Saturday, 12 November 2022 10:30

የሴቶችና የሕፃናት ሰብአዊ መብቶች ዓመታዊ ሪፖርት ምን ይላል?

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  የኮቪድ ወረርሽኝ፣ ድርቅ፣ ጦርነትና ግጭት በሴቶችና ሕፃናት መሰረታዊ መብቶች ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደራቸው ተጠቁሟል

        የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፤ ከመስከረም 2014 ዓ.ም. እስከ ነሐሴ 2014 ዓ.ም. ያለውን ጊዜ የሚሸፍን የሴቶችና የሕፃናት ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ ሪፖርቱን ሰሞኑን ይፋ አድርጓል።
ይህ ባለ 36 ገጽ ዓመታዊ የሴቶችና የሕፃናት መብቶች የዘርፍ ሪፖርት፣ ኢሰመኮ ሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ይፋ ካደረገው አጠቃላይ የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት በተጨማሪነት በተለይ የሴቶችና የሕፃናት ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ በዝርዝር በማተኮር ኮሚሽኑ የለያቸውን አበረታች እመርታዎች፣ ዋና ዋና አሳሳቢ ጉዳዮችና ምክረ-ሃሳቦችን አካቷል። ኮሚሽኑ ሪፖርቱን ያዘጋጀው ባከናወናቸው ክትትሎች፣ ምርመራዎችና የመስክ ምልከታዎች፣ ባስተናገዳቸው የግለሰቦች አቤቱታዎች፣ የሕግና የፖሊሲ ግምገማዎች፣ ጥናቶችና ምክክሮች፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች እንዲሁም የውትወታና ሌሎች ሥራዎቹ ላይ በመመስረት መሆኑን ጠቁሟል።
የሴቶችና የሕፃናት ሰብአዊ መብቶችን ከማስጠበቅና ከማስፋፋት አንፃር በሕግ ረገድ የታዩ ክፍተቶች፣ የሴቶችና የሕፃናት ከጥቃትና ከብዝበዛ የመጠበቅ፣ ፍትሕና ውጤታማ መፍትሔ የማግኘት፣ ሕዝባዊ ተሳትፎ የማድረግ፣ በፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ያለው አያያዝ፣ የቤተሰብ መብቶች እንዲሁም የሴት ሠራተኞች ሁኔታ ሪፖርቱ ትኩረት ያደረገባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው ተብሏል።
በኢትዮጵያ በተከሰቱት ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት ሕፃናት ከመንግሥት፣ ከማኅበረሰብና ከቤተሰብ ማግኘት ያለባቸው ጥበቃ በመጓደሉ ለተደራራቢ የመብቶች ጥሰት መጋለጣቸውና ሴቶች በተፈጸሙባቸው ጾታዊ መድሎዎችና ጥቃቶች ምክንያት መሰረታዊ መብቶቻቸውን የሚጥሱ፣ ነጻነቶቻቸውን የሚገድቡ እንዲሁም ሰብአዊ ክብራቸውን የሚያጎድፉ በደሎች እንደደረሱባቸው በሪፖርቱ ተገልጿል። በተጨማሪም በብሔራዊ የሕግ ማዕቀፍ ውስጥም ለሕፃናትና ለሴቶች ሰብአዊ መብቶች በቂ የሕግ ከለላ በመስጠት ረገድ የተለያዩ ክፍተቶች መስተዋላቸው ተጠቅሷል።
በኢትዮጵያ የሰሜኑ ክፍል በተነሳው ጦርነትና ቀጥሎም በየመሀሉ ማገርሸቱ በሴቶችና በሕፃናት ላይ መጠነ-ሰፊ ጥቃቶች፤ በአንዳንድ ሁኔታዎች ለጦርነት ዓላማ ስልታዊ በሆነ መልኩ ጭምርም መፈጸማቸውም ተዘግቧል። ይሁን እንጂ ለተፈጸሙ ጥቃቶች ውጤታማ ፍትሕና መፍትሔ የሚያስገኝ የወንጀልና የፍትሐ-ብሔር የሕግ ማዕቀፍ አለመኖር፣ ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን ያሟላ የወንጀል ምርመራና የክስ አመሰራረት መጓደል በሪፖርቱ ከተዘረዘሩት ዋና ዋና አሳሳቢ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ። በሌላም በኩል በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሶማሌ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልሎች በተለያየ ወቅት በተነሱ ግጭቶችም ሴቶችና ሕፃናት ለተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መጋለጣቸው በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሴቶችና ሕፃናት ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸው፣ በተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥም ለጾታዊ ጥቃቶችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ተጋላጭ መሆናቸውና ልዩ ፍላጎታቸውን መሰረት ያደረጉ የሰብአዊ ድጋፎች አለማግኘታቸው ተደራራቢ የመብቶች ጥሰትን አስከትሏል ተብሏል። በሀገሪቱ በተከሰቱ የኮቪድ ወረርሽኝ፣ ድርቅ፣ ጦርነትና ግጭት ሳቢያ የትምህርትና የጤና አገልግሎቶች በመቋረጣቸው፣ ወይም የተለያዩ ገደቦች መኖራቸው በሴቶችና ሕፃናት ትምህርትና ጤና የማግኘት መሰረታዊ መብቶች ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደራቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል።
