Saturday, 19 November 2022 19:45

ዓለም በጉጉት የሚጠብቀው የዓለም ዋንጫ ነገ በኳታር ይጀመራል

Written by  ግሩም ሰይፉ - ከዶሃ ኳታር
Rate this item
(3 votes)

 በመንግስት የሥራ ሰአቶች ላይ ለውጥ ተደርጓል። ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል።
                   
      22ኛው የዓለም ዋንጫ  በአልክሆር ከተማ በሚገኘው አልባይት ስታዲየም  አዘጋጇ ኳታር ከኢኳዶር ጋር በሚያደርጉት የመክፈቻ ጨዋታ ነገ ይጀመራል፡፡  በዓለም ዋንጫው የመክፈቻ ስነስርዓት ላይ ከቢቲኤስ የሙዚቃ ቡድን ጃንኮክ፤ የኮሎምቢያዋ ሻኪራ፤ብላክ አይድ ፒስ፤ ሮቢ ዊልያምስና ኖራህ ፋቲህ ሙዚቃቸውን ያቀርባሉ፡፡
የኳታር መንግስት ከዓለም ዋንጫው ጋር በተያያዘ በከፍተኛ የፀጥታና ደህንነት አገሪቱን ማስተዳደሩን ቀጥሏል፡፡ ባለፉት 3 ቀናት በኳታር ከተማ ዶሃ በመገኘት እንዳስተዋልነው፤ የኳታር ህዝብ የዓለም ዋንጫውን በጉጉት እየተጠባበቀ ይገኛል፡፡ የኳታር ዜጎች በነጫጭ ባህላዊ አልባሳቶቻቸው ተውበውና ደምቀው እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅታቸውን  አጠናቅቀዋል፡፡ የኳታር መንግስት በመንግስት የስራ ሰዓቶች ላይ ለውጥ ማድረጉ የተነገረ ሲሆን ትምህርት ቤቶችም እንዲዘጉ ተወስኗል። የዶሃ ከተማ ዋና ዋና አውራጎዳናዎችና አደባባዮች  በታዋቂ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ግዙፍ ቢልቦርዶችና ምስሎች ተጥለቅልቀዋል።  አመሻሽ ላይ የዶሃ ሰማይ ጠቀስ ህንፃዎች  የዓለም ዋንጫ ተጫዋቾች ምርጥ የቪድዮ ምስሎችን  በቴሌቭዠን ስክሪን  እያሳዩ ናቸው። ትልልቅ ሱፕር ማርኬቶች፤ ህዝብ በብዛት የሚገኙባቸው አደባባዮችና  የከተማዋ መለያ የሆኑ ህንፃዎች በተሳታፊ አገራት  ሰንደቅ አለማዎች አሸብርቀዋል፡፡ የዓለም ዋንጫውን ከስታድየሞቹ ውጭ ለሚታደሙ ሰዎች  ወደተሰሩት  የደጋፊ መናኸርያዎች የሚወስዱ መንገዶች ከትራፊክ ነፃ ሆነው መስተንግዶውን እየተጠባበቁ ናቸው፡፡
ለዓለም ዋንጫው ከ2.89 ሚሊዮን በላይ የስታድዬም መግቢያ ትኬቶች ተሸጠዋል፡፡ የምድብ ጨዋታዎችን ለመመልከት የስታድዬም መግቢያ ትኬቶች  ዋጋቸው ከ70 እስከ 220 ዶላር  ሲሆን የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎችን መመልከቻ ትኬቶች ዋጋቸው ከ600 እስከ 1600 ዶላር ነው፡፡
በግዙፉ ሃማድ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት ያገኘናቸው የኢኳዶር ደጋፊዎች ለስፖርት አድማስ በሰጡት አስተያየት የመክፈቻ ጨዋታውን በድል እንደዲሚወጡት ተናግረዋል፡፡ ከሚኖርባት የአሜሪካዋ ግዛት ኬኔቲኬት ወደ ኳታር በመጓዝ የትውልድ አገሩን በዓለም ዋንጫ ላይ ለመደገፍ  የገባው ጆርጄየቺ  በሰጠው አስተያየት ቡድናቸው የኳታር አቻውን በሜዳው አሸንፎ፤ በአንድ ጨዋታ ተጨማሪ ድል በማስመዝገብና በአንዱ ጨዋታ አቻ በመውጣት ወደ ጥሎ ማለፍ ምዕራፍ ውስጥ ይገባል፡፡
