Saturday, 24 September 2022 21:01

የግጥም ጥግ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

  በራ የመስቀል ደመራ

የአደይ ችቦ እየፋመ እየጋመ
ኢዮሃ እያስገመገመ እየተመመ
የመስቀል ደመራ
በራ።
በራ የአዲስ ዘመን ችቦ
በመስከረም ሰብል አብቦ
ከዋክብቱን ፈነጠቀ
ርችቱን አንጸባረቀ
ተኳለ አዲስ ደመቀ
መስኩን በቀለም አዝርዕት፤ በጥበብ አጥለቀለቀ
ሸለቆው ተንቆጠቆጠ፤ ተራራው አሸበረቀ
ኢዮሃ ኢዮሃ አበባዬ፤ ምድር ህይወት አፈለቀ
ነጋ የአዲስ ዘመን ችቦ
ፈካ፣ ጸዴ አረብቦ
ሌሊቱ እንደጎህ ቀደደ፣ ጨለማው እንደቀን  ጠራ
እንደውቅኖስ ዕፀዋት፣ እንደጠፈር ኮከብ ደራ
ምድር ሥጋጃ ለበሰ፣ የጌጥ አልባሳት ተቀባ
ሰማይ በእልልታ አስተጋባ
ኢዮሃ መስከረም ጠባ።
ነጋ  የአዲስ ዘመን ችቦ፣ ምድር ሕይወት አፈለቀች
የምስራች አዝርእቷን፤ አዲስ ቡቃያ ወለደች
 የአደይ አበባን ለገሰች
ለአዲስ ዘመን አዲስ ብርሃን፤ አዲስ መስከረም ገበየች።
ነጋ፤ የአዲስ ዘመን ችቦ
ፈካ፤ ፀደይ አረብቦ
በራ፤ የመስቀል ደመራ።
(መስከረም- ፲፱፻፰፫ መስቀል አደባባይ)

Read 1441 times