Saturday, 03 December 2022 12:09

“እግር ኳሱን ‘ቦተለኩብን!’”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ... የሰላም፣ የወንድማማችነት፣ የህዝቦች መቀራረቢያ ሲባል የኖረውን እግር ኳስ ቦተለኩብንና አረፉት! እኮ፡፡ የምር እኮ በአንድ በኩል የኳስ ጥበብ በ‘ቦተሊካው’ እየተዋጠ ሲመስል ያሳዝናል፡፡
እኛ ዘንድ በወዲያኛው ዘመን እንትናና እንትና ቡድኖች (መለዮ ለባሾችና ሲቪሎች ማለትም ይቻለል) ሲጫወቱ  በዚያኛው ወገን  “ይናዳል ገደሉ! ይናዳል ገደሉ!” ሲባል፣ በዚህኛው ወገን ደግሞ “እኛው ነን! እኛው ነን!” ይባል ነበር፡፡ 
እናማ...ግራ ተጋባን፡፡ ‘ቦተሊካው’ ምን ያህል ስፖርቱን እየተጫነው እንደሆነ ከአሜሪካና ኢራን ቡድኖች ጨዋታ የተሻለ ማሳያ አይኖርም። አሀ...ስለ እግር ኳስ ታሪክም ሆነ ህጎች ቤሳ ቤስቲን የማያውቁትን የአሜሪካ ጋዜጠኞችና ‘ተንታኞች’ ብትሰሟቸው እኮ የሀገራቱ ቡድኖች ለእግር ኳስ ግጥሚያ በሰላም ሜዳ ላይ የሚገናኙ ሳይሆን ኑክሌር ምናምን የተማዘዙ ነበር ያስመሰሉት፡፡
እግር ኳሱን ‘እየቦተለኩብን’ ነው! የአውሮፓ ሀገራት ደጋፊዎች “ብሄራዊ ቡድናችን ተሸነፈ፣” ብለው ከተማቸውን ሲቀውጡ፣ ዘንድሮ እንጂ መች አይተን እናውቃለን! የቤልጂግ ብሄራዊ ቡድነ ተሸነፈ ተብሎ አይደል ብረስልስን ያመሷት! ለነገሩ ነውጠኞቹ ገሚሶቹ በውጤቱ በሽቀው ሲሆን፤ ሌሎቹ ደግሞ በዛች ሀገር ባሉ ሞሮካውያን ጭፈራ ‘ክሬዚ’ ሆነው ነው ይባላል። እዛች ሀገር  ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ የሞሮኮ ተወላጆች አሉ ነው የሚባለው። እነ አርሴና ማንቼ መቆራቆስ ባቆሙበት፣ ብሄራዊ ቡድን ተሸነፈ ተብሎ ረብሻ! እንደውም ከሽንፈቱ በኋላ የተወሰኑ ተጫዋቾች መልበሻ ቤት ሊፈሳፈሱ በመከራ ተገላግለው ነው አሉ፡፡
ስሙኝማ...ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...ስለ መልበሻ ቤት ውዝግብ ሲነሳ የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ሳናወራት አንቀርም። ‘በወዲያኛው ዘመን’ ነው፡፡ ሁለት ሀያላን ቡድኖች ውጤቱ በሌሎች ቡድኖች ላይ ጫና ሊያሳድር የሚችል ግጥሚያ ነበራቸው፡፡ እና ይወራ እንደነበረው እኩል ለእኩል ለመውጣት ሳይስማሙ አልቀረም፡፡ በቃ...አለ አይደል... “እኛም አናገባም፣ እናንተም አታግቡ፣” አይነት ነገር፡፡ እኩል ለእኩል ውጤቱ ቡድን ‘ሀ’ን የሚጠቅም ሲሆን፣ ቡድን ‘ለ’ ላይ ምንም አይነት ለውጥ አያመጣም፡፡ እናላችሁ... አንድ የቡድን ‘ለ’ ታዋቂ ተጫዋች መሀል ሜዳ ሊባል ምንም ከማይቀረው እርቀት ኳሷን የፈለገችበት ትሂድ አይነት ድብን አድርጎ ሲመታት ምን ብትሆን ጥሩ ነው....የክፍለ ዘመኑ ልትባል የምትችል አሪፍ ግብ! እናም...መስተካከል ነበረበት፡፡