ኳታራውያን ለዓለም ዋንጫው ከፍተኛ በጀት ማውጣታተቸው ብቻ ሳይሆን መላው ዓለም በመልካም መስተንግዶና ምቹ ሁኔታዎች የማይረሳ ትዝታ እንዲያገኝ መስራታቸውን ከአየር ማረፊያው አንስቶ መታዘብ ይችላል፡፡ በሃማድ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የተሰማሩት የበጎ ፈቃድ አገልጋዮች፤ የዓለም ዋንጫን የመረጃ ዴስክ የሚመሩ ሰዎች ለዓለም ዋንጫ እንግዶች ሙሉ ልብ እየሰጡ ናቸው፡፡
በ22ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ለሚሳተፉ 32 አገራት የሚሰለፉ 826 ተጨዋቾች ዝርዝር በፊፋ ታትሟል። 32 ብሔራዊ ቡድኖች እያንዳንዳቸው 26 ተጨዋቾችን  በየስብስባቸው አስመዝግበዋል።
በትራንስፈርማርከት transfermarkt የዝውውር ገበያ ዋጋቸው እስከ 12.46 ቢሊየን ዮሮ ወይም 13 ቢሊዮን ዶላር ተተምነዋል። እስከ 693 ቢሊዮን ብር ይሆናል። በውድ ተጨዋችነት ግንባር ቀደም የሆነው የፈረንሳይ ኪሊያን ምባፔ 160 ሚሊዮን ዮሮ ነው። የብራዚሉ ቪንሸየስ ጁኒየር 120 ሚሊዮን ዮሮ፤ የእንግሊዙ ፊል ፎደን 110 ሚሊዮን ዮሮ፤ የጀርመኑ ጀማል ሞሳየላ 100 ሚሊዮን ዮሮ  እና የስፔኑ ፔድሪ 100 ሚሊዮን ዮሮ እንደ የዋጋ ተመናቸው እስከ አምስተኛ ደረጃ ወስደዋል። በተጨዋቾች ስብስብ በከፍተኛ ዋጋ የተተመነው በ1.26 ቢሊዮን ዮሮ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ነው። ብራዚል በ1.14 ቢሊዮን ዮሮ፤ ፈረንሳይ በ1.08 ቢሊዮን ዮሮ ፖርቱጋል በ937 ሚሊዮን ዮሮና ስፔን በ902 ሚሊዮን ዮሮ እስከ አምስተኛ ደረጃ ወስደዋል።
ኳታር የእስልምና እምነት ተከታይ ሀገር እንደመሆኗ፣ መጠጥ እንደተፈለገ በየቦታው ባይገኝም፤ በተወሰኑ ቦታዎች ግን ተፈቅዷል። በፋን ዞኖች፣ ደጋፊዎች በሚሰበሰቡበት ቦታዎችና፣ በሆቴሎች፣ ይፈቀዳል። የመጠጥ ባሮች ግን እንደ ልብ አይገኙም። እንደ ራሺያ የመጠጥ ባሮች በየቦታው የለም። 20 ካርድ የተባለውን የኳታር ልዩ ቪዛ ሳይይዙ መንቀሳቀስ አይቻልም። የዓለም ዋንጫውን የሚያዘጋጀው ፊፋ እና ኳታር በትብብር እየሰሩ ናቸው፤ 22ኛውን የዓለም ዋንጫ ደማቅና አይረሴ ለማድረግ ከተማዋ በከፍተኛ ጸጥታና ደህንነት ውስጥ ነው የምትኘው።
ታዋቂ ዓለም አቀፍ የስፖርት ሚዲያዎች ኳታር ገብተዋል። ፊፋም ትልቅ የራሱ ቻናል ያለው ሲሆን ዛሬ ቅዳሜ ስራውን ጀምሯል። ባጠቃላይ ከ12ሺ በላይ የሚዲያ ባለሙያዎች 22ኛውን የዓለም ዋንጫ በቀጥታ ሥርጭት (Live) ለመዘገብ ኳታር ገብተዋል።
በኳታር የዓለም ዋንጫ መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች መሳተፋቸውን ዘገባዎች ያመለክታሉ። በሜትሮ ባቡር ግንባታ፣ ስቴዲየሞቹን በሚያገኙ የከተማው ዋና ዋና አውራ ጎዳናዎች ሥራ ላይ እንደሆነ በስታዲየም ግንባታ ላይ በኮንቴነር በተገነባው 974 በተባለው ስታዲየም ግንባታ ጉልህ አስተዋጾ ማድረጋቸውን ይናገራል።
አዲስ አድማስም ከ20-25 የሚሆኑ ጨዋታዎችን ከስፍራው ከዶሀ ኳታር በአስደናቂዎቹ 8 ስታዲየሞች ሆኖ ይዘገባል።


Read 14532 times