Monday, 28 November 2022 16:56

የአንተነህ ህያው ገጸባህሪያትና “ምልጃ”

Written by  አብዲ መሐመድ
Rate this item
(2 votes)

 (ክፍል አንድ)
ቀደም ሲል.. ገጣሚ አንተነህ አክሊሉን በሥራዎቹ አውቀዋለሁ፡፡ ቢያንስ ለአስር አመታት ያህል በተለያዩ ጋዜጣና መጽሄቶች ላይ ልዩ ልዩ ይዘት ያላቸው ጥበብ-ነክ ጽሁፎችን፣ ግጥሞችን፣ ሂሳዊ ትንታኔዎችን ሲያቀርብ ተከታትዬ አንብቤለታለሁ፡፡ ነባሮቹን አቆይተን ከቅርቡ ብናነሳ እንኳን አንድ ወቅት ላይ ብቅ ብላ ከህትመት የተሰወረችው “አለላ” መጽሔት ላይ በአምደኝነት “ህያው ምናቦች” በሚል ንዑስ ርዕስ ስር፣ በተከታታይ ዝነኛ የምድራችን ፈርጥ ደራሲያን እጹብ ድንቅ ስራዎችና ፈጠራዎችን ተንተርሶ ግሩም ምልከታዎቹን አስነብቧል፡፡ አዲስና አንድ እርምጃ ወደፊት የቀደመ የገጸባህሪ አተያዩንና አረዳዱን አጋርቷል፡፡ አይረሴና ህያው የሆኑ ገፀባህሪያትን አጉልቶ በማሳየት ተንትኗል፤ ከውጭ ከሶመርሴት ሞም፣ከኤዲጋር አላንፖ፣ ከጊዶ ሞፖሳ፣ ከአሌክሳንደር ዱማስና ከሌሎችም ሥራዎች እየመዘዘ፡፡ ከሀገራችን ደግሞ ከፍቅረማርቆስ ደስታ፣ ከበአሉ ግርማ፣ ከሀዲስ አለማየሁ ... ለአብነት የሚጠቀስለት ነው፡፡ እነዚህን ፈርጥ ደራሲያን ስራዎቻቸውን ያነበብነው ገና በአፍላነት እድሜ ላይ እንደመሆኑ ከገጸባህሪያቶቹ ጋር ያለን አብሮነትና ትዝታ በሂደት የሚዘነጋ እንጂ ዘመናችንን ሙሉ አብሮን የሚቀር አልነበረም፡፡ ለአንተነህ ግን እንዲያ አይደሉም፤ ገጸ ባህሪያቶቹን ያወቃቸው በእናት ቋንቋቸው አንብቦ እንጂ እንደኛ በውርስና በተዛማጅ ትርጉም ቀርበውለት አይደለም። ያለው ትውስታና አቀባበል የሚደንቅ ነው። ከማስታወስም ባሻገር ከነፍሱ የተጣቡ አብሮአደጎቹ፣ ወዳጆቹና ጓደኞቹ ናቸው፡፡ ሀገር በቀል ከሆኑት የፍቅር እስከ መቃብሮቹ በዛብህና ሰብለወንጌልን እንኳን ከእነ ራስ ኮልኒኮቭና ኤድመንድዳንት የበለጠ ጠንቅቆ ያውቃቸዋል ለማለት እቸገራለሁ፡፡ ይህንን ስሜቱን አንድ ሀተታው ውስጥ እንዲህ ሲል አስፍሯል…
‹‹በአለም ረጅም የሥነ-ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ በፈጠራ ድርሰቶች አማካኝነት ተፈጥረው በአንባቢያን ልቦና ውስጥ ለዘለቄታው ሲታወሱ ከሚኖሩ ህያው ገጸባህሪያት መሀል ከስጋና ከደም ከተሰሩ የሰው ልጆች ባልተናነሰ በየማህበረሰቡ የአኗኗር ባህል ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳረፉ የምናብ ፍሬዎች ይልቃሉ፣ ይበልጣሉ፡፡” (አለላ፤ ቅጽ1)
አንተነህ አክሊሉ ከጥቂት ወራት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ለንባብ ካበቃው “ምልጃ” የሥነግጥም መድበሉ በፊት ባልተለመደ መልኩ ትዝ የማይሉንን ገጸባህሪያት ከተረሱበት፣ ከተዘነጉበት ስርቻ አንቅቶ ህያውነት በማላበስ እስትንፋስ ዘርቶባቸዋል፡፡ በኪነ-ጥበብ ምናባዊ ዓለም… በጠቢባን አእምሮ ግዘፍ ነስተው በልባችን ውስጥ ህያው ሆነው እድሜ ዘመናችንን ሙሉ አብረውን የሚኖሩ ገጸባህሪያት አያሌ ናቸው፡፡ በተለይም ደግሞ በአጭርና ረጅም ልቦለዶች ውስጥ የሚሳሉ ባህርያት በገሀዱ ዓለም በቅርበትና ለረጅም ዘመን ከምናውቃቸው ሰብዖች እኩል ሆነውና አንዳንዴም ይበልጥ ገዝፈው ዘወትር እናስታውሳቸዋለን፡፡ ይሁን እንጂ በየፈጠራ ስራው አውድ ውስጥ ኖረው ታሪካቸው ተወስኖ የተቀነበበበት ገጽ ፍጻሜ ሲያገኝ በመጽሐፉ የመጨረሻ ገጽ ላይ ንባባችን እየተገታ፣ ከዚያ ውስን የህይወታቸው ቁንጽል ታሪክ ብንለይም፣ ከእነዚያ ህያው ባህሪያት ጋር ያለን ግንኙነት ግን በዚያው አይቋጭም፣ ልባችን ውስጥ የሚኖር ነው፡፡ አብሮነትና ትዝታቸው ዘመናችንን ሙሉ ከኛው ጋር የሚቀር እውነት ይሆናል፡፡ ህያው ባህሪያቱ ውጪያዊ ገጽታቸው በቃላት ኃይል ተገልጾ፣ አካላዊ ማንነታቸውን በዓይነ-ህሊናችን ሸራ ላይ ከምንከስትበት የስነ-ጽሁፍ ፀጋ አንስቶ እነርሱን ማዕከል አድርጎ መጽሐፉ ሙሉ ከሚሽከረከረው የሕይወት እውነታ ጋር እየተሰናኘ በየገጹ በሚንፎለፎለው ህልው ውስጥ የሚገለጠው የባህሪያቱ ነፍስና ህሊና ህያው እውነት ሆኖ ህያው ካልሆነው መንፈሳችን እየሰረፀና ባህሪያቱን በምልዓት እየገነባ ከልባችን ያኖራቸዋል፡፡
በርግጥ በሁሉም የፈጠራ ስራ ውስጥ የሚገጥሙን ገጸባህሪያት ሁሉ ይህን ጸጋ ይታደላሉ ማለት አይደለም፡፡ አይረሴና ህያው የልቦናችን እውነት የሚሆኑት ገጸባህሪያት በደራሲዎቻቸው ጥልቅ ኪናዊ ብቃት የሚፈጠሩ፣ የሚታወቁና ከተመረጡ ደማቅ የህይወታቸው አንጓዎች ጋር ተዋህደው የሚቀናበሩት ብቻ ናቸው፡፡ (ከአዳም ረታ እቴሜቴ ታደሰን… ከግራጫ ቃጭሎች ደግሞ መዝገቡን) ዝርው በሆነ ሕይወት ፍዝ በሆነ ድርጊት እያለፉ፣ሞገድ አልባ ታሪክ ያላቸው ባህሪያት ውስጣቸው እየፈተለ የሚመጣ ጉልህ የማንነት ቀለም ስለማይኖራቸው በልቦናችን ሰርፀው አይገቡም፡፡ ህይወታቸው እለት-ተለት ከሚገጥመን ተራ እውነታ ስለማይለይ ገጠመኞቻቸው የውስጣቸውን ሀቅና ውበት የመግለፅ ሃይል አይኖረውምና፣ ከተፈጠሩበት መጽሐፍ ገጽ ፍፃሜ ጋር ህልውናቸውም ይደመደማል፡፡ አንድ ገጸባህሪ በሚያልፍበት የህይወት መንገድ ላይ በደራሲው በሚቀናበሩ የተመረጡ አጋጣሚዎች ሞገድነት እየተላጋ በስጋና በነፍስ፣በህሊናና ስሜት መሀል ወድቆ፣ ጥልቅና ረቂቅ ውዥንብር ውስጥ እየተናጠ መንፈሱ ካልተብራራ በቀር በተደራሲ ልቦና ውስጥ ህያው ሆኖ አይቀመጥም፡፡ አንተነህ እነዚህ ገጸባህሪያት የተረሱበትን ምክንያት በዘመናቸው ከገጠሟቸው ሁነቶች ጋር በንቃትና በላቀ ትንታኔ፣ ብርቅ የሆነ የህልውና ጫፍ ላይ በማድረስ ህይወታቸውን ለመተርጎም ይታትራል፡፡ በልደታቸውና በሞታቸው መሀል ያለ አጭር ህይወታቸውን ዘመን የማይሽረው ልዕልና በማጎናፀፍ፣ በተደራሲ ልቦና ውስጥ ህያው ህይወትን ያውጃል፡፡ ከዚህ  ባሻገር አንተነህ ገጣሚ እንደመሆኑ መጠን ነፍሱ አብዝታ ለግጥም ታደላለች፡፡ የካህሊል ጂብራንን ግጥሞች ተርጉሞ በተመሳሳይ አስነብቧል፡፡ ዲለንቶማስ የተሰኘ ገጣሚ እንደተናገረው .. “አንድ ምርጥ ግጥም ከተፃፈ አለም ቀድሞ የነበረችውን አትሆንም፤ በአንድ ትጨምራለች” ነውና፤ እነሆ እርሱም በ“ምልጃ” በኩል ሌላ አለም ይዞ መጥቷል፡፡ ወደ ሌላ አለም ይወስደናል፡፡ እኔም በክፍል ሁለት ጽሁፌ፣ የሥነጽሁፍ ሃያስያኑ ብርሀኑ ገበየሁና ደረጀ በላይነህ ባስታጠቁን የስነግጥም አተያይ መነጽርነት፣ “ምልጃ”ን ለመቃኘት እሞክራለሁ። እስከዚያው ግን ከመድበሉ “የዕጣ ሌጣ” የተሰኘች አጭር ግጥሙን ልጋብዝ፡-
አጥርቼ እንዳላልም÷ አይኔን ግምጃ ጋርደህ
አስልቼ እንዳልገኝ÷በልቤ አዚም ገምደህ
ሰቀቀን ተግቶ÷ ላይ ቆረጥጥሜ÷ ራቤ ላይሰፈር
ካልቸገረ አላባ÷ መብከንከን እንድዝቅ ÷ ቁጭት እንድሰፍር
“የዕጣ ሌጣ” ወንፊት÷ በባዶ አይንህ ጠልፈህ ÷ እያንዘረዘርከኝ
በአገር ገበያ ፊት÷ ክቡር ወርቄን ወስደህ ÷ በአፈር መነዘርከኝ፡፡


Read 4313 times