Saturday, 26 November 2022 00:00

ጎጆ…የካንሰር ሕሙማን ማረፊያ

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

 ጎጆ የካንሰር ህሙማን ማረፊያ በአዲስ አበባ ተክለሀይማኖት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አካባቢ ወደጎላ ሚካኤል በሚወስደው መንገድ ከተክለሀይማኖት ጤና ጣቢያ ውስጥ የራሱን ማረፊያ በማሰራት ስራ የጀመረ ነው፡፡ ጎጆ እንዲመሰረት ምክንያት ከሆኑት መካከል ዶ/ር ቤተልሄም ይስሀቅ አንድ ታሪክ አላቸው፡፡ አንድ የካንሰር ታማሚ ከሰአት በፊት በጥቁር አንበሳ ሆስፒ ታል ኬሞ ቴራፒ ሲወስድ አይ ተውታል፡፡ ከአስር ሰአት በሁዋላ ደግሞ ወደ ቤታቸው ሲሄዱ  መንገድ ላይ ተኝቶ ያገኙታል፡፡ ..ምነው… ስትታከም አይቼህ ነበር፡፡ አሁን እዚህ ለምን ተኛህ? ይሉታል፡፡ እሱም… ምን ላድርግ… ገንዘብ የለኝ…. አዲስ አበባ የማውቀው የለኝ…. ወደሐገሬም ለምኜ እንኩዋን እንዳልሔድ ሕክምናው አላለቀልኝ… ግራ ቢገባኝ ነው …ከጎዳና የወደ ቅሁት… የሚል ነበር መልሱ…. ዶ/ር ቤተልሄም ይስሀቅ ከጎጆ የካንሰር ህሙማን ማረፊያ መስራቾች መካከል ናቸው፡፡ የማረፊያው ምክትል ፕሬዝዳንት ሲሆኑ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሰርጅን ወይንም ቀዶ ሕክምና ክፍል መምህር ወይንም ሌክቸረር ናቸው፡፡ ጎጆ የካንሰር ህሙማን ማረፊያ እንዲመሰረት ምክንያት ከሆኑት መካከል ይህ አንዱ ነው የሚለውን ምስክርነት ያገኘነው…በጎጆ …ቆይታ ባደረግንበት ወቅት ነው፡፡ በመቀጠል በማረፊያው አርፈው ካገኘናቸው የካንሰር ታካሚዎች ጋር ቆይታ ይኖረናል፡፡
‹‹…አስናቀች አለሙ እባላለሁ፡፡ የመጣሁት ከሚዛን ቴፒ ነው፡፡ ሕመሜ የደም ካንሰር ነው፡፡ ሕክምናው በአንድ ወይንም በሁለት ቀን የሚቋጭ አይደለም፡፡ ሁልጊዜም ክትትል ይፈል ጋል፡፡ ስለዚህ እኔ አልጋ መያዝ የማልችል አቅመ ደካማ ስለሆንኩ እዚያው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አግዳሚ ወንበሮች ላይ ተኝቼ አድር ነበር፡፡ የብርዱ ነገር አይወራም፡፡ በዚህ ሁኔታ ከበሽታው በላይ በሁኔታው ስሰቃይ ሰዎች ጎጆ የሚባል የካንሰር ህሙማን ማረፊያ እኮ አለ የሚል ነገር ጠቆሙኝ፡፡ እኔም አጠያይቄ ስመጣ ይኼው ካለምንም ችግር ልክ እንደቤቴ አርፌአለሁ። በፊት በፊት መድሀኒቱ ለሶስት ወር ስለሚሰጠኝ የሶስት ወሩን ይዤ ወደሀገሬ እሄድ ነበር፡፡ አሁን ግን እጥረት አለ ተብሎ መድሀኒት የሚሰጠኝ የአስራ አምስት ቀን ነው፡፡ የትራንስፖርቱ አልጋና ምግብ ሳይጨምር አንድ ሺህ አምስት