ጥቂት ቆይቶ የቡድን ‘ሀ’ አንዱ የዘመኑ አሪፍ አጥቂ፣ ኳስ ‘እየፈጠረ’ ወደ ግብ ሲገሰግስ በ“አላየንም፣ አልሰማንም!” ዓይነት ‘አሳለፉት፡፡’ እናም... በረኛው ጋር ተፋጠጠ፡፡ በረኛው ደግሞ የዘመኑ ምርጡ በረኛ ነበር፡፡  አጥቂው አንድ ለክፉ የማትሰጥና  የመጨረሻው ቀሺም በረኛ ላፍ ሊያደርጋት የምትችል  ኳስ በዚህ በኩል ለከፍ ያደርጋል፡፡ መግባት ስላለባት በረኛው በወዲያኛው በኩል ወደቀላችኋ! የቡድኑ ደጋፊዎች በብሽቀት አድርገው የማያውቁትን አርማውን ቡን ነው ያደረጉት፡፡
እናላችሁ...መልበሻ ቤት ያቺን ጦሰኛውን ግብ ያገባው አጥቂና ያቺን ጦሰኛዋን ኳስ የለቀቀው በረኛ ሊደባደቡ በመከራ ነው የገላገሏቸው፡፡ ለታሪክ ያህል ነው፡፡
እኔ የምለው... ይሄ ተስማምቶ መልቀቅ የሚባለው ነገር አሁንም ኳሳችን ውስጥ ተደጋግሞ ይከሰታል የሚባል አሉባልታ ነገር አለ፡፡ በበፊተኛው ጊዜ የእግር ኳስ ቡድኖች፣ በቃ እግር ኳስ ቡድኖች ናቸው፡፡ ግፋ ቢል የወታደርና የሲቪል የሚል ነገር ይኖር እንደሁ ነው፡፡ ዘንድሮ እኮ ነገሩ የሚጀምረው ገና ከብዙዎቹ መጠሪያ ስም ነው፡፡ ይህንን እንኳን ማስተካከል ያቅተን!
በነገራችን ላይ...በአንድ ወቅት የኢራቅ ቡድን ተሸንፎ ሀገራቸው ሲገቡ ወፌ ምናምን ገለበጧቸው የሚባል ታሪክ አለ፡፡
እናማ ምን ለማለት ነው፣ ዘንድሮ እግር ኳሱን “ቦተለኩብን!”
ፖርቱጋልና ኡራጋይ ሲጫወቱ በብሩኖ ፌርናንዴስ ስም የተመዘገበችውን ግብ “የለም ሮናልዶ ነው በጭንቅላት ጨርፎ ያገባት” የሚል ንትርክ ይዘውላችኋል፡፡ አንደኛው ወገን  ኳሷ ውስጥ የተገጠመው ቴክኖሎጂ ሮናልዶ አለመንካቱን ያሳያል ሲሉ፣ በሌላው ወገን ደግሞ የ‘ስሎው ሞሽን’ ካሜራዎች መንካቱን ያሳያሉ እያሉ ሲወዛገቡ ነው የሰነበቱት፡፡ ኮሚክ እኮ ነው...ቡድኑ አሸንፎ ወጥቶ የለም እንዴ! የምን ንትርክ ነው! ስሙኝማ...ተቺና ትችት የበዛበት ሮናልዶን “ዘለዓለምህን እዩኝ እዩኝ እያልክ!” ምናምን እያሉ እየወረዱበት ነው፡፡ ግንማ...እንግዲህ ጨዋታም አይደል... ‘ሲ አር 7’ ምነዋ ጠላት በዛበትሳ! ነገሩ ሁሉ እኮ “ሲያልቅ አያምር!” አይነት እየሆነ ይመስላል፡፡
እናማ... የአሜሪካንና ኢራን ጨዋታ የተፈራውን ብጥብጥ አለማስነሳቱ ሸጋ ነው፡፡ እንደ ዘገባዎች ከሆነ ለእግር ኳስ ይችን ታክል ስሜት የሌለው ሁሉ  ቴሌቪዥን ፊት ተኮልኩሎ ነበር ይባላል፡፡ እና የሜዳ ውስጥ ውዝግብ የተፈራውን ያህል ባይሆንም አልጠፋም። ፑሊሲች ግቧን ሊያስቆጥር ሲል ደርሶባት የነበረው የመጨረሻው ተከላካይ ተጎትቶ የወደቀ ስለሆነ ፍጹም ቅጣት ምት ይገባናል ብለው ነበር፤ ዳኛው ፍጹም ቅጣት ምቱን አለመስጠታቸው ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ብዙ ትችቶች ሲያስከትልባቸው ነው የሰነበተው። “ተከፍሎት ነው!” “የእስራኤል ሰላይ ነው!” ምን ያልተባሉት ነገር አለ፡፡ ስፔናዊው ዳኛ ግን ከዓለም ምርጦቹ አንዱ ስለመሆናቸው የእግር ኳስ ‘ቦተሊካ’ ጉዳዩ አይደለም፡፡
