Saturday, 22 October 2022 17:07

የኤች ፒ ቪ (HPV) በሽታ እና ክትባት

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(3 votes)

ኢትዮጵያ የኤች ፒ ቪ (HPV) ክትባት 90% በመስጠት ከአፍሪካ ቀዳሚ ናት
            አቶ ዮሀንስ ላቀው የጤና ሚንስትር የብሄራዊ ክትባት ፕሮግራም አስተባባሪ
ኤች ፒ ቪ (human papilloma virus) ከአባላዘር በሽታዎች ውስጥ የሚመደብ በሽታ ነው። በአለም አቀፍ ደረጃ ከ15 እስከ 59 የእድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ 5 ሰዎች መካከል በ2 ሰዎች ወይም 40% የኤች ፒ ቪ (HPV) በሽታ እንደሚገኝ ይገመታል። በዚህም በአለም አቀፍ በአንድ አመት ውስጥ 570 ሺ ሴቶች እና 60ሺ ወንዶች የበሽታው ተጠቂ ይሆናሉ። የግብረ ሥጋ ግንኙነት በሚፈጽሙ ሴቶች እና ወንዶች ላይ በሕይወት ዘመን ውስጥ ቢያንስ አንድ ጊዜ በበሽታው የመያዝ እድል አለ። እንዲሁም በአንዳንዶች በተደጋጋሚ ይከሰታል። ከበሽታው ተጠቂዎች ውስጥ ከ90% በላይ የሚሆኑት ሰዎች ያገግማሉ።
የኤች ፒ ቪ (human papilloma virus)  በሽታ አይነቶች
ከ100 በላይ የቫይረሱ አይነቶች ያሉ ሲሆን ሁሉም ግን ጎጂ አይደለም። 14 የፓፒሎማ ቫይረስ አይነቶች ለካንሰር በሽታ የማጋለጥ እድል ሲኖራቸው ኤች ፒ ቪ 16 [HPV 16] እና ኤች ፒ ቪ 18 [HPV1 8] በመባል የሚጠሩት ሁለት የበሽታው አይነቶች ግን በዋነኘት የካንሰር ምክንያቶች ናቸው።
የአለም የጤና ድርጅት እንዳስቀመጠው ለማህፀን ጫፍ ካንሰር በሽታ ከ95% በላይ መንስኤ የሚሆነው ፓፒሎማ ቫይረስ (HPV) ነው። ምንም እንኳን አብዛኛው የኤች ፒ ቪ (HPV) ኢንፌክኣን ሊድን የሚችል ቢሆንም በሴቶች ላይ ግን ወደ ማህፀን ጫፍ ካንሰር የመለወጥ ከፍተኛ እድል አለው።
መተላለፊያ መንገድ
እንደ ሌሎች የአባላዘር በሽታዎች በግብረ ስጋ ግንኙነት ይተላለፋል። ይህም በመራቢያ አካል በሚደረግ የግብረስጋ ግንኙነት ብቻ ሳይሆን በሌሎች የሰውነት ክፍሎች የሚፈጸም ወሲብን ያካትታል። እንዲሁም በመራቢያ አካላት ንክኪ የመተላለፍ እድል አለው።
ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች
ሁሉም የግብረስጋ ግንኙነት የሚፈጽም ሰው በበሽታው የመያዝ እድል ቢኖረውም የመያዝ እድላቸው ከፍተኛ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ይገኛሉ። እነዚህም ከብዙ ሰዎች ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነት የሚፈጽሙ ሰዎች ወይም የእነርሱ አጋር፣ በሽታ የመከላከል አቅማቸው አነስተኛ የሆኑ ሰዎች ለምሳሌ የኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታ ተጠቂ የሆነ ሰው፣ በሌሎች የአባላዘር በሽታዎች ተጠቂ መሆን እና ሲጋራ ማጨስ በበሽታው የመያዝ እድልን ይጨምራል። በተጨማሪም በልጅነት የግብረ ስጋ ግንኙነት መጀመር ለኤች ፒ ቪ ኢንፌክሽን ብቻ ሳይሆን እሱን ተከትሎ ለሚከሰተው የማህጸን በር ካንሰር ተጋላጭ ያደርጋል።  
የበሽታው ምልክት
አብዛኛው የኤች ፒ ቪ በሽታ ምልክት ሳያሳይ ሊቆይ የሚችል እና ተጠቂው መታመሙን እንኳን ሳያውቅ ያለ ህክምና በርሱ ጊዜ በሽታው የሚጠፋበት ሁኔታ አለ። ነገር ግን በሽታው ምልክት ሳያሳይ ለአመታት ሲቆይ ተጠቂው ወደ ሌሎች ሰዎች ያስተላልፋል። እንዲሁም ምልክት ሳያሳይ የካንሰር በሽታ ሊያስከትል ይችላል። ለዚህም በሽታው አደገኛ ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያመላክት የማሳከክ ወይም የመድማት ምልክት ሊያሳይ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪም በሴቶች እና ወንዶች የመራቢያ አካል ላይ ኪንታሮት መሰል ምልክት ያሳያል። እንዲሁም በእጅ፣ እግር፣ ፊት እና ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ቆዳ ላይ ኪንታሮት መሰል ወይም የቆዳ ቀለም ተቀይሮ ጉዳት የደረሰበት የሚመስል አሊያም የቁስል መልክ ሊያሳይ ይችላል። ይህም ማሳከክ፣ የህመም ስሜት እና ምቾት የመንሳት ስሜት ያለው ነው።   
መከላከያ መንገድ
