Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 20 October 2012 10:35

የመጽሐፍት ነገር

Written by 
Rate this item
(5 votes)

እኒህ በአቋራጭ ብዙ ፍራንክ ማግኘት የሚፈልጉ አዟሪዎች የማፈጥሩት ጉዳትን አሰብኩኝ፡፡ ደራሲ፤ አሳታሚ እና አታሚ ባልፈጠሩት የተጋነነ የዋጋ ውድነት ብዙ አንባቢዎች መጽሐፍ ገዝተው ማንበብ እየፈለጉ ሊገዙ እንዳልቻሉ መገመት ይቻላል፡፡
በተጨማሪም አንባቢ መጽሐፉን ለገበያ ባቀረቡ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ላይ ትዝብት እና ምሬት ይኖረዋል፡፡
አጋጣሚ አንድ 
ከሁለት አመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ለእረፍት እንደመጣሁ ቦሌ መንገድ አካባቢ በአንድ ካፌ ውስጥ ማኪያቶ እየጠጣሁ ነበር፡፡ አንድ መፅሐፍ አዟሪ በሁለት እጆቹ ደርድሮ ያቀፋቸውን መፅሐፍቶች አሳየኝ፡፡ ጥራዙ ላይ ያለውን የመጽሐፍቶችን ርእስ እየተመለከትኩ ያላነበብኩት መፅሐፍ በአይኔ ብፈልግ አጣሁ፡፡ ጭንቅላቴን በመነቅነቅ እንደማልፈልግ ስነግረው፡፡
“ጋሼ አንድ መጽሐፍ ላሳይዎ?”፡፡ አለኝ
“ምን የሚል መጽሐፍ?”

“የደራሲው ማስታወሻ…ቆንጆ መጽሐፍ ነው፡፡ ላሳይዎት?...ይገዛሉ?”
“የተስፋዬ ገብረአብ መጽሐፍ?”
“እ!...” ብሎ ፈገግ አለ
መጽሐፉ በውጭ አገር ታትሞ ለውጭ አገር ገበያ መዋሉን እንጂ አገር ውስጥ ለሽያጭ መግባቱን አላውቅም ነበር፡፡ “እስቲ አምጣው” ስለው ያቀፈውን መጽሐፍ መሬት ላይ አስቀምጦ፤ ያዘለውን ቦርሳ አውረደና አንድ በጋዜጣ የተለበደ መፅሐፍ አቀበለኝ፡፡ የሚሸጥ መጽሐፍ በጋዜጣ ሲለበድ አይቼ አላውቅም፡፡
2“ለምን በጋዜጣ ለበድከው?” ብዬ ስጠይቀው
“የመንግስት ሰዎች ካዩት ችግር እንዳይፈጥሩብኝ ብዬ ነው፡፡”
“ችግር ፈጥረውብህ ያውቃሉ?”
“እንዲያውም …ግን መጠንቀቁ ይበጃል፡፡”
“እምታውቀውስ ችግር የተፈጠረበት ሻጭ አለ?” ብዬ ስጠይቀው የፍርሃት የሚመስል ዝምታ ፊቱ ላይ አነበብኩ
ልጁ ላይ ፍርሃት የፈጠረበትን ጥያቄ ያለ መልስ ትቼ፤ መጽሐፉ የተለበደበትን ጋዜጣ ስገፈው..ቀይ፤ አርእስትም፤ ስእልም የሌለው የመጽሐፍ የፊት ገጽ አገኘሁኝ፡፡ ግራ ገባኝ፡፡
“ይሄ መጽሐፍ ርዕስ የለውም እንዴ?”
“ጋሼ እኔ ስገዛው እንዲህ ነው የተሸጠልኝ፡፡ የሚገዙ ከሆነ ዋጋ እንነጋገር፡፡”
ሁሉ ነገሬ እንዳላማረው ተረዳሁኝ፡፡
“እንዴ!...ይሔ መጽሐፍ የደራሲው መሆኑን በምን አውቃለሁ?...አንተ ስላመጣህልኝ ብቻ መግዛት አለብኝ እንዴ!”
“ሰው ሁሉ ተረባርቦ የሚገዛውን መፅሐፍ እርስዎ መጠራጠርዎ ምን ይባላል!...ከተጠራጠሩት ደግሞም ይቅርብዎ፡፡”
“እኔ …እኔ ነኝ፡፡ ስለሌላው አያገባኝም፡፡ እዚህ መጽሐፍ ውስጥ ያለው ነገር የደራሲው እንደሆነ እስቲ በምን ልወቅ? ንገረኝ …አርእስት የለው …የሽፋን ምስል የለው”
“በቃ ተዉት” ብሎ የንጥቂያ ያህል ከእጄ ከወሰደ በኋላ ቦርሳው ውስጥ አስቀምጦ፤ “አደጋ ላይ የማይጥሉትን” መጽሐፍቶች አቅፎ ከአጠገቤ በፍጥነት ራቀ፡፡
መጽሐፍ አዟሪው ያሳየኝ “የደራሲው ማስታወሻ” መጽሐፍ ፀሐፊው በውጭ አገር ያሳተመው እንዳልሆነ አውቄአለሁ፡፡
በውጭ አገር የታተመውን መፅሐፍ የገጽ ሽፋን በኢንተርኔት አይቼዋለሁ፡፡ አሁን ሻጩ ያሳየኝ መጽሐፍ ውስጡ የያዘው ነገር ደራሲው ከጻፈው ተቀንሶ ይሁን ተጨምሮ፤ ወይም ተፐውዞ ላለመቅረቡ ምንም ማረጋገጫ የለም፡፡
አሁን በቅርቡ ደግሞም የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ኮ/ል መንግስቱ ኃ/ማርያም “ትግላችን - የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ የትግል ታሪክ” በሚል አርእስት የጻፉትን መጽሐፍ አዟሪዎች እጅ አየሁኝ፡፡ ይህ መጽሐፍ ልክ ቅድም እንደጠቀስኩት መጽሐፍ ህጋዊው እና ትክክለኛው ህትመት አይደለም፡፡
ሆኖም ግን ከወር በኋላ “ፀሐይ አሳታሚና አከፋፋይ ድርጅት” ያሳተመውን ዋናውን መጽሐፍ በፋርኢስት በኩል እዚህ ሀገር ታትሞ አዟሪዎች እጅ አገኘሁት፡፡ ቀድሞ ማንነቱ ባልታወቀ ሰው የታተሙትን መጽሐፍት የገዙ ሰዎች ይህን ሲያዩ ምን ይሰማቸዋል? ግርታውን ማን ያጠራዋል? “ፀሐይ አሳታሚና አከፋፋይ ድርጅት” እንዲሁም ፋርኢስት የሚያጣው የሽያጭ ገቢስ?
ከዚህ በተጨማሪ የአገራችን ደራሲያን የስራ ውጤቶች ያልሆኑ ስራዎችም እዚሁ ሀገር ታትመው ወይም ትክክለኞቹ የህትመት ቅጂ ያልሆኑ ለሽያጭ ቀርበውም አይቼአለሁ፡፡ ለአብነት ያህል የማርክ ትዌንስ “1986” የፖውሎ ኮኤልሆ “The Alchemist”፣ የኤካርት ቶሌ “The Power of Now” ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የተለያዩ የአማርኛ መጽሐፍቶች “ስካን” ተደርገው ወይም ወደ “ሶፍት ኮፒ” ተቀይረው በተለያዩ ድረ - ገፆች ያለምንም ሀፍረት ለአንባቢያን በነጻ የሚያቀርቡ ድረገጾች እንዳሉም ታዝቤአለሁ፡፡
ሁለቱም በአገር ውስጥ በህገ - ወጥ መንገድ ታትመው ሲቸበቸቡ የነበሩት መጽሐፍት ቀድሞ በ”ሶፍት ኮፒ” ኢንተርኔት ላይ ተሰራጭተው ነበር፡፡ ከእነዚህ መጽሐፍት በተጨማሪም የዘነበ ወላ “ልጅነት” መፅሐፍ ሶፍት ኮፒ አንድ የኢትዮጵያዊ ጦማር (ብሎግ) ላይ አይቼዋለሁ - የድረገጹ ጐብኚዎች ዳውን ሎድ አድርገው እንዲያነቡት፡፡
አጋጣሚ ሁለት
“ስንት ገዛኸው ይህን መጽሐፍ?” ብሎ ጠየቀኝ ጓደኛዬ፤ የይስማእከ ወርቁን “ተከርቸም” መጽሐፍ አገላብጦ ካየ በኋላ፡፡
“75 ብር”
“ተሸውደሃል”
“እንዴት? እንዲያውም ተከራክሬ ከተጻፈበት ዋጋ አምስት ብር ቀንሶልኝ ነው የሸጠልኝ” አልኩት
“ዋጋው 80 ብር ሳይሆን 30 ብር ነው”
“ምን ነካህ ወዳጄ…እስቲ አምጣው” ከእጁ ተቀብዬው ዋጋው የተጻፈበትን የመፅሃፉን ጀርባ ተመለከትኩት፡፡ አልተሳሳትኩም፤ 80 ብር ነው የሚለው፡፡
“እያየኸው 80 ብር እያለ!...ወይስ አጭበርባሪዎች እንደገና አትመው በ80 ብር እየሸጡት ነው?” ብዬ ስጠይቀው
“አይደለም 3 ቁጥርን በነጭ ቀለም ወደ 8 ለውጠው ዋጋውን 80 አስመስለው ነው የሸጡልህ”
“እውነትህን ሳይሆን አይቀርም”
“ሳይሆን አትቀርም አይደለም...እውነቴን ነው”
“ይገርማል፡፡ እኔም እንዴት የ200 ገጽ መጽሐፍ በ80 ብር ይሸጣል ብዬ ስጠይቀው ‘ደራሲው እኮ ይስማእከ ነው፤ እንኳን 80 ብር 800 ብር ቢባል ገዢ አያጣም፡፡ ከተማዋ ውስጥ መጽሐፍዋን አያገኟትም’ ብሎ አግባብቶ እና 5 ብር ምሮኝ ነው የሸጠልኝ”
“ትንሽ ብትከራከረው 50 ብርም ይሸጥልህ ነበር፡፡
አንዳንድ መጽሐፍ አዟሪዎች አጭበርባሪዎች ናቸው፡፡
በተለይ የታዋቂ ደራሲያን እና የማይገኙ መፅሐፍትን ያለ ምንም ሀፍረት ዋጋቸውን ፍቀው እነሱ ባሰኛቸው ዋጋ ነው የሚሸጡት”
“ይገርማል! ይኼን ነገር ግን አሳታሚዎች ወይም ደራሲዎች ያውቁታል?” ብዬ ስጠይቀው “እኔ የማውቀው አሳታሚና ደራሲ የለም፡፡ ይልቁንስ አንተ መጽሐፍ ስትገዛ ጥንቃቄ አድርግ” አለኝ፡፡
በአንድ ወቅት በፕሮፌሰር ጌታቸው ሐይሌ፣ ከግእዝ ወደ አማርኛ የተተረጐመውን “ደቂቀ እስጢፋኖስ” መጽሐፍ ለመግዛት ያላዳረስኩት መፅሐፍ መደብር የለም፡፡ ላገኘው ግን አልቻልኩም፡፡ በመጨረሻም አንድ አዟሪ እንደሚያመጣልኝ ቃል ገብቶልኝ ዋጋ መደራደር ጀመርኩኝ፡፡ በመጨረሻም 250 ብር ያለውን በ150 ብር ሊሸጥልኝ ተስማማን፡፡ በነጋታው ይዞልኝ መጣ፡፡ ግን መጽሐፉ ላይ ዋጋው የተጻፈበት ቦታ ተፍቋል፡፡ መጽሐፉን ስለፈለግሁት እና በቀላሉ ስለማላገኘው እንደተጭብረበርኩ እያወቅሁ እንዲሁም እየተናደድኩ የተጠየቅሁትን ዋጋ ከፍዬ ወሰድኩት፡፡
ከጥቂት ጊዜ በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 6 ኪሎ ካምፓስ ግቢ ውስጥ የመጽሐፍ ትእይንት ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ እዚያ ሄጄ የተለያዩ መጽሐፍት ቤቶች፤ አሳታሚዎች እና ሻጮች ለገበያ ያዋሉትን መፅሐፍት ስመለከት “አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ” የህትመት ውጤቶችን የሚያሳይበት ቦታ ደረስኩ፡፡
የ“ደቂቀ እስጢፋኖስ” መጽሐፍ ይኖራል ብዬ ጠብቄ ነበር፡፡ ግን ለእይታ ከተደረደሩት ውስጥ አልነበረም፡፡ አስጐብኚዋን “ደቂቀ እስጢፋኖስ መጽሐፍ አላችሁ?” ብዬ ስጠይቃት
“እሱማ ተሸጦ ካለቀ ስንት ጊዜው!” አለችኝ፡፡
አጠገቤ ሆነው መጽሐፍቶችን እያገላበጡ ሲመለከቱ የነበሩ ሰውዬ ቀና ብለው አዩኝና “እሱን መጽሐፍ እኔም እዚህ አገኛለሁ ብዬ ነበር የመጣሁት፡፡” አሉኝ፡፡
የኔ ፍላጐት መጽሐፉን ለመግዛት ሳይሆን ዋጋውን ለማወቅ ነበርና “ግን ስንት ነበር ዋጋው?” ብዬ ስጠይቃት
“ስንት ነበር!? 70 ነው ወይስ 60 ብር?” ብላ አጠገብዋ ያለችውን ባልደረባዋን ጠየቀቻት
“60 ወይም 65 ብር መሰለኝ” አለቻት
“እዛ ገደማ ነው” ብላ አስረግጣ ነገረችኝ
መፅሃፍ አዟሪው ቢያንስ በአንድ መጽሐፍ አላግባብ 80 ብር እንዳተረፈብኝ ተረዳሁ፡፡ እንደኔ ስንቱ ተጭበርብሮ ይሆን እያልኩ እያሰብኩኝ፡፡
“ለምን ታዲያ ቶሎ ተሸጦ ካለቀ ድጋሚ አልታተመም?” ብዬ ስጠይቃት “እሱን አላውቅም” አለችኝ፡፡
አጠገቤ የቆሙት ሰውዬ “እኔ እምልሽ ልጄ…ለሽያጭ የሚሆን ኮፒ ባይኖር እንኳን…ይሄ ኤግዚቢሽን አላማው ለህትመት የበቁ መጽሐፎችን ለጐብኚዎች ማሳየት ከሆነ…ቢያንስ እንኳን ሁለት ሶስት ኮፒ ለምን ለእይታ አልቀረበም?” ብለው ሲጠይቋት
“እሱንም አላውቅም፡፡” ብላ መለሰችላቸው፡ የዩኒቨርስቲ ፕሬሱ፣ አንባቢ የሚፈልገውን መጽሐፍ ደግሞ ደጋግሞ ማሳተሙን ለምን እንደዘነጋው መረዳት አልቻልኩም፡፡
እኒህ በአቋራጭ ብዙ ፍራንክ ማግኘት የሚፈልጉ አዟሪዎች የማፈጥሩት ጉዳትን አሰብኩኝ፡፡ ደራሲ፤ አሳታሚ እና አታሚ ባልፈጠሩት የተጋነነ የዋጋ ውድነት ብዙ አንባቢዎች መጽሐፍ ገዝተው ማንበብ እየፈለጉ ሊገዙ እንዳልቻሉ መገመት ይቻላል፡፡ በተጨማሪም አንባቢ መጽሐፉን ለገበያ ባቀረቡ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ላይ ትዝብት እና ምሬት ይኖረዋል፡፡
በመጽሐፍ ዋጋ እና ማጭበርበር ዙሪያ አትኩሮቴን ከሰበሰብኩ በኋላ የታዘብኩትን እነሆ:-
የቴዎድሮስ ተ/አረጋይ - ፍልስምና (የሐሳብ መንገዶች) ቅጽ - አንድ 25 ብር የሚለው ወደ 50 ብር ተለውጦ
የቴዎድሮስ ተ/አረጋይ - ፍልስምና 28 ብር የሚለው ወደ 80 ብር ተለውጦ
የዘነበ ወላ - ልጅነት -35 ብር የሚለው ወደ 85 ብር ተለውጦ
የፍቅሩ ኪዳኔ የፒያሳ ልጅ ከ80 ብር ወደ 300 ብር ተለውጦ
የበዓሉ ግርማ ከአድማስ ባሻገር ከ35 ብር ወደ 85 ብር ተለውጦ
በዘፈን የህትመት እና ስርጭት መብት (Copyright) ላይ የሙዚቀኞች ማህበር እና ሙዚቀኞች ምሬታቸውን በተለያየ ወቅት አሰምተዋል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍም ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ተንቀሳቅሰውም እርምጃ ሲወስዱ አይተናል፡፡ በመጽሐፍት ዙሪያ በሚፈፀሙ በእነዚህ ህገወጥ የሕትመት ስርጭት እና ትክክለኛ ዋጋቸውን እየፋቁ፤ በመጽሐፉ ጽሕፈት፤ ህትመት እና ስርጭት ላይ ምንም ሚና የሌላቸው ግለሰቦች በአቋራጭ ለመክበር የሚፈጽሙትን ወንጀል ለመከላከል እና ከቁጥጥር ውጪ ሳይወጣ በአጭሩ ለመቅጨት የሚመለከታቸው አካላት እና የደራሲያን ማህበር ምን እያደረጉ እንደሆነ ባላውቅም ቢረፍድም እርምጃ መውሰዱ ወደፊት ሊደርስ ከሚችል ጉዳት አንጻር ቢታሰብበት የሚበጅ ነው እላለሁ፡፡ ክርስቶፈር ሒችንስ እንዳለው “ወደፊት ልንፀፀትበት የሚገባንን ነገር ልንመርጥ ይገባናል”

Read 4438 times Last modified on Saturday, 20 October 2012 11:06