Saturday, 20 October 2012 12:06

ትንሽ እውቀትና ጭፍን አመለካከት ፕሪንስ ጆንሰን እና ፓውሊን ንይራማሱሁኮ

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(1 Vote)

በክርስቲያኖች ቅዱስ መጽሐፍም ሆነ በአይሁዶች ታናካህ ውስጥ አምላክ ከፈጠራቸው ህዝቦች ሁሉ አይሁዳውያንን ለይቶ “ህዝቤ” እያለ እንደሚጠራቸው በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡ ይህ ገለፃ ለአይሁዶች የሁልጊዜም መጽናኛቸው ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአለማችን ካሉት ህዝቦች ሁሉ ለጭፍጨፋና ለእልቂት የጣፋቸው እንደእነሱ ያለ ህዝብ ለሞት መድሀኒት እንኳ ቢፈለግ አይገኝም፡፡
ማንኛውም ሰው ቢሆን ስለ አይሁዶች መጨፍጨፍ ሲያስብ በቅድሚያ የሚመጣለት የኦሽዊትዝ እልቂት ነው፡፡ ነገሩ እውነት ነው፡፡ በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት ከተፈፀሙት እጅግ አስከፊ ወንጀሎች ውስጥ ከሁሉም የላቀው በእነዚሁ የአይሁድ ህዝቦች ላይ የደረሰው እልቂት ነው፡፡ ያኔ ስድስት ሚሊዮን ይሁዲዎች በናዚ ጀርመን ወታደሮች እጅ እንደ ኦሽዊትዝና ቢርከናው ባሉ የጅምላ መግደያ ካምፖች ዝርዝሩ ተነግሮ የማያልቅ የምድር ላይ መከራ ተቀብለው አልቀዋል፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ይህ አስከፊ ፍጅት የሚገልፀው የቅርብ ጊዜውን የአይሁዶች የጭፍጨፋ ታሪካቸውን ብቻ ነው፡፡ ሁለቱ የአለም ጦርነቶች ከመከሠታቸው መቶ አመታት በፊት ጀምሮ በአውሮፓም ሆነ በመካከለኛው ምስራቅ አይሁዶች በሚኖሩበት ሀገር ሁሉ በሰበብ አስባቡ ሳይጨፈጨፉ ያሳለፉት ዘመን የለም፡፡ በእነዚህ ሀገራት ያንን ሁሉ ዘመን ያሳለፉት ጊዜ የመገለልና የመጨፍጨፍ፣ የተፃፈው ታሪካቸውም የእልቂትና የፍጅታቸው ታሪክ ብቻ ነው፡፡ 
በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት በአይሁዶች ላይ የተፈፀመው ፍጅት አሁንም ድረስ የእልቂቶችና የፍጅቶች ሁሉ እናት ተደርጐ ይቆጠራል፡፡ በዚህ እጅግ አስከፊ እልቂት ውስጥ ግን በሚሊዮን የሚቆጠሩ የበርካታ ሀገራት ህዝቦች በግፍ የተጨፈጨፉበት በርካታ ዘግናኝ እልቂቶች ታጭቀዋል፡፡ የጃፓንን ጥቁር ታሪክ የምናገኘውም በዚህ እጭቅ ውስጥ ነው፡፡
እንደ እድል ሆኖ የናዚ ጀርመንን ያህል ስሟ ገኖ አይነሳ እንጂ በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት በሰው ልጅ ላይ ወደር የለሽ ግፍና አስከፊ እልቂት በመፈፀም ረገድ ጃፓንም የዋዛ ሀገር አልነበረችም፡፡ በጦርነቱ ወቅት በቻይናውያን፣ በኮሪያውያንና በፊሊፒኖች ላይ የፈፀመችው ግፍና ፍጅት በቀላሉ ተነግሮ የሚያልቅ ታሪክ አይደለም፡፡ ጀርመናዊው የናዚ ዶክተር ጆሴፍ ሜንጌሌ፤ በአይሁዳውያን ላይ የፈፀመው አሰቃቂ ድርጊት እንኳን በሌሊት በቀንም ቢሆን የሚያባንነውን ያህል የጃፓናዊውን ጀነራል ቶሞዩኪ ያሽማታን ታሪክ ማንበብም ልብን በሀዘንና በድንጋጤ ያደነዝዛል፡፡
