Print this page
Monday, 28 November 2022 16:53

‹‹የፈረንጅ ሚስት››

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 ደራሲ፡- እስከዳር ግርማይ (የ‹‹ሰውነቷ›› ፊልም ደራሲ ተዋናዪትና ፕሮዱዩሰር እንዲሁም የ‹‹ጥቁር እንግዳ›› ፊልም ፕሮዱዩሰርና ተዋናዪት)
ሒሳዊ ዳሰሳ፡- ዮናስ ታምሩ ገብሬ
ንቁ፣
……ብቁ፤
ቁጡ፣
…...ቅንጡ፤
ጥንቁቅ፣
……ምጡቅ፤
ድንብልቅ፣
……ፍልቅልቅ፤ (ለእስከዳር ግርማይ)
መነሻ፡-
ሪዛሙ ደራሲ በርናንድ ሾው ‹‹Major Barbara›› በሚል ድርሰቱ አንዲት ልባም ሴት አስተዋውቆናል። በበኩሌ የበዓሉ ግርማ ሴቶችም ለእኔ ጎምቱ ናቸው፤ እነ ሒሩት፣ ሉሊት፣ ፊያሜታ…
…ካለፈው ዓመት (2014 ዓ.ም.) አንስቶ የሴት ደራሲያን ቁጥር እየተበራከተ መምጣት ለሥነ-ጽሑፋችን ጉልህ አበክሮ ይኖረዋል፤ በጣም ደስ ተሰኝቼአለሁ፤ ለመሆኑ ሴት የሌለችበት ነገር ምኑ ይጥማል?...
….ከእነዚህ መካከል እስከዳር ግርማይ አንዷ ናት፤ ‹‹ኢትዮጵያዊ ሀገሩ የት ነው?›› በተነበበ በወራት ልዩነት ‹‹የፈረንጅ ሚስት››ን አስነበበችን፤ ለአሁን ስለ ‹‹የፈረንጅ ሚስት›› እናውጋ፡-
‹‹የፈረንጅ ሚስት›› በተሰኘ ድርሰት እስከዳር ግርማይ በፈረንጅ ሚስትነት - የእራስዋን ተመክሮዎች፣ ገጠመኞች አሳዛኝ ወላ አስደሳች ቀናት፣ ሞግታ የረታችባቸውን አጋጣሚዎች - ከሌሎች - ከወዳጅ ጓደኞችዋ (ከፈረንጅ ሚስቶች) ጋር እያጣቀሰች የተረከችበት ድርሰት ነው፤ ቋንቋው ግልጽ ግና ውብና ትረካው ፈጣን ድርሰት ነው፤ ሳነበው እንዲህ ሆነ፡-   
1ኛ. ነገረ መቃን/Frame-work - አንድን የድርሰት ወላ የጥናታዊ ጽሑፍ ሀሳብ ለማስኬድ መቃን ሁነኛ ዘዴ ነው፤ ፎቶ በመቃን ሲሆን ውበት ይኖረዋል። እስከዳር የታላቁን ባለቅኔ የጸጋዬ ገ/መድኅንን ‹‹አድባር›› የሚል ግጥምና ከቲያትሮቹ መካከል ደግሞ ‹‹ማነው ምንትስ?›› የሚል ሴቶችን የሚያበቃ ሀሳብ ላይ ተመርኩዛ፣ ወይም መቃን አድርጋ በመገልገል ሀሳቧን ትተርካለች። በእርግጥ ድርሰቱ በተለያዩ ገጠመኞች፣ ትንታኔዎች፣ መዘርዝሮችና ምሳሌዎች የተሞላ ቢሆንም ሲቋጭ ከመቃኑ ፈቅ አይልም፤ ሴቶች በማኅበረሰቡ ዘንድ አበክሮ እንዳላቸው ይጠቁማል የሚል ዕምነት አለኝ። አልቆጨኝም፤ ረክቼአለሁ!!