በሽታውን በመታቀብ፣ በመወሰን እና ኮንዶም በመጠቀም እንደ ሌሎች የአባላዘር በሽታዎች መከላከል እንደሚቻል ይመከራል። ነገር ግን እነዚህን ዘዴዎች የተጠቀመ ሰው ላይም የመከሰት እድል አለው። በቆዳ ንክኪ የሚተላለፍ እንደመሆኑ በኮንዶም የማይሸፈን የመራቢያ አካል ወይም ፊንጢጣ አከባቢ ባለ ንክኪ ሊተላለፍ ይችላል። ስለሆነም ይህ በሽታ ከሚያስከትለው ጉዳት እራስን ለመከላከል ምልክት ባያሳይም ምርመራ ማድረግ ተገቢ ነው። ሌላው በዚህ በሽታ ምክንያትነት የሚከሰተውን የማህፀን በር (ጫፍ) ካንሰር አስቀድሞ ለመከላከል በዋነኝነት የተቀመጠው መፍትሄ የኤች ፒ ቪ ክትባትን መውሰድ ነው።
የኤች ፒ ቪ (human papilloma virus) ክትባት  
የኤች ፒ ቪ ክትባት በ1 አመት ውስጥ በ6 ወር ልዩነት 2 ጊዜ የሚሰጥ ሲሆን ክትባቱን መውሰድ ከቫይረሱ ጋር ተያይዞ ለሚመጡ ካንሰሮች 90% ይከላከላል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአለምአቀፍ ደረጃ ከሚፈለገው መጠን 12% ወይም 61 ሚሊዮን 15 አመት የሞላቸው ሴቶች ክትባቱን አግኝተዋል። የአለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመላክተው ይህንን ክትባት በአለም አቀፍ ደረጃ 100 ሀገራት፣ በአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ25 ሀገራት እየተሰጠ ይገኛል።
የኤች ፒ ቪ (human papilloma virus) ክትባት በአፍሪካ
በአዲስ አበባ ከተማ ከተለያዩ የአለም ሀገራት በተውጣጡ የህክምና ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት በኤች ፒ ቪ (HPV) ክትባት ላይ ከመስከረም14 እስከ መስከረም 16 ለ3 ቀናት የቆየ የልምድ ልውውጥ ተደርጓል። የልምድ ልውውጡ በዋነኝነት ቺክ [CHIC ወይም Coalition to strength the HPV immunization community] ከኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚንስቴር እንዲሁም ከኢትዮጽያ የፅንስ እና ማህፀን ሀኪሞች ማህበር ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው። ይህ የውይይት እና የልምድ ልውውጥ መድረክ በአፍሪካ አህጉር ላይ ትኩረት ያደረገ ነው። በጤና ሚንስቴር የብሄራዊ ክትባት ፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት አቶ ዮሀንስ ላቀው እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ክትባቱን በመስጠት 90% ውጤታማ በመሆን  መርሀ ግብሩን አስተናገዳለች።
እንደ አቶ ዮሀንስ ላቀው ንግግር ከ9 እስከ 14 አመት የእድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ሴት ልጆች የሚሰጠው ይህ ክትባት እ.ኤ.አ ከ2018 ጀምሮ ለ4 አመታት ኢትዮጵያ እየሰጠች ትገኛለች። ይህ ክትባት ከ9 እስከ 14 የእድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ሴቶች የሚሰጥበት ምክንያት ጾታዊ ግንኙነት [የግብረ ስጋ ግንኙነት] ያልጀመሩ ሴቶች ክትባቱን እንዲያገኙ ለማድረግ ሲሆን ይህም በት/ቤቶች ዘመቻ በማድረግ ተደራሽ ተደርጓል። ቅስቀሳ በሚደረግበት ወቅት የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የማህበረሰብ አንቂዎች እና ታዋቂ ሰዎች ተሰታፊ መሆናቸው የክትባቱ አሰጣጥ ስኬታማ እንዲሆን አስተዋጽኦ ማበርከቱን  ባለሙያው ተናግረዋል። አክለውም ኢትዮጵያ ስኬታማ የሆነችው “ህብረተሰቡ ለክትባት ያለው አመለካከት ጥሩ በመሆኑ ነው” ብለዋል።
በአለምአቀፍ ደረጃ የኤ ች ፒ ቪ(human papilloma virus)  ክትባት ምርት እጥረት በመከሰቱ እና በኮቪድ ወረርሺኝ ሳቢያ መስተጓጎል ማጋጠሙን ባለሙያው ጠቁመዋል። ነገር ግን ግብአቱ ሲስተካከል በቋሚነት 9 አመት ለሞላቸው ሁሉም ሴት ልጆች ክትባቱን የመስጠት እቅድ መኖሩን አቶ ዮሀንስ ላቀው ተናግረዋል።
የማህፀን ጫፍ ካንሰር በሽታ መንስኤ ለሆነው (human papilloma virus) ሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ መከላከያ የሚሰጠው ክትባት በሀገር አቀፍ ደረጃ በጤና ተቋም ወይም በት/ቤት በሚሰጥበት ወቅት ክትባቱን መውስድ፣ የማህጸን በር ካንሰር ምርመራ ማድረግ እና በሽታው ከተገኘም በኋላ ሳይባባስ አስፈላጊውን የህክምና ክትትል ማደረግ ይገባል” በማለት የኢትዮጽያ ፅንስ እና ማህፀን ሀኪሞች ማህበር ፕሬዝደንት ዶ/ር አብዱልፈታህ አብዱልቃድር መልእክት አስተላልፈዋል።

Read 10435 times