Saturday, 03 December 2022 12:33

Equalize-እኩል ማድረግ፡፡

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)


       የኤችአይቪ ኤድስ ስርጭት እንዳያበቃ የማያደርጉ አለመመጣጠኖችን በአለም ዙሪያ ያሉ የሰው ልጆች ሁሉ በአንድነት ሊያስወግዱ ይገባ ል፡፡  UNAIDS
Equalize- እኩል ማድረግ እ.ኤ.አ ዲሴምበር 1/ወይም ህዳር 22/ በየአመቱ የሚውለው የአለም ኤድስ ቀን የ2022/ መሪ ቃል ነው፡፡ የአለም ኤድስ ቀን በየአመቱ የተለያዩ መፈክሮች ወይም መሪ ቃሎች የሚኖሩት ሲሆን ለማስታወስም ያህል፡-
በ2021     አለመመጣጠን ያብቃ፤ ኤድስ ያብቃ፤ ወረርሽን እናስቁም የሚል ስሜት የነበረው ነው። 2020 አለምአቀፍ ትብብር፤ የጋራ ኃላፊነት የሚል ሀሳብ ነበር፡፡
2019   ማህበረሰቡ ለውጥ ያመጣል የሚል ነበር፡፡
2018 ያለህበትን ሁኔታ እወቅ የሚል መልእክት የነበረው ነው፡፡
ከላይ እንደተመለከተው የአለም ኤች አይቪ ቀን መከበር ከተጀመረበት እ.ኤ.አ ከ1988 ጀምሮ በየአመቱ የተለያዩ መሪ ቃሎች እየተሰጡት አልፎአል፡፡
የዘንድሮው (2022) Equalize ስያሜ የኤችአይቪ ወረርሽኝን ለማስቆም የሚረዱ ነገሮችን የሚያስቆሙ ወይንም የኤድስ ስርጭት እንዲቀጥል የማያደርጉ አለመመጣጠኖች በፍጹም ሊፈቀዱ የማይገባቸው እና መወገድ ያለባቸው መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ UNAIDS ባወጣው መረጃ በአለም ዙሪያ ሁሉም ለዚህ አላማ የድርሻውን መወጣት ይገባዋል ብሎአል፡፡
የአለም የኤድስ ቀን የተጸነሰው በመጀመሪያ በአለም የጤና ድርጅት (WHO) በአለም አቀፍ የኤችአይቪ ፕሮግራም የመረጃ ኦፊሰሮች በነበሩት James W. Bunn and Thomas Netter እ.ኤ.አ በ1987 በጄኔቫ ስዊዘርላንድ ሲሆን በአለም ዙሪያ መከበር የጀመረው December 1/ 1988 ነው::
እ.ኤ.አ የ2022/ እኩል አድርግ የሚለው መፈክር ወይንም መሪ ቃል ለድርጊት የሚጋብዝ ነው፡፡ ይህ ለተሻለ ስራ የሚጋብዝ፤ ከኤድስ ጋር በተያያዘ አለመመጣጠንን ለማስቀረት የሚቻለው ሁሉ እንዲደረግ የሚጋብዝ ነው፡፡
ምቹ ሁኔታን፤ ጥራት እና ተስማሚ የሆነ አገልግሎት ለኤችአይቪ የህክምና አገልግሎት፤ እራስን ለማወቅ የሚደረጉ ምርመራዎች እና መከላከል ላይ አተኩሮ ሁሉም ተገቢውን እርዳታ እንዲያገኝ ማድረግን እስከአሁን ከነበረው አሰራር በተጨማሪነት ለማቅረብ ያስችላል፡፡
ህጎች፤ ፖሊሲዎች እና የኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ያለባቸው ሰዎች ላይ የሚፈጸምን አድሎና መገለልን ለማስቆም እና እነዚህን ሰዎች ሁሉም ሰው በሚገባቸው ወይንም ሰው በመሆናቸው የሚገባቸውን ክብር ሰጥቶ እንዲያስተናግዳቸው የማድረግ ኃላፊነት በአለም ዙሪያ የሁሉም ሰው ድርሻ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡
በአለም ዙሪያ የሚፈጠሩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ኤችአይቪን ለማብቃት እስከረዱ ድረስ በአለም ያሉ ህዝቦች ሁሉ በተመሳሳይ በእኩልነት እንዲጠቀሙባቸው ለማስቻል በመተባበር፤ አንዱ ለአንዱ ማቅረብ ይገባል፡፡
በአለም ላይ መላው ህዝቦች Equalize እኩል ማድረግ የሚለውን መፈክር ወይንም መሪ ቃል ለመጠቀም ዝግጁነቱን እንዲያሳይ ይጠበቃል። ለዚህም “Equalize” የሚለውን መልእክት ለመጠቀም የማያስችላቸው አለመመጣጠን በገጠማቸው ጊዜ ይህንን መረጃ ለሚመለከተው አካል መጠቆም ይጠበቅባቸዋል፡፡
ባለፉት ሁለት አመታት በተፈጠሩ የተለያዩ ሁኔታዎች በተለይም በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት የኤችአይቪን ስርጭት ለመግታት በመሰራት ላይ የነበረውን እንቅስቃሴ ወደሁዋላ መጎተቱ እሙን ሲሆን በአለም ዙሪያ ኤችአይቪን በሚመለከት ትክክለኛ መረጃዎችን ለማግኘት የሚያስችሉ ስራዎች ተሰርተዋል ለማለት አያስደፍርም እንደ UN መረጃ፡፡
