Print this page
Saturday, 08 October 2022 09:53

ስትሮክን በአገር ውስጥ ማከም የሚያስችል ማዕከል ተከፈተ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

     3 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጎበታል
                       
        በአገራችን በየዓመቱ ከሚመዘገበው አጠቃላይ የሞት ምጣኔ መካከል 6 ነጥብ 23 በመቶውን የሚሸፍነውን  ስትሮክ  በአገር ውስጥ ለማከም የሚያስችል የህክምና ማዕከል 3 ሚሊዮን ዶላር በሚጠጋ ወጪ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።  
ማዕከሉ ከደም ቱቦ መዘጋት፣ መርጋትና መጥበብ ጋር በተያያዘ አካልን መንቀሳቀስ እንዳይችል በማድረግ ሚሊዮኖችን ለሞትና ለአካል ጉዳት ሲዳርግ ለኖረው የስትሮክ በሽታ፣ በውጪ አገር የሚሰጠውን ህክምና ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ለመስጠት ያስችላል ተብሏል ።
ማዕከሉ ለአንጎል ቀዶ ህክምና የሚያገለግል መሳሪያ በ1.5 ሚሊዮን ዶላር መግዛቱ ተገልጿል።
ከአሥር ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ አገልግሎት ሲሰጡ  ከቆዩት  የአሜሪካ ሜዲካል ማዕከልና  ሰማሪታን የቀዶ ሕክምና ማዕከል ጋር በትብብር አገልግሎት መስጠት የጀመረው አክሶል የስትሮክና ስፓይን ማዕከል፤በስትሮክ ሕክምና ስፔሻላይዝድ ባደረጉ ብቁ የሕክምና ባለሙያዎች በውጪ አገር የሚሰጡ ህክምናዎችን ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ለመስጠት እንደሚያስችል ተገልጿል። በዚህም ህሙማን ለሕክምና  ወደ ውጪ አገር በመሄድ የሚያባክኑትን ከፍተኛ ገንዘብና ጊዜ  እንደሚያስቀር ተጠቁሟል፡፡ ህሙማን በማዕከሉ ለሚሰጠው ሕክምና  የሚያወጡት ወጪ ወደ ኬንያና ህንድ አገሮች ቢሄዱ ከሚያወጡት በአሥር እጥፍ ያነሰ እንደሆነም ተገልጿል።
 የአክሶል  የስትሮክ እና ስፓይን ማዕከል አጋር መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ወንደወሰን ገብረ አማኑኤል እንደተናገሩት፤ ማዕከሉ ባለፉት ስድስትና ሰባት ወራት ውስጥ የድንገተኛ ክፍል፣ የቋንቋ ቴራፒዎች፣ የአካል ቴራፒዎችና ሌሎች ባለሙያዎችን ሲያሠለጥን ቆይቷል፡፡ አገራችን ድሀ ከመሆኗ አንፃር ትኩረት መደረግ ያለበት ቅድመ መከላከል ላይ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ በቅድመ መከላከሉ ላይ ያተኮረ ትምህርት በስፋት ለመስጠት መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል ።
የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የአክሶል ስትሮክ እና ስፓይን ማዕከል  በአገራችን መከፈቱ በኢትዮጵያ የስትሮክ ሕክምናን አንድ ምዕራፍ ወደፊት የሚወስድ ነው ብለዋል፡፡ ላለፉት ዓመታት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የሚያስከትሉት ሞት እየጨመረ መምጣቱን የገለጹት ሚኒስትሯ፣ ችግሩን ከመቅረፍና ከመከላከል ጎን ለጎን የስፔሻሊቲ ሕክምና አገልግሎት ለማስፋፋት የአሥር ዓመት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ እየተተገበረ መሆኑንም አስረድተዋል። የጤናው ዘርፍ በርካታ መሻሻሎችን እያሳየ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ብዙ የሚቀሩ ሥራዎችን ወደፊት መሥራት ይጠበቃል ብለዋል።
የአክሶል የስትሮክና ስፓይን ማዕከል አጋር መሥራች ዶ/ር  አከዛ ጠአመ  በበኩላቸው፤ ማዕከሉ በኢትዮጵያ አዲስ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑንና አገልግሎቱ የሚሠጠው ለአገር ውስጥ ታካሚዎች  ብቻ ሳይሆን ከጎረቤት አገሮች ለሚመጡ ታካሚዎችም ጭምር  እንደሚሆንና በዚህም ለአገራችን ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ እንደሚያስገኝ ተናግረዋል ፡፡
በዓለም ላይ በየአመቱ ከ13 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በስትሮክ በሽታ የሚጠቁ ሲሆን  ከ5 ሚሊዮን በላይ ሰዎችም ህይወታቸውን በዚሁ በሽታ ሳቢያ ያጣሉ።
በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከሚመዘገበው አጠቃላይ የሞት ምጣኔ መካከል 6 ነጥብ 23 በመቶው የሚከሰተው  በስትሮክ ሳቢያ ነው።





Read 1890 times
Administrator

Latest from Administrator