Saturday, 19 November 2022 19:44

መፍትሄ የታጣለት ግሽበት ለኢኮኖሚው ፈታኝ ሆኗል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(4 votes)

      -  የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ከምስራቅ አፍሪካ ግዙፉ ኢኮኖሚ በመሆን በአንደኝነት ተቀምጧል - ጠ/ ሚኒስቴር ዐቢይ አህመድ
      - ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ከተመዘገበባቸው አገራት መካከል ትገኛለች
      - የውጪ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ መግባት ችግሩን ያቃልለዋል ተብሎ ይታመናል፡፡
          
       የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ባለፉት አመታት በርካታ ሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ አደጋዎች ቢያጋጥሙትም በቀላሉ የማይሰበር ግዙፍ ኢኮኖሚ መሆኑን አሳይቷል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ተናግረዋል፡፡ ሰሞኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በሰጡት ማብራሪያ ላይ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ከምስራቅ አፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ በመሆን በአንደኝነት ደረጃ ላይ እደሚገኝና ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት ሶስተኛ ግዙፍ ምጣኔ ሃብት ደረጃ ላይ መድረሱን ገልፀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአለም ባንክ የተገኘ መረጃን በመጥቀስ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት፤ ማብራሪያ፤ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት በ2014 የበጀት ዓመት ማጠናቀቂያ 6.16 ትሪሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን የነፍስ ወከፍ ገቢም 1212 መድረሱን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ባለፉት አመታት በርካታ ሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ ፈተናዎች ገጥመውት እንደነበር ያስታወሱት ጠ/ሚኒስትሩ በአገር ውስጥ ያለው ጦርነት እንዲሁም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝና ድርቅ ከፈተናዎቹ መካከል ይጠቀሳሉ ብለዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ፈተናዎች ምጣኔ ሃብቱን ቢደቁሱትም በቀላሉ የማይሰበር እንደሆነ ለአለም ማሳየቱንም ተናግረዋል፡፡  
አገሪቱ ያጋጠማትን የዋጋ ግሽበት አስመልክቶ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ጠ/ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ፤ በአሁኑ ወቅት በዋጋ ግሽበት ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን በርካታ አገራት እየተፈተኑ እንደሆነ ጠቅሰው፤ የፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠንና በሰሜኑ ጦርነት ሳቢያ የአቅርቦት መስተጓጎል ማጋጠሙን ገልፀዋል፡፡ የዋጋ ግሽበት ለማክሮ ምጣኔ ሃብት ስብራት ቢሆንም፣ ባለፉት አራት ወራት የዋጋ ግሽበቱ መቀነስ እየታየበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ኢትዮጵያ በታሪኳ ያሳየችውን ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ያስመዘገበችው ባሳለፍነው ዓመት ግንቦት ወር ላይ እንደነበር የሚናገሩት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዶ/ር አንተነህ ተስፋዬ፤ በወቅቱ የዋጋ ግሽበቱ 37.2 በመቶ ደርሶ እንደነበርና በነሐሴ ወር መጨረሻ ወደ 32.5 በመቶ መቀነሱን የኢትዮጵያ ስታቲክስ ኤጄንሲን ዋቢ አድርገው ይናገራሉ፡፡
አገሪቱ በአፍሪካ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ካጋጠማቸው አገራት ተርታ መሰለፏን የተናገሩት ዶ/ር አንተነህ ዚምቧቤ፤ሱዳንና ጋናን አስቀድማ በአራተኛነት ደረጃ ላይ እንደምትገኝም ገልፀዋል፡፡
መንግስት የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠርና ግሽበቱን ለመቀነስ እየወሰደ ያላቸው እርምጃዎች ቢኖሩም ገና ብዙ ስራ ይጠበቅበታል ያሉት ባለሙያው፤ ችግሩን በመሰረታዊነት ለመቅረፍ መንግስት ወሳኝ እርምጃዎችን ሊወስድ ይገባል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ ያቀረቡትና የዋጋ ግሽበቱን ለመቆጣጠር ያስችላሉ ያሏቸውን የመፍትሄ ሃሳቦች በተመለከተ ዶ/ር አንተነህ ሲናገሩ በአገሪቱ የተከሰተው የዋጋ ግሽበት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተከሰተው ጋር የሚያያዝ  መሆኑን ጠቁመው፤ የሩስያና የዩክሬን ጦርነት በነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል ብለዋል።
“መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች እንደ ስንዴ ዘይትና ስኳር ያሉትም በተመሳሳይ ሁኔታ ጭማሪ አድርገዋል። ይህ ራሱን የቻለ ትልቅ ራስ ምታት ሆኖ እያለ፤ መንግስት በበኩሉ የነዳጅ ዋጋ ድጎማን እንዲነሳ አደረገ። ይህ ችግሩ የበለጠ እንዲባባስና የዋጋ ግሽበቱ እንዲጨምር ምክንያት ሆነ” ሲሉ ያብራራሉ።
አሁን ጠ/ሚሩ ለምክር ቤቱ ያቀረቧቸው የመፍትሄ እርምጃዎች (መንግስት ጣልቃ በመግባት ምርቶችን ለገበያ ማቅረብና አርሶ አደሮች አዲስ አበባ መጥተው የእሁድ ገበያ ላይ ምርቶቻቸውን እዲያቀርቡ ማድረግ፣ የተማሪዎች ምገባና፣ የማዕድ ማጋራት ተግባራት) የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር የሚኖረው አስተዋፅኦ የጎላ አይደለም ብለዋል።
ይልቁንም መንግስት አስፈላጊነታቸው መሰረታዊ ያልሆኑና ጊዜ ሊሰጡ የሚችሉ ፕሮጀክቶችን ለጊዜው በማዘግየትና በማቋረጥ መሰረታዊ ፍጆታዎች ላይ ድጎማ በማድረግ፤ ያለውን የዋጋ ግሽበት ማረጋጋት ይጠበቅበታል ብለዋል።
በሌላ በኩል የውጪ አገር ባንኮች ወደ አገር ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ መፈቀዱ የዋጋ ግሽበቱን በማረጋጋቱ ረገድ ያለው ሚናም ከፍተኛ መሆኑን ዶ/ር አንተነህ ገልጸዋል።
መንግስት በቅርቡ ቅድሚያ የማይሰጣቸው በተባሉ 38 ዓይነት ሸቀጦች ላይ የጣለው ዕገዳም በአገሪቱ ውስጥ የተከሰተውን የውጪ ምንዛሬ እጥረት ለመግታት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል ሲሉም ተናግረዋል።
አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤም ኤፍ፤ ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2023 ዓ.ም የሚኖራት የውጪ ምንዛሬ አቅም፣ መሰረታዊ የሚባሉ እንደ ነዳጅ ማዳበሪያና መድሃኒት ለመግዛት  ብቻ የሚሆን ነው ሲል ተንብይዋል።          


Read 14520 times