2ኛ. ነገረ ጥናታዊ ጽሑፋዊነት - ድርሰቱ ለቀለም ትምህርት ብሎም ለዓለም-አቀፍ ንባብ መዋል የሚችል ጥናታዊ ጽሑፍ ነው ብዬ አምናለሁ፤ ደራሲዋ ተሳታፊ ቀጂ እና የጥናቱ አካል በመሆን /participant observant/ በፈረንጅ ሚስትነት የገጠማትን ዕክል፣ መድሎ፣ ኢ-ፍትሕና ሌላም ነገር ትተርካለች፤ ትረካው ደግሞ በሁኔታዎችና በሰዎች አኳኋን ላይ መሠረት ያደረገ - interpretive analysis ነው (እመለስበታለሁ)። እናም ድርሰቱ ሴቶችን በተመለከተ ለሶሾሎጂ፣ ለሥነ-ልቡና፣ ለምጣኔ-ሀብትና ለሌሎች የትምህርት ዓይነቶች ሁነኛ ምንጭ በመሆን ያገለግላል ብዬ አምናለሁ። ‹‹Challenges that Hampers Yeferenj Mist›› በሚል ርዕስ ለዓለም እንደምታስነብብ አልጠራጠርም።    
3ኛ. ነገረ ቁጣ - በወንዴ ጾታ በኩል ትክክል የሚመስሉ ግና መረንና መቀጮ የሆኑ ድርጊያዎች፤ በትንሹ አላስፈላጊ፣ ወይ፣ መናኛ፣ ወይ፣ ክብረ ነክ ቃላት አጣጣላችን ምን ያክል የሴትዋን መንፈስ እንደሚያስቆጣ፣ አልፎም ጫና እንደሚያሳድርባት የሚያስገነዝብ ድርሰት ነው፤ መረንና ፈር ከሳቱ አባባሎች እስካልተቆጠብን ድረስ የሴቶቹን ሥነ-ልቡና እንደምናለምሽ የሚያስጠነቅቅ ድርሰት ነው፤ ለምሳሌ፡-
በገጽ፡- 23፣ 34 እና በሌሎች የቀረቡ ተረኮችን ማየት ይቻላል።    
4ኛ. ነገረ ትንተና/interpretive analysis - በqualitative research መስክ ተመራጩን የትንተና ዘዴ (interpretive analysis) በመጠቀም፣ የሰዎችን ፊት በመፈተሽ ብሎም የቃላት አጣጣልን ከግምት በማስገባትና ከሁኔታው/ከጉዳዩ በማናበብ የሚከናወን ትንተና ማለት ነው፤ ለምሳሌ፡-
በገጽ 32፣ 33 ላይ ከአንድ ጋዜጠኛ ጋር የምታደርገውን ውይይት፣ ትንተና እና ሌሎችንም ማየት ይቻላል፤  
5ኛ. ነገረ ፍካሬ - እውነትን በሥነ-ውበት መፈከር የዚህ ድርሰት በጎ ጎኑ ነው፤ አንዳንድ ውበታም ቃላት፣ ገላጭ ሐረጋትና ዓረፍተ-ነገሮች በብዛት ይስተዋላሉ። የዓረፍተ ነገር አጀማመርዋም ቢሆን መሳጭና ሁሉን አቀፍ ነው።  
ማሳያ፡- ገጽ 36 ‹‹የሰይጣን ጆሮ ይደፈንና ከባለቤቴ ጋር ተፋትተን ንብረት ክፍፍል ውስጥ ብንገባ፣ ባለቤቴ መቀመጫዬን ከራሱ ድርሻ ንብረት ጋር ሳይደምረው አይቀርም….››
6ኛ. ነገረ ሚዲያ እና ክብረ-ነክ ጋዜጠኞች - በድርሰቱ አንዳንድ ሚዲያና የሚዲያ ባለሙያዎች ክፍተት ተቃኝቷል፤ መረንና ለሙያቸው ክብርና ግንዛቤ የሌላቸው ጋዜጠኞች ምን ያክል የሴትዋን መንፈስ እንደሚያስቆጡ ያሳስባል፤ ለምሳሌ፡-