ስሙኝማ... ፑሊሲች ተንሸራቶ ያገባትን ግብ አንዳንድ የአሜሪካ ሚዲያዎች ምን እያሉ ቢገልጹት ጥሩ ነው...“ጀግናው ፑሊሲች አካሉን ለመስዋት አቅርቦ...” ምናምን፡፡ ኸረ በህግ! ከጨዋታው በፊት ጀምሮ ሲዘግቡ የሁለቱ ሀገራት የእግር ኳስ ቡድኖች የሚገጥሙ ሳይሆኑ ኑክሌር የተማዘዙ ነው ያስመሰሉት፡፡
ታዲያላችሁ.... ከሌሎቹ ግጥሚያዎች አንዱንም እንኳን ያላየውን ጨምሮ ያ ሁሉ ሚሊዮን ህዝብ ቴሌቪዥን ፊት የተኮለከለው ይህን ያህል ቁጭ፣ ብድግ የሚያስደርግ ችሎታ ስላላቸው ሳይሆን፣ ምን ይፈጠር ይሆን ተብሎ የሆነ ‘የሜዳ ላይ ጉድ’ እንዳያመልጥ ነው። ምን እንዲፈጠር ጠብቅን እንደነበር አንድዬ ይወቅ፡፡ በነገራችን ላይ ዳኛው አብዛኛውን ጊዜ የሁለቱንም ቡድኖች ተጫዋቾች ከፊታቸው ፈገግታ ሳይጠፋ እያናገሩ፣ ጨዋታውን የተቆጣጠሩበትን ዘዴ ዝም ብሎ ማለፍ ትክክል አይሆንም፡፡  
ታዲያላችሁ... እኛም ሀገር ለሁለቱ ቡድኖች የነበረው ድጋፍ በአብዛኛው ከኳስ ችሎታ ጋር የተያያዘ ሳይሆን በወዳጅነትና ጠላትነት ፍረጃ አይነት ነበር፡፡ አማሪካን ኩም እንድትል ይፈልግ የነበረው ሰው ብዛት፣ እውነትም የባይደን ሀገር፣ እዚህ አካባቢ ምን ያህል ወዳጅ እያጣች እንደሆነ ሳይጠቁም አይቀርም፡፡ አንድ ከአትላንቲክ ማዶ ያለ የሀገራችን ሰው፣
አሜሪካውያን ወዳጆቹ፤ “ጨዋታውን አብረን እናያለን፣” ይሉታል፡፡ እሱም “አይ ከእናንተ ጋር አላይም፣” ይላቸዋል፡፡ ለምን እንደሆነ ሲጠይቁት ምን ቢላቸው ጥሩ ነው...“ኢራን ስታገባ ስጨፍር ተሰብስባችሁ ልትቀጠቅጡኝ ነው!”
ስሙኝማ... እኛ በእነሱ አፍ ጭምር “ፉትቦል” የምንለውን እነሱ ‘ፉትቦል’ አይሉትም። ይልቁንም “ሶከር“ ብቻ ነው የሚሉት! ያኛውን ለራሳቸው ብቻ አድርገው “አሜሪካን ፉትቦል፣” ይሉታል፡፡ የእነሱ ዘመድ ፉትቦል፣ ባስኬትቦልና ቤዝቦል ናቸው ይባላል፡፡ እግር ኳስ እንደነሱ ፉትቦል መሬት አንቀጥቃጭ አካላዊ ግጭት፣ መቆራቆስና ብሎም በየመሀሉ ዝሆን በሚያካክሉት ተጫዋቾች መሀከል  ጠብ ቢጤ ማየት ያረካቸዋል ነው የሚባለው፡፡ ከሁለት አስርት በፊት ሀገራቸው ላይ የዓለም ዋንጫ በተካሄደ ጊዜ፣ ጎል ከሚገባ ይልቅ ኳሷ ማእዘኖቹ ላይ ተንገጫግጫ ስትመለስ ነው ደስ የሚላቸው ይባል ነበር፡፡
እናላችሁ... ስፖርት መከታተል አንዱ ከፖለቲካ ንትርክ ማምለጫ ነው ይባል ነበር፡፡
“አንተ በቃ ዝም ብለህ ቅሪላ ማየት ብቻ ነው! ሀገሪቱ ውስጥ ስንት ፖለቲካ እየተካሄደ...”
“ስማ፣ ፖለቲካችሁን ያዙና እዛው!” ይባል ነበር፡፡ አሁን እግር ኳሱንም ‘ቦተለኩብን!’ እነ እንትና...ግን ለአሜሪካኖቹ ቁጭ፣ ብድግ ስትሉ የነበረው በጤናችሁ ነው! ቂ...ቂ...ቂ....!
ደህና ሰንብቱልኝማ!



Read 1346 times