በተጨማሪም፣ ሴቶችና ሕፃናት ለሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ለብዝበዛ መጋለጥ፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚሠሩ ሴት ሠራተኞች መሰረታዊ መብቶች ጥሰቶች መቀጠልና በእነዚህ የመብቶች ጥሰት ረገድ የቁጥጥርና የተጠያቂነት መላላት ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑ ነው በሪፖርቱ የተጠቆመው።
በሕዝባዊ ጉዳዮች ላይ ከመሳተፍ መብት ጋር በተያያዘም፣ ሕፃናት በማናቸውም ጉዳይ ላይ ሃሳባቸውን በነፃ የመግለጽና በሚመለከታቸው ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ የማድረግ መብታቸውን ለመተግበር የሚያስችል ሕግ አለመኖር፤ ሴቶችም በምርጫና በፖለቲካ ውስጥ ውጤታማ ተሳትፎ እንዳያደርጉ የአመለካከት ችግሮችና ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እክል መፍጠራቸው፤ እንዲሁም በሰላም ግንባታና በሀገራዊ ምክክር እና ሌሎች የሕዝባዊ ውይይት መዋቅሮች ውስጥም ጾታዊ አካታችነት በእጅጉ ውስን በመሆኑ፣ የሴቶች ተሳትፎ ተገድቧል ብሏል፤ ሪፖርቱ።
ከወንጀል ጉዳይ ጋር በተያያዘ በፍትሕ ሥርዓት ውስጥ የሚያልፉ ልጆች አያያዝ ከሕፃናት ፍትሕ መርሆዎችና መመዘኛዎች ውጪ መሆን፣ በወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩ ሴቶች ሁኔታ ከመሰረታዊ የሴት እስረኞች አያያዝ መስፈርቶች ጋር አለመጣጣም፣ ከእናቶቻቸው ጋር በእስር ቤት የሚቆዩ ሕፃናት ትምህርትና አማራጭ እንክብካቤ የማግኘት መብቶች መጓደል፣ በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ ያሉ ክፍተቶች በሪፖርቱ ከተለዩ ጉድለቶች መካከል ናቸው። ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መስፈርቶች ጋር በተጣጣመ ሁኔታ ለሕፃናት ነፃና ለሁሉ ተደራሽ የሆነ የልደት ምዝገባ አሠራር በሀገር አቀፍ ደረጃ በሕግ አለመደንገጉ እንዲሁም በተወሰኑ ክልሎች ደግሞ የቤተሰብ ሕግ አለመውጣቱ ከተስተዋሉት የሕግ ክፍተቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የደኅንነት ሥጋቶች መቀጠላቸው የሴቶችንና ሕፃናትን ሁኔታ በሚፈለገው ቅርበት እና ፍጥነት ለመከታተል እንዳይቻል እንቅፋት የፈጠረ መሆኑ፣ በእነዚህ አካባቢዎች የሚሠሩ የሲቪል ማኅበራትና አጋሮች አቅምም መዳከሙና በኮሚሽኑ የሚሰጡ ምክረ ሃሳቦችን ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ በቅንጅት ለመሥራት የሚያስችል ጠንካራ የጋራ መድረክ አለመኖር ፈታኝ ሁኔታ መፍጠሩም ተጠቁሟል።
የኢሰመኮ የሴቶችና የሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ፣ የሴቶችንና የሕፃናት መብቶችን በተመለከተ ኮሚሽኑ ባከናወናቸው ክትትሎች፣ ምክክሮችና የተለያዩ ክንውኖች ትብብር በማድረግና ግብዓት በመስጠት ኃላፊነታቸውን ለተወጡ መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበው፣ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ሕፃናትና ሴቶች ከግጭት፣ ከጥቃትና ከመድልዎ ነፃ የሆነ፤ ዘላቂ ሰላምና እኩልነት የሰፈነበት ሕይወትን እውን ለማድረግ በሪፖርቱ የተካተቱትን ምክረ-ሃሳቦች በመፈጸምና በማስፈጸም የተቀናጀ ጥረትና ርብርብ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
ኮሚሽነር መስከረም አክለውም፤ “ሰብአዊ መብቶችን ማክበር፣ ማስጠበቅና ማሟላት የመንግሥት ዋነኛ ግዴታ በመሆኑ የሕግ ማዕቀፎችን፣ ተቋማትንና አሠራሮችን በማሻሻል፣ ፍትሕን ተደራሽ በማድረግ፣ በግጭቶች የወደሙ የትምህርትና የጤና ተቋማትንና ሌሎች መሰረተ-ልማቶችን መልሶ በመገንባትና ለተጎጂዎች ሁለንተናዊ ተሐድሶን በማመቻቸት የሕፃናትንና የሴቶችን ሰብአዊ መብቶች የማሻሻል ኃላፊነቱን መወጣት አለበት። በተጨማሪም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላትና ጠቅላላ ማህበረሰቡ በሰብአዊ መብቶች ማዕቀፍ በተቀመጠው አግባብ በሀገሪቱ የሴቶችና የሕፃናት መብቶች አፈጻጸምን በማረጋገጥ ረገድ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቀርባለሁ” ብለዋል።

Read 12632 times