Saturday, 01 October 2022 12:33

“ችግር የለም...”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ...አሁን፣ አሁን በተደጋጋሚ የምትሰሟት ነገር አለች፡፡ ስለ አንድ የሆነ ችግር አንስታችሁ ስታወሩ “ችግር የለም፣ ይስተካከላል፡፡” ችግር ቢሆን አይደል እንዴ መጀመሪያውኑ ስለዛ ጉዳይ ያወራችሁት! ችግር የለም?! እንክት አድርጎ ነው ችግር ያለው፡፡  የሆነ ጉዳያችሁ ከሳምንት፣ ሳምንት እየተንከባለለ መከራ ያበላችሁ መሥሪያ ቤት እንደምንም ብላችሁ አለቃው ዘንድ ወይም “አለቃ” ተብሎ ወንበሩ ላይ የተቀመጠው ሰው ዘንድ ለሁለተኛ ጊዜ ትቀርቡና ጉዳያችሁን ለማስረዳት ትሞክራላችሁ፡፡
“ይኸው ሁሉንም ነገር አሟልቼ ከሦስት ሳምንት በፊት ሊያልቅ ይችል በነበረ ነገር እያመላለሱኝ ነው፡፡ በመመላለስ ወር እኮ ሊሞላኝ ነው!”
“ችግር የለም፣ የዛሬ ሳምንት ያልቅልሀል፡፡”
ጭራሽ! እንዴት ነው ችግር የሌለው? ከሳምንት በፊት እንዲሁ ቀርባችሁ ያስረዳችሁት ጊዜ እኮ እንዲሁ ነው ያላችሁ፣ “ችግር የለም፡፡” እናላችሁ ሁለት፣ ሦስቴ ስትመላለሱ እውነተኛው ችግር ያለበት ቦታ ይታያችኋል...እልቅናው ላይ። “ችግር የለም፣” በማለት የሚፈታ ነገር ቢኖር ኖሮ፣ እዚህ ሀገር ምናልባት የሚናፍቀን ነገር ቢኖር መፍትሄ ሳይሆን ራሱ “ችግር፣” የሚባለው ነገር ምን አይነት እንደሆነ ይሆን ነበር! (ለልብ ወለድም አይመችም...አይደል!)
እማወራዋ... “ምሳ ቀርቧል፡፡ ደግሞ ቀዘቀዘ ብለህ እንዳትረብሸኝ!”
አባወራም ፈጠን ካላለ የሚከተለው “ኮንፍሊክት፣” ምናምን ስለሚያስፈራው ተጣድፎ ቁጭ ይላል፡፡ (ወጥዬው እኮ ራሱ ምግብ ጠረጴዛው እስኪደርስ ድረስ ስድሳ አምስት በመቶ ቀዝቅዟል!) እናላችሁ... እንደተቀመጠ አንድ  ወፈር ያለች ጉርሻ ጠቅለል አድርጎ ወደ አፉ! ምን ቢሆን ጥሩ ነው...ግንባሩ የተራራ የመስኖ እርሻ መስሎላችሁ ቁጭ። ሁለተኛውን ሲደግም ፊቱ... አለ አይደል... ቅልጥ ባለ ብርድ ውጭ እንዳደረ ፎጣ ‘ሽሪንክ’ ያደርጋል፡፡ (‘ኢማጂኔሽን’ ነው እንጂ እንደዛ አይነት ፎጣ ገጥሞኝ ያውቃል ለማለት አይደለም፡፡ ቂ...ቂ...ቂ... ለነገሩ ‘ሽሪንክ’ የሚል የፈረንጅ አፍ ከተጠቀሙ በኋላ እንደዛ አይነት ምክንያት አይሠራም፡፡)
“ምንድነው ይሄ?”
“ምኑ?”
“ወጡ ነዋ! ምን ጨምራችሁበት ነው?”
“ችግር የለም፣ ትንሽ ጨው በዝቶበት ነው፡፡”
ችግር የለም! የሹሮውን አንድ አምስተኛ የሚያህል ጨው እንደ አሸዋ ከገለበጡ በኋላ “ችግር የለም...” ብሎ አማርኛ ምን ማለት ነው!  
ስሙኝማ... እንግዲህ ጨዋታም አይደል...እነኚህ ሀያላን የሚባሉት ሰሞኑን እንዴት፣ እንዴት እያደረጋቸው ነው! አለ አይደል...አንዳንዴ እኮ “አስራ አምስት ጥርስህን በእጅህ እንዳላስታቅፍህ!” አይነት የጎረምሳ ጠብ ሊያስመስሉት ምንም አይቀራቸው! 
“እንዲህ፣ እንዲህ ብታደርጉ ኑክሌር እንጠቀማለን፡፡”
“እኛም በኑክሌር ምላሽ እንሰጣለን፡፡”
እንዴት ነው ነገሩ? ኑክሌርን የተድቦለቦለ ጭቃ አደረጉት እንዴ!
እኔ የምለው...እኝህ የአሜሪካው ዋነኛው ሰውዬ ቤተ ክርስትያን ዛፍ ስር ቁጭ ብሎ የተጣሉትን በማስታረቂያ ዕድሜ ዋነኛ አስፈራሪ ሆነው ቀሩ! በአንድ ወቅት ኡጋንዳና ታንዛንያ ተጣልተው ኢዲ አሚን (‘ዘ ላስት ኪንግ ኦፍ ስኮትላንድ!’) በአፍሪካ አንድነት ስብሰባ ላይ መሰለኝ... “ለምን እኔና ኔሬሬ አይዋጣልንምና አይለይም!” አይነት ነገር ብለው ነበር፡፡ ለእነዚህ ሀያላን እንደዛ አይነት ሀሳብ እንዳናቀርብ ደግሞ ቴክኖሎጂው ምናምኑ  ነገሮችን ሁሉ ለወጠብን!
ስሙኝማ...የሚገርመው እኮ ነገርዬው እነሱን ብቻ ሳይሆን መላው ዓለምን የሚመለከት ሆኖ እንደዛ ሲባባሉ አፋቸውን እንኳን ያዝ አያደርጋቸውም፡፡ ጦሱ ድንበር አልፎ ሊደርስብን ባይችል ኖሮ “በቃ ያላቸውን ይወራወሩና ይለይላቸዋ!” አይነት ነገር እንል ነበር! ሦስተኛ የዓለም ጦርነት ማለት ይሄ አይደለም እንዴ! በኑክሌር አንዳቸው ጠፍተው ሌላኛቸው ይተርፉ ይመስል ምን የሚሉት ክርክር ነው!
ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታም አይደል... በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ አካባቢዎች “ጫፋችንን የሚነካን የለም!” ይሉ የነበሩ ሀያላን የውስጣቸውን መቆራቆሶቻቸውን ምናምን ስታዩ...አለ አይደል...ከዚህ በፊት “እንዲህ አይነት ነገር አታውሩልኝ...” የምትሏቸውን ነገሮች መልሳችሁ መርምሩ፣ መርምሩ አያሰኛችሁም! ለምሳሌ እነኚህ የምናያቸው ነገሮች ሁሉ የዘመን ፍጻሜ መድረስ ምልክቶች መሆናቸውን አይነት ነገሮች፡፡
እኔ የምለው...እንዴት ነው ነገር ሁሉ እንዲህ መላ ቅጡ እየጠፋ ያለው! “ነገሩ ነው እንጂ፣ ጩቤው ሰው አይጎዳም፣” ይባልባት በነበረች ሀገር ትንሹም፣ ትልቅ የሚመስለውም ‘ነገር’ እኮ አባልቶ፣ አባልቶ ዓይን ለዓይን እንኳን እንዳንተያይ እያደረገን ነው ያለው፡፡ በአደባባይ እየተባሉ ያሉ ነገሮችን ስትሰሙ (በተለይም በማህበራዊ ሚዲያው) አንዳንድ ጊዜ እኮ የ‘ሹክሹክታ’ ወሬ ይናፍቃችኋል፡፡ በ‘ሹክሹክታ’ እኮ ሁለቱም፣ አምስቱም አፍና ጆሮ ገጥመው ያወሩት ሁሉ ምንም ይሁን ምን እዛው ይቀር ነበር፡፡ አሁን እኮ በአደባባይ የሚባሉ ነገሮች በተለይ ደግሞ ግለሰቦችን የሚመለከቱት የሚሰቀጥጡ እየሆኑ ነው፡፡ ደግሞላችሁ...የስድድቡ መብዛት! እኔ የምለው...ጨዋታም አይደል...ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ?! አንዳንዶቻችን ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ስንትና ስንቱ ሰው ያየውን ነገር ‘ምስጢር’ ብሎ ሊነግራችሁ ሲሞክር ስታዩ “የምስጢር ትርጉም ተለወጠ እንዴ!” ያስብላችኋል!
“ስማኝ.. ስማኝ እያልኩህ እኮ ነው!”
“ታዲያ ምን ያንሾካሹክሀል! ጮክ ብለህ አታወራም እንዴ! ቤት ውስጥ አይደል እንዴ ያለነው!”
“ቤት ውስጥ ቢሆንስ!”
“አንተ ደግሞ ዘላለምህን አይገባህም...ምስጢር በአደባባይ ጮክ ብዬ ልነግርህ ነው!”
“ቤት ውስጥ ስለሆንን ማን ይሰማናል ብዬ ነው፡፡”
“ስማ.. ዘንድሮ ግድግዳውም፣ ጣራውም ሁሉም ነገር ነው ጆሮ ያለው፡፡ አንተ ሰውዬ ሰልጥን እንጂ!”
“እሺ እሰለጥናለሁ፣ ይኸው ጆሮዬን አስጠጋሁልህ...በል ንገረኛ፡፡”
“ስለዛ ሰውዬ የሆነ ነገር ልጠይቅህ ፈልጌ ነበር፡፡”
“ስለየትኛው ሰውዬ?”
“ያ ቁመት ሲታደል አብሰንት ነበር የምንለው ሰውዬ...”
“ደግሞ እሱ ምን አደረገኝ ልትል ነው?”
“ምን ያደርገኛል፡፡ የሆነ ምድር ለምድር የሚሳብ ተንኮለኛ ነው ሲሉ ሰምቼ ነው፡፡ እኔ እኮ  እንዲህ አይነት ሰው አይመስለኝም ነበር!”
“አንተ የት ነው የሰማኸው?”
“ፌስቡክ ላይ የሆነ ሰው ለጥፎት ነዋ!” ‘ጉድ በይ የምናምን ምናምን’ ማለት ይሄን ጊዜ ነው፡፡
“ፌስቡክ ላይ የተለጠፈውን ነው ምስጢር የምትለኝ!”
“ማለቴ...”
እኔ የምለው ...ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...አንዳንድ ቦታዎች ይሄ ከመጠን በላይ የሚለቀቅ ሀይል አስቸጋሪ እየሆነ ነው እኮ! የምር እኮ “ናፋቂ አትሁኑበት...” በምንባልበት በዛኛው ጊዜ ከመጠን በላይ በተለቀቀ ሀይል የተለያዩ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶች ሲበላሹ የሆነ ቦታ “አቤት!“ ማለት ይቻል ነበር፡፡ ጥፋቱ የደንበኛው ሳይሆን የአገልግሎት አቅራቢው ነዋ! እንደውም...አለ አይደል...ትንሽም ቢሆን ካሳ ቢጤም አይጠፋም ነበር መሰለኝ፡፡ እናማ...በቃ እንደሱ አይነት ነገር ‘ሂስትሪ’ ምናምን ሆኖ ቀረ እንዴ!
የምር... ፍሪጆች ከባዶ ሳጥን የማይሻሉ ሆነው ስለተበላሹባቸው፣ የሀምሳ አምስት ኢንች ቴሌቪዥን ስክሪኖች ሀምሳ አምስት ትናንሽ ስለሆኑባቸው ሰዎች እየሰማን ነው፡፡ ማነው ተጠያቂ!
ነው... ወይስ ለእንዲህ አይነት ነገሮችም መልሱ ‘ቀላል’ ነው!
“ችግር የለም!”
 ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1324 times