Print this page
Saturday, 24 September 2022 20:56

ይቅርታዬን ይቅር በለው

Written by  በድረስ ጋሹ
Rate this item
(5 votes)

  [...የመጀመሪያዋን የውኃ ጠብታ የእጁ ንቃቃት ዋጣት። ደግሜ ከኮዳዬ እንዳላፈስለት ልቤ ደነደነ፣ የማርያምን ስም ጠርቶ ለመነኝ_ዳሩ ከብሊዐሰብ ከፋሁበት። ሰባ ነፍስ ያጠፋው አረመኔ በጥርኝ ውኃ ነፍሱን አትርፏል። የጥርኝ ውኃ ወንድሜን የነፈግኩት እኔስ ሰባ ነፍስ እንዳጠፋሁ እቆጠር ይሆን?...
...ቸግሮት! ማዳበሪያ ይዞ እህል ሊበደረኝ መጣ። ጎተራዬ ይጎድል ዘንድ አልፈቀድኩምና ፊት ነሳሁት። ረሃቡ አይሆኑ አድርጎ ገደለው። ሲኖር ያልደረስኩት ሰው ሲሞት ለአስከሬኑ የወርቅ ሳጥን ገዛሁለት። (አስተሳሰቤን ምን በላው? እውን ሥልጣን አእምሮ ይደፍናልን? እውን ወንበር ወንድምን እንዳያግዙ ያቅባልን?...እንዲሁ ለምድር እኔ ትርፍ ገላም አይደለሁ? እንዲሁ  ከነጭ ነጠላ ላይ ጎልታ እንደምትታይ ጥቁር ነጥብ ...ጽድቅን ብሰራ ለእኔስ ይኼውም አይደል?
...የእጁ ሸንተረር ስለእኔ ነበር _ልጄን ከእሳት አደጋ ሲያተርፍ የተጎዳው። ስለመኖሬ በአካል ቆሰለ፤ ስለመኖሬ በንፍገቴ ቆሰለ...አንገርግቤ ደፋሁት። ምድር ሁሉን ከታች_ዋጠችው። እኔ ለምድር ቀረሁ። እንድባክን...ራሴን እንድረግም...በክፋቴም ላይ ክፋት እንድጨምር...
...ወንበር አለኝ በሕዝብ ያገኘሁት፤ ሕዝብን ለማሰቃየት የምጠቀመው። ብዕር አለኝ በክብር የተሰጠሁት፤ ክብር ለመግፈፍ የምጠቀምበት። ደመወዝ አለኝ ለልፋቴ ዋጋ የተባለ፤_ከፍዬ ተፎካካሪዎቼን ለማስመታት የማውለው። ሁሉም ያለኝ ሁሉም የሌለኝ ከንቱ ሰብዕ መሆኔን ማን ደፍሮ ይንገረኝ?...እያልኩ መብሰልሰል ጀመርኩ።
ከሦስት ደሳሳ ጎጆዎች መሐል ...ከትልቁ የሳር ክምር ስር የተቀመጠች አሮጊት ትታያለች...
ከወገቡ ሰበር፣ ከአንገቱ ቀለስ ብሎ የአሮጊቷን ሃበሻ ቀሚስ የሚያስተካክል ሰው ይታየኛል። የዓይኔ ጨረር እንደ ቀስት ወጋው። ትህትናው ጸሎተ ሐሙስን አስታወሰኝ። ዝቅ የማለት ቀን ... መኮፈስን የመናቅ ቀን ...። ደግሜ ደጋግሜ ከአካሉ የገዘፈ ትህትናውን አየሁ። ሰው መልካም ሲሆን ሰውነቱ ይረሳኛል። ከወንድሜ በቀር ሰውን የማውቀው በክፋት ቢሆን፤ እኔም ክፉ ብሆን ነው።
“አንተ ብላቴና!” የሚል ትልቅ ድምጽ ወጣኝ...