መረጃው በማከልም በአፍሪካ ያሉ ወጣት ሴቶች ኤችአይቪን በሚመለከት ተገቢውን መረጃና አገልግሎት ባለማግኘታቸው በኤችአይቪ ኤድስ መጠቃታቸው በገሀድ እየታየ ነው፡፡ በተለይም ኑሮአቸው በጣም ዝቅተኛ በሆኑ 19 የአፍሪካ አገሮች በኤችአይቪ ላይ ያተኮረ ፕሮግራም ተዳክሞአል ማለት ይቻላል፡፡ ኤችአይቪን በመከላከሉ ረገድ በእነዚህ የአፍሪካ አገራት ውስጥ ሴት ታዳጊዎች እና ልጃገረዶችን በሚመለከት ከፍተኛ የኤድስ ስርጭት ባለባቸው ቦታዎች ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ፕሮግራሞች 40% ያህል ብቻ ናቸው፡፡
አለም ኤችአይቪን ለማብቃት የተስማማበት 2030 የቀረው ስምንት አመት ብቻ ነው። ከኢኮኖሚው፤ ማህበራዊ፤ ባህላዊ እና በይፋ የሚታየው አለመመጣጠን በአስቸኳይ መልስ ማግኘት ያለባቸው ናቸው፡፡ ለቫይረሱ ስርጭት አለመመጣጠን ከፍተኛው አደጋ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ስለዚህም የኤችአይቪ ስርጭት ያበቃል ተብሎ የሚታሰበው አለመመጣጠን ሲወገድ ነው በሚለው ሁሉም ሊስማማ እና ሊተገብረው ይገባል፡፡ ስለዚህም የአለም መሪዎች ይህንን አላማ ተግባራዊ ለማድረግ ለማስፈጸም አቅም ካላቸው እና በኃላፊነት ከሚሰሩ የአመራር አካላት ጋር አብረው መስራት ይጠበቅባቸዋል። በተረፈ ሁሉም ሰው በየትም ቦታ ኤችአይቪን በመከላል ረገድ ሁሉንም በእኩልነት ማገልገልን፤ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝባቸውን ሰዎች ሰብአዊ ክብር ሰጥቶ ማስተናገድን፤ እራስን አስቀድሞ ማወቅን፤ ባጠቃላይም የሚጠበቅብንን ሁሉ በማድረግ ለኤችአይቪ መወገድ አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅብናል ብሎአል UNAIDS፡፡
በየአመቱ የሚከበረው የአለም ኤድስ ቀን ሁልጊዜም የተለየ መፈክር ወይንም መሪ ቃል ይዞ እንደሚወጣ የታወቀ ነው፡፡ የዚህ አመት መፈክርም እኩል አድርግ የሚል ነው፡፡ ይህንን UNAIDS በአለም ዙሪያ ያለ ሰው ሁሉ እንዲፈጽመውም ይጠበቃል፡፡ የዘንድሮው መፈክር በአለም ዙሪያ ያሉ ሰዎችን በአንድነት እንዲቆሙ እና ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ ያስችላል ተብሎ ይታመናል፡፡
እ.ኤ.አ በ1988 የተጀመረው የአለም የኤድስ ቀን በአለም አቀፍ ደረጃ የጤና ቀን ተብሎ ሲሰየም የመጀመሪያው ነበር ይላል መረጃው። እለቱን በሚመለከትም በየአመቱ የተባበሩት መንግስታት ወኪሎች፤ የአለም መንግስታት እና ሲቪል ማህበረሰቡ በአንድነት በመሆን ለቀጣይ አመት ልዩ ትኩረት የሚያሻውን መፈክር ወይም መሪ ቃል ከኤች አይ ቪ ጋር በተያያዘ ያወጣሉ፡፡ በዚህ ተመስርቶም፡-
በአለም አቀፍ ደረጃ የኤችአይቪን ቫይረስ በመከላከል ረገድ ንቃተ ህሊናን ለማዳበር፤  
ብዙ ሰዎች በደረታቸው ላይ ቀይ ሪቫን በማድረግ አለምአቀፍ ምልክቱን በማሳየት በጋራ ኤችአይቪ ኤድስን መከላከል እንደሚገባ እና ጥምረትን በመፍጠር ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ያለባቸውን ሰዎች በምን መልክ መርዳት እንደሚገባ እንዲታሰብ ማድረግ፤
የኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ያለባቸው ሰዎች በጥንካሬ ድምጻቸው እንዲሰማ ማድረግና አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እንዲሁም ሕይወታቸውን ለመቀጠል አስፈላጊ ስለሆኑት ነገሮች በአደባባይ ወጥተው ለወደፊት ለተሻለ አሰራር ሀሳባቸውን እንዲያጋሩ፤ እንዲናገሩ፤ እንዲመሰክሩ ማስቻል፤
ኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ የሚኖር ሰዎች በቡድን ሆነው ከሌሎች በኤድስ ላይ ከሚሰሩና ከሚመለከታቸው ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ድጋፍ የማሰባሰብ ስራዎችን እና ህብረተሰቡ በጉዳዩ ላይ በቂ እውቀት እንዲኖረው ማድረግ፤
ወረርሽኙ ያለበትን ደረጃ አጉልተው የሚያሳዩ የተለያዩ አጋጣሚዎችን ተጠቅሞ ጎጂነቱን ማጉላት የመሳሰሉትን እድሎች ይፈጥራል፡፡


Read 10607 times