ከገጽ 32-41 ያለውን ውይይት መመልከት ተገቢ ነው።
7ኛ. ነገረ ተጽዕኖ - ድርሰቱ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ተጽዕኖ (በውጭም በአገር ውስጥም) በሚገባ ያስቃኛል፤ የሞራል፣ የአካል፣ የመንፈስ፣ ኢ-ፍትሐዊነት…ወዘተ ጫናዎች በፈረንጅ ሚስቶች ላይ ሲደርሱ እናያለን።
8ኛ. ነገረ ተራ ግምት/wild-guess - የውጭ አገር ብሎም የአገራችን ሰዎች ለፈረንጅ ሚስት ያላቸውን ተራና መናኛ ግምት ከዚህ ድርሰት መገንዘብ ይቻላል፤ የፈረንጅ ሚስት በራስዋ ጥረት እንደማትኖር አድርጎ መሳል አንዱ ክፍተት እንደሆነ በመረጃ አስደግፋ ትሞግታለች።
9ኛ. ነገረ ሙግት/discourse - በዚህ ድርሰት ያልተገባ ንግግርና ተራ ግምት ሲገጥማት ከተሳሳተው ግለሰብ ጋር ቀጥተኛና ግልጽ ውይይት በማድረግ የተሳሳተ ግንዛቤን መቀየር እንደሚቻል ያሳየችበት መጽሐፍ ነው፤ ሴቶች በምክንያታዊነት ላይ ተንተርሰው ክርክርና ሙግት ሲገጥሙ ታስቃኛለች፤ ሴቶችን ማብቃት ነው ይኼ! ለአብነት፡-
ገጽ 74 ላይ ደራሲዋ/ተራኪዋ ከአንድ የአረብ ሰው ጋር ስትሞግት ወላ ስታሳምን እናገኛለን!
10ኛ. ነገረ መሰናሰል እና የፍሰት ወጥነት - ድርሰቱ ከምዕራፍ ምዕራፍ የተያያዘና በቂ መዘርዝሮችን ያቀፈ ነው። በተጨማሪም ምሳሌዎችና ምዕራፎቹ ከዋናው ሀሳብ የማይጋጩ ናቸው፤ ረክቼአለሁ!!
11ኛ. ነገረ ምክረ-ሀሳብ/recommendations - ደራሲዋ በተለያዩ ጊዜያት የገጠሟትን ክስተቶች ወ ገጠመኞች ተንትና ካቀረበች በኋላ፣ ‹ከእጄ ውጪ› ብላ አትገላገልም፤ ለጠቀሰቺው ችግር መፍትሔ ይሆናሉ ብላ ያሰበችውን (ሚዛን የሚደፉ) የምክር ሀሳቦችን ትለግሳለች። እንዲያ ይሻላል!!
መውጪያ፡-
በጥናታዊ ጽሑፍ አንድ የተለመደ አባባል አለ፤ ‹‹Publish or Perish›› ይሉት ብሒል ነው ታዲያ። የምርምር ወላ የድርሰት ሥራዎች ለውጥ እንዲያመጡ ከተቻለ ለኅትመት ማብቃት፤አሊያ ወዲያ መጠቅለል። በአጠቃላይ፣ አንድ ድርሰት ወላ ጥናታዊ ጽሑፍ በተደራሲው ወይም በተጠኚው ላይ ፈጣን አሉታዊ ጫና ማሳደር ከቻለና ትክክለኛውን መንገድና መፍትሄ እንዲመርጥ ካስቻለ ግቡን መቷል ማለት ይቻላል፤ ‹‹የፈረንጅ ሚስት›› በእራሴ ላይ ፈጣን እርምጃ እንድወስድ አድርጎኛል፤ ምናልባት ከዚህ በፊት ለፈረንጅ ሚስቶች ወላ ለሴቶች የነበረኝን ተራና መናኛ ግምት እንድከልስና ትክክለኛውን እሳቤ እንድፈትሽ አስችሎኛል ብዬ ብናገር ከሕሊናዬ አልጋጭም!!   

Read 1334 times
Administrator

Latest from Administrator