እስከ ዛሬ ድረስ በአለማችን የተካሄዱትን አስከፊና ዘግናኝ ጭፍጨፋዎችን ታሪክ መርምረው ያጠኑ ሰዎች፣ የጭፍጨፋውና የእልቂቱ ተዋናዮች ያንን የመሠለ ለመንገር የሚከብድ የጭፍጨፋ ወንጀል ለመፈፀም ያነሳሳቸውን በርካታ ምክንያቶች ዘርዝረው አቅርበዋል፡ ባለሙያዎቹ ካቀረቧቸው ረዥም ዝርዝር ውስጥ የዘር ጥላቻና ጭፍን የሀይማኖት አስተሳሠብ በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳሉ፡፡ እነኚህ ሁለቱ ከሁሉም የበለጡ እጅግ አደገኛ ናቸው፡፡ በተግባር ላይ ሲውሉ ጠንቃቸው እንዲህ ነው ተብሎ የሚነገርበት መስፈሪያ የለውም፡፡
ኡም ሽንሪኪዬ (ታላቁ እውነት) የተሰኘ የራሱን እምነት ፈጥሮ በርካታ ተከታዮች ማፍራት የቻለው፣ ሶኮ አሳሀራ በቶኪዮ የምድር ውስጥ የባቡር ጣቢያ ላይ የሳሪን ጋዝ በመልቀቅ የጅምላ ፍጅት ለመፈፀም የሞከረው፣ አለምን “ከሀጢያተኞችና ከእርኩሶች” ለማድዳት ከሚል የራሱ ጭፍን የሀይማኖት አስተሠሳሠብና ግብ በመነሳት ነበር፡፡
ጃፓናዊው ጀነራል ቶሞዩኪ ያሽማታ ደግሞ ጃፓንና ጃፓናውያን የድፍን እስያ አህጉር አውራና ቀዳሚም ሆነ ተከታይ የሌላቸው የበላይ ገዥ ናቸው ብሎ ያምን ነበር፡፡
ጀነራሉ እንደሚለው ጃፓን በሁለተኛው የአለም ጦርነት ጊዜ ቻይናን፣ ኮርያን፣ ፊሊፒንስንና ሌሎች የእስያ ሀገራትን የወረረችው እንዲሁ የወረራ ሱሷን ለማርካት አልነበረም፡፡ በበላይነቷና በገዥነቷ ያልሰለጠኑትን ለማሰልጠን ያለባትን ታሪካዊ ሀላፊነት ለመወጣት ብላ ነው እንጂ ብሎ ከልቡ ያምን ነበር፡፡ የጃፓንን የበላይነትና ገዥነት ለማይቀበሉትም እንጥፍጣሪ ርህራሄ ብሎ ነገር አልፈጠረበትም ነበር፡፡
ታዲያ በውጊያም ይሁን በሌላ አጋጣሚ በእጁ የወደቁትን እድለ ቢስ ሰዎች ከግንድ ጋር ታስረው በእሳት እንዲቃጠሉ፣ እጅ እግራቸው ታስሮ ከፊትና ከሁዋላ በበርካታ ወታደሮች ተጐትተው ተበጣጥሰው እንዲሞቱ፣ እስከ አንገታቸው ድረስ ከነህይወታቸው እንዲቀበሩና ወታደሮቹ የኢላማ ተኩስ መለማመጃ እንዲያደርጓቸው በማዘዝ፣ ተለይቶ በተሠናዳለት መቀመጫ ላይ ዘና ብሎ ተቀምጦ ያገሩን አረቄ እየጠጣና ሲጃራውን እያቦነነ፣ ልክ እንደ ህፃን ልጅ እየቦረቀና ልቡ እስኪፈርስ ድረስ እየሳቀ፣ ይዝናና ነበር፡፡
የናዚ ጀርመኑ አዶልፍ ሂትለርም ስድስት ሚሊዮን የሚሆኑትን ይሁዲዎች በማጐሪያ ካምፖች ውስጥ አጉሮ የፈጃቸው የተጠናወተውን የዘር ጥላቻ ዛር ተገቢውን ምስ ለማጉረስ ነበር፡፡ ቀድሞውኑ ሀ ተብሎ ሲጀመር አዶልፍ ሂትለርም ሆነ ጀነራል ያሽማታ እንዲህ ያለውን አስከፊ ወንጀል ለመፈፀም ያስቻላቸውን የዘር ጥላቻ ከየት አመጡት ብላችሁ ከጠየቃችሁ ደግሞ ትክክለኛው መልስ ከእውቀት ማነስና ከጭፍን የጥላቻ አመለካከት የሚል ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን እንዲህ ያለ ነገር ሲያጋጥማቸው “በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ” እያሉ ይተርታሉ፡፡ በእርግጥ እውነታቸውን ነው፡፡ የእውቀት ማነስና ጭፍን አመለካከት እጅግ አደገኛና በበርካታ ሀገራት በተግባር ተደጋግሞ እንደታየው አጥፊ ውህድ ናቸው፡፡ ሰዎች ትንሽዬ እውቀት አደገኛናት ሲሉ ከሰማችሁ እመኗቸው፡፡ ለምን ቢባል እውነታቸውን ነዋ! በአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን የአውሮፓ ዘረኞች፤ ኢንዶ አውሮፓውያን ዝቅተኛዎቹንና የበታቾቹን የሴሜቲክና ኤሽያቲክ ህዝቦችን ያስገበሩ ምርጥ ነጮች ናቸው ይሉ ነበር፡፡ ከዚህ አስተሳሠብ በመነሳትም በሀያኛው ክፍለ ዘመን ላይም አዶልፍ ሂትለር “ምርጥና ንፁህ የሆኑት የአርያን ዘሮች” ባለ ዘንፋላ ነጣ ያለ ፀጉርና ባለ ሰማያዊ አይኖቹ ጀርመኖች ብቻ ናቸው፡፡ ስለዚህ የጐረቤቶቻቸውን ሀገራት ህዝቦች ለማስገበር ነፃ መብት አላቸው በማለት የዘረኝነት ሰበካውን ያቀነቅን ነበር፡፡
እነዚህ የዘረኝነት ስብከቶችና ጭፍን እምነቶች ግን አንዳች አይነት ታሪካዊም ሆነ ሳይንሳዊ መሠረት ጨርሶ የላቸውም፡፡ አዶልፍ ሂትለር ለሩስያውያን በነበረው ከፍተኛ ጥላቻ የተነሳ ንፁህና ምርጥ የሆኑት የአርያን ዘሮች የመጡት ከአይስላንድ አጠገብ ከምትገኝ ቱሌ የተሠኘች ደሴት ነው በማለት ሽንጡን ገትሮ ይሟገት ነበር፡፡
ሂትለር ይህን ሀሳብ ሰንዝሮ ሲሟገት የሀሳቡን ታሪካዊና ሳይንሳዊ ተጨባጭ መሠረት ነገሬ ወይም ጉዳዬ ብሎት አያውቅም ነበር፡፡ የእውቀት ማነስና ጭፍን አመለካከት ማለት ደግሞ ይኸው ነው፡፡
የሰው ዘርን አመጣጥ የሚያጠኑ ባለሙያዎች፣ በአፋር ክልል በቁፋሮ ባገኙት በሚሊዮን አመት የሚቆጠር እድሜ ያለው የሰው ቅሬተ አካል አማካኝነት፣ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ሀገር እንደሆነች አስረግጠው ይናገራሉ፡ኢትዮጵያውያን ይህንን እውነት ጠንቅቀው ያውቃሉ፡ ነገር ግን የአዳም ዘር ግንድ እኛ ነን፣ አርያኖችም ሆኑ ሴሜቲኮች የዘር ግንዳቸው የሚቀዳው ከእኛው ነው በሚል “ጉራቸውን” ሲነዙ ታይተውም ሆነ ተሰምተው አይታወቅም፡፡
አዶልፍ ሂትለር እንዲህ ያለውን ጉዳይ በቀላሉ ሊረዳው አይችልም ነበር፡፡ ሽንጡን ገትሮ ይሟገትለት ለነበረው ሀሳብ የሚያቀርበው ማስረጃም አልነበረውም፡፡
ቀደም ብለን እንደገለጽነው የዘረኝነት እምነቱን የመሠረተው በትንሽ እውቀትና በጭፍን አመለካከት ብቻ ነበር፡፡ የምርጦቹ የአርያን ዘሮች ቀደምት መፍለቂያ ናት ተብላ በሂትለር የተገለፀችው የቱሌ ደሴት፤ ትናንትም ሆነ ዛሬ የምትገኘው እንደተባለው በአይስላንድ አጠገብ ሳይሆን በእነ ሂትለር ዘረኛ አፈታሪክ ውስጥ ብቻ ነው፡፡
ንፁህና ምርጥ የተባሉትን የአርያን ዘሮችን ማንነትና ሁለንተናዊ ገጽታ እንዲያው ለአመል ያህል እንኳ የሚያሳይ የቅሬተ አካልም ሆነ ሌላ ተጨባጭ ማስረጃ ማቅረብ የቻለ አንድም ሰው ዛሬም ድረስ ከቶውንም አልተገኘም፡፡