መቶ ብር ነው፡፡ ደርሶ መልሱ ሶስት ሺህ ብር ይፈልጋል፡፡ በየአስራ አምስት ቀኑ ይህ ገንዘብ ከየት ይመጣል? ይህ ሕመም ከጀመረኝ አስር አመት ሆነው፡፡ በፊት ልጆቼንም ቤቴንም የምደግፈው ጠጅ እየነገድኩ ነበር፡፡ አሁን ካንሰር ከያዘኝ ጀምሮ ይሄው አስር አመት ሆነኝ ምንም ሰርቼ አላውቅም፡፡ ልጆቼን እንደእናትነቴ ከዳር ለማድረስ አልቻልኩም፡፡ አባታቸው ብቻውን እየተንገላታ ነው፡፡ እኔ እስከአሁን እየታመምኩ ነው። በእርግጥ አብረውኝ የሚታከሙ እየሞቱ ነው…… የእኔን መጨረሻ አላውቅም…..››
አስናቀች ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ይታይባታል። ይሁን እንጂ በሌላ በኩል ደግሞ መውደቂያ ጎጆን በማግኘትዋ እግዚአብሔርን ታመሰግናለች፡፡ ጎጆ ወንድ ሴት ህጸን አዋቂ ሳይል ሁሉንም የካንሰር ሕሙማን የሚያሳርፍ በጎ አድራጊ ድርጅት ነው። በቦታው ህጸናቱን ተመለከትን ምንድናቸው ብለን ስንጠይቅ የካንሰር ታካሚዎች መሆናቸውን ተረዳን፡፡
‹‹…እኔ ስሜ በላቸው ይባላል፡፡ የመጣሁት ከወለጋ ነው፡፡ አሁን ያለሁት ጎጆ መጠለያ ውስጥ ነው፡፡ ደራርቱ የተባለች የአስራ አራት አመት እድሜ ያላት ልጄ የደም ካንሰር ሕመም ስለገጠማት ቤቴን ንብረቴን ትቼ ይኼው ሁለት አመት ሊሆነኝ ነው። እስዋን በማሳከምና አዲስ አበባ በመቆየት ገንዘቤ ስላለቀ አስጠጉኝ ብዬ ነው ከጎጆ የገባሁት።  በእርግጥ ሌሎች ልጆችም አሉኝ፡፡ ግን ምን ላድርግ…. ቤቴን በትኜዋለሁ ማለት ይቻላል፡፡ ገበሬ ነበርኩ፡፡ ይቺ ልጅ ከታመመች ጀምሮ ሁሉም ነገር ስለቀረ ቤቴም ተበትኖአል ማለት ይቻላል፡፡ እስዋ እስክትድን ድረስ እኔም እዚሁ የቀን ስራ እየሰራሁ ልጆቼን መደጎም የምችል ከሆነ ብዬ እያሰብኩ ነው….››
በላቸውን ስናናግረው በጣም የሀዘን ስሜት ነበረው፡፡ በሁለት ችግር መካከል ሆኖ ማዶ ማዶ እያየ ነበር ያናገረን፡፡ በሀገር ቤቱ ልጆቹና ሚስቱ…ቤቱ…. የሚጠብቃቸው … ቀለባቸውን አርሶና አምርቶ የሚያቀርብላቸው የለም፡፡ አጠገቡ ደግሞ ገና ሮጣ ያልጠገበች የአስራ አራት አመት ታዳጊ ልጁ አልጋ ላይ እጥፍ ብላ ተኝታለች፡፡ እጅግ በጣም ሰውነት የሚረብሽ ነው፡፡
ሌላዋ ታካሚ ከአማራ ክልል ነች፡፡  
‹‹…ዘውዴ ይመር እባላለሁ፡፡ የመጣሁት ከደሴ ነው፡፡ የካንሰር ሕመሙ ወደአንገቴ አካባቢ ነው። ሕመሙ ከያዘኝ አምስት አመት ገደማ ሆኖኛል፡፡ በጊዜው ትንሽዋን ልጄን እያጠባሁ ስለነበር ሐኪም ግን ከዚህ በሁዋላ አታጥቢ ብሎ ከለከለኝ፡፡ ከዚያም እንደገና ከባለቤትሽ ጋር ምንም ግንኙነት እንዳትፈጽሚ ተብዬ ባለቤቴ ተጠርቶ ደብዳቤ ተሰጠው፡፡ በቃ ከዚያ በሁዋላ ሕክምናውን እየተከታተልኩ ነው፡፡ ሲጀምረኝ በአንገቴ ዙሪያ እብጠት እየተከሰተ አንገቴ ሶስት ጊዜ ቀዶ ሕክምና ተደርጎለታል፡፡ ግን እየተካ ስላስቸገረ ከዚያ በሁዋላ የጨረር ታካሚ ሆንኩ፡፡ በተከታታይ 33 ጊዜ የጨረር ሕክምና ተደርጎልኛል፡፡ ግን አሁንም በዚህ ዳነ ሲባል በዚህ …እብጠት እያመጣ… እብጠቱ አፌን ሁሉ እያጣመመ ያስቸግረኛል፡፡ የነርቭ ችግርም አስከትሎብኛል፡፡ እንግዲህ ልጆቼንም ትቼ …ቤቴን ጥዬ ይኼው ህክምናዬን እያደረግሁ ከዚህ ከጎጆ ተጠልያለሁ፡፡ ማረፊያ ስለሆኑኝ በጣም አመሰግናለሁ…››
በጎጆ የህሙማን ማረፊያ ስታስተባብር ያገኘናት ወ/ሮ ስንታየሁ ወርቁ ናት፡፡ ስንታየሁ የደብረማርቆስ ነዋሪ የነበረች ስትሆን ወደጎጆ የመጣችበት ምክንያት አላት፡፡
‹‹….እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2010 በኢትዮጵያ አቆጣጠር እናቴ የማህጸን ካንሰር ታማሚ ነበረች፡፡ እናቴን ለማሳከም ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ይዤ ስመጣ በጊዜው የካንሰር ሕክምናው በተለይም ኬሞ ቴራፒ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቻ ይሰጥ ስለነበር ህክምናውን ለማግኘት እጅግ አታካች ነበር፡፡ ያለኝን ገንዘብ ጨርሼ በስተመጨረሻ ከጥቁር አንበሳ በረንዳ አንድ ጥግ ላይ ካርቶን አንጥፌ እናቴን ይዤ መተኛት ጀመርኩ፡፡ ጊዜው ክረምት ስለነበር በተለይም እናቴ ልትቋቋመው አልቻለችም፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር ሰዎች ጎጆን የጠቆሙኝ፡፡ እናቴን ይዤ ገባሁ፡፡ በእርግጥ እናቴ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2011 ከዚህ አለም በሞት ተለይታለች፡፡ እኔ ግን በጎጆ አገልግሎት በጣም ስለረካሁ ቤቴንና ልጆቼን ለቤተሰብ ትቼ ቢያንስ ቢያንስ በጉልበቴ በማገልገል ህክምና እስኪያገኙ ማረፊያ ያጡ የካንሰር ህሙማንን መርዳት እንደምችል አስረድቼ ስራዬን ጀመርኩ…›› ብላለች፡፡
ወ/ሮ ስንታዩ በአሁኑ ጊዜ የመስሪያ ቤቱ ወኪል ናት ማለት ይቻላል፡፡ ጎጆን እንደሚከተለው አስረድታናለች፡፡
‹‹….ጎጆ ሀምሳ ሁለት አልጋዎች አሉአት፡፡ ነገር ግን ሁልጊዜ የሚያገለግሉት 36 አልጋ ዎች ናቸው፡፡ እነዚህ 36 አልጋዎች ነጻ ሆነው አያውቁም፡፡ መቀበል መሸኘት የሚባል ነገር ስላለ ማረፊያ ፈላጊዎቹ ሲበዛ በቀን እስከ ሰባ ሊደርሱ ይችላሉ፡፡ አነሰ ብንል ግን ከሀምሳ በታች አይሆኑም፡፡ ግን ይህም መሸኘት መቀበል የሚባለውን የሚያካትት ነው፡፡ በጎጆ የሚያርፉ የካንሰር ታካሚዎች ካለሐኪም ግንኙነት ከሀያ ቀን ላላነሰ ጊዜ ወደሐኪም ቤቱ እየሄዱ ጨረር ሲወስዱ የቆዩ ቢችሉ በራሳቸው አቅም… ካልቻሉም ወደሀገራቸው መመለሻ ትኬት እየተገዛ ጭምር ይስተናገዳሉ፡፡
