Saturday, 22 October 2022 14:13

መንግስት በተቆጣጠራቸው የትግራይ ክልል ከተሞች ሰብአዊ እርዳታ መስጠት ጀመረ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

- ንግድ ባንክ ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ በሽሬ ከተማ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል።
- ከሁለት ዓመታት በላይ ተዘግተው የቆዩት ጎንደርን ከሽሬና ወሎን ከመቀሌ የሚያገናኙ መንገዶች በቅርቡ ይከፈታሉ ተብሏል


  መንግስት በተቆጣጠራቸው የትግራይ ክልል ከተሞች ውስጥ ለሚኖሩ ዜጎች ሰብአዊ እርዳታን መስጠት ሊጀምር ነው። ወልዲያ፣ ቆቦ፣ አላማጣና ሽሬ ሰብአዊ እርዳታው እንዲደርስ እየተደረገ ነው።
የሰብአዊ እርዳታውን በተሻለ ሁኔታ ለማዳረስ በሚያስችሉ መንገዶች ሁሉ ለመጠቀም ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን የሽሬ አውሮፕላን ማረፊያ ዕርዳታውን ለማድረስ አገልግሎት እንዲሰጥ ይደርጋል ተብሏል።
ከህውሓት አስተዳደር ነፃ በወጡ የትግራይ ክልል ከተሞች መንግስት መዋቅሩን መልሶ እያደራጀ መሆኑንና በቅርብ ቀናት ውስጥም የሰብአዊ እርዳታ መስጠት እንደሚጀመር ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የሰብአዊ እርዳታውን በተገቢው መንገድ ለማዳረስ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣  ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት ከአገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከፌደራል ፖሊስ ከኢትዮያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የተውጣጣ ቡድን መቋቋሙንና ሰብአዊ እርዳታ የሚደርስባቸውን መንገዶች እያስፋፋ መሆኑን መንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሰሞኑን መግለፁ ይታወሳል።
በሰሜን ጎንደር በኩል ወደ ሽሬ የሚወስደውንና ጎንደርን ከመቀሌ የሚያገናኘውን እንዲሁም ከኮምቦልቻ ደሴ ወልዲያ ቆቦ አላማጣ  ያለውን መንገድ ለመክፈት እየሰራ መሆኑን መንግስት አስታውቋል።
ከህውሓት ሃይሎች ነፃ በወጡ የትግራይ ክልል ከተሞች ውስጥ መሰረታዊ አገልግሎት የሚሰጡባቸው ተቋማትን የማደራጀትና ወደ ስራ እንዲገቡ የማድረጉ ተግባር እየተከናወነ ሲሆን  የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሽሬ ከተማ ውስጥ የሚሰጠውን አገልግሎት በመጪው ሳምንት ይጀምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ታውቋል። በተያያዘ ዜና የተባሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አለማቀፉ ማህበረሰብ ለሲቪሎች የሰብአዊ እርዳታ የሚሰጥበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚገባቸው ጠቁመው በትግራይ  ክልል እየተካሄደ ያለው ጦርነት በአስቸኳይ እንዲቆምና የነፍስ አድን ሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ የሚቻልበት መንገድ እንዲመቻች ጠይቀዋል፡

Read 11069 times