮች አሉ። በርካታ የኢትዮጵያ ሬስቶራንቶች ያሉበት አንድ አካባቢ አለ። አዲስ አበባ የሚል ስያሜ ያለው ፀጉር ቤት አይቻለሁ። እኔ ከጎበኘኋቸው ሬስቶራንቶች በአንዱ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ተሰባስበው አይቻለሁ።”
“ኢትዮጵያውያን በኳታሮች ዘንድ ይከበራሉ።” የሚለው ግሩም፤ “የሥራ ሰዎች ናቸው ይባላሉ” ብሏል።
ጋዜጠኛ ግሩም ከዚህ ቀደም ወደ ደቡብ አፍሪካ እንዲሁም ሩሲያ ተጉዞ የዓለም ዋንጫን መታደም ችሏል። ነገር ግን የዶሃው በብዙ መልኩ እንደሚለይ ይገልጻል።
አንደኛው ምክንያት፤ ስታድየሞቹ የተቀራረቡ በመሆናቸው እሱና የሙያ አጋሮቹ በአንድ ቀን የተለያዩ ጨዋታዎችን መታደም መቻላቸው ነው።
ለምሳሌ በሩሲያው የዓለም ዋንጫ ከዋና ከተማዋ ሞስኮ ወደ ሶቺ ለመሄድ 72 ሰዓታትን በባቡር ተጉዞ ነበር።
ከዚህ በፊት ከተመለከታቸው የዓለም ዋንጫዎች በተለየ በምድብ ጨዋታዎች የታየው ፉክክር፣ የተመልካቾች ብዛትና የስታዲየሞቹ ልዩ ‘ዲዛይን’ ይህንን የዓለም ዋንጫ “ለየት አድርጎብኛል” ባይ ነው የአዲስ አድማሱ ግሩም ሰይፉ።

Read 11111 times
Administrator

Latest from Administrator