“እንደጠሩኝ ደግ ይጥራዎ ፣ እንዳዩኝ ደግ ይይዎ ፣ ምን ልታዘዝዎ”...አለኝ እጁን በጀርባው አመሳቅሎ።
እንደመደንገጥም፣ እንደማፈርም፣ እንደመሸማቀቅም አደረገኝ። አንቱታ ለእኔ ይገባልን? አልኩት ራሴን። “ክርስቶስን አንተ የሚሉት ሰዎች  አንተን ለምን አንቱ ይሉሃል?...ለማክበር እንዳትለኝ ...ክብር ከአንተ እና ከፈጣሪ ለማን ነበር የሚገባው ?...በል ‘አንተ’ እንዲልህ ንገረው... ንገረው ያለኝ _ የውስጤ ገፊ ሐሳብ ነበር።
“ጳጉሜ ዕለተ ምጽዓትን ትመስላለች” አለ በዝምታችን መሐል።
ውስጤን ብርክ ያዘው። ዕለቱም ጳጉሜ ውስጥ ነው። ናቅ አድርጌ የጠራሁት ታላቄን ይሆንን? ስል አሰብኩ። የናቁት ያስረግዛል ይሉት ብሂል ትዝ አለኝ።
“ከመጥራቴ ጋር ምን አገናኘው?” አልኩት ቆጣ ብዬ...
ስትመጣ በመንገድህ ላይ ቢጫ ጀሪካ ያዘለች ልጃገረድ ጠርተህ ስለ መቅዳትና መድፋት ጠይቀሃል?_አዎ፣እልፍ ስትል መንሽ የያዘ ገበሬ ጠርተህ ስለ ፍሬና ገለባ ተረድተሃል?_አዎ፣ በፕሮቴስታንቶች ቸርች አጠገብ ያገኘኸውን አገልጋይ ጠርተህ ስለሚለፍፈው ኢየሱስ ጠይቀኸዋል?_ አዎ፣ በቤተክርስቲያንና በመስጅዶችም ዙሪያ ያገኘሃቸውን አማኞች  እየጠራህ እንዲሁ ስለ ሚከተሉት እምነት ጠይቀሃል?_አዎ፣...ዳሩ አሁንም እኔን ጠርተሃል። የጠራሃኝ ስለ እምነት ልትጠይቀኝ እንዳይደለ ገብቶኛል። ስለመልካም ስብዕናዬ እንጅ። እንዳየኸው “የተጠሩት ብዙ ናቸው የተመረጡት ግን ጥቂቶች”...።
ነገሩ ግራ ገባኝ። እንደ መንፈስ ሲከታተለኝ የዋለ እሱ ማን ቢሆን ነው? (ለራሴ የቀረ ጥያቄ ነው)
ነገሩን ቀጠለ...
በፈጣሪያቸው ፊት ያለነቀፋ እንደኖሩ የሚነገርላቸው የዘካሪያስ ቤተሰቦችን ብነግርህ ወደድኩ። በፈጣሪያቸው ፊት ያለነቀፋ መኖር ምን ይረቅ? (ለዚህም አንክሮ ይገባል)። ዘጠና ዓመት ያስቆጠረችዋ ኤልሳቤጥና፣ መቶ ዓመት የሞላው ዘካሪያስ...በመላዕኩ የተነገራቸውን ትዕንቢት ለመቀበል የተቸገረው ዘካሪያስ ዱዳ መሆን..ዮሐንስም “ሲጸነስ የአባቱን አንደበት የቆለፈ፣ ሲወለድም የፈታ የተባለ ልጅ ወለዱ።
“ስብከቱ አይበቃም ብላቴናው?”
“ለምን ይበቃል? ደግ ለምድር አይበጅ በሔሮድስ ዓይን ገባ። ከሕጻናቱም ተርታ ተሰልፎ አንገቱ በሰይፍ እንዲቀላ ፈረዱበት። ተሳደዱ...ተሳደዱ...ለቅሶውን የሰማች አክስቱ ልጇን ብታማክረው ይሄን ቁመቱ ቀጥ ያለውን፣ ጽሕሙ እንደተፈተለ ሐር የወረደውን፣ ጸጉሩ እንደ ቁራ መልክ የጠቆረውን ፣ ግርማው የሚያስፈራውን መጥምቀ መለኮት ይፈልግ ነበርና “ለአገልግሎት እስክጠራው እዚያው ይቆይ አላት” ...አገሪቷን የሚያሽከረክሯት አንተንም ጨምሮ ሳትጠሩ የመጣችሁ መሆናችሁን ልብ በል።
“ብላቴናው አፍህ እንዳመጣልህ አትሳደብ!”
