Saturday, 22 October 2022 14:12

አኩፋዳ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ዛሬ በደብረ ብርሃን ስራ ይጀምራል

Written by 
Rate this item
(3 votes)

በብሄራዊ ባንክ ደንብና መመሪያ መሰረት በስድስት አደራጆች የተቋቋመው “አኩፋዳ” ማይክሮ ፋናንስ ተቋም ዛሬ ረፋድ ላይ ዋና መስሪያ ቤቱ በሚገኝበት ደብረ ብርሃን ከተማ በይፋ ስራ ይጀምራል። ተቋሙ ከ1 ሺ 886 ባለአክስዮኖች በሰበሰበው 21 ሚሊዮን የተከፈለና 33 ሚሊዮን የተፈረመ ካፒታል መቋቋሙን አደራጆቹ በሳምንቱ አጋማሽ በስራ አምባ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።
አኩፋዳ ማይክሮ ፋይናንስ ሀገራዊ ባህልና እሴቶችን የማይንዱ ኢንቨስትመንቶችን ለመደገፍ፣ የስራ ዕድል ለመፍጠር፣ የቢዝነስ ክህሎት ሥልጠናዎችን ለመስጠትና የቁጠባና ብድር አገልግሎትን ለማሳደግ አልሞ የተነሳ ተቋም መመሆኑን የገለፁት ሃላፊዎቹ በተለይም የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን የማይችሉና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙትን የማህረተሰብ ክፍሎች በተመጣጣኝ ወለድ የብድር አገልግሎት ለማቅረብ አይነተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል- ሃላፊዎቹ።
በአሁኑ ወቅት በሀገራችን እየተከሰተ ያለውን የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት መቋቋም ያቃታቸውና ልዩ ትኩረት የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች ባላቸው አቅም አማራጭ የስራ መስኮችን እንዲመለከቱ ለማስቻል ከሌሎች አቻ ተቋማት አንፃር በዝቅተኛ ወለድ ብድር ለማቅረብ መዘጋጀቱንም የተቋሙ ሃላፊዎች ጨምረው ገልጸዋል።
“ስኬትን በተግባር” የሚል መሪ ቃል ይዞ የተነሳው አኩፋዳ ማይክሮ ፋይናንስ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ቅርንጫፍ የሚከፍት ሲሆን በዚህ ዓመት መጨረሻ እስከ ሰኔ 30 የቅርንጫፎቹን ብዛት 50 የማድረስ እቅድ ያለው ሲሆን በቀጣዮቹ 3 ዓመታት ተቋሙ በሀገሪቱ ካሉ የግል የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት መካከል አንዱና ተቀዳሚው ሆኖ እንዲገኝ በትጋት እንደሚሰሩም ሃላፊዎቹ አብራርተዋል፡፤
ተቋሙ ከሌሎች የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት እለይባቸዋለሁ ያላቸውን አሰራሮች በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ያብራራ ሲሆን፣ ከነዚህም መካከል ወጣቶችንና ሴቶችን ተጠቃሚ ማድረግ፣ በዝቅተኛ ወለድ መጠን ብድር ማቅረብ፣ የፋይናንስ ተቋማት አገልግሎት ያልደረሰባቸውን የገጠር ክፍሎች ተደራሽ ማድረግ፣ “የቆሎ ተማሪ” የተሰኘ የቁጠባና ብድር አገልግሎት መስጠት፣ የፈጠራና ቱሪዝም ስራዎችን በፋይናንስ በመደገፍ ዘርፎቹ ሚናቸውን እንዲወጡ መስራትና ሌሎችም ይገኙበታል።
አኩፋዳ ማይክሮ ፋይናንስ ዋና መስሪያ ቤቱን ከአዲስ አበባ ውጪ ያደረገ የመጀመሪያው ተቋም ነው የተባለ ሲሆን ይሄም ከባለአክስዮኖቹ አብዛኞቹ በደብረ ብርሃን ስለሚገኙ መሆኑን ሃላፊዎቹ ገልጸዋል። ዛሬ  በይፋ ስራውን በሚጀምርበት ጊዜ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች፣ የግልና የመንግስት የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ሃላፊዎች፣ ባለአክስዮኖችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይታደማሉም ተብሏል።

Read 1769 times