ጎጆ ከሌሎች ተቋማት የሚለይበት ምክንያት በሕክምና ላይ ያሉ እና ሕክምናው ያላለቀላቸው ታካሚዎች በአቅም ችግር ምክንያት ከደጅ ማደር የለባቸውም የሚል እምነት ስላለው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ህጸን አዋቂ፤ ሴት ወንድ፤ ሽማግሌ ወጣት ሳይል ማረፊያ አጣሁ የሚለውን ሁሉንም ሰው አቅሙ በፈቀደ መንገድ ማረፊያ የሚሰጥ ነው። የካንሰር ሕክምናን በተመለከተም የቆዳ፤ የደም፤ የአንጀት፤ የጡት፤ የማህጸን፤ የፕሮስቴት…. ወዘተ….ሳይመርጥ ሁሉንም ታካሚዎች በመቀበል ማረፊያ ይሰጣል፡፡ በእርግጥ የካንሰር ታካሚዎች የጀመሩት ሕክምና በቀላሉ የማይቋጭና ወረፋ መጠበቁም እጅግ አሰልቺ በመሆኑ እንዲሁም ጎጆ የህሙማን ማረፊያ ለጥቁር አንበሳ ቅርብ በመሆኑ እንጂ ማንኛውም ታካሚ በቀጠሮ ምክንያት በአዲስ አበባ መክረም ካለበትና መቆያ የሚሆን አቅም ከሌለው በረንዳ መውደቅ የለበትም የሚል እምነት ስላለ ማረፊያው አይከለከልም ብለዋል ወ/ሮ ስንታየሁ ወርቁ፡፡
ወ/ሮ ስንታየሁ በጎጆ ያለውን መስተንግዶ ሲገልጹ ጎጆ መንግስታዊ ያልሆነ በበጎ አድራጊዎች ድጋፍ የተቸገሩ ወገኖችን የሚረዳ ድርጅት ነው። በመሆኑም የአቅም ውስንነት አለ፡፡ የምግብ አቅርቦትን በሚመለከት በማረፊያው ለተጠለሉ ታማሚዎች በሳምንት ውስጥ ሰኞ፤ እሮብ እና አርብ (ሶስት ቀን) በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ምግብ ያቀርባል፡፡ ነገር ግን በበጎ አድራጎት ወይንም በተለያዩ ፕሮግራሞች ምክንያት ምግብ ለማቅረብ የሚፈልጉ ሲገኙ በሌሎቹም ቀናት ቢሆን ምግብ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ሌላው እጅግ አስፈላጊው ነገር የጽዳት አቃ ነው፡፡ ሕመምተኞች የሚያርፉባቸው ክፍሎች የግል ልብስና አንሶላዎች የመሳሰሉት ነገሮች የሚታጠቡባቸው ፈሳሽ ሳሙናዎች የመሳሰሉት በእርዳታ ቢቀርቡላቸው በእግዚአብ ሔር ስም እንደሚያመሰግኑ ወ/ሮ ስንታየሁ ገልጸዋል፡፡
በተለይም አንዳንድ ህመሞች ….ለምሳሌ የማህጸን ካንሰር ፈሳሽ ሊኖረው ስለሚችል ያንን ለመቆጣጠር የሚያስችል የንጽህና መጠበቂያ (ሞዴስ) የመሳሰሉትን ነገሮች ከድርጅቱ ጋር በመነጋገር ቢያቀርቡላቸው በጎ ነገር መሆኑን ወ/ሮ ስንታየሁ ወርቁ ገልጸዋል፡፡ ጎጆ የህሙማን ማረፊያ ጥቁር አንበሳ አካባቢ ወደጎላ ሚካኤል በሚወስደው መንገድ ተክለሀይማኖት ጤና ጣቢያ ውስጥ ይገኛል።     

Read 7491 times