Saturday, 26 November 2022 00:00

ኢትዮ ቴሌኮም እና ሲኔት ሶፍትዌር ቴክኖሎጂ፤ ክፍያዎችን

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 በቴሌብር ለመፈጸም የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ አደረጉ

        ኢትዮ ቴሌኮም እና ሲኔት ሶፍትዌር ቴክኖሎጂ፣ የሲኔት ሶፍትዌር ተጠቃሚ አጋሮች ደንበኞቻቸው የአገልግሎትና የግብይት ክፍያቸውን በቴሌብር አማካኝነት ለመፈጸም የሚያስችላቸውን አሰራር ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ተግባራዊ አደረጉ::
 ይህም አሰራር ቴሌብርንና ሲኔት ሶፍትዌርን በማስተሳሰር፣ የሲኔት ሶፍትዌር ተጠቃሚ አጋሮች ደንበኞቻቸው ግብይት ሲያከናውኑ፣ ቴሌብርን ተጠቅመው፣ ክፍያቸውን እንዲፈጽሙ ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡
በተለይም ይህ አሰራር የሲኔት ሶፍትዌርን በመጠቀም አገልግሎት የሚሰጡ ሆስፒታሎች፣ ፋርማሲዎች፣ ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ ካፌዎች፣ ሱፐር ማርኬቶች፣ የመዝናኛና የመስተንግዶ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች እንዲሁም ሌሎች መሰል ተቋማት፣ ደንበኞቻቸው ቴሌብርን በመጠቀም፣ በቀላሉ የተለያዩ የአገልግሎትና የግብይት ክፍያዎቻቸውን እንዲያከናወኑ እንደሚረዳቸው ተጠቁሟል፡፡
በዚህም መሰረት ደንበኞች ለአገልግሎት ወይም የግብይት ክፍያዎችን ለመፈጸም የአገልግሎት ሰጪውን ተቋም/ድርጅት ኪው አር ኮድ (QR code) በማንሳት (scan) እንዲሁም በቅድሚያ ክፍያቸውን በቴሌብር እንደሚከፍሉ በማሳወቅ፣ በሞባይል ስልካቸው በሚደርሳቸው የክፍያ የሚስጥር ቁጥር፣ ለሂሳብ ባለሙያው/ዋ በመናገር ክፍያቸውን በቴሌብር መተግበሪያ ወይም አጭር ቁጥር (USSD) ሲፈጽሙ፣ ከ127 የክፍያ ማረጋገጫ አጭር የጽሁፍ መልዕክት የሚደርሳቸው ይሆናል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም  በቴሌብር አገልግሎት እስከ አሁን ድረስ 25.85 ሚሊዮን ደንበኞችን፣ 101 ዋና ወኪሎችን  (Master Agents) ፣ 87 ሺህ ወኪሎችን፣ 23 ሺህ ነጋዴዎችን /Merchants/ያፈራ  ሲሆን፤ ከ153 ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት ማስተናገዱ ታውቋል፡፡
 በተጨማሪም ከ17 ባንኮች ጋር ትስስር  በማድረግ፣  ከባንክ ወደ ቴሌብር ገንዘብ ማስተላለፍ የተቻለ ሲሆን፣ ከ14 ባንኮች ጋር ደግሞ ከቴሌብር ወደ ባንክ የገንዘብ ዝውውር እየተደረገ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል፤ ከበርካታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና ድርጅቶች ጋር ስምምነት በማድረግ የአገልግሎት አሰጣጥና የክፍያ ስርአታቸውን በማቀላጠፍ ለተቋማቱም ሆነ ለደንበኞቻቸው እፎይታን ማጎናጸፉን ይገልጻል፡፡

Read 8425 times