እንግዲህ ልብ አድርጉ፡፡ የካምቦዲያውን ፖል ፖትና የሰርቢያውን ሰሎቦዳን ሚሎስቪችን ጨምራችሁ እያሰባችሁ እንደ ሂትለርና ጀነራል ያሽማታ አይነት የጥቁር ታሪክ ባለቤቶች የሚገኙት በአውሮፓና በእስያ ብቻ ይሆናል ብላችሁ ከገመታችሁ አንድም የአፍሪካን ታሪክ በቅጡ አያውቁትም አሊያም የነገሩን ዙሪያ መለስ ገጽታ በወጉ አልጨበጡትም ብለው ሰዎች ሊታዘቧችሁ ይችላሉ፡፡ የዘር ጥላቻና ጭፍን የሀይማኖት አመለካከት በዘር፣ በቀለምና በድንበር አይከለሉም፡፡
በአፍሪካ ለዘመናት ሲካሄድ የነበረውን የግጭት፣ የጦርነትና የታሪክ መጽሀፍ ማገላበጥ ከቻላችሁ ስለ ላይቤሪያ ከሚተረከው ምዕራፍ ውስጥ የፕሪንስ ጆንሰንን፣ የሩዋንዳን ታሪክ ከሚዘግበው ሰፊ ምዕራፍ ውስጥ ደግሞ የፓውሊን ንይራማሱሁኮን ታሪክ በሰፊው ተጽፎ ታገኙታላችሁ፡፡
ጋና ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ነፃነቷን ከመቀዳጀቷ ከአንድ መቶ አስር አመታት በፊት በአሜሪካኖች የተመሠረተች አፍሪካዊት ሀገር ማን ትባላለች ተብላችሁ ቀላል የታሪክ ጥያቄ ብትጠየቁ መልሳችሁ መሆን የሚገባው ላይቤሪያ የሚል ብቻ ነው፡፡ በዚያን ዘመን አሜሪካኖች ላይቤሪያን እንደ ሀገር ያቋቋሟት ነፃነታቸውን የተጐናፀፉ አፍሪካውያን ባሮችን እዚያ ወስደው በማስፈር ነበር፡፡ ይህን የአመሠራረት ታሪኳን በሚገባ ያውቁ የነበሩ የታሪክ ባለሙያዎችና ነጋዴዎች ላይቤሪያን ያኔ ወላጅ አልባዋ አፍሪካዊት የአሜሪካ የበኩር ልጅ እያሉ ይጠሩዋት ነበር፡፡
ጋና ጀመረችው እየተባለ የሚነገረው አፍሪካ ከአውሮፓ ቅኝ ግዛት ነፃ የወጣችበት የታሪክ መዝገብ ውስጥ በአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች እጅ ያልወደቁ ተብለው ሁለት አገራት ብቻ ተመዝግበው ይገኛሉ፡፡ እነሱም ኢትዮጵያና ላይቤሪያ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ነፃነቷን እንዴት አስከብራና ጠብቃ እንደኖረች ታሪኩን መላው አለም ጠንቅቆ ያውቀዋል በማለት ኢትዮጵያውያን ይናገራሉ፡፡ ላይቤሪያን በተመለከተ ግን ቅኝ ገዢዎቹ አውሮፓውያን ያልገዟት ያን ጊዜ ላይቤሪያን የሚቆጥሯት እንደ አንድ አፍሪካዊት ሀገር ሳይሆን እንደ አንድ የአሜሪካ ግዛት ወይም ደግሞ በአሜሪካ ጥበቃ ስር እንዳለች ሀገር ስለነበረ ነው ይባላል፡፡ ይህንን የሚሉት የአለም አቀፍ ታሪክ ተመራማሪዎች እንጂ ኢትዮጵያውያን አይደሉም፡፡ የላይቤሪያ ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ መጽሐፍ አብዛኛውን ገጽ ሞልተው የያዙት ሁለት አይነት ጉዳዮች ናቸው፡፡ በአፍሪካ የመሪዎች ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት ፕሬዚዳንት ያስመረጠች ብቸኛዋ ሀገር መሆኗና ከ1989 እስከ 1995 ዓ.ም ድረስ የተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነትና እሱን ተከትሎ የመጣው የፖለቲካ ውጣ ውረድ ናቸው፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ተመርጠው ላይቤሪያን በፕሬዚዳንትነት እየመሩ የሚገኙት ኤለን ጆንሰን ሲርሊፍ በአፍሪካ ታሪክ የመጀመሪያዋ በህዝብ ድምጽ የተመረጡ (አጭበርብረውም ቢሆን) ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ በ1989 ዓ.ም ተጀምሮ ለስድስት አመታት ሳያቋርጥ የተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ትቶት የሄደው ጠባሳ እስከዛሬ ድረስ እንኳ አልጠገገም፡፡
ታዲያ የዚያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን ላይቤሪያውያንን ህይወት ቅርጥፍ አድርጐ የበላውና ሀገሪቱንም እንዳልነበረች ያህል ያንኮታኮታተው ጠንቀኛ ጦርነት ታሪክ ሲነሳ፣ ምንም አይነት ሰበብ ቢደረደር ስማቸው ሳይነሳ የማይታለፉ ሶስት ላይቤሪያውያን አሉ፡፡ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ዶ፣ ቻርለስ ቴይለርና ፕሪንስ ጆንሰን፡፡
የእርስ በርስ ጦርነቱ በ1989 ዓ.ም የተጀመረው ፕሬዚዳንት ቶልበርት ተብማንን በተገኙበት በጥይት ደብድበው በመግደል፣ የፕሬዚዳንትነት ስልጣኑን የያዙትን የሀምሳ አለቃ ሳሙኤል ኪንየን ዶን ከስልጣን ለማስወገድ በሚል ነበር፡፡ ያኔ ቻርለስ ቴይለርና ፕሪንስ ጆንሰን የአማፂያኑ መሪዎች ነበሩ፡፡
ከመጀመሪያው ዙር የእርስ በርስ አሰቃቂ ጦርነት ፍፃሜ በኋላ ከ1997 እስከ 2005 ዓ.ም ድረስ ላይቤሪያን በፕሬዚዳንትነት የመሩት ቻርለስ ቴይለር፤ ናቸው፡፡ እኒህ ሰው ዛሬ የሚገኙት በስልጣን ዘመናቸው በሰብአዊነት ላይ በፈፀሙት ወንጀል በአለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት የሀምሳ አመት እስር ተፈርዶባቸው ዛሬ የሚገኙት ዘሄግ በሚገኘው ወህኒ ቤት ውስጥ ነው፡፡
ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ዶ ደግሞ በጦርነቱ ወቅት በአማፂያኑ ተማርከው ተገድለዋል፡፡ ፕሪንስ ጆንሰንስ ያላችሁ እንደሆነ ደግሞ የምታገኙዋቸው በላይቤሪያ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት ውስጥ አንቱ የተባሉ ፖለቲከኛ ሆነው ነው፡፡ የላይቤሪያም ሆነ የአለም አቀፍ ፖለቲካ አዋቂዎች ፕሪንስ ጆንሰንን የላይቤሪያ አዲሱ “ንጉስ ሿሚ” በማለት ይጠሯቸዋል፡፡
ነገሩ ምንም አይነት ስህተት የለውም፡፡ ፕሬዚደንት ኤለን ሲርሊፍ በ2011 ዓ.ም በተካሄደው ህዝባዊ ምርጫ በድጋሚ መመረጥ የቻሉት በፕሪንስ ጆንሰን እርዳታ አማካኝነት ነው፡፡ ፕሪንስ ጆንሰን ደጋፊዎቻቸው ለኤለን ሲርሊፍ ድምፃቸውን እንዲሰጡ ባያደርጉላቸው ኖሮ ሀይለኛ ተፎካካሪያቸው የነበሩትን ዊንስተን ተብማንን ጨርሶ ማሸነፍ አይችሉም ነበር፡፡
አሁን መቅረብ ያለበት ጥያቄ እንዲህ የሚለው ነው፡፡ ለመሆኑ አዲሱ የላይቤሪያ ንጉስ ሿሚ ለመሆን የበቁት ፕሪንስ የርሚ ጆንስን ማን ናቸው? እኒህ ሰውዬ ትናንትና ማንና ምን አይነት ሰው ነበሩ? የሩዋንዳዋ ወይዘሮ ፓውሊን ንይራ ማሱሁኮስ ብትሆን ማን ናት?

 

br /

Read 6704 times Last modified on Saturday, 20 October 2012 12:42