Wednesday, 16 November 2022 09:48

በትግራይ ህዝብ መቀለድ ይብቃ! (#NO More!)

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(0 votes)

  - የሰላም ስምምነቱ የጎረበጣቸው ጽንፈኛ ዳያስፖራዎች እየቀወጡት ነው
      -”TDFን እንጂ TPLFን አናውቀውም፤የትግራይን መንግስት አይወክልም”
      - የትግራይ ህዝብን ዕጣፈንታ የምንወስነው እኛ ነን ባዮች ተፈጥረዋል

       ባለፈው ሰኞ የኢትዮጵያ መከላከያና የህወሓት ወታደራዊ አመራሮች በናይሮቢ ተገናኝተው በህወሓት ትጥቅ አፈታት ዙሪያ ንግግር መጀመራቸው ይታወቃል። በሌላ በኩል በርካታ የህወሓት ታጣቂዎች እጃቸውን ለመከላከያ ሠራዊት እየሰጡ እንደሚገኙም ተሰምቷል። (አስደሳች ዜና ነው!)
ባለፈው ሳምንት በደቡብ አፍሪካ በመንግስትና በህወሓት መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ታዲያ በትግራይ በምግብ ፍጆታዎች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ ታይቷል ተብሏል። (የሰላም አንዱ ትሩፋት ይኼ እኮ ነው!) ቢቢሲ እንደዘገበው፤ ቀደም ሲል የአንድ ኩንታል ጤፍ ዋጋ 14ሺ ብር የነበረ ሲሆን አሁን ወደ 8ሺ ብር ዝቅ ብሏል። 9ሺ ብር ደርሶ የነበረው የአንድ ኩንታል ስንዴ ዋጋ ደግሞ ወደ 3ሺ ብር ወርዷል። (ገና በደንብ ይወርዳል!) በተመሳሳይ ሁኔታ የዘይት፣ የስኳርና የበርበሬ ዋጋም መጠነኛ ቅናሽ እንደታየበት ነው የተነገረው።
በመቀሌ የሚገኘው የቢቢሲ ጋዜጠኛ በከተማዋ ተዘዋውሮ እንደታዘበው፣ የበርካታ ነዋሪዎች የመነጋገሪያ አጀንዳ ባለፈው ሳምንት በፕሪቶሪያ የተፈረመው የሰላም ስምምነት ነው። (ባይሆን ነበር የሚገርመው!)
የመቀሌ ከተማ ነዋሪና የሁለት ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ  ራሄል አባይ፣ በሰላም ስምምነቱ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ለጋዜጠኛው ነግረውታል።
“….ጦርነቱ በሚደረግበት ቦታ የምንኖረው እኛ ነን። መሬት ላይ ምን እንዳለ የምናውቀው እኛ ነን። አሁን ቢያንስ የድሮን ጥቃት ሳያሳስበን መንቀሳቀስ ጀምረናል።” ብለዋል ወ/ሮ ራሄል፡፡
ሌላው የመቀሌ ነዋሪ የ32 ዓመቱ በላይ ታከለ፣ የሰላም ስምምነቱን አስመልክቶ በሰጠው አስተያየት፤ “እኛ የትግራይ ህዝቦች እንደተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ  ሁሉ በሰላም መኖርን ነው የምንሻው። ጦርነቱ ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለን እኛ ነን የምናውቀው። አሁን የምንሻው ፈራሚዎቹ ወገኖች ስምምነቱን እንዲያከብሩ ነው።” ብሏል።
ባለፈው ሳምንት የጀርመን ድምፅ ያነጋገራቸው የመቀሌ ነዋሪዎችም በተደረሰው የሰላም ስምምነት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፤ ሁሉም ወገኖች ለስምምነቱ ተግባራዊነት በቁርጠኝነት እንዲሰሩ ተማጽነዋል። ባለፉት ሁለት ዓመታት በህወኃት ተፅዕኖ ሥር ወድቀው የነበሩ የሃይማኖት አባቶችም ሳይቀሩ የሰላም ስምምነቱን እንደሚደግፉ ሰሞኑን  ገልጸዋል - በትግራይ ቴሌቪዥን ቀርበው። (ሌላ ምርጫ የላቸውም!)
 የሰላም ስምምነቱ በስኬት እንዲጠናቀቅ የሚፈልጉት የትግራይ ተወላጆች ብቻ ግን አይደሉም። አማራውንና አፋሩን ጨምሮ መላው ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆችም የሰላም ስምምነቱ ወደ መሬት ወርዶ እውን ሆኖ ማየትን ይሻሉ። ኢትዮጵያውያን ጦርነቱ በዘላቂነት እንዲያበቃ፣ የጥይት ድምፅ ጨርሶ እንዳይሰማ፣ ወንድማማቾች እርስ በርስ እንዳይተላለቁ አጥብቀው ይሻሉ። ለዚህም ነው በደቡብ አፍሪካ ለተደረሰው የሰላም ስምምነት በአንድ ቃል የድጋፍ ድምጻቸውን ያሰሙት።
ይህ በዚህ እንዳለ፣  የትግራይ ህዝብ የተጀመረው የሰላም ስምምነት እንዳይደናቀፍ፣ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር በመሆን ዘብ ሊቆም ይገባል ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሃም በላይ ገልጸዋል። ይሄንን የሰላም ጅማሮ ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች ስላሉ፣ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ፣ ተዉ ሊላቸው እንደሚገባም  አስታውቀዋል፡፡
በተቃራኒው  የሰላም ስምምነቱ የቆረቆራቸው ጥቂት በአሜሪካና አውሮፓ የሚኖሩ ጽንፈኛ ትግራዋይ ዳያስፖራዎች፣ እንደለመዱት በፈረንጅ ጎዳና ላይ ሲቀውጡት ሰንብተዋል። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ በሲያትል  በህገወጥ መንገድ ዋናውን አውራ ጎዳና በተሽከርካሪዎች ዘግተው በፖሊስ ሃይል መበተናቸውን ነው ፎክስ ኒውስ የዘገበው፡፡  የሰላም ስምምነቱን በመቃወም አደባባይ የወጡት እነዚህ ጽንፈኛ ትግራዋይ ዳያስፖራዎች፤ በትግራይ የሚካሄደውን ጦርነት ለመቃወም ነው የወጣነው ሲሉ የፎክስ ኒውስ ዘጋቢን እንደለመዱት አሳስተውታል - Misinform አድርገውታል። (መንግስትና ህወሓት የተፈራረሙት የጦርነት ስምምነት ነው እንዴ?)
እነዚህ ትግራዋይ ዳያስፖራዎች “የሰላም ስምምነቱን ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የተፈራረመው ህወሓት፤ የትግራይ መንግስትን አይወክልም፤TPLF ማለት TDF አይደለም” የሚል አስቂኝ ጨዋታ ይዘው ከተፍ ብለዋል። (አለማፈራቸው!) ስታሊን የተባለ የተጨበጨበለት ኮሜዲያናቸው፤ “ህወሓት በትግራይ እንደሚገኙ ሌሎች ፓርቲዎች እንደ እነባይቶና አንድ ፓርቲ ነው። እንደውም ህወሓት ከብርቱካን ሚደቅሳ ቢሮ  የተሰረዘ ፓርቲ ነው” በማለት  ያልተዋጣለት ቀልድ ቀልዷል።  (ከዚህ በላይ በትግራይ ህዝብ መቀለድ አለ?!) ይሄ ሁሉ እንግዲህ የትግራይ ህዝብና መላው ኢትዮጵያውያን በደስታ የተቀበሉትንና ተግባራዊነቱን በጉጉት የሚጠብቁትን የሰላም ስምምነት ለማጣጣልና ለማደናቀፍ ነው። (የሚሳካላቸው ባይመስልም!) እነዚህ በሪሞት ኮንትሮል ትግራይንና ጦርነቱን መምራት የሚሹ ትግራዋይ ዳያስፖራዎች፣ ስለ ትግራይ ህዝብ እውነቱን በጥቂቱ  ማወቅ ይገባቸዋል። (ከኋላ ፀፀት እንዲድኑ!)
እውነት 1- የትግራይ ህዝብ ከእንግዲህ በምንም ዓይነት ሁኔታ የራሱንና የልጆቹን ህይወት ለጦርነት እየገበረ መቀጠል አይፈልግም።
እውነት 2- የትግራይ ህዝብ ከእንግዲህ በምንም ዓይነት ሁኔታ ከጎረቤት ወንድም እህት- የአማራና አፋር ህዝቦች ጋር ደም እየተቃባ መኖር አይሻም። (የራሱን ዘመን በመከራና በሰቆቃ አሳልፎ ለቀሪው አዲስ የትግራዋይ ትውልድ ቂምና በቀልን ማውረስ ምርጫው አይደለም!)
እውነት 3- የትግራይ ህዝብ ከእንግዲህ በምንም አይነት ሁኔታ የጥይት ድምጽ እየሰማ ኑሮውን በስጋትና በሰቀቀን መግፋት አይፈልግም።
እውነት 4- ከእንግዲህ በምንም ዓይነት ሁኔታ ነፍጥ ባነገቡ ጥቂት ቡድኖች መዳፍ ስር ህይወቱን በአፈና  መግፋት አይመርጥም።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በሃሰት የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ፣ ተከበሃል፤ ተብሎ ለጦርነት የተቀሰቀሰው የትግራይ ህዝብ፤ ከአሰቃቂው ጦርነት ያተረፈውን  ያውቀዋል። በብዙ መቶ ሺዎች  ወጣቶቹን ነው ያጣው። ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር ተብሎ የእርዳታ ስንዴ ጠባቂ ነው የተደረገው። በመድኃኒትና ህክምና እጦት ወገኖቹን ነው የተነጠቀው።
ባለፉት ሁለት ዓመታት የትግራይ ህዝብ ተኝቶ መነሳት፣ ተርቦ መብላት፣ ታሞ መዳን፣ ወልዶ መሳም፣ ነገን ማለም… ባጠቃላይ ኑሮ  ቅንጦት ሆኖበት ነው ያሳለፈው። የትግራይ ህዝብ ማንም ከሚናገረውና ከሚደሰኩረው የከፋ የሲኦል ህይወት አሳልፏል- በጦርነቱና መዘዞቹ። ለዚህም ነው የደቡብ አፍሪካውን የሰላም ስምምነት ሲሰማ ደስታውን የገለፀው- ፀሎቴ ሰመረ ብሎ ፈጣሪውን ያመሰገነው! እውነቱን ነው፡፡ ከሁሉም በፊት በህይወት መኖር ይቀድማል። በህይወት ለመኖር ደግሞ ሰላም ያስፈልጋል። ስለዚህ ሁሉም ወገን ለሰላም ስምምነቱ እውን መሆን ከልቡ እንዲተጋ ተማፀነ። በልቡ ለፈጣሪው እየፀለየ!!
በአሜሪካና አውሮፓ ማክዶናልድ እየገመጡ ለሁለት ዓመታት ጦርነቱን ግፋ በለው ሲሉ የከረሙ ፅንፈኛ ትግራዋይ ዳያስፖራዎች ግን የሰላም ስምምነቱን በመቃወም  ጩኸት ጀመሩ። በተቃውሞ የአሜሪካ አውራጎዳናዎችን ዘጋግተው አረፉ - በህገወጥ መንገድ። እነሱ ምን ቸገራቸው! የጦርነቱ ወላፈን ጫፋቸውን አይነካቸውም። ልጆቻቸው የጥይት እራት አይሆኑባቸውም። በህክምናና መድሃኒት እጦት አይሰቃዩም፡፡ በረሃብ አያልቁም። መከራና ሰቆቃ አይደርስባቸውም።
እነርሱ እንግዲህ ለሁለት ዓመታት በጦርነቱ የተሳተፉት በፌስቡክ፣ በዩቲዩብና በትዊተር ብቻ ነው። ቢበዛ ከእነ ደብረፅዮን ጋር የዙም ስብሰባ  አድርገው ይሆናል። እርግጥ ነው ጦርነቱ እንዲፋፋም ዶላር አዋጥተዋል። በአሜሪካ ጎዳናዎች ተንከባለዋል። ይኸው ነው ተጠቃሽ  ተሳትፏቸው። ለእነሱ ጦርነቱ የትርፍ ጊዜ ስራ ነበር- ሆቢያቸው- መዝናኛቸው! ስለዚህ ጦርነቱ ቢቀጥል ብዙ አይጨንቃቸውም። ትጥቅ መፍታት ለእነሱ ውርደት ነው። እጅ መስጠት ነው፡፡ (የትግራዋይ እልቂትስ?) እናም የሰላም ስምምነቱን ለማደናቀፍ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ በትግራይ ምድር ለሚኖረው ትግራዋይ ግን ብቸኛው ተስፋው የሰላም ድርድሩ ነው። የነገ ህይወቱን አሻግሮ የሚያልምበት ድልድይ ነው። ሌላ ምርጫ የለውም- ከሰላም ውጪ!!
ስለዚህ ለጽንፈኛ ትግራዋይ ዳያስፖራዎች እንዲህ እንላቸዋለን - እባካችሁ አሁን እንኳን የትግራይን ህዝብ ተውት! የመረጠውን ይኑር!! ሞትና ጦርነት አንገፍግፎታል። የሰላም አየር  ናፍቆታል።  በፈጠራችሁ ተውት! ይኑርበት!
ፈጣሪ ለኢትዮጵያ ሰላምን ያውርድ!


Read 823 times