Saturday, 12 November 2022 11:39

በኦሮሚያ ክልል በንፁሃን ላይ የሚፈጸመው የግፍ ጭፍጨፋ ተባብሶ ቀጥሏል

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(11 votes)

   - ኢሰመጉ የፌደራል መንግስትና የኦሮሚያ ክልል መንግስት በንፁሃን ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ባስቸኳይ እንዲያስቆሙ አሳስቧል
    - ባለፈው ጥቅምት ወር ብቻ ቁጥራቸው ያልታወቀ በርካታ ንፁሃን በታጣቂዎች ተገድለዋል
    - በሸኔ ታጣቂዎች በተከበበችው ጊምቢ ነዋሪ የነበሩ ከ1800 በላይ አባወራዎች በፌደራል ፖሊስ ታጅበው ወደ ሌላ ቦታ ተወስደዋል
    - ከአዲስ አበባ አዋሳ ፈጣን መንገድ ላይ በሚጓዙ መኪኖች መቂ ከተማ አካባቢ ታጣቂዎች ተኩስ ከፍተው መንገደኞችን በመግደል መኪኖችን   አቃጥለዋል
             
        በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ላይ በንፁሃን የሚፈጸመው የግፍ ጭፍጨፋ ተባብሶ መቀጠሉ ተገለጸ። በሸኔ ታጣቂዎች ተከባ በምትገኘው የጊምቢ ከተማ ቶሌ ቀበሌ ውስጥ ነዋሪ የነበሩ ከ1800 በላይ አባወራዎች በፌደራል ፖሊስ ታጅበው አካባቢያቸውን ለቀው ወጥተዋል ተብሏል። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባዔ፣ የፌደራል መንግስትና የኦሮሚያ ክልል መንግስታት፣ በንፁሃን ላይ የሚፈጸመውን የግፍ ጭፍጨፋ ባስቸኳይ ሊያስቆሙ እንደሚገባ ገልጿል፡
ታጣቂ ቡድኑ ከአራት ወራት በፊት በፈጸመው ጥቃት፣ ከ400 በላይ ሰዎች በግፍ እንደተጨፈጨፈባት በተገለጸችው የምዕራብ ወለጋ  ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌን ለዳግም ጥቃት ወርሮ መያዙንና ይኼን ተከትሎም በአካባቢው የሚኖሩ ከ1800 በላይ አባወራዎች፣ በፌደራል ፖሊስ ታጅበው አካባቢያቸውን ለቀው እንዲሄዱ መደረጉም ታውቋል።
በዚሁ የምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ከተማ ቶሌ ቀበሌ ውስጥ ነዋሪ የነበሩት ከ1800 በላይ አባወራዎች ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ላይ ከመንግስት የፀጥታ ሃይሎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ እንደተናገራቸውና በያዝነው ሳምንት መጀመሪያም በፌደራል ፖሊስ ታጅበው በምስራቅ ወለጋ ዞን ወደሚገኘው አርጆ ጉደቱ ወደተባለ አካባቢ መሸሻቸውን ለማወቅ ተችሏል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ትናንት ባወጣው መግለጫ ይህ በንፁሃን ላይ  በሸኔ ታጣቂ ሃይሎች እየተፈፀመ የሚገኘው የግፍ ጭፍጨፋ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መሄዱን አስታውቋል። ተቋሙ በዚሁ መግለጫው የታጠቁ ቡድኖች ባደረሱት ማንነትን መሰረት ባደረጉ ጥቃቶች በአንድ ወር ብቻ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ በርካታ ንፁሃን ዜጎች  በግፍ መጨፍጨፋቸውን አስታውቋል።
መግለጫው እንዳመለተው፤ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ከሳስጋ ወረዳ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኝ ፅጌ ከተማ ጥቅምት 8 እና 9 ቀን 2015 ዓ.ም ታጣቂ ቡድኖች ባደረሱት ጥቃት፤ በቁጥር ያልታወቁ ነዋሪዎች ለሞትና ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል ብሏል። ጥቅምት 19 ቀን 2015 ዓ.ም ከጊዳ አያና ወደ ነቀምት በሚወስደው መንገድ ላይ በህዝብ ትራንስፖርት ሲጓዙ በነበሩ ተማሪዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት፤ ለጊዜው ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች ተገድለዋል። ከጥቅምት 21 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ከነቀምት ወደ ምዕራብ ወለጋ ቄለም ወለጋ እና አሶሳ የሚወስደው መንገድ በሸኔ ታጣቂዎች መዘጋቱን የገለጸው መግለጫው፤ በዚህ ስፍራ ላይ ከመንግስት የጸጥታ  ሃይሎች ጋር የተኩስ ልውውጥ መደረጉንና በርካታ ንፁሃን መገደላቸውን አስታውቋል። ጥቅምት 27 ቀን 2015 እና ጥቅምት 28 ቀን 2015 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ አርሲ ዞን ጀጁ ወረዳ ሐሩታ ዶሬ ቀበሌ እንዲሁም አምሻራ መንበር ህይወት፣ ተስፋ ህይወት፣ መርቲ እና አጫሞ ቀበሌዎች ውስጥ በሚኖሩ ሰዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙንና በሁለት ቀናት ብቻ ከ27 በላይ ንፁሃን በግፍ መጨፍጨፋቸውን መግለጫው አመላክቷል።
ጥቅምት 27 ቀን 2015 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ዞን ሳሰጋ ወረዳ ውስጥ በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ 15 የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች በአሰቃቂ ሁኔታ በታጣቂዎቹ መገደላቸውን ማረጋገጡን ኢሰመጉ በመግለጫው ጠቁሟል። በምዕራብ ሸዋ ዞን ኢመያ ወረዳ ቡርቃ ቀበሌ ጥቅምት 24 ቀን 2015 የሸኔ ታጣቂዎች በእርሻ ስራ ይተዳደሩ የነበሩ 4 ሰዎችን አግተው ከወሰዷቸው በኋላ እያንዳንዳቸው 300 ሺ ብር ከከፈሉ ከእገታው እንደሚለቋቸው የነገሯቸው ሲሆን የታጋቾቹ ቤተሰቦች ገንዘቡን አሰባስበው ቤተሰቦቻቸውን ለማስለቀቅ ሲሄዱ ታጋቾቹ እጅግ ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ ተገድለው መገኘታቸውንም መግለጫው አመላክቷል።
ከአዲስ አበባ ወደ አዋሳ በተከፈተው አዲሱ የፍጥነት መንገድ ላይ ጥቅምት 28 ቀን 2015 ዓ.ም መቂ ከተማ አካባቢ ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ ሰላማዊ መንገደኞችን እንደገደሉና በርካታ መኪኖችን እንዳቃጠሉም ኢሰመጉ በመግለጫው ላይ ጠቁሟል።
ይህ በታጣቂዎች በተደጋጋሚ በተለያዩ አካባቢዎች እየተወሰዱ ያሉ ጥቃቶች እና የንጹሃን ግድያ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል ያለው ሰብአዊ መብቶች ጉባዔ መግለጫ የፌደራል መንግስቱም ሆነ የኦሮሚያ ክልል መንግስታት በንጹሃን ላይ እየደረሱ ያሉ ጥቃቶችን በአስቸኳይ እንዲያስቆሙ ጠይቀዋል። ከላይ በተዘረዘሩት አካባቢዎች የደህንነት ሁኔታ አመቺ በሚሆንበት ጊዜ  ሰፋ ያለ የምርመራ ስራን በመስራት ዝርዝር ዘገባን እንደሚያዘጋጅም ጉባኤው በመግለጫው አስታውቋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የፈረጀው የሸኔ ታጣቂ ቡድን፣ በተለያዩ ጊዜያት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በምዕራብ ወለጋ ዞኖች ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ቀበሌዎች በተደጋጋሚ በፈጸማቸው ጥቃቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች በግፍ የተጨፈጨፉ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፤ ለስደት ተዳርገዋል፤ እርዳታ ጠባቂ ሆነዋል።



Read 26089 times