“አሄ!.. መቼም በዚህ ዘመን ሐቀኛ አይወደድም። አንተና መሰሎችህ በወንበር ጫካ ውስጥ ተሸሽጋችሁ፣ በብዕር ዲሽቃ ስንቱን ገደላችሁት? “እውነት” እንደ ስድብ እየታየቻችሁ ለምትኖሩት መጥኔ ለእናንተ። ታሪኬን እቀጥላለሁ፣ ዮሐንስን ነብይ፣ ሐዋሪያ፣ ሰማዕት፣ ጻድቅ፣ ቃል አውዲ ተንከተም፣ ጸያሔ ፍኖት፣ መጥምቀ መለኮት ፣ መምህር ወመገስጽ፣ ዘየዐቢ እምኩሉ እልፍ ብሎም “እውነት እላችኋለሁ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል መጥምቁ ዮሐንስን የሚበልጥ አልተነሳም” የተባለለት ለምን መሰለህ?....”እስከሚጠራ ስለጠበቀ፣ ጥሪውም ምርጫ ስለሆነለት” ነው። ስለ ጳጉሜ የጀመርኩልህን በራስህ መርምረህ ድረስበት ብሎኝ ተሰወረ።
“በትህትና ለምድ ቀርቦ ምኑ ሰይጣን ነበር ሲፈታተነኝ የቆየ” አልኩ ጮኽ ብዬ።
“(አምላክም አገር፤ ይሁዳም አንተ...ታዲያ አምላኩን ስሞ ከሸጠ ይሁዳ እኔ አልሻልም?” የሚል ድምጽ ከበበኝ...
(እውነት በወንበሬ ተመክቼ አገሬን ሸጫለሁ እንዴ?_አዎ፣ እውነት ብዕሬ ለሰው ልጆች ሞት ሰበብ ሆኗል?_አዎ፣ ጨነቀኝ...ጠበበኝ...ምድር ተከፍታ ብትውጠኝ ወደድኩ። ሰማይ መጅ፤ ምድር ወፍጮ ሆነው ቢደቁሱኝ ለመንኩ። ሳላውቅ በስህተት፣ አውቄ በድፍረት የሰራሁትን ኃጢያት ይቅር በለኝ ብዬ የምናዘዝለት ንስሃ አባት አጠገቤ የለም...ራሴን እወረውርበት ገደል፣ የደም ስሬን እቆርጥበት ምላጭ ሁሉ ቸገረኝ። ሞት ሲለምኑት ሩቅ ነው። በዋዛ አይገኝም። የቀበጡለት ሞት አይገኝም ይሉት ይትበሃል ሸበበኝ፡፡ ጳጉሜ...ምጽዓት...ጳጉሜ ...ምጽዓት...ጰጉሜ...ምጽዓት...ጆሮዬን ደፍኜ ወደ መሬት ወደቅሁ።)
ፈራ ተባ እያልኩ ከወደቅሁበት አቀናሁ። እንደ እባብ አፈር ልሼ .. ዙሪያ ገባዬን ይኸው ሰባኬ አይሉት ጨዋ ልጅ ከቦኛል። ዓይኔ አንዱን እንደ ሺ አየው። እንደ ጦር ፈራሁት፤ እንደ መብረቅም እራድኩለት። እንደምንም...ልብ ገዛሁ። አቤቱ አልኹት።
“ምን አደርግ ዘንድ ፈቀድክ?” ነበር ጥያቄዬ።
“ታደርግ የፈቀድከውን አድርግ፤ ታደርግ የወደድከውን መርምር፣ ልታውቅ የወደደከውን...”
“አንዱን መንገድ ምራኝ እባክህ”
“እንግዲያውስ በአንተ እና በመሰሎችሁ ቢሮ ላይ ወረቀት ለጥፍ። ወረቀቱም “ለአገልግሎት እስክትጠሩ ባላችሁበት ቆዩ” የሚል... ጌታ ለዮሐንስ እንደተናገረው”
“ለምን?”
“ሳይጠራ የመጣ አለ፤ አለህምና።”
“አንድ ያጣላል ሌላም ድገመኝ...እባክህ!”
“(አጥፊውን ሔሮድስ የሚገስጽ ዮሐንስ ሁን። ይሰርህም፣ በልደቱም ለዘፋኟ ሔሮድያዳ ይማልላትም፣ ራስህን አሰቆርጦ በወጪት ይስጣትም፣ “እምሔሶ ለሄሮድስ ይብልዓ መሐላሁ” |ሄሮድስ መሃላውን በበላ በተሻለው| ይበሉት፣ ራስህ የጸጋ ክንፍ ይሰጣት ዘንድ እድል አላት፣ የእውነት አምላከህን ፍለጋ ደብረዘይት ሔዳ ትሰግዳለችና። በመላው ዓለም የማስተማር ሥልጣን ይሰጣታልና። ከ15 ዓመት ያላነሰ ስብከትን ታደርግማለችና...” ብሎኝ ድጋሚ ተሰወረ።
...አንዳች ኃይል ተዋረረኝ። ያለፈውን የኃጢያት ስዕል አጠፋበት ዘንድ ላፒሱን ንስሐ ሻትኩ፣ ያለፈ የክፋት ባህሬን እከፍልበት ዘንድ የምህረት በትር ለመንኩ፣ ከአናብስት ጉድጓድ አመልጥበት ሥልጣን፣ ጎልያድን ያህል ችግር እጥልበት ወንጭፍ አማረኝ። ውኃ ያለ እሳት እንዳይፈላ፣ ስኬትም ያለ ምኞት እንዳይሆን ሲገባኝ_ተመኘሁ!  
(ቢሮዬ ውስጥ በጥፊ የተመታች እናት፣ ያለ አግባብ ያስፈረሰኩት የድሃ ቤት፣ ለችግር የድሃን ልጅ ለሽልማት የሀብታም ልጅ ያጨሁበት ቀን፣ ዘር ብሔር ቆጥሬ ሥራ የቀጠርኩበት፤ ከሥራ ያባረርኩበትም፣ ምድራዊ ሥልጣኔ አላቂ ስላልመሰለኝ ክፉ እኔ...ይቅር!
(ስለእኔ አይሆኑትን ለሆነው፣ ስለ እሱ ይሆኑትን ስላልሆንኩ _ለወንድሜ! ንቄ ስለጠራሁት ብላቴና፣ ስለመከረኝም እሱ፣ ትኅትና ስለሚበጃት አገሬ፤ ትኅትና ስለነፈግኳት እኔ... ይቅር!
(የበደልኩት ስላወቅኩ፣ የበደሉን ጥልቀት ስላየሁ፣ በዳይነቴን ስለተቀበልኩ፣ ይቅር ልልም ስላመንኩ፣ ልጠግነው ባልችልም ላልደግመው እንድችል፣ ከስህተቴም አውቅ ዘንድ እላለሁ ይቅር ለእኔ...ጌታ ሆይ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ይቅር ልበለው? ቢለው...”ሰባ ጊዜ ሰባት እንጅ መቼም እስከ ሰባት ብቻ አልልህም” እንዳለው እንደሰማንም ...ይቅር ለእኔ ...ይቅር ለመሰሎቼም!
እያልኩ ...ላልደግም እየማልኩ እየተገዘትኩ...ጳጉሜ _ምጽዓት፣ ጳጉሜ _ምጽዓት እያልኩ ሳለ ለሦስተኛ ጊዜ ይኼ ሰባኬ አይሉት ጨዋ ከፊቴ ተበገረ። ይኼም ሲሆን ጊዜ አልወሰደም።
“ምነው ወዳጄ ልቤ? ምነው በአውላላ ሜዳ እንዲህ መሆንህ?” (ከአሁን ቀደም ያገኘኝ በማይመስል አነጋገር)
“አንተ ነሃ...”
“እኔ ምን?”
“ጳጉሜ _ምጽዓት፣ መጠራት _መመረጥ፣ መንገድ መጥረግ ...ምንቴስ ቅብጥሬስ ስትለኝ ቆይተህ ደስ ይበልህ እንዲህ ሆንኩልህ።” (ላቤ እየተንቆረቆረ)
“ረጋ በል! እኔን ካለአሁን አላየኸኝም፤ ካለአሁንም አታየኝም። በደለኛ ሰው በየኼደበት እንደሚለፍፍ አውቃለሁ። የሰው ላብ አፍ አወጥታ ስትወቅሰው መቅበዝበዙም ይገባኛል።”
“በዳይማ ነኝ! እሺ የጳጉሜና ምጽዓት ዝምድና ምንድን ነው? ልትነግረኝ ትችላለህ?”
“...ጳጉሜ የአሮጌው ዓመት መገባደጃ የአዲሱ ዓመት የመጀመሪያ ላይ ትገኛለች። የኖርከው ዕድሜ እንደ አሮጌ፣ ከሞት በኋላ የሚጠብቅህን እንደ አዲስ ቁጠረው። አሮጌው በአዲስ ይተካ ዘንድ በመሐል ምጽዓት አለ። ምጽዓት ላይ የሚወራ ይጠፋል። ስራብ አበላኸኝ፣ ስጠማ አጠጣኸኝ...የሚሉት ጥያቄዎች መዥጎድጎጃቸው ነው። አንተም በዳይ ከነበርክ ከነበረህ የክፋት መስመር ወደ መልካሙ ትገባ ዘንድ ጊዜህ አሁን ነው። ምጽዓትህ። ተናዘዝ ...ተጸጸት ...ይቅር በል ወደ ተለወጠው ጎዳናህ ግባ..”
“መልካምን አይ ዘንድ ምን ላድርግ?”
“ከመናገረህ በፊት አስብ፣ ሁልጊዜም ለማሰብ ክፍት ሁን፣ ከመከራከር  ይልቅ ተወያይ ፣ አዎንታዊ ነገሮችን አስብ፣ መልካም ቃላቶችን አውራ፣ ለትችቶች ተዘጋጅ፣ የሌሎችን ስሜት አክብር፣ የሌሎች ስህተት ላይ አታፍጥ፣ ከተግባራዊ ስራ ጋር ተጣመር፣ ከመጥፎ ዜናዎች እራቅ”
“ቃልህን እተገብር ዘንድ ይርዳኝ”
“ይርዳህ! ...”ብሎኝ ለሦሥተኛ ጊዜ ተሰወረ፡፡
[...አንዳች መንቃት ነቃሁ። ያየኹትን አላየሁም። ሦስት ጎጆ፣ አሮጊት ሴት፣ ወጣት ሳባኪ ገለመሌ አልነበሩም፤የሉምም። አእምሮዬ በየፊናቸው እየከሰተ ያስወራኝ ምናቦች ናቸው (እንደ ሰው)። በድንጋጤ ዓይኔን ለመንገድ ገለጥኩ። መንገዱ ከተንኮሌ በቀር እንቅፋት የለበትም። የራሴ ክዋኔዎች አካል ፈጥረው፣ እሳት ቋያ ለብሰው እንዲያወሩኝ ማን ጉልበት ሰጣቸው? የወንድሜ ስቃይ በትዝታ ይገዝፍ ዘንድ ማን ግርማ አደለው? ያዋራኝ ሳይኖር አወራሁ፣ የተነፈሰ ሳይኖር ቃል ሰማሁ፣ ወቀሳ ...ስብከት ...ሁሉን ሰማሁ ዓየሁ፣ ለደግ ጻድቅ ይገለጥለታል፤ ለእኔ ኃጥያቴ አፍ ዘርቶ ተገለጠልኝ። የነጋበትን ጅብ ዶሮ እንደምታባርረው _ለግዙፉ እኔ አናሶች እንዲሁ ሆኑ። የጠራኝ ሳይኖር _ወዬ፤ የመረጠኝ ሳይኖር _አቤት ያልኩ ወፈፌ.. ስለሆነውም ስለሚሆነውም ይቅርታ...ወርኃ ጳጉሜ (በግሪክ ኢፓጉሜኔ) በአለቃ መዝገበ ቃላት (ጭማሬ የተሰኘችዋ) ከክረምት ወደ ጸደይ መዝለቂያዬ ላይ እገኛለሁ። ጭማሬ ቀኔን እጠቀም ዘንድ ሻትኩ። ያለፈው አለፈ ...የሆነውም ሆነ ...ስለፍ የሰማኸኝ ሆይ ይቅርታ፤ ሁለት ሞኝ ልብ ይሻልና ... ሞኝ ሆነህ! ይቅርታዬን ይቅር በለው።


Read 1023 times