Saturday, 03 December 2022 12:00

የኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ችግርና እልባት ያጣው የምስራቅ ወለጋው እልቂት

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(3 votes)

 - በዚህ ሳምንት ብቻ ከ100 በላይ ንፁሃን ተገድለዋል
      - በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳና በአካባቢው የሸኔ ቡድን በከፈተው ተኩስ ቁጥሩ በውል ያልታወቀ ሰው ተገድሏል
      - በክልሉ ወለጋ ዞኖች ብቻ ከ700 ሺ በላይ ነዋሪዎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል
      - የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሰራተኞች በሸኔ ታጣቂዎች ታግተዋል
        
        በኦሮሚያ ክልል  በተለይም በወለጋ ዞኖች የተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ  የፀጥታ ችግሮች፣ ህይወታቸውን የሚያጡና ከመኖሪያቸው የሚፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ነው። ሰሞኑን በክልሉ ምስራቅ ወለጋ  ዞን ጉትን  ከተማና አካባቢው በተከሰተ የፀጥታ ችግር፣ የልዩ ኃይል አባላትን ጨምሮ የ11 ሰዎች ሕይወት ማለፉንና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መኖሪያቸውን ለቀው መሰደዳቸው ታውቋል። የጉትን ወረዳ አጎራባች በሆነችው በኪረሙ ወረዳም ሠሞኑን በሸኔ ቡድንና በመንግስት ሃይሎች መካከል በነበረው ከፍተኛ ተኩስ፣ ቁጥሩ በውል ያልታወቀ ሰው መምቱንና ቤቶችም መቃጠላቸውን  ምንጮች ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል።
ምሥራቅ ወለጋ  ዞን ውስጥ እልባት አልባ ሆኖ የዘለቀው ግጭት ተባብሶ  በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ታጣቂዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ ግድያ ፈጽመዋል።  ባለፈው ሣምንት ቅዳሜ  ማታ በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ የታጠቁ  ሃይሎች በ24 ሰዎች ላይ የፈጸሙትን ግድያን ጨምሮ በዚህ ሣምንት ብቻ ከ100 በላይ ንጹሃን  ዜጎች በታጣቂዎች ተገድለዋል  ተብሏል።
ከምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ሀሮ ቀበሌ ተፈናቅለው በኪረሙ ወረዳ  ውስጥ ተጠልለው ከሚገኙ ተፈናቃዮች መካከል አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው አንድ ተፈናቃይ እንደሚናገሩት፣ የሸኔ ቡድን አባላት አካባቢውን ተቆጣጥረው  ከቆዩበት ካለፈው መስከረም ወር ጀምሮ በታጣቂዎች የሚፈፀመው ግድያና ማፈናቀል ተባብሶ ቀጥሏል። ነዋሪው እንደሚሉት፣ በዚህ ወረዳ የሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው አንጻራዊ ሰላም ወደሚታይባቸው አካባቢዎች  የተሰደዱ ቢሆንም፣ የእለት ተእለት ስጋቱ አሁንም አይሎ እንደቀጠለ ነው ብለዋል፡፡
ነዋሪዎቹ የተሰደዱባቸው አካባቢዎች ኤሌክትሪክና የተለያዩ ማህበራዊ መገልገያዎች የሌሉባቸው ሲሆን አሁንም ድረስ በታጣቂዎቹ የተከበቡ  በመሆናቸው ኑሮአቸውን የሰቀቀን እንዳደረገው እኚሁ አስተያየት ሰጪ ተናግረዋል።  “ሁላችንም ሌሊት አንተኛም። ቀንም አናርፍም፡፡ በብዙ አቅጣጫ ጥቃት ይከፈትብናል፡፡  ባዶ እጃችንን ከታጠቁ ሰዎች ጋር መፋለም አንችልም፤ ሞታችንን ተኝተን እንዳንጠብቅ ማለት እንጂ መንቃታችን ከምን ሊያድነን።
የተረጋጋ ሰላም ከራቀን ቆይቷል፡፡ መንግስት የሚባለው አካል ካለ ይድረስልን። እስከመቼ በዝምታ ይመለከተናል፤ እኛስ ዜጎቹ አይደለንም ወይ? ሲሉ ጠይቀዋል- ተፈናቃዩ። ከቤታቸው ሲወጡ 3 ልጆቻቸውንና ባለቤታቸውን ጭምር ይዘው የወጡ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ከአንድ ልጃቸው ጋር ብቻ  ዋዮ ጡቃ በተባለ ስፍራ እንደሚኖሩ ነግረውናል። ባለቤታቸውና ቀሪ ልጆቻቸው የት እንደሚገኙ እንደማያውቁም ገልጸዋል።
የምስራቅ ወለጋ ዞኗ  ኪረሙ ወረዳ  በሸኔ ታጣቂዎች ተደጋጋሚ ጥቃት የሚደርስባት ወረዳ ስትሆን  ከጥቅምት ወር መጀመሪያ አንስቶ ከአራት ጊዜ በላይ ጥቃቶች  ደርሰውባታል። በወረዳዋ  ጉትን  ከተማ  ከባለፈው ሳምንት አርብ ኅዳር 16 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ  ከበባውና ስጋቱ እየጨመረ በመምጣቱ  በሺ የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ቤታቸውን ጥለው ተሰደዋል።
ከዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች  የተፈናቀሉ ከ52ሺ በላይ  ሰዎች የሚገኙባት የምስራቅ ወለጋ ዞኗ  ኪረሙ ወረዳ ሰምኑን በተፈጸሙ ጥቃቶች በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል።  በወረዳው ከተማ የንግድና መኖሪያ ቤቶች መውደማቸውን እንዲሁም ጀነረተሮችና የተለያዩ ቁሳቁሶች መዘረፋቸውን ቤቶች መቃጠላቸውን ምንጮች ጠቁመዋል። በኪረሙ ወረዳ ውስጥ ከሚገኙት 19 ቀበሌዎች ውስጥ  ይኖሩ የነበሩ ተፈናቃዮች  ተጠልለው የሚገኙባት ወረዳ ናት።
በአካባቢው በማኅበረሰቡ ላይ የሚደርሱትን ጥቃቶች ለማስቆም የተወሰደ ምንም አይነት  እርምጃ አለመኖሩንም ምንጮች ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል። ይህ በእንዲህ እያለ  በርካታ ቁጥር ያላቸው የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሠራተኞች በክልሉ ምዕራብ ሸዋ ዞን አደአ በርጋ ወረዳ  በሸኔ  ቡድን ታጣቂዎች ታግተው ወዳልታወቀ ቦታ መወሰዳቸው ተጠቁሟል። ምንጮች ለአዲስ አድማስ እንደገለጹት ቁጥራቸው ከ30 በላይ የሆኑ የሲሚንቶ ፋብሪካው ሠራተኞች  ረቡዕ ኅዳር 21 ቀን 2015  ዓ.ም ማለዳ 12፡30 አካባቢ  በፋብሪካው አውቶብስ ሲጓዙ የነበሩ  የፋብሪካው ሠራተኞች በሸኔ ቡድኑ አባላት  ታግተዋል። ታጣቂ ቡድኑ የያዛቸውን የሲሚንቶ ፋብሪካ ሠራተኞች ለመልቀቅ በነፍስ ወከፍ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ጠይቋል ተብሏል። ታጣቂዎቹ ሰራተኞቹን የጫነውን ተሽከርካሪ ከተቆጣጠሩ በኋላ ከመካከላቸው ሴቶችና አዛውንቶችን ለይተው በመልቀቅ የተቀሩትን አፍነው መውሰዳቸው ተነግሯል። ታጣቂ ቡድኑ በተለያዩ ጊዜያት ንጹሀን ዜጎችን በማገት ከ100 ሺ ብር እስከ 1 ሚሊዮን ብር የእገታ ማስለቀቂያ ገንዘብ የሚጠይቅ ሲሆን፤  ከጥቂት ወራት በፊት በተመሳሳይ ሁኔታ  የሙገር ሲሚንቶ ሠራተኞችን አግተው ማስለቀቂያ ገንዘብ በመቀበል እንደለቀቋቸው የሚታወስ ነው ።
በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በዜጎች  ላይ የሚፈጸሙና ማንነትን መሰረት ያደረጉ  ጥቃቶችን ለማስቆም  በመንግሥት በኩል የተወሰደ እርምጃ አለመኖሩ ግራ እንዳጋባቸው የሚገልጹ ወገኖች፤ “መንግስት ችግሮች ባሉባቸውአካባቢዎች  በመግባት ሁኔታውን ለመቆጣጠር የሚያስችል አቅም ቢኖረውም ፍላጎቱ ግን ያለው አይመስልም” ሲሉ ይናገራሉ።
በኦሮሚያ ክልል በተለይም በደቡባዊና በምዕራባዊ ክፍሎች ውስጥ የሚታየው ቀውስ ላለፉት 4 ዓመታት የቀለቀ ሲሆን በሰላም እጦት ምክንያት በወለጋ ዞኖች ከ7 መቶ ሺ በላይ ሕዝብ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሎ በተለያዩ አካባቢዎች እንደሚገኝ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት (UNOCHA) በቅርቡ ያወጣው መረጃ አመልክቷል።

Read 11465 times