Saturday, 03 December 2022 12:05

ህውሓትን ትጥቅ ለማስፈታት የተሰጠው ቀነ ገደብ ተጠናቋል

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(4 votes)

  በትጥቅ ማስፈታት ዙሪያ በሽሬ ከተማ እየተካሄደ ያለው ውይይት ዛሬ ይጠናቀቃል
               
       በመንግስትና በህውሃት ታጣቂ ሃይሎች መካከል በደቡብ አፍሪካ መዲና ፕሪቶሪያ የተደረገውና ህውሐትን በ30 ቀናት ውስጥ ትጥቅ ያስፈታል የተባለው የሰላም ስምምነት ከተፈረመ ትናንት 30 ቀናት ሞለቶታል፡፡ በስምምነቱ መሰረት፤ የህውሃት ታጣቂ ሃይሎች ሙሉ በሙሉ ትጥቃቸውን በመፍታት ወደተዘጋጀላቸው ካምፕ መግባት የነበረባቸው ቢሆንም፤ እስከአሁን ግን ትጥቅ የማስፈታቱ ሂደት አለመጀመሩ ታውቋል።
በአፍሪካ ህብረት በተመራው የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት፤ የህውሃት ታጣቂ ሃይሎች ስምምነቱ በተደረገ 30 ቀናት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ትጥቃቸውን መፍታት ይኖርባቸዋል፡፡
በደቡብ አፍሪካው ፕሪቶሪያ ከተማ ለ10ቀናት ሲካሄድ በቆየው የሰላም ድርድር፤ መንግስትና የህውሃት ታጣቂ ሃይሎች በ12 ነጥቦች ላይ ከስምምነት መድረሳቸው ይታወቃል። ይህንኑ የሰላም ስምምነት ተከትሎ ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ የሰላም ድርድሩ በስኬት መጠናቀቁንና ኢትዮጵያ ያቀረበቻቸው ሃሳቦች መቶ በመቶ ተቀባይነት ማግኘታቸወን በመግለጽ ለህዝቡ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈው ነበር። ከዚህ በማስከተል ጥቅምት 28 ቀን 2015 ዓ.ም መንግስትና የህውሃት ከፍተኛ የጦር አመራሮች በኬንያ ናይሮቢ ተገኝተው የሰላም ስምምነቱን የማስፈጸሚያ አንዱ አካል በሆነው ትጥቅ የማስፈታቱ ጉዳይ ዙሪያ ሲነጋገሩ ሰነበቱ። በዚህ ንግግር ላይ ተሳታፊ የነበሩት የህውሃት ሃይሎች ዋና አዛዥ ጀነራል ታደሰ ወረደ ለትግራይ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ፤ ስለሰላም ስምምነቱ ለታጣቂዎቻቸው የማስረዳቱ ተግባር እየተገባደደ መሆኑን በመጠቆም ሰራዊታቸው ተቆጣጥሯቸው ከሚገኝባቸው አካባቢዎች መውጣት እንሚጀምር ገልጸው ነበር።
በሌላ በኩል ደግሞ የህውሃት ቡድን ቃል አቀባዩ አቶ ጌታቸው ረዳ፤ የኤርትራ ሃይሎችና የአማራ ልዩ ሃይል የትግራይን ምድር ለቀው ካልወጡ በስተቀር ትጥቅ የማስፋታቱ ጉዳይ የማይታሰብ ነው ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።
የሚኒስትሮቹ ምክር ቤት ህዳር 3 ቀን 2015 ባካሄደው 15ኛ መደበኛ ስብሰባው፤ ትጥቃቸውን የሚፈቱ የህውሃት ሃይሎች ወደ ማህበረሰቡ በዘላቂነት እንዲቀላቀሉ ለማስቻል ብሄራዊ የተሀድሶ ኮሚሽን ለማቋቋም ውሳኔ ላይ ደረሰ።
በዚሁ ቀን ደቡብ አፍሪካ ላይ  የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ዝርዝር አተገባበርን የሚመለከት ሰነድ፣ በመንግስትና በህውሃት ከፍተኛ የጦር አመራሮች መካከል በኬንያ  ናይሮቢ ተፈረመ። ይህንኑ ተከትሎም ህዳር 6 ቀን 2015 ዓ.ም አለም አቀፍ የቀይ መስቀል ማህበር ምግብና መድሃኒት የጫኑ ተሸከርካሪዎች የትግራይ ክልል መዲና በሆነችው መቀሌ መድረሳቸውን ይፋ አደረገ።
በሰላም ስምምነቱ መሰረትም የትግራይ ሃይሎች ከተሰለፉባቸው ግንባሮች የማስወጣቱ ሂደት እንደሚጀመር ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ ተናገሩ። ሰራዊቱን አጓጉዞ ወደ ትክክለኛው ስፍራ እንዲገባ የማድረጉ ስራ በሁለትና ሶስት ቀናት ውስጥ ይጀመራል ሲሉም ገለጹ።
በሰላም ስምምነቱ መሰረት መሰረታዊ አገልግሎቶችን፤ እንዲጀምሩ ለማድረጉ በትጋት ሲሰራ መቆየቱን የገለጸው መንግስት በክልሉ የኤሌክትሪክና ስልክ አገልግሎት፣ የምግብና መድሃኒት አቅርቦቶችን በማስጀመሩ ተግባር ላይ ሲሰራ መቆየቱን በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎችም አገልግሎቱ እንዲጀመር ማድረጉን ገለጸ። በክልሉ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ኤሌክትሪክ ሃይል አገልግሎትን ለማስቀጠልም ጥረት እያደረገ መሆኑን መንግስት አስታወቋል። ስምምነቱ ከተፈረመበት ቀን ጀምሮ ባሉት 30 ቀናት ውስጥ ተግባራዊ መሆን እንደሚገባው የተጠቀሰው የህወሃት ታጣቂ ሃይሎችን ትጥቅ የማስፈታቱ ጉዳይ ተግባራዊ ማድረግ አለመጀመሩ ግን ግርታን ፈጥሯል። ታጣቂዎቹ ትጥቅ የሚፈቱበትን ዝርዝር ዕቅድ የሚሰራና ትጥቅ የማስፈታቱን ሂደት ተግባራዊ የሚያስደርግ የሁለቱ ወገኖች የባለሙያዎች የጋራ ኮሚቴ ካለፈው ረቡዕ አንስቶ ሽሬ ላይ እየመከረ ይገኛል። ይኸው የጋራ ኮሚቴ በዛሬው እለት ስራውን ያጠናቅቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ምንጮች ጠቁመዋል።
ይህ በዚህ እንዳለ ሰሞኑን በመቀሌ ከምሽጋቸው እየወጡ ቦታውን ለመከላከያ ሰራዊት በማስረከብ ሂደት ላይ የነበሩ የሕወሃት ወታደሮች  እንደተናገሩት፤ ለትግራይ ህዝብ ሰላም ሲሉ ትጥቃቸውን ለመፍታት ሙሉ በሙሉ ፈቃደኛ ናቸው። የትግራይ ህዝብ የሰላም ፍላጎትን በማክበርም ትጥቅ እንደሚፈቱ ነው የተናሩት